ኢትዮጵያ ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታና መፍትሔ ፍለጋ

0
783

በኢትዮጵያ ከ2010 ግንቦት ወር የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ስር ነቀል ሳይሆን ገገናዊ ነው ብለው የሚጀምሩት ካሳዬ አማረ፤ በዓመቱ ኢትዮጵያ ያሳለፈቻቸውን ውጣውረዶች ዳስሰዋል። አያይዘውም መፍትሄ ይሆናሉ ያሉትን ሃሳብ አቅርበዋል።

ካለፈዉ መጋቢት 2010 ጀምሮ በኢትዮጲያ የተጀመረዉና ከዓመት በላይ የሆነዉ የለዉጥ እንቅስቃሴ ከኢህአዴግ ጉያ በወጡ የለዉጥ ኃይሎች ፊታአዉራሪነት እየተካሄደ መሆኑ የሚታወቅ ነዉ፡፡ ታዲያ ሀገር ለዉጥ ሲከሰት ወይ ጥገናዊ ሆኖ ይዘልቃል፣ ካልሆነም ስርነቀል በሆነ መንገድ የሚከናወን ይሆናል፡፡
በእኛም ሃገር ከአንድ አመት በፊት የተካሄደው የለዉጥ እንቅስቃሴ ስር ነቀል ሳይሆን ጥገናዊ ሆኖ በብዙ ዉጣዉረዶች ዉስጥ ቀጥሏል፡፡ ለዉጥን ተከትለው የሚመጡ መመሰቃቀሎች መኖራቸዉ ባይካድም የተዋናዮቹ ስብጥር፣ የችግሩ ስፋት፣ ዓይነት እና የአፈፃፀሙ ስልት እና በህዝቡ ስነ ልቦና ላይ እያመጣ ያለዉ ጉዳት አይሎ የተስፋ ጭላንጭል ማየት አለመቻላችን ትኩረት የሚሻ ጉዳይ አድርጎታል፡፡ ወደፊት የሚካሄዱትን የ2012 የህዝብ ቆጠራ እና ምርጫ ሳይካተቱ ከተለያዩ ፈተናዎች ጋር ተጋፍጠናል፡፡

በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ግድያዎች፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝዉዉር፣ የኢኮኖሚው መታመም፣ ያገጠጠ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲሁም በክልል ልዩ ፖሊሶች መካከል ያለው የጡንቻ ማሳየት እና ፉክክር ከብዙዎቹ ጥቂቶች ናቸው፡፡

ወደኋላ የሚጎትቱን አገራዊ ፈተናዎች
በአለም ደረጃም የተፈናቀሉ ሰዎች (Internally Displaced Persons) ብዛት አንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጣችን በሃገራችን ውስጥ ለነበረው የዜጎች የግፍ ግድያ እና ማፈናቀል ምሳሌ ሆኖ ይቀርባል። ሌላዉ ዘግናኝ ሁነት ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዉስጥ በተማሪዎች ላይ የተፈፀሙ ህይወት የማጥፋት ርምጃዎች ናቸው፡፡ ከዕዉቀት ይልቅ በስሜት መነዳት፣ የጠባብ ቡድኖች ፍላጎት ግፊት፣ የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ስብከቶች ማየል እና የብሔር ፖለቲካ ጡዘቶች ለደረሱት ጉዳቶች መነሻ ነበሩ።

ለዜጎች ሞት አንዱ ምክንያት የሆነዉ ገደብ ያጣዉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝዉዉር በዓይነትም በመጠንም ተበራክቶ የሀገርን እና የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ ጥሏል፡፡ ለዚህም ገፊ ምክንያት የሚባለው የፖለቲካ ሃይሎች በጉዳዩ እጃቸዉ መስደዳቸው እና አንዳንድ ራስ ወዳድ የመንግሥት አካላት የዝዉዉሩ ተዋናይ መሆናቸው ይጠቀሳል። ብሎም ታጣቂ የነበሩ ሃይሎች ሙሉ በሙሉ ትጥቃቸዉን ባለመፍታታቸዉ ምክንያት የጦር መሣሪያ ዝዉዉር እንዲንር እና ህዝብና አገርም አደጋ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡

በሌላ መልኩ በክልሎች የተመሠረተዉ ልዩ ኃይል ለብሔራዊ ደኅንነታችን ከሚያበረክተዉ ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ እየታዬ ነዉ፡፡ በቀድሞዉ ኢህአዴግ ዘመን ይሁንታን አግኝቶ በየክልሉ የተመሠረተዉ ልዩ ፖሊስ አላስፈላጊ ሃይል በመፍጠር ክልሎችን ወደ አላስፈላጊ ፉክክር እንዲገቡ ዳርጓቸዋል፡፡ ክልሎች የመሠረቱት ልዩ ኃይል ኢ-ህገ መንግሥታዊ ከመሆኑ በተጨማሪ በአንዳንድ ክልሎች የታጠቀዉ የጦር መሳሪያ ዓይነትና ብዛት መከላከያን የሚገዳደር መሆኑ ለብሔራዊ ደኅንነት ደጋፊ ከመሆን ይልቅ በአካባቢው ላለዉ ብሔር / ቡድን ታማኝ መሆን ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

የዐብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ከተረከባቸዉ ህመሞች አንዱ የኢኮኖሚው ሲሆን ለማሳያነትም በቅርቡ የወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ የብድር መረጃ የዉስጥ እና የዉጭ ዕዳ 1.3 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ያስረዳል፡፡ ይህንንም ለመፈወስ ባለፈዉ አንድ ዓመት ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት በተለይም በማክሮ ኢኮኖሚ ዉስጥ የሚሰተዋለዉ መዋቅራዊ ችግሮች እና ያስከተላቸዉ ዉጤቶች ለኢኮኖሚው ህመሞች እንደምክንያት ይነሳሉ። ኢኮኖሚዉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ካደረጉ ምክንያቶች ጥቂቶቹ መካከልም የዋጋ ግሽበት ከነጠላ አኃዝ ወደ ሁለት አኃዝ ማደጉ እና ያስከተለዉ የኑሮ ዉድነት ውጤቱ መታየት ጀምሯል፡፡ የዉጭ ንግድ ሥራ አፈፃፀም ከጊዜ ጊዜ ዝቅተኛ መሆን ወደ ሀገር የሚገቡ ሸቀጦች ከአስፈላጊነት እና ለብዙሃኑ ህዝብ ከሚሰጡት አኳያ ሳይመዘኑ የውጪ ምንዛሪ ማግኘታቸው በምሳሌነት ይነሳል።

ወደዉጭ የሚላክ ቡና ላይ ዝርፊያና ቅሸባ ማካሄድ፣ ወደ ዉጭ ሊላኩና የዉጭ ምንዛሬ ሊያመጡ የሚችሉ እቃዎችን በኮንትሮባንድ ከሀገር ማስወጣት፣ ለህብረተሰቡ መቅረብ ያለባቸዉ ሸቀጦች በደላላ ጣልቃ ገብነት የናረ ዋጋ እየቀረበባቸዉ ሸማቹ የኑሮ ዉድነቱን መቋቋም የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱም በእለት ተእለት ኑሮ የሚታዩ ህፀፆች ናቸው።

ኢትዮጲያ እና ህዝቦቿ ሰላም እንዳያገኙ አጀንዳ ፈጣሪ የሆኑ የተማሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች የህዝቡን ስነ ልቦና በሚጎዳ እና የርስበርስ ግንኙነት እንዲደፈርስ በተለያየ መደረኮች ብቅ እያሉ ድብቅ ፍላጎታቸዉን ማንፀባረቃቸው ሌላዉ ቁልፍ ጉዳይ ነው።

