ብሔራዊ ማንነት መፍጠር ባለመቻላቸው የፈራረሱ አገሮች አሉ።

0
902

በአሜሪካ ቺካጎ ግዛት እ.ኤ.አ በ1952 የተወለዱት ፈራንሲስ ፉኩያማ (ፕሮፌሰር) በሃርቫርድ ዩኒቨሪቲ ፖለቲካል ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥናት፣ ምርመር እና ትምህርት የሚሰጡት ፍራንሲስ አወዛጋቢ በሆኑት መፅሃፍቶቻቸው ይታወቃሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በስታንፎርድ ዩኒቨስርሲቲ የዲሞክራሲ፣ የልማትና የሕግ የበላይነት ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር በመሆን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

‹‹The End of History and the Last Man›› የተሰኘው መፅሃፋቸው ረጅሙ የቀዝቃዛ ጦርነት በሊብራል የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰብ አሸናፊነት በተደመደመበት ወቅት እጅግ አወዛጋቢ ሆኖ የመጣ መፅሐፍ ነበር፡፡ መፅሐፉ በወቅቱ ዓለም የምትመራበት ስርዓት የመጨረሻው ዓይነት እንደሆነና የምዕራባውያኑ አኗኗር የተቀረው ዓለም የደረሰበትን ባህልና አኗኗር ደፍጥጦ በበላይነት የተቆጣጠረበት መሆኑ ዓለም ከዚህ በኋላ ብዙም አዲስ ነገር እንደማታይ ተንብየዋል፤ ያለነውም የታሪክ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነው ሲሉ ሞግተዋል በሚል የተለያዩ ትችቶች ይቀርቡባቸው ነበር፡፡

በተጨማሪ የሚታወቁ ቢሆንም በ2010 ያሳተሙት ‹‹ማንነት›› የተሰኘው እና በዓለም ላይ የተንሰራፋውን የማንነት ፖለቲካ በስፋትና በጥልቀት የተነተኑበትን መፅሀፍ በቅርቡ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፈርመው ሰጥተዋቸዋል፡፡

በጉብኝታቸው በፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ላይ ያተኮረ የአንድ ሳምንት ስልጠና ለግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾችና የመንግስት ባለስልጣናት የሰጡት የዘር ሐረጋቸው ከጃፓናዊ ቤተሰቦች ሚቀዳው ፍራንሲስ በደብረዘይት አዱላላ ሪዞርት በነበራቸው ቆይታ ከአዲስ ማለዳዋ ሐይማኖት አሸናፊ ጋር ቆይታ አድርገዋል። በልማታዊ መንግሥት አሠራርና ስርዓት ዙሪያ እንዲሁም ኢትዮጵያ ስላለችበት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

አዲስ ማለዳ፡ የልማታዊ መንግሥት ብያኔ ላይ ሰፊ ልዩነቶች ይታያሉ፣ በአንድ በኩል የልማታዊ መንግሥት መርህ መንግሥት የግድ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል ማለት አይደለም የሚል መከራከሪያ ቢነሳም መንግሥት ግን ለዓመታት በዚህ እንደማይስማማ ሲገልጽ ነበር። ይህንን የኢኮኖሚ ስርዓት ይበልጥ የሚገልፀው ምንድን ነው?
ፉኩያማ (ፕሮፌሰር)፡ የልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ሞዴል ዓለም ላይ ባሉ የተለያዩ አገራት ገበያው የሚፈልገውን መንገድ በመተው ለተወሰኑ ዘርፎች ልዩ ድጋፍ የሚደረግበት ስርዓት ሲሆን በተለይም እንደ ጃፓን፣ ኮሪያ እና ታይዋን ባሉ የእስያ አገራት የተለመደ የኢኮኖሚ ስርዓት ነው። ገበያው ሁል ጊዜ በኢኮኖሚው ውስጥ ስለሚያጋጥሙ ችግሮች እና መልካም አጋጣሚዎች ትክክለኛ መረጃ ላይሰጥ ይችላል፤ ይህም ገበያውን ወደ መውደቅ ሊያመራው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም መንግሥት ጣልቃ በመግባት እና መሰረታዊ በሆኑ ዘርፎች ላይ ካፒታሉን ፈሰስ በማድረግ መፍትሔ ለማበጀት ሊሞክር ይችላል።
የልማታዊ መንግሥት ግድፈቶችም በአብዛኛው እንደ ሙስና ያሉ ፖለቲካዊ ችግሮች እንጂ ኢኮኖሚያዊ አይደሉም። በተለይም ልማታዊ ግብ በሌላቸው መንግሥታት፤ መንግሥት ሀብትን ሲያከፋፍል ብዙ ጊዜ ኢኮኖሚያዊ በሆኑ መለኪያዎች ሳይሆን በፖለቲካዊ መስፈርቶች ስለሚሆን ነው። በእኔ እምነት ልማታዊ መንግሥት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውጤታማ ሊሆን ያልቻለው ለዚህ ነው።

