ቋንቋና የተሻሻለው አዲሱ የትምህርት ስርዓት

0
1257

መላኩ አዳል በቅርቡ የትምህርት ሚኒስቴር አዲሱን የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታን ባስተዋወቀበት ወቅት የብዙዎች ቀልብ በመሳብ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ከሆኑት መካከል የተመረጡት ላይ ያላቸውን መከራከሪያ ነጥቦች አቅርበዋል።

 

ቋንቋ የባሕል አካል ከሆኑት እሴቶች፣ ትዕምርቶች፣ ወግና ልምድ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተጨማሪ አንዱና በሰዎች ዘንድ የተደረጉ ድርጊቶችን ለመመዝገብና ወደሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚጠቅም አንዱ መሣሪያ ነው። ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያም ነው። ሰዎች ሐሳባቸውን የሚወክልላቸው ምልክት ወይም ፊደል፤ ብሎም ጽሑፍን በመፍጠር የቋንቋንና የሐሳብን ግንኙነት ፈጠሩ። ከዚህ ተያያዥ ስለሆነው የቋንቋ አጠቃቀምና ትምህርት ስርዓት፤ እንዲሁም ቋንቋ አጠቃቀምና የቋንቋ ፖሊሲ ትንሽ ማለት ወሳኝ ነጥብ ነው።

ትምህርት፣ ዕውቀት ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍበትና ማኅበራዊ ትችቶችም የሚዳብሩበት መንገድ ነው። የትምህርት ዓላማ ዕውቀትን፣ ክህሎትንና አመለካከትን በማስተካከና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ዜጎች ለአገርና ለራሳቸው ጠቃሚዎች ማድረግ ነው። ከሰዎች ለሰዎች ዕውቀት ማግኛ፣ ማስተላለፊያና ሰንዶ ማስቀመጫ አንዱ መሣሪያም ነው። መደበኛ ትምህርት የአንድን አገር ወጣት ትውልድ ባሕል በሚፈለገው መንገድ መቅረጽና በምክንያት የሚኖር ኅብረተስብ ለመፍጠር የሚዘይድ ስርዓት ነው። እናም የትምህርት ስርዓት የአገርን ጠቅላላ የወደ ፊት አቅጣጫ መሰረት ያደረገ፣ ወጥና አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመቅረጽ በሚያስችል መልክ መቀረጽ ይኖርበታል። ይህን ለማሳካት ደግሞ መሰረታዊ የሆነ ሌላ ጉዳይ አለ። እሱም የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲ ነው።

የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲ ወጥ የትምህርት ስርዓት እንዲኖረን ብቻ አይደለም የሚጠቅምን፤ የቃላት መዋስንና አጠቃቀምን ስርዓት በማስያዝ ጭምር እንጂ። ይህም የትምህርት ሒደትን፣ የመግባባት አቅምን በማሳለጥ ዕውቀትን ይጨምራል፣ የአገርን አንድነትንና ዕድገትን ያፋጥናል። የቋንቋን አጠቃቀምና አመራር በተመለከተ ያለው የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ለራሳችን እንዲያመች አድርጎ መጠቀምም ጥሩ ነው። የምንጠቀምባቸው ቃላት (ከውጭም ይምጡ ወይም ነባር) በሕግ የሚመሩ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚመለከተው ተቋም ማቋቋምና በብቁ የሰው ኀይል ማደራጀት ያስፈልጋል። ይህም ቋንቋዎች የታለመላቸውን ዓላማ እንዲመቱ፣ የኅብረተሰብ ዕድገት ምንጭ እንጂ መሰናክል እንዳይሆኑ ያደርጋል።

የጋራ እሴትን መሰረት ያደረገና ወጥ የሆነ ትምህርት መስጠት የማትችል አገር የነገ ህልውናዋ አደጋ ውስጥ ነው። ቋንቋ በአገራችን የቋንቋ ፌዴራል አወቃቀርን ተከትሎ የተቀረጸው የትምህርት ስርዓት የአፈፃፀምና የአገር አንድነት ችግሮች መፍጠሩ የታወቀ ነው። ለመጀመሪ ደረጃ ትምህርት በራስ ቋንቋ መማር ጥሩ ሆኖ እያለ፣ የጋራ የሚያደርግ የጋራ ቋንቋ በተለይም አማርኛ በትምህርት ቤቶች ልጆች በደንብ እንዲማሩ አለመበረታታቱ ለአገር አንድነትና ዕድገት እንቅፋት እንደሆነ ተረጋግጧል። አሁን የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል ፍኖተ ካርታ መሠራቱንና እሱንም መሰረት አድርጎ ለውጥ መደረጉ ተገቢ ነው። በተለይም አማርኛ ከእንግሊዝኛ ጋር ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ መሰጠቱ አንድ የፖሊቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እጅግ በጣም ጥሩ ጅምር ነው።