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በዉስጡ ሃላፊነት ያለበት መሆኑ ተዘንግቶ አዳዲስ አነታራኪ ትርክቶች በማቅረብ ግጭት ለመፍጠር እየተሞከረ ነዉ፡፡ ብዙኃኑ በኑሮ ዉድነት፣ በሥራ አጥነት እና በድህነት ውስጥ ሳለ በታሪክ፣ በቋንቋና በማንነት ዙሪያ በጥናት ሥም ለትርምስ የሚጋብዝ እና ትኩረት የሚያስለዉጥ አጀንዳ በምሁራኑ በመቅረብ ላይ ነዉ።

በሌላ መልኩ በክልሎች መካከል የሚደረገዉን ሰላማዊ ትስስር ከአመራሩ ወደ ህዝቡ ወርዶ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲካሄድ የማስተካከያ ሀሳብ ከማቅረብ ይልቅ ግንኙነቱ ዘረኝነት ነዉ ብሎ መፈረጅ ነዉ፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጥንካሬ እንደሚያመጣ ስለሚታወቅ አገር እና ህዝብ የማዳከሚያ መንገድ ማራመዱ አይነተኛ መገለጫቸዉ ነዉ።

ስለ ሀገር አንስቶ ዜግነትን ማለፍ የማይታሰብ ጉዳይ ነዉ፡፡ ዜግነት በሀገር እና በግለሰብ መካከል የሚመሠረት ቀጥተኛ የሆነ ህጋዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ሲሆን በሌላ ጎኑ ደግሞ ለሀገር ያለንን ታማኝነት የሚያመለክት ነዉ። ስለሆነም አስተሳሰባችን እና ድርጊታችን መቃኘት ያለበት መነሻችንን ሀገር አድርግን ከዚያም ለብሔራችን /ለብሔረሰባችን፣ ለአካባቢያችን የማድረጉን መንገድ ስንከተል ነዉ፡፡ ከ1983 ወዲህ የገነነዉ አስተሳሰብ ብሔሬ ሲኖር ነዉ ኢትዮጲያ የምትኖረዉ የሚል መሆኑ እና የብዙ ሺ ዓመታት ታሪክ ያላትን የ100 ዓመት ታሪክ ያላት ሀገር አድርጎ በማቅረብ ኢትዮጲያ በመፈቃቀድ ላይ በቅርብ የተመሠረተች አገር አድርጎ በማቅረብ በተሠራ የሸፍጥ ሥራ በብሔራዊ አንድነታችን ላይ አደጋ ፈጥሮ ፍሬዉ በተግባር እየታየ ነዉ።

የ1987ቱ ህገ መንግሥት የራሱ ክፍተቶች ቢኖሩትም ማሻሻያ እስከሚደረግበት ድረስ ወደድንም፣ ጠላንም የምንተዳደርበት የበላይ ህግ መሆኑን አምነን መቀበል እንጂ ሲመች ህገ መንግሥቱን መጥቀስ ሳይመች ደግሞ መዝለል አዋጪ መንገድ አይደለም።

በአንዳንድ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ጎራ የሚቀነቀነዉ እና ለእነሱ አይነኬ ጉዳዮችን (ህገ መንግስቱን፣ ፌዴሬሽኑን፣ የክልሎች ወሰን…) በመዘርዘር ከተነካኩ አገር ይፈራርሳል በማለት ያስፈራሩበታል፡፡ ለሀገር የሚጠቅሙ ጉዳዮችን ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ የራስን ብሔር ብቻ ማስቀደም የተለመደ ከሆነ ሰነባበተ። የሁሉንም ዜጎች መብት በማክበር የብሔሮችን መብት ማክበር የሚቻል መሆኑን ዉድቅ በማድረግ፤ ጠባብ ፍላጎትን ለማራመድ የሚቻለዉ አገርን በማተራመስ የሚያልሙትን ክልል መመሥረት ለአንዳንዶች ደግሞ መገንጠልን ተግባራዊ ማድረግ ነዉ። እዉን ህዝቡ ይፈልገዋል ወይ? የህዝብ ጥያቄ ነዉን? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን።