መርሁን ያለመረዳት ከላይ ላነሳኋቸው ችግሮች መንስዔ መሆኑ እርግጥ ነው። ነገር ግን ብቸኛ ምክንያት ነው ብዬ አላምንም። ለምሳሌ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ልማታዊ መንግሥትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ከተገበሩት እንደ ደቡብ ኮሪያ ካሉ አገራት ሞዴል አድርገው ለመተግበር ሞክረው ነበር። እነዚህ በተለይም “የእስያ ነብሮች” ተብለው የሚጠሩት አገራት ጠንካራ በሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ስኬትን ማስመዝገብ የቻሉ ናቸው። ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር ስትከተለው የነበረው በርግጥም ልማታዊ መንግሥትነት ነበረ ለማለት እቸገራለሁ፣ ምክንያቱ ልክ እንደ ኮሪያ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ የግል ዘርፍ ስላልነበራት ነው።
ካየኋቸውና በእስያ ካሉ ልማታዊ መንግሥታት ጋር ሳነፃፅረው በኢትዮጵያም የግል ድርጅቶች አሉ። ነገር ግን እንደ ኮሪያ ግዙፍ እና ኢኮኖሚውን መምራት የቻሉ ሳይሆኑ አነስተኛ የሚባሉ ናቸው፤ በተቃራኒው ኢኮኖሚውን የሚዘውረው መንግሥት ነው። ኢትዮጵያ እንደ ትክክለኛው የልማታዊ መንግሥት መርህ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በሚመሰርተው አጋርነት ሳይሆን ብቻውን የሚመራው ልማት ያላት፤ በአጭሩ እንደ ድሮዋ የሶቪየት ኅብረት ዓይነት የኢኮኖሚ ሞዴል የምትከተል አገር ነበረች።

ስለዚህ ልማታዊ መንግሥት ማለት የግድ መንግሥት ወሳኝ የሚባለውን ሚና የሚጫወትበት የኢኮኖሚ ስርዓት አይደለም ማለት ነው?
አዎን! ምክንያቱም ስኬታማ ልማታዊ መንግሥት እንዳልኩት በግሉ ዘርፍ እና በመንግሥት መካከል በሚፈጠር አጋርነት የሚመጣ እንጂ መንግሥት ለብቻው የሚፈጥረው አይደለም። ኢትዮጵያም የልማታዊ መንግሥትን መስፈርቶች የሚያሟላ ትክክለኛ ስርዓት ዘርግታለች ብዬ አላምንም። ይልቁንም እንደ ሶቪየት ኅብረት ያለ የመንግሥት የበላይነት የሚታይበት ነው።

ልማታዊ መንግሥትን የተገበረችው ኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት ባለ ኹለት አሃዝ ዕድገት አስመዝግባለች። ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ታዳጊ አገራት ልማታዊ መንግሥትን ሲተገብሩም ገበያ መሩ ኢኮኖሚ የሞተ እና የተቀበረ ነው የሚል መከራከሪያ ነበራቸው። በዚህ ላይ ያሎት አስተያየት ምንድነው?
ገበያ መሩ የኢኮኖሚ ስርዓት የሞተ ወይም የተቀበረ ነው በሚለው ሐሳብ አልስማማም። በዓለም ላይ ብንመለከት እንደ ቻይና እና ሕንድ ያሉ አገራት ላስመዘገቡት የኢኮኖሚ ስኬት ገበያ መር የኢኮኖሚ ስርዓት አይነተኛ አስተዋፆ ነበረው። ቻይና እስከ 1978 (እ.ኤ.አ) በመንግሥት የሚመራ የኢኮኖሚ ስርዓት የነበራት አገር ናት። ነገር ግን ኢኮኖሚዋን ለዓለማዓቀፍ ንግድ ክፍት በማድረግ የውጪ ባለሀብቶች ያለገደብ እንዲሰሩ ፈቀደች፤ እንዲሁም ቻይናውያንም በአገራቸው ውስጥ እንደልባቸው እንዲገዙ እና እንዲሸጡ በማድረግ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ማስቀረት ችላለች። ስለዚህ ቻይና እና ሕንድ የነፃ ገበያ መርህን በመተግበር የተሳካላቸው እና ምሳሌ መሆን የሚችሉ አገራት ናቸው።

