ዳሸን ባንክ በ1.2 ቢሊዮን ብር የናሽናል ሲሚንቶን ብድር ጠቀለለ

0
777

ናሽናል ሲሚንቶ ከልማት ባንክ ተበድሮት የነበረውን 1.2 ቢሊዮን ብር እዳ ዳሸን ባንክ ገዛው። ባንኩ ክፍያውን በአንድ ጊዜ የፈፀመ ሲሆን ብድሩ በባንኩ ታሪክ በአንድ ጊዜ የተፈፀመ ትልቁ የብድር ውል እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ ውሉ ከመፈረም አልፎ ገንዘቡ ለናሽናል ሲሚንቶ ተለቋል።

ከዚህ ቀደም አዋሽ ባንክ ለቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ የሰጠው የ1.5 ቢሊዮን ብር ብድር በግል ባንኮች ታሪክ ትልቅ የሚባለው ብድር ሲሆን ገንዘቡም በኹለት ዙር ተከፋፍሎ የተለቀቀ ነበር።

በተገባደደው የበጀት ዓመት 1.4 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ያተረፈው የዳሸን ባንክ ምክትል ፕሬዘዳንት ጥበቡ ሰለሞን እንደዚሁም የልማት ባንክ ፕሬዘዳንት ኃይለኢየሱስ በቀለ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። የናሽናል ሲሚንቶ እናት ድርጅት የሆነው ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግስ የህዝብ ግንኙነት ኀላፊ ፍፁም ደምሴ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ከጣሊያን ወረራ በኋላ የተቋቋመው ናሽናል ሲሚንቶ በ1997 ወደ ግል ይዞታ የተሸጋገረ ሲሆን በድሬ ዳዋ ከተማ በሚገኘው ፋብሪካው በቀን 30 ሺህ ቶን የማምረት አቅም አለው። ምርቱን ወደጎረቤት አገሮች በመላክ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የሚታወቅ ሲሆን በኢስት አፍሪካን ሆልዲንግስ ስር ከሚገኙ 12 ኩባያዎች መካከል አንጋፋውና 70 ዓመት ያስቆጠረ ፋብሪካ ነው፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here