ዴሞክራሲን እንደመፍትሄ
በአገራችን ተግባራዊ ዲሞክራሲ አልተጀመረም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ዲሞክራሲ ባለብዙ መልክ የሆነ ራስን ከመምራት እስከ መንግሥትን መምራት፣ ከመርሆዎች ስብስብ እሰከ ተቋማዊ ነፃነት ድረስ የሚዘልቅ ፅንሰ ሀሳብ ነዉ። የዲሞክራሲ አንዱ ምሰሶ የሆነዉ ተግባራዊ ዲሞክራሲ የሚገለፀዉ በህዝባዊ ምክክር ሆኖ መድረኮችን በማሰናዳት የህዝቡን ጥያቄዎች፣ ፍላጎቶች፣ ስጋቶች እና ምኞቶችን ለማወቅ እና ለመረዳት ያስችላል።

ከተቀባቡ ሪፖርቶች ይልቅ ባለቤት ከሆነው ህዝብ የሚገኘዉ መረጃ ስለአገራችን ትክክለኛ ስዕል ይሰጣል፡፡ በተለይ ሀገራችንን ወጥረው የያዟትን አሳሳቢ ጉዳዮች ለመለየት እና መፍትሔ ለመሻት የሚቻልበት አስተማማኝ መንገድ ነዉ። የካድሬ መር ህዝባዊ ምክክር ዳግመኛ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

የመወያያ አጀንዳ በማዘጋጀት በየአካባቢዉ ህዝቡ እንዲወያይበት ማድረግ፣ አስከትሎም ከተሳተፉት ዜጎች መካከል በራሱ በህዝቡ ቀጥተኛ ምርጫ የተመረጡ አባላት በተገኙበት በክልል ደረጃ እንዲወያዩ ማድረግ፣ በመጨረሻ በብሔራዊ ደረጃ ህዝባዊ ምክክር በማድረግ ለሀገር እና ለህዝብ የሚበጀዉን መፍትሔ በሚያመላክት መንገድ ቢሰራበት ዉጤቱ አመርቂ ይሆናል። ካለፈዉ አንድ ዓመት ወዲህ መድረኩን የተቆጣጠሩት ምሁራን ሲሆኑ አሁን የህዝቡ ሃሳብ የሚደመጥበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። ዲሞክራሲ ትክክል የሚሆነዉ ከታች ወደላይ በሆነ አቀራረብ ተግባራዊ ሲሆን እንጂ ከላይ ወደታች በሆነ መንገድ ሲተገበር አይደለም። ያሳለፍናቸዉ አራት አሰርተ ዓመታት የሚያስረዱት በቃል ላይ የተንጠለጠለ ዲሞክራሲ መኖሩን እና ከላይ ወደታች የተዘረጋ አገዛዝ መንሳራፋቱን ነዉ። በተለይ ኢህአዴግ የሚያወራዉ ዲሞክራሲ ባዶ ጩኽት የነበረ፤ በኢ-ዲሞክራሲያዊ አሠራር ስርዐት ዉስጥ ህዝቡን አፍኖ የገዛበት ወቅት ነዉ።

አሁን በአገራችን እየተስተዋለ ያለዉ ችግር ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ ሆኖ ችግሮቹን ለመፍታት ስንረባረብ ወደ ዉጤት ልንደርስ እንችላለን።
በሌላ ጎኑ ኢትዮጵያዊያንን በመወከል የሚመረጥ መንግሥት አንዱ ሊሰራዉ የሚገባዉ ዉስጣዊ የበላይነት እና ቅቡልነት እንዲኖረዉ በተግባር ማረጋገጥ ነዉ፡፡ በአንፃሩ አሁን ባለዉ ሀገራዊ ሁኔታ የፌደራል መንግሥት ዉስጣዊ የበላይነት እና ቅቡልነት ጥያቄ ዉስጥ መግባቱ እሙን ነዉ፡፡ ለዚህ ማሳያ የዉስጥ ደኅንነታችን በየጊዜዉ በሚከሰቱ በጦር መሣሪያ ላይ የተመሠረቱ ግጭቶች መበራከት እና የሰዉ ህይወት መጥፋት፣ መፈናቀል እና በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎችን አሳልፎ አለመስጠት እንደማሳያ ያገለግላሉ፡፡ አንድ መንግሥት ዉስጣዊ የበላይነቱ እና ቅቡልነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ባለዉ ግዛት ዉስጥ የበላይነቱን በተለያዩ ህጋዊ ርምጃዎች ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡

የዞኖች / ወረዳዎች የርስ በርስ እና ከክልላቸዉ ጋር እንዲሁም ክልሎች ከፌደራል መንግሥት ጋር ያላቸዉ ግንኙነት መልክ መያዙ ለሰላማዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መሠረት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ጤናማ ያልሆነ እና ጤናማነት የጎደለዉ ፉክክር የክልሎችን መስተጋብር ወደ አገራዊ ያለመረጋጋት ያመራል፡፡

ስለሆነም ዳር ሆኖ ከመመልከት የኢህአዴግ መሥራች ፓርቲዎች፣ አጋዥ ፓርቲዎችን እና በተቃሙሞ ጎራ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈ ተከታታይ የጋራ መድረክ በማዘጋጀት ከጥል ይልቅ ትብብርን እና ሰላማዊ ፉክክርን ማዕከል ያደረገ ግንኙነት እንዲኖር መሠራት አለበት፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉብንን ችግሮች የጋራ በማድረግ እና በጋራ በመጣር እና ለዚህ ጥረት ደጋፊ እንዲሆን የማስታረቅ ፖሊቲካ በማራመድ ድርሻቸዉን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ በተቃሙሞ ጎራ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በመሠረቱት የተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ አማካኝነት የሚወክሏቸዉን የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄዎቻቸዉን በሰለጠነ መንገድ እንዲያቀርቡ በማስቻል ችግሮቹ በሰላማዊ፣ በትዕግሥት እና ሀገርን በማይጎዳ መልኩ ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን የማመቻቸት ኃላፊነት አለባቸዉ፡፡

በኢኮኖሚዉ የሚታየዉን ችግር አገሪቱ ካፈራቻቸዉ የኢኮኖሚ ጠበብቶች ጋር በመመካከር እና አዋጪ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍ ደረጃ በደረጃ ችግሮቹን መፍታት የሚያስችል ሥራ ቢሠራ መልካም ነዉ፡፡ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈፅሙት ክፍሎች ላይ ደግሞ በድጋሜ እንዳይፈፀም ዘላቂ የሆነ መፍትሔ መፈለግ፣ ህገ ወጥ ተግባሩን ባከናወኑት ላይ ጠበቅ ያለ አሰተማሪ እና ህጋዊ ርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል፡፡

በመንግሥት በኩል ደግሞ ያሉበትን ክፍተቶች የሚጠቁሙትን የሚዲያ አባላትን ከማዋከብ፣ ከማስፈራራት እና ከማሰር ታቅቦ ሃሳባቸዉን በነፃነት እንዲገልፁ በማድረግ ከሚነሱ ሃሳቦች ጠቃሚ እና ለሀገር ደኅንነት ደጋፊ ናቸዉ ያላቸዉን ወደ ተግባር በመተርጎም፣ እኩልነት የሰፈነባት፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲሁም የህግ ልዕልና የተከበረባት እና የተጠናከረች ዲሞክራሲዊት ኢትዮጲያን በመገንባት በኩል በጋራ ልንሰለፍ ይገባል፡፡

በመጨረሻ የመልካም አስተዳደር ኃይሎች የሚባሉት መንግሥት፣ ሲቪል ማህበረሰቡ፣ የግሉ ሴክተር ህዝቡን ማዕከል በማድረግ ዲሞክራሲያዊ ሰርዓትን በመዘርጋት እና የሁሉም ዜጎች እና ቡድኖች መብት ሳይሸራረፍ የሚረጋገጡባት ሀገር እንድትኖረን ተግተን መሥራት ይገባናል፡፡

ካሳዬ አማረ በ አድማስ ዩኒቨርስቲ በሥነምግባርና ሥነዜጋ ትምህርት ረዳት ፕሮፌሰር

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here