ቻይና የነፃ ገበያ መርህን በመጠቀም ኢኮኖሚዋን ወደ ስኬት መለወጥ የቻለች አገር ናት። ሕንድም በ1990ዎቹ መጨረሻ እና በ2000 መጀመሪያ በተለይም የወጪ ንግዷን ለማነቃቃት የተለያዩ አሳሪ ሕጎችን በማንሳት እና የግብር ማበረታቻዎችንም በመስጠት ባደረገቻቸው የለውጥ ሥራዎች በየዓመቱ ከሰባት እስከ ስምንት በመቶ ዕድገት ማምጣት ችላለች።

ስለዚህ የነፃ ገበያ ስርዓት እነዚህ አገራት አስደማሚ የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲያመጡ ማድረግ የቻለ እንዲሁም ገና ያላረጀ ስርዓት ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ማለት ግን የገበያ መሩ የኢኮኖሚ ስርዓት ፍፁም እና ችግሮች የሌሉበት ነው ማለት አይደለም፣ በ1990ዎቹም እነዚህ ችግሮች ጫፍ ድረስ ሔደው ተመልክተናቸዋል። በወቅቱ የመንግሥት ንብረቶችን ወደ ግል በማዞሩ ረገድ በተለይም የሕዘብ መገልገያ የሆኑትን እንደ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ እና ቴሌኮም ላይ ያን ያህል የተሳካ አልነበረም።
በቀድሞው የሶቪየት ኅብረት የገበያ መር ኢኮኖሚ በሚተገበርበት ወቅት የመንግሥት ንብረትን ወደግል የማዞር ሒደት ችግር ስለነበረበት በድሃው እና በሀብታሙ መካከል ከፍተኛ የኃብት ልዩነት ተፈጠረ፤ ጥቂት ግለሰቦች የበላይ የሆኑበትን ኢኮኖሚ ያስከተለ ነበር። ይህም ሊሆን የቻለው የገበያ መር የኢኮኖሚ ስርአትን ጫፍ ድረስ መጎተት እና ለዚህም መሰረታዊ የሆኑትን የመንግሥት መዋቅር፣ የንብረት መብቶች እና የሕግ የበላይነት ሳያሟሉ ኢኮኖሚን ክፍት በማድረጋቸው የተከሰተ አላስፈላጊ ውጤት ነው።

በአጠቃላይ ገበያ መር ኢኮኖሚ ማለት መንግሥት የሌለበት ስርዓት ማለት ሳይሆን እንደውም የበለጠ ጠንካራ ነገር ግን መሰረታዊ የሆነውን ሕግ እና የፖለቲካ ስርዓቱን በመጠበቅ እና በማስከበር ላይ ራሱን የሚገድብበት ስርዓት ማለት ነው።

በዓለም ላይ ኒዮ-ሊብራሊዚም ተቀባይነቱን እያጣ ባለበት በዚህ ወቅት የልማታዊ መንግሥት ሚና ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?
እነዚህ የኢኮኖሚ ስርዓቶች ሁሌም ተመሳሳይ ውጤት ያላቸው እና ስኬታማ አይደሉም። ገና ጀማሪ በሆነ ዕድገት ውስጥ ጠንካራ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ውጤታማ ሊሆን ቢችልም ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት ሲመጣ ጥቅሙ እየቀነሰ ይመጣል። ለዚህም ምክንያቱ መንግሥት ግትር እየሆነ መምጣቱ ሲሆን በአጠቃላይም የልማታዊ መንግሥት ስኬት በአመራር ብቃት ላይ የሚመሰረት ነው። ልማታዊ መንግሥት በእስያ ውጤት ያመጣበት ምክንያት ጠንካራ፣ ቀልጣፋ እንዲሁም ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነና የሰለጠነ የመንግሥት ሠራተኛ (bureaucracy) ስለነበራቸው ነው።

