የኹለቱ ደብዳቢ ፖሊሶች ጉዳይ

0
430

ሰሞኑን በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የብዙዎችን ቀልብ የሳበ፣ ያወያየና ያናደደ በኋላም ውጤት ያመጣ አንድ የቪዲዮ ምስል ተሰራጭቶ ነበር። ምስሉ በአዲስ አበባ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ጎፋ ማዞሪያ አካባቢ ሰኞ፣ ነሐሴ 20 ኹለት የፖሊስ ደንብ ልብስ የለበሱ አባለት – አንዱ ጠብ መንጃ የታጠቀ ሌላው ባለቆመጥ – በተለይ አንድን ግለሰብ በማዋከብ እና በመደብደብ እንዲሁም ለመገላገል የሞከሩ እናትን በማመናጨቅና በመገፍተር ያሳዩትን ያልተገባ ድርጊት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
በፖሊስ አባላት እንደዚህ ዓይነት ድብደባ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች መመልከት እምብዛም አስገራሚ ጉዳይ አይደለም። የዚህኛውን ለየት የሚያደርገው ግን ድርጊቱ ሲፈጸም የተቀረጸ መሆኑ እንዲሁም በተለይ በፌስቡክ እና በትዊተር ገፆች ላይ ብዙዎች የተነጋገሩበትና የተጋሩት መሆኑ እንዲሁም መንግሥት ድርጊቱን በፈጸሙ የፖሊስ አባላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ የሚማጸኑና ባስ ሲልም በቁጣ መውሰድ ስለሚገባው እርምጃ የሚያሳስቡ መሆናቸው ነው።

የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ምን ያክል ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን በሚያስመሰክር መልኩ በአንድ ቀን ውስጥ ውጤቱ ታይቷል። መንግሥታዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ – የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን – በማግስቱ ማክሰኞ፣ ነሐሴ 21 በቀኑ አራት ማዕዘን የዜና እወጃ ሰዓቱ ላይ ጉዳዩን ከመዘገብ ባሻገር ይመለከታቸዋል ያላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኢንዶክትሪኔሽን እና የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክትር የሆኑትን ኮማንደር ፋሲካ ፈንታን በቀጥታ ስቱዲዮ በማስገባት ምላሽ እንዲሰጡ አስደርጓል።

ኮማንደር ፋሲካ እምብዛም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በኹለቱ ፖሊስ አባለት በተፈጠረው ድርጊት ኅብረተሰቡን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። ይህ የኀላፊው ይቅርታ መጠየቅ አንድምታ ፖሊስ የኅብረተሰቡን ጸጥታና ደኅንነት ለማስጠበቅ ያለበት ኀላፊነት ብቻ ሳይሆን ለሚፈጽመው ሕገወጥ ድርጊት ተጠያቂ እንደሚያደርገው ጭምር ያመላከተ ሆኗል። በተጨማሪም የድርጊቱ ተሳታፊ የነበሩት ኹለቱ የፖሊስ አባላት መታሰራቸውና ጉዳዩን ኮሚሽኑ እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው ኮማንድር ፋሲካ ኹለቱ አባላት አዲስ እንደሆኑ እና ምንም ዓይነት የሥልጠና ጉድለት እንደሌለባቸው የገለጹት ግርታንም ግርምትንም ፈጥሯል፤ እርስ በርሱ የሚጣረሱ ጉዳዮች አገናኝተዋል በሚል። የብዙዎቹ ጥያቄ በደንብ የሰለጠነ የፖሊስ አባል እንዴት ነው “የሰብኣዊ መብት አያያዝን አያውቅም” ሲሉ ተሳልቀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ብዙዎች የፖሊስ ኮሚሽኑን ይቅርታ መጠየቅና በበጎ ያዩትን ያክል አንዳንዶች የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንዳይሆን ሲሉ ጥርጣጣሬቸውን ገልጸዋል። የፖሊሶቹ በሌላ ቴሌቪዥን ቀርቦ ምንም ጥፋት እንዳላጠፉ በሚመስል ሁኔታ ጉዳዩን ለማስተባበል መሞከራቸውን ለአስረጅነት ይጠቅሳሉ።
ለማንኛውም የፖሊስ ኮሚሽኑ ይቅርታ ከምር ቢሆን ጥሩ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አባላቱ ትምህርት ይወስዱበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here