- ቫይረሱ በኢትዮጵያ ያለው የስርጭት መጠን 0.96 ነው
በኢትዮጵያ ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው እንደሚገኝ ከሚገመት 54 ሺህ ህፃናት ሕፃናት መካከል 39 በመቶ የሚሆኑት ብቻ የፀረ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድሃኒት እንደሚያገኙ ተገለፀ።
የፌደራል ኤች. ኤይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጣሪያ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መረጃ መሰረት ግን በሀገራችን ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ እናቶች ከሚወለዱ ህጻናት መካከል ምርመራውን የሚያደርጉት ህጻናት ቁጥር ከ40 በመቶ በታች ነው። ለዚህም በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው የህክምና ሽፋን ዝቅተኛ መሆን እና ማህበረሰቡ ስለ በሽታው ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን በምክኒያትነት ይነሳሉ።
ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ተመርምረው በሽታው በደማቸው መኖሩ ከተረጋገጠት ጊዜ ጀምሮ መድሀኒቱን መከታተል እንዲጀምሩ ጥረት እንደሚያደረግ የፌደራል ኤች. ኤይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጣሪያ ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዳንኤል በትረ ተናግረዋል።
የአለም የጤና ድርጅት በሚያስቀምጠው መስፈርት መሰረት ለቫይረሱ ተጋለጭ ናቸው ተብለው የሚታስቡ ህጻናት ከተወለዱ ጀምሮ ባሉት ከ4 እስከ 6 ሳምንታት ውስጥ የኤች ኤይ ቪ ኤድስ ምርመራ እንዲያደርጉ እና አስፈላጊው ህክምናም እንዲገኙ ይመክራል።
መድሃኒቱን ከማቅረብ በፊት ተጋላጭ ለሆኑት ህጻናት ምርመራውን ለመድረግ ወላጆች እና አሳዳጊዎች ህጻናትን ወደ ህክምና ለማመጣት ፈቃደኛ አለመሆናቸው እና ከወረዳ እስከ ፌደራል የሚመጣው የመረጃ ፍሰትም ያልተሟላ እና ያልተደራጀ መሆኑ ለቁጥሩ ዝቀተኛነት አስተዋጽኦ እንደሚበረክት ይናግራሉ።
ለ ኤች .አይ .ቪ የሚሰጠው ትኩረት ከመንግሰት ተቋማት ጀምሮ እሰከ ሚዲያው የሚሰጠው ትኩረት እየቀነሰ መምጣቱን የሚናገሩት ዳንኤል በትረ የኤች .አይ. ቪን ጉዳይ ለሚመለከተው ሁሉ አጀንዳ ለማድረግ ጽሕፈት ቤቱ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ከእነዚህ መስሪያ ቤቶች መካከልም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ምርመራውን በማስተባበር እና ህፃነቱንም በመለያት ሃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል።
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ረዳት ዳይሬክተር የሆኑት ነቢዩ ንጉሱ የህጻናት ኤች. ኤይ. ቪ ምርመራ እንደ አዋቂዎች ምርመራ አለመሆኑን ገልጸው ለህጻናት የኤች. ኤይ.ቪ ምርመራ ያለ ወላጅ እና አሳዳጊ ፈቃድ ማካሄድ የተከለከለ በመሆኑ ጥረቱን ፈታኝ ያደርገዋል ይላሉ።
ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል ከሚባሉት ህፃናትም ውስጥ አብዛኛው መድሃኒት አለማግኘታቸው ችግር መሆኑን ገለፀው በ2012 ዓ.ም ህጻናት የሚመረመሩበትን እና ህክምናውን የሚገኙበትን አሰራር እናሻሽላለን ብለዋል።
የህክምና ሽፋኑን ካለበት 39 በመቶ በቀጣዩ አመት ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ ሚኒስቴሩ ጥረት እንደሚያደርግ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ለበሽታው ተጋላጭነት የሚታይባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ በማተኮር ምርመራው በማድረግ ህክምናውን ያልጀመሩ ህጻናትና አዋቂዎችን በመለየት ህክምናውን እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰራም አክለዋል።
በአለም የጤና ድርጅት መለኪያ መሰረት በሀገራት የበሽታው ስርጭት ከ1 በመቶ ከበለጠ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ሲሆን የሀገራችን የስርጭት መጠኑ 0.96በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የበሽታው ስርጭት ያለበት ክልል ሲሆን በ2011 የስርጭት መጠኑ 4.3 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው መዲናዋ አዲስ አበባ 3.6 በመቶ የስርጭት መጠን እንዳላት የፌደራል ኤች. ኤይ.ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጣሪያ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ ተብሎ የሚገመቱ ሰዎች ጠቅላላ ብዛት ሰድስት መቶ ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን የፀረ ኤች ኤይ ቪ ህክምና ሽፋኑም 79 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ በየአመቱ 13ሺህ ሰዎች በበሽታው የሚሞቱ ሲሆን 13ሺህ ሰዎች እንደ አዲስ በበሽታው ይያዛሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011