በሌላ በኩል እንደ ፓኪስታን እና አርጀንቲና ያሉ በልማታዊ መንግሥት ስኬትን ማምጣት ያልቻሉ አገራት ልምድ ደግሞ ተቃራኒ ነበር። ለዚህም ነው እንደየሁኔታው የሚመዘን አቀራረብ መከተል ያለባቸው። ገበያ መሩ የኢኮኖሚ ስርዓት የበለጠ ውጤት ያመጣል አንዳንዴ ደግሞ መንግሥት መሩ ይሳካል። ነገር ግን ሁሉም ሀገራቱ ካሉበት ነባራዊ ሁኔታ ይወሰናል እንጂ አንዱን መርጦ ሁሌም ስኬታማ ነው ማለት አይቻልም።

ጀማሪ በሆነ ዕድገት ልማታዊ መንግሥትን መተግበር አዋጪ ነው ብለዋል። አንድ ኢኮኖሚ ታዳጊ ነው የሚባለው በምን መለኪያ ነው?
ጀማሪ ማለት ለምሳሌ ኢትዮጵያ በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ የነበረችበት ወይም ብዙ መሰረተ ልማት ያልነበሩበት ወቅት ማለት ነው። መንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ወደብ እንዲሁም ሌሎች ብዙ መሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶች ባልተሟሉበት ዕድገትን ማምጣት ማለት በጣም ከባድ ነገር ነው። ሁል ጊዜ እነዚህ መሰረታዊ አገልግሎቶች በመንግሥት ቢሟሉ መልካም ነው ስለሚባል ነው መንግሥት እጅግ ትልቅ መዋዕለ ነዋይ በመሰረተ ልማት ላይ ፈሰስ የሚያደርገው።

ችግሩ ግን አንዴ ይህ ደረጃ ሲታለፍ መንግሥት በምን ላይ ነው መዋዕለ ንዋዩን ፈሰስ ማድረግ ያለበት የሚለው ነው ግልፅ ያልሆነው። ለምሰሌ አንድ የመድኀኒት ፋብሪካ በኢትዮጵያ መንግሥት መዋዕለ ንዋይ ተመሰረተ ብንል እና ያለ መንግሥት ድጋፍ ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል ባይችል፤ እንደነዚህ ዓይነት አካባቢዎች ላይ ነው ገበያ መር አማራጭ የሚያስፈልገው።

ልማት መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብዙውን ጊዜ ውጤታማ ያልሆኑ የመንግሥት ድርጅቶችን ከመፍጠር ባለፈ የአገር ኢኮኖሚ በጥቂት ግለሰቦች እጅ እንድትወድቅ ያደርጋል የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ። ይህም በተወሰኑ የደቡብ አሜሪካ አገራት ላይ የታየ ነው። አንዳንዶች ይህ በኢትዮጵያም የታየ እና የተወሰነ ቡድንን እንዲሁም የፖለቲካውን ልኂቅ ባለጠጋ ያደረገ ስርዓት ነው ሲሉ ይሞግታሉ። የእርሶ አስተያየት ምን ይመስላል?
ትክክል ነው። መንግሥት የበላይነቱን በተቆጣጠረበት ኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ባለፀጋ የመሆን መስፈርቱ ፖለቲካዊ እንጂ ኢኮኖሚያዊ አይደለም። ስለዚህም ሥራ ፈጣሪዎች እና የተሳካላቸው የድርጅት አስተዳዳሪ ያላቸው ኩባንያዎች ሳይሆኑ የፖለቲካ ትውውቅ ያላቸው ሀብታም የሚሆኑት። አንዴ የፖለቲካ ሥልጣኑን የጨበጠ ሰው ለውድድር እንቅፋት የሆኑ አሠራሮችን በመተግበር ገበያውን ወደ ትልቅ የምርታማነት መቀነስ የሚከትበትን መንገድ ሊከተል ይችላል።

