ከስጋ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከዕቅዱ 49.7 በመቶ ብቻ ነው

0
699

በተገባደደው የ2011 የበጀት ዓመት ወደ ተለያዩ የዓለም ሃገራት የተላኩ የስጋ ምርቶች ያስገኙት ገቢ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ89 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ ከሥጋ ወጪ ንግድ 177.32 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ ቢታሰብም፣ ማግኘት የተቻለው ግን 88.20 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ሲሆን አዲስ በተያዘው በጀት ዓመትም ተመሳሳይ ማሽቆልቆል እንደታየ ለማወቅ ተችሏል። የሐምሌ ወር የሥጋ የወጪ ንግድ 14.9 ሚሊዮን ዶላር ይገኝበታል ተብሎ ቢታቀድም 36.6 በመቶውን ብቻ በማሳካት 5.46 ዶላር ገቢ ተደርጓል፡፡

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ካሳ አላምረው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ክንውኑ መቀነስ ማሳየቱን እና ለእዚህም ለዕርድ የሚቀርቡ የቁም እንስሳት ምርታማነታቸዉና የጥራት ደረጃቸዉ ዝቅተኛ መሆን ለረጅም ዓመታት ዘርፉን ወደኋላ ያስቀረ ችግር ነው ብለዋል። አክለውም በያዝነው ዓመት ተከስቶ የነበረው የመብራት መቆራረጥ ከድርጅቶች የአመራር ብቃት ውስንነት ጋር ተደማምሮ ለምርት መቀነሱ ዋና ምክንያት እንደነበርም ጠቁመዋል።

በዕቅድ ታሳቢ የተደረጉ 27.6 ከመቶ ድርሻ የነበራቸው የሥጋና እርድ ተረፈ ምርት ኤክስፖርቶች፣ ቄራዎች በተለያዩ ዉስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮቻቸው ምክንያት 12.5 በመቶውን ብቻ ወደ ውጪ መላካቸውም ለገቢ ማሽቆልቆሉ ሌላው ምክንያት መሆኑን ካሳ አስታውቀዋል።

የቁም እንስሳት ወጪ ንግድም በተመሳሳይ ዝቅተኛ አፈጻጸም በማስመዝገብ 568ሺህ ለእርድ የሚውሉ የቁም እንስሳት ተልከው 145 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ ቢታሰብም ይህንን እቅድ ማሳካት አልተቻለም። ከዘርፉም 45 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን 444 ሺህ ከብቶችም መላክ ተችሏል። ይህ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በቁጥር 14.64 ከመቶ ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም በገቢ ግን 25.04 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ የሚኒሰቴሩ መረጃ ይጠቁማል፡፡

በሐምሌ ወርም ለመላክ ከታሰበው አንፃር 42 በመቶ ብቻ በማከናወን 26 ሺህ የቁም እንስሳት ወደ ውጪ ተልከው ስድስት ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል።

የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ወደ ውጭ ከተላኩት የቁም እንስሳት ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው በግና ፍየል መሆኑና የአብዛኛው የቁም እንስሳት ከዋጋ በታች ሆነው መሸጣቸው ሌላው አንገብጋቢ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የቁም እንስሳት ንግድ በተለያዩ የሀገራችን መውጫ በሮች በኩል በህገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሃገሮች መውጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የጉምሩክ ኮሚሽን ያደረገው ጥናት ያመለክታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here