አንዳንድ ኮርሶች በአንድ ሆነው፣ የዲፓርትመንቱ ኮርሶች ክሬዲት የሚጨምርበት መንገድ ቢታሰብበት ጥሩ ነው። ለምሳሌ ፍሬሽማን ላይ ‘Moral Education and Critical Thinking’, ‘Emerging Technologies and Global Trends’, and ‘Inclusiveness’, and ‘Anthropology’ በአንድ ቢሆኑ ጥሩ ይሆን ነበር ባይ ነኝ። ለማንንኛውም ሙሉ የትምህርት ስርዓቱን ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያለውን በአንዴ ማየትና መስተካከል ያለበትን ያለበትን አሁኑኑ ማስተካከል ይስፈልጋል። የአገር ውስጥ ዕውቀት የሚሰነድበት መንገድም ሊታስብበት ይገባል። ይህን የሽምደዳ የቃል ትምህርት ማቆም፣ የትምህርቱን መሰረታዊ ዓላማ ታሳቢ ባደረገ መንገድ፣ የተግባርና የህልዮት ትምህርቱ አብሮ መሔድ አለበት። ለዚህም የሜዳ፣ የላብና የወርክሾፕ ሥራዎች መበረታታት አለባቸው። በሥራ ላይ ያለው የትምህርት ስርዓት ችግር እነኝህን አለመሟላቱ መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በየዩኒቨርሲቲው ያለው መምህር ብቃት ያለውና መስፈርቱን የሚያሟላ እንዲሆን መሠራትም አለብት። የግብዓት አቅርቦት በተለይም፣ መምህር፣ ላቦራቶሪ፣ ወርክ ሾፕ፣ ኬሚካሎች፣ ጥቅማ ጥቅም እና ጥራት ላይ መነጋገርና ችግሮችን መፍታት ያስፈለጋል። ሁሉም የመምህር መስፈርትን ማሟላቱን መፈተሽ የትምህርትን ዓላማ ለማረጋገጥ ያስችላል።

ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ የኦነግን የኦሮሞኛ ጽሑፍ በግዕዝ ፊደላት ሳይሆን በላቲን ፊደላት ይሁን የሚል ጥያቄ የራሱ በማድረግ እንዲፈፀም አድርጓል። በላቲን የመፃፍ ሒደትን አዋጭ አለመሆንና የአገርን አንድነት ከመሸርሸር አንጻር ያለውንና የሚኖረውን አስተዋፅዖ ስምምነት መደረስ አለበት፣ በላቲን መጻፍ የተወሰነበት ምክንያትን በግእዝ መጻፍ ስለማይቻል ሳይሆን የኦነግ/ኦሕዴድ/ሕወሓት አማርኛን የማዳከም የፖለቲካ ሴራ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም የብዙ ኦሮሞ ወገኖቻችን የሥራና የቦታ ምርጫ ተወስኗል። አሁን ደግሞ ኦሮምኛ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን እየተጠየቀ ነው።

ማንኛውም ከሰማንያ በላይ የኢትዮጵያ ቋንቋ፣ ኦሮምኛን ጨምሮ ሕዝብ ከወሰነ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ከተደረገና ይህን የላቲን ፊደል ትተው በግእዝ ፊደል ከተጻፈ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ቢሆን ችግር የለብኝም። ነገር ግን ከምንም ውሳኔ በፊት መታሰብና መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ማንም ቋንቋ የፌዴራል ቋንቋ ሆኖ ከመወሰኑ በፊት የትምህርት ስርዓታችን በምን ቋንቋና ለምን በዚያ ቋንቋ መሰጠት እንዳለበት፣ የግብዓት አቅርቦትን፣ የፖሊሲ ውሳኔዎችን፣ የቋንቋዎች ድርሻንና ትግበራን መሰረት ያደረገ ጥናት አድርጎ ስምምነት መደረስ አለበት። ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን ለፖለቲካችን ትርምስ ሌላ ግብዓት መጨመር እንዳይሆን ያሰጋል። ጥያቄው፣ የኦሮሞ ልኂቃን ወጣቱን ማንነቱን እንዲያጣና ተወዳዳሪ እንዳይሆን ካደረጉት በኋላም ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ ወይስ ኦሮምኛ የፌዴራል ቋንቋ፣ ቀጥሎ ደግሞ የኩሽ ሁሉ ቋንቋ ይሁን እያሉ አገር ያተራምሳሉና ነው።

አንድ ቋንቋ የፌዴራል ቋንቋ ይኹን ሲባል በቢሮክራሲው የሚያመጣው ችግር ሊታሰብበት ይገባል። ታሳቢ የተደረገው በላቲን መማርና አማርኛን የጠላት ቋንቋ አድርጎ በመስበክ ዜጋን ከፌዴራል ቅጥር ውጭ ካደረጉ በኋላ “የእኔ ቋንቋ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ የሚሆነው ሥራ ለማግኘት ነው” ከተባለ የቢሮክራሲው ችግር እንደሚመጣ የታወቀ ነው። ለችግሩ ተጠያቂዎቹ ኦነጎችና የቋንቋ ምሁራን ነን ባይ እና ደጋፊዎቻቸው እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። አሁንም መፍትሔው ዜጎች ሁሉ አማርኛ በደንብ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ማድረግ ነው። በኦሮሚያ ክልል ብዙ አማርኛ ተናጋሪ ባለባቸው ቦታዎችም ከኦሮምኛ ጎን አማርኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆንም በሩ መከፈት አለበት። እናም ለምን የፌዴራል ቋንቋ እንደሚሆን፣ እንዴት እንደሚተገበር ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ በተጨማሪ ዝርዝር በሆነ ሕግ ጭምር መቀመጥ አለበት።