“የእስያ ነብሮች” የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚችል ምሳሌ ናቸው ብለዋል። ነገር ግን እነዚህ አገራት በኢትዮጵያ ያለውን ድኅነት ለመቀነስ እና ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣት ምሳሌ መሆን ይችላሉ?
“የእስያ ነብሮች” በተለይም ዕድገታቸው በጀመረበት ወቅት የተወሰኑ ዘርፎችን የበለጠ አበረታተዋል። ጨቅላ ኢንዱስትሪዎችን የተለየ ከለላ መስጠታቸው ውጤት አምጥቶላቸዋል። ነገር ግን ይህ ከለላ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች አድገው ትልልቅ እስከሚሆኑ ድረስ ብቻ ነበር። ድርጅቶቹ ዓለማቀፍ ተወዳዳሪ ከሆኑ በኋላ መንግሥት ድጎማውን እና ጥበቃውን መቀነስ እንዲሁም እነዚህ ትልልቅ ድርጅቶች በራሳቸው ወጥተው በዓለማቀፍ ደረጃ እንዲወዳዳሩም ማድረግ አለበት፣ የእስያ ነብሮችም ይህንን ነው ያደረጉት።

ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ ትንንሽ ኢንዱስትሪዎቿ ግዙፍ መሆን ሲጀምሩ ድጎማዋን አቋርጣለች። ይህ ነው እንግዲህ ለአብዛኛው አዳጊ አገር እንደችግር ሆኖ የሚታየው፣ ለዚህም ምክንያቱ ድጎማው እንዲቀጥል ፖለቲካዊ ጫናዎች ስለሚደረጉ ነው። ለምሳሌ በአርጀንቲና በመንግሥት ድጎማ የመኪና ኢንዱስትሪ ለማቋቋም እና በብዙ ማበረታቻ በአገር ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ ተሞክሮ ነበር። ነገር ግን መኪናው በዓለማቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ሳይችል ቀርቷል።

ምንም እንኳን ከአርጀንቲና ውጪ ያለ ሌላ ሰው ምርቱን ባይፈልገውም መንግሥት ግን ገንዘብ ወደ ድርጅቱ ማንቆርቆሩን አላቆመም ነበር። እንዲህ ዓይነት ብዙ ምሳሌዎችን ማንሳት እንችላለን፤ ኢንዶኔዢያም የኤሮ ስፔስ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ሙከራ ታደርግ ነበር። ነገር ግን ሳይሳካ ቀርተዋል፣ ለዚህም ምክንያቱ ገበያቸው በጣም ውስን ስለነበር ነው። ስለዚህ መንግሥት ገንዘቡን አባክኖ ቀረ ማለት ነው።

“የእስያ ነብሮች” ካስመዘገቡት ስኬት ባሻገር ከፍተኛ የፖለቲካ ጫና ያለበትን ስርዓት ዘርግተዋል በሚል ሲተቹና ዕድገታቸውም በሰብኣዊ መብቶች ረገጣ የመጣ ነው ሲባል ይሰማል። እነዚህ ኹለቱን አጣጥሞ መሔድ አይቻልም?
አገራቱ ካላቸው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ውስጥ ምን ያህሉ ነው በአምባገነን መንግሥት ላይ የተመሰረተው የሚለው ነው አከራከሪው ነጥብ። እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ኹለቱ አብረው የሚሔዱ ናቸው፤ ምክንያቱም መንግሥት በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው በጣም ጠንካራ መሆን አለበት። ነገር ግን አስፈላጊ ነው ብዬ የማምነው መንግሥት ግልፅ የሆነ የልማት ርዕይ ባለው ሕዝብ መመራት እንጂ ራሳቸውን ብቻ ማበልፀግ በሚፈለጉ ግለሰቦች መመራት የለበትም።

በአብዛኛው ታዳጊ አገር በተለይም ከሳሃራ በታች ባሉት ያለው ትልቁ ችግር እንደዛ ያለው አመራር አለመኖሩ ነው። መሪዎች የራሳቸውን ቤተሰብ ሀብታም ማድረግ እንጂ አገራዊ ግቦችን ማሳካት ዓላማ ያደረጉ አይደሉም። ስለዚህ በገበያው ውስጥ ጣልቃ ሲገቡ ለራሳቸው ሲሉ እንጂ ለሕዝቡ በሚጠቅም መንገድ አይደለም።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ልማታዊ መንግሥት መተግበር አይቻልም ማለት ነው?
ይቻላል! ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ጀመሮ ጃፓን ዲሞክሲያዊ አገር ስትሆን እስካሁንም የልማታዊ መንግሥት መርህን ትተገብራለች። በእስያ ለረጀም ዘመናት የቆየ እና ከቻይና እንደተወረሰ የሚነገር የመንግሥት ሥራን በሊቃውንት መምራት ልምድ አለ። ስለዚህ ውጤታማ የኢኮኖሚ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የሚችሉ በጣም ጠንካራ የሚባሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አሏቸው። ለዚህም ምክንያቱ በተማሩ እንዲሁም በአገረዊ አጀንዳ ላይ ባተኮሩ ሠራተኞች የተገነቡ በመሆናቸው ሲሆን ለዛም ነው በልማታዊ መንግሥት ሞዴል ዴሞክራሲዊ አገር ሆነው መቀጠል የቻሉት።

