ከቱሪዝም የተገኘው ገቢ ቅናሽ አሳየ

0
580

በ2011 የበጀት ዓመት ኢትዮጵያን የጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር አንድ መቶ ሺህ ገደማ ቅናሽ በማሳየት 849 ሺህ ሆኖ መመዝገቡን እና ከእነዚህ ጎብኚዎች የተገኘውም ገቢ በአራት መቶ ሚሊዮን ዶላር ቀንሶ 3.1 ቢሊዮን ዶላር አንደሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በተጠናቀቀው ዓመት ይገኛል የተባለው የውጪ ምንዛሬ 5.1 ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ማሳካት የቻለው ግን 62 በመቶ ብቻ ነው። በበጀት ዓመቱ 1.5 ሚሊዮን ገደማ ጎብኚዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ከአጠቃላይ እቅዱ ከግማሽ በላይ አለመሳካቱን የሚኒስቴሩ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተወካይ ታሪኩ ነጋሽ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተመሳሳይም የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር 37.1 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዶ 23.6 ሚሊዮን ገደማ እንደደረሰም ጨምረው ተናግረዋል።
‹‹ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ተከስተው የነበሩ ግጭቶች ጎብኚዎች በፀጥታ ችግር ፍርሃት ወደ ሃገራችን እንዳይመጡ የራሱ ጫና ነበረው›› ያሉት ታሪኩ ‹‹የመልካም አስተዳዳር ችግሮች፣ የቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ ችግር ፈቺ ያለመሆን፣ ለቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ትኩረት አለመስጠት እና የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግሮች አለመቀረፋቸው ለዘርፉ ራስ ምታት ሆነው ቀጥለዋል›› ብለዋል።

በጋዜጠኝነት ሞያ በቱሪዝም ላይ በማተኮር ለዘጠኝ ዓመታት ያገለገሉት እና የሀገረ ሰብ ሬድዮ ፕሮግራም አዘጋጅ አስናቀ ብርሀኑ እንደሚሉት የታየው የቁጥር መቀነስ እንብዛም የማይደንቅ እና የሚጠበቅ ነበር።

‹‹በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለማቀፍ ስብሰባዎች አንዲሁም ለግብይት ከሚመጡት ጎብኚዎች ውጪ የሃገሪቱን መዳረሻዎች ለመጎብኘት የሚመጡት ጎብኚዎች ቁጥር 60ሺህ ገደማ ነው። ከሌላ ግዜ ይሻላል፤ በሃገሪቱ በነበሩ ያለመረጋጋቶች ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ትሳተፍባቸው የነበሩ ትልልቅ ኤግዚቢሽን እና ባዛሮች ባለመካሄዳቸው የጎብኚ ቁጥሩ እንዳይጨምር ብሎም እንዲቀንስ አድርጎታል›› ሲሉ ይናገራሉ።

በተጨማሪም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያለውን አቅም እና ማሳካት የቻለውን ቁጥር በማይመጥን መልኩ በመጪው ዓመትም 1.5 ሚሊዮን ቱሪስቶችን አመጣለሁ በሚል የያዘው እቅድ የተጋነነ ነው ሲሉ አስናቀ ይናገራሉ።

‹‹ሀገሪቱ በታሪኳ አንድ ሚሊዮን ቱሪስት አስጎብኝታ አታውቅም፣ ያንን እንኳን ሳናሳካ አንዲህ ያለ የተለጠጠ እቅድ መያዝ ጥቅሙ አይገባኝም›› ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም ‹‹ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ እቅዱን ከማስቀመጥ ባሻገር የቱሪስቶቹ ደኅንነት የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።›› ብለዋል
በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ ቱሪስቶችን ሊስብ በሚችል መልኩ በዓለም ላይ ማስተዋወቅ ያለመቻሉ ሌላው ችግር ነው ያሉት ባለሞያው፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በራሳቸው ተነሳሽነት መጥተው ከሚያስተዋውቁት ውጪ በጀት ተመድቦ እንዲተዋወቅ ማድረግም ግዜ ሊሰጠው የማይገባ እርምጃ መሆን አለበት ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here