እያየንና እየሰማን ያለነው ግን የኦሮሞ ልኂቃን አገር የማተራመስ ሒደታቸውን እንደቀጠሉ መሆኑን ነው። በአመጽ መንግሥትን ማውረድ እንጂ አገር መመስረትና መገንባት፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ መንደፍ፣ ሕግ ማውጣት፣ ተቋማት መገንባት እንደማይቻል አልተረዱም። ኢትዮጵያን ኦሮሞ ማድረግና የኩሽ መንግሥት መመስረት ይቻላል በሚል ቀቢጸ ተስፋ፣ ማንነትን መካድና አባቶቹ የፈጠሩትን የግእዝ የፊደልና ቁጥር ሥነ ጽሑፍ ትቶ ወደ ባሕር ማዶ ተሻግሮ የላቲን ፊደል ተጠቃሚ መሆን ማንነትን ማግኘት ሳይሆን መካድ ነው። የኦሮሞ ልጆች አማርኛን አይማሩም፣ እንግሊዝኛን ግን ይማራሉ ማለት የአገርን እና የዜጎቿን ተስፋ ማሳጣትና የቀኝ ተገዥ ዝቅተኝነት ስሜትም ነው፤ አማርኛ በአገር ውስጥ፣ እንግሊዝኛ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መግባባት እንድንችል ያግዙናልና።

አማርኛ አልማርም የሚለው እያከራከረ ያለው፣ የጋራ እሴት የሌለው ሕዝብ ራሱን መርዳት ስለማይችል፣ ነገ ለሁላችን ችግር ፈጣሪ ስለሚሆንም ነው። የጋራ እሴት የሚኖረው ደግሞ የጋራ ቋንቋ ሲኖር ነው። አማርኛ ቋንቋን አንማርም ማለት ግን ኢትዮጵያዊነትን መካድ ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቋንቋ ነውና። የትምህርት ስርዓቱና ቋንቋ አጠቃቀም አይቀየርም፣ ሕገ መንግሥቶች አይሻሻሉም፣ በዘውግ ፓርቲ ማቋቋም አይከለከልም፣ የፌዴሬሽኑ አወቃቀሩ አይስተካከልም፣ የመሬት ባለቤትነት ሕግ አይሻሻልም፣ ልዩ ኀይልን ማፍረስ አይቻልም እያሉህ ይቆዩና ኦሮምኛ ግን የፌዴራል ቋንቋ መሆን አለበት ይሉሃል፤ ያለ ሕገ መንግሥት መሻሻል እንዴት ሊሆን እንደሚችል ግን አይነግሩህም። እንዲያው የተምታታበት የአገር ክህደት ቧልት ነው የያዙት። ኢትዮጵያ ካፈጣጠሯ በአማርኛ ተናጋሪው ርዕዮት የተቃኘች መሆንዋን መርሳትና ይህን ለመናድ መሞከር፣ አገርንም እራስንም ማፍረስ መሆኑን የረሱትም ይመስላሉ።

ሕገ መንግሥትንና የዘር ፌዴራል አወቃቀርን ሕዝብ ሳይፈልግና ሳይወስን ሕወሓትና ኦነግ በሕዝቡ ላይ በኀይል እንደጫኑበት ሁሉ፣ የቋንቋ ጉዳይንም በተመሳሳይ መንገድ እንሒድ ካሉ የነገ መዘዙ ብዙ ይሆናል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደርም ሕዝብ ሳይመክረበት፣ በቄሮ ማስፈራሪያ፣ የቋንቋ ጥናትና ፖሊሲ ሳይውጣ የኦሮምኛን ቋንቋ ብቻ የፌዴራል ቋንቋ ሊያደረገው መሞከር አደጋውን ማወቅ አለበት። ምክንያቱም፣ ይህ ድርጊት የአገሪቱን የቋንቋ አጠቃቀም ችግር የማይፈታ፣ የሌሎችን ማኅበረሰቦች ቋንቋ የመጠቀም የፍትሐዊነትና የእኩልነት ጥያቄ አይመልስምና። እናም የአንድ አገር ዜጎች የጋራ መግባቢያ እንዳይኖራቸው አስቦ መሥራት ወንጀል ነውና፤ መንግሥት እየታዩ ባሉት ነገሮችና በፈጻሚዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። ይህን ፈጻሚዎች በጊዜ ልካቸውን ካላዎቁ የአገር ደኅንነትና የሕዝብ አንድነት እንዳይናጋ እሰጋለሁ።

መላኩ አዳል የዶክትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here