አቅርቦትን የመፍጠር የኢኮኖሚ አካሔድ እንደ ኢትዮፕያ ባሉት አገራት መተግበር ይቻላል?
መንግሥት በሚመራው የኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ከሚፈጠሩ ችግሮች መካከል ዋነኛው መንግሥት የሚያደረገው ኢንቨስትመንት ፍላጎትን የሚጨምር መሆኑ ነው። ነገር ግን ይህንን ማስቀጠል በጣም ከባድ ነው። በኢትዮጵያ የሆነውም ከዚህ የተለየ አይደለም፣ የአገሪቱ ኢንቨስትምንት ሲመራ የነበረው በብድር ነበር። የዚህ አካሔድም ቀጣይነት ግለፅ አይደለም። ከፍተኛ አቅርቦት በመፍጠር የሚመራ የገበያ ስርዓት ብዙ ጊዜ የቅልጥፍና እና የምርታማነት ችግሮች የሚታዩበት ነው። ነገር ግን ማንኛውም ኢኮኖሚ ስለ ቅልጥፍና እና ምርታማነት መጨነቅ አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህ አንድም በመንግሥት የሚመራ ልማት ድክመት ነው። ምክንያቱም መንግሥት ሁሌም ትክክለኛውን የድጎማ መንገድ ስለማይጠቀሙ ቀልጣፋ ተቋማትን መፍጠር አይችልም።

በመጻሕትዎት፣ በሚያደርጓቸው ንግግሮች እንዲሁም በዚህ ቃለ ምልልስ እንደጠቀሱት የመንግሥት ሠራተኞች በብቃት ላይ ብቻ በተመሰረተ መስፈርት ካልተመለመሉ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማስመዝገብ አይቻልም ብለዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በብሔር በሚሰጥ ኮታ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም ኀላፊዎች ይሾማሉ። ይህንን እንዴት ይመለከቱታል?
ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እውነታውን መዘንጋት አለባት ብዬ አላምንም። እንደ ኢትዮጵያ የብሔር ማንነት እጅግ ወሳኝ በሆነበት አገር አንድ ሰው ድንገት ተነስቶ “ብቁ የሚባለውን ሰው መርጬ እቀጥራለሁ፣ የብሔር ማንነቱ ምንም ይሁን ምን” ማለት የሚችል አመስለኝም፣ ለብሔር ማንነት ያለውን ቦታም ማስቀረት አይቻልም።
ጥያቄው መሆን ያለበት ለብሔር የሚሰጠውን ዕውቅና ከእውቀት እና ብቃት ጋር እንዴት ማመዛዘን ይቻላል የሚለው ነው። ሌላው ትኩረት መስጠት ይገባዋል ምለው ግን የብሔር ስሜቶችን ከአገራዊ ስሜት ጋር ማመጣጠን ነው። ኹለቱ ስሜቶች ጎን ለጎን መሔድ የሚችሉ ሲሆኑ ሰዎች ብሔራቸው አባል ብቻ ሳይሆኑ የሰፊው አገራዊ ማኅበረሰብ አባል እንደሆኑ እንዲሰማቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። ይህንን ማድረግ ደግሞ ጠንካራ አመራር የሚጠይቅ ሥራ ነው።

ይህ በአጭር ጊዜ የሚሳካ ነው ብለው ያምናሉ?
በፍፁም በአጭር ጊዜ የሚከወን ተግባር አይደለም። ይህ በጊዜ ሒደት በሕዝቡ ልብ ውስጥ የሚገነባ እና ትምህርት፣ ጠንካራ አመራር እና ልምድ የሚጠይቅ በመሆኑ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።

እንደኢትዮጵያ ያሉ አገራት ምን ዓይነት የሥነ ምጣኔ ሀብት ሞዴል ቢጠቀሙ ይመክራሉ?
የልማታዊ መንግሥት ሥርዓትን ሙሉ ለሙሉ መተው አይገባም፤ ነገር ግን የመንግስት ቁጥጥር ለቀቅ ማለት አለበት ብዬ አስባለሁ። መንግሥት ብዙ የኢኮኖሚ ፖሊስ ውሳኔዎችን ከላይ ወደታች መወሰኑን መቀነስ እና ሕዘቡ በራሱ ነገሮችን እንዲያስተካክል መፍቀድ አለበት ብዬ አስባለሁ። ይህም የተወሰነ የሕግ እና ደንቦችን ለመቀነስ እንዲሁም ግሉን ዘርፍ እንዲተጠነክር በመፍቀድ መፈጸም ይቻላል። በእስያ ነብሮች እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ልዩነት ይኸው ነው፤ በእስያ የግል ዘርፉ ጠንካራ ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ያለው አመራር በነጻ ገበያ ላይ ትኩረት አድረጓል። መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር እየተንቀሳቀስ ነው። እዚህ ላይ ምን አስተያየት ይሰጣሉ?
መንግሥት እንደ ኤሌክቲሪክ ኀይል፣ ውሃ፣ ቆሻሻ ማስወገድ እና መሰል ትላልቅ ተቋማትን ወደግል ሲያዞር፤ የግል ዘርፉን በአግባቡ መምራት ስለመቻሉ፤ ክፍያቸው ፍትሃዊ መሆኑን ማረጋገጥ እንዲሁም ከብዙኀኑ ማኅበረሰብ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም መሆኑ ላይ እርግጠኛ ሲሆን ብቻ ነው መሆን ያለበት። ብዙ አገራት በተለይ በ1990ዎቹ የተሳሳቱት እዚህ ላይ ነው፤ የመምራት አቅም ሳይኖራቸው ነበር ወደ ግል ማዞሩ ላይ ያተኮሩት።

እናም እነዚህን ትልልቀ ተቋማት ወደ ግል ማዞሩ ጉዳት አለው ወይስ የለውም የሚለው የመንግሥት የመምራት አቅም ላይ ተመርኩዞ ነው። አልያም እነዛን ተቋማት ራሱ መንግሥት በአግባቡ ይይዛቸዋል ወይም የግል ይዞታን ሊመራ ይገባል። ትላልቅ ተቋማትን ግን ያለ በቂ መመሪያና ክትትል ወደ ግል ማዞር መዘዙ ብዙ ነው።

ብዙዎች ግን በነጻ የኢኮኖሚ ስርዓትና ተቋማትን ወደ ግል ማዞር የአገሪቱን የሥነ ምጣኔ ሀብት ሉዓላዊነት ያሳጣል የሚል ሥጋት አላቸው?
ኢትዮጵያ በራሷ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመዘርጋት የገብያዋ መጠን በጣም ውስን ነው። አገራት በዓለማቀፉ ገበያ ተሳታፊ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ይህም ዓለማቀፍ ቴክኖሎጂ እንዲሁም የሰው ኀይልና ገንዘብና ዘመናዊ አሰራሮች ከሌላ አገራት ሊገቡላቸው የሚገቧቸው ግባዓቶች ያስፈልጋቸዋል።

ዛሬ ላይ የተሻለ የምጣኔ ሀብት ደረጃ ላይ ያሉ አገራትን ስንመለከት፤ ያሉበት ደረጃ የደረሱት በራቸውን ለውጪ አገራት ባለሙያዎች፣ ካፒታል እንዲሁም የሰው ኀይል ክፍት በማድረጋቸው ነው። ያንን ማድረጋቸው ሉዓላዊነታቸው ላይ ተጽዕኖ አላደረገም። እንደምሳሌ በኤምሬትስ በሥራ ከተሠማራው የሰው ኀይል ውስጥ ምናልባት አንድ ዐሥረኛው ቢሆን ነው የአገሩ ተወላጅ። ነገር ግን አሁንም የአራገቸው ሙሉ ኅልውና እና ሉዓላዊነት በቁጥጥራቸው ሥር ነው፣ የራሳቸውን ጉዳይ ራሳቸው ናቸው የሚወስኑት።

ከሌሎች አገራት በመጡ ወይም መጤ በሆኑ ሰዎች የመወረር ሥጋት ትክክል አይደለም። የውጪ አገራት ዜጎች ያስፈልጋሉ፤ ምክንያቱም ቴክኖሎጂውን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳዩት እነሱ ናቸው። በተለይም እንደኢትዮጵያ ያሉ አገራት የሚፈልጓቸው ሙያዎችና ክህሎት ስለሌላቸው ራሳቸውን ክፍት ቢያደርጉ ይጠቀማሉ።

የዓለማቀፍ ገንዘብ ተቋማት እንዲህ ባሉ የኢኮኖሚ ስርዓት ለውጦች ወቅት የሚኖራቸውን ጣልቃ ገብነት እንዴት ይመለከቱታል?
ለምሳሌ የዓለም ገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የሚያሳድራቸውን ጫናዎች በሌሎች አገራት ላይም ብትመለከቺው አገራቱ ራሳቸው ሊፈልጓቸው እና ጫና ሊያሳድሩባቸው የሚገቡ ነገሮችን ነው እንዲፈፀሙ የሚወተውተው። ለምሳሌ ሙስና እንዲቆም ስለሚፈልጉ ወደ መንግሥት ባለሥልጣናት ኪስ የሚገባ ገንዘብን ማበደር አይፈልጉም። ስለዚህ በግልጽነት እና በመልካም አስተዳደር ላይ የለውጥ ሥራ እንዲሠራ ሊጠይቁ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች ኢትዮጵያ ራሷ ልታስወግዳቸው የሚገቡ ነገሮች እንጂ የውጪ አገር ጥቅም እና ፍላጎት ሆነው የሚጫኑ ነገሮች አይደሉም። የገንዘብ ተቋሙ የተረጋጋ የ‘ፊሲካል’ ከባቢ እንዲኖር የሚሠራው ገንዘብ ያበደራቸው አገራት በአግባቡ እንዲመልሱለት ስለሚፈልግ ነው። ስለዚህ ፍርሃቱ ምን እንደሆነ አይገባኝም።

አስቀድሞ የማንነት ፖለቲካን ሲያነሱ፤ በጣም መከፋፈል ባለባቸው አገራት የሚታዩ የመፍረስ ምልክቶችን ለይተው ነበር። ከዛ አንጻር አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ኢትዮጵያ በርግጥም አደጋ ውስጥ ናት፣ አደጋው ምናልባትም የመፈራረስ ሊሆን ይችላል። ይህም የሆነው የብሔራዊ አንድነት ስሜት ያልተሰማቸውና በኢትዮጵያ ውስጥ ራሳቸውን ማየት ያልቻሉ ብዙ የብሔር ቡድኖች ስላሉ ነው። ይህ በጣም አደገኛ ሁኔታ ነው። ሶርያ፣ ኢራቅና ሶማሊያን አይተናል። ሁሉን የሚያስማማ አንድ ብሔራዊ ማንነት መፍጠር ባለመቻላቸው የመፈራረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል በቅርቡም የፈረሱ አገራትን ተመልክተናል። ኢትዮጵያ በዚህ መንገድና አቅጣጫ ልትሔድ አይገባም።

ችግሩን እዛ ደረጃ ሳይደርስ ለመፍታት ምን ቢደረግ ይላሉ?
መፍትሔው የሚመሰረተው እንዳልኩት ብሔራዊ አንድነትን በመፍጠር ላይ ነው። ይህም በተለይም በአገር መሪዎች ላይ የሚጣል ኀላፊነት ነው። ሰዎች ከብሔር ማንነት ጋር ሚዛናዊ የሆነ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብን ሊፈጥሩ ይገባል። ለምሳሌ ሶሪያን ብትወስጂ ሁሉም ስለራሱ ሃይማኖት እና ጎሳ ላይ ያተኩራል እንጂ ስለ ሶሪያ የሚያስብ አልነበረም። ይህም በመጨረሻ ወደ እርስ በርስ ጦርነት አምርቷል።

ከዚህ ቀደም በነበሮት ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይን የማግኘት ዕድል ነበረዎት። በእሳቸው እና በመንግሥታቸው ላይ ያሎት አሰተያየትስ ምንድን ነው?
በወቅቱ በጣም አስደምመውኝ ነበር። እጅግ የተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር ህልም አላቸው። የአገሪቱን አንድነት ማስጠበቅ የሚችል ፕሮጀክት ይዘው መጥተዋል ብዬ አምናለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here