የማኅበራዊ ሚዲያ ምፅዓት

0
1248

የማኅበራዊ ሚዲያን አደገኛ ጎን ለመቀነስ ኹነኛው መፍትሔ ማገድ አይደለም የሚሉት በፍቃዱ ኃይሉ፥ በዚህ የመረጃ ዘመን ዴሞክራቶችና አሪስቶክራቶች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ አተያይን ተመሳሳይነት እና ተቃርኖ ቃኝተውታል።

 

 

ምሁራን አሁን ያለንበትን ዘመን ‘የመረጃ ዘመን’ ይሉታል። ይሁንና የመረጃ ፍሰቱ ፍጥነት መንግሥታትም ይሁኑ ሌሎች የሚቆጣጠሩት አልሆነም። ሁሉም ደንግጠዋል። በዚህም ምክንያት ‘የማኅበራዊ ሚዲያ ምፅዓት’ ብዬ ልጠራው የምፈልገው፣ በተለይም ደግሞ የፌስቡክ መከሰት ዴሞክራቶች እና አውቶክራቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ አሥማምቷል ማለት ይቻላል። ኹለቱም ቡድኖች ማኅበራዊ ሚዲያን ይጠላሉ። ልዩነታቸው ዴሞክራቶቹ የማስወገድ ሥልጣን የሌላቸው በመሆኑ ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ፥ አውቶክራቶቹ ደግሞ ሊያፍኑት ይሞክራሉ።

ዴሞክራሲያዊ vs. አውቶክራሲያዊ አረዳድ
ዴሞክራሲን እንደ አንድ የመንግሥታዊ ስርዓት “የተሻለ ነው፣ አይደለም” በሚል የሚደረጉ ዘመን አቋራጭ ክርክሮች አሉ። ዴሞክራሲ ሕዝባዊ ተሳትፎን መርሕ ያደረገ መሆኑ ዋነኛ መገለጫው ነው፤ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሪዎች ተራ የሕዝብ አገልጋይ ናቸው ተብሎ ይታሰባል። ሕዝብ አድርጉ ካላቸው በላይ የማይሠሩ መሆን አለባቸው። የሚያምኑበትን ሕግ ለማውጣት ሳይቀር የሕዝቡን ይሁንታ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። አለበለዚያ በድምፅ እንቀጣለን ብለው ይፈራሉ።

አውቶክራሲ በተቃራኒው በልኂቃኑ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ ስርዓት ነው። ሕዝብ የሚፈልገውን ሳይሆን የሚያስፈልገውን በመስጠት መርሕ ላይ ነው የሚንቀሳቀሰው። ዴሞክራሲ ከፈለቀባት የአቴና መንደር የበቀለው ፈላስፋ ፕሌቶ ‘ዘ ሪፐብሊክ’ የተሰኘ መጽሐፍ አበርክቷል። መጽሐፉ ከዴሞክራሲ ይልቅ ለአውቶክራሲ ቢባል ለማመን ይቸግር ይሆናል። ነገር ግን እንደ ፕሌቶ “የአገር መሪ መሆን ያለበት ፈላስፋ ነው፤ አለበለዚያ ደግሞ የአገር መሪ የሆነው ሰው መፈላሰፍ መጀመር አለበት”። የአውቶክራሲ አስተሳሰብ ይኸው ነው፤ ብዙኀን የሚያስፈልጋቸውን አያውቁም ወይም ፍላጎቶቻቸውን አያስታርቁም በሚል ሰበብ የሚጠቅማቸውን የሚወስንላቸው የላቀ ክሕሎት ያለው መሪ ያስፈልጋቸዋል በሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ ስርዓት ነው።

የአብርኆት ዘመን ፈላስፋዎች ዴሞክራሲ ላይ የተከፋፈለ አቋም ነበራቸው። “ዴሞክራሲ የአማካይ (mediocre) ሰዎች ስርዓት እንጂ የልኂቃን አይደለም” የሚለው ክርክር የተነሳው ያኔ ነበር። የሆነ ሆኖ በፈረንሳይ አብዮት እና በአሜሪካ ነጻነት የተቀጣጠለው ዴሞክራሲያዊ አብዮት አሁን በዓለም ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ስርዓት ሆኗል። ነገር ግን ዴሞክራሲ የጥቂቶች ሆኖ መክረሙም የአደባባይ ምሥጢር ነው።

በዴሞክራሲ ሥር የሰደደ ልምድ እና ታሪክ አለን የሚሉት ምዕራባውያን በማኅበራዊ ሚዲያ ምፅዓት ዴሞክራሲያዊ ባሕላችን ተናጋ በሚል ደንግጠዋል። ቀድሞ የነበሩት ምርጫዎቻቸው በኮርፖሬት ሚዲያዎች የሚመሩ እና ሚዲያዎቹ እና ልኂቃኑ ከሌላው ሁሉ የበለጠ ድምፅ የሚያገኙበት ዴሞክራሲ ነበር። ትውፊታዊዎቹ ብዙኀን መገናኛዎች (traditional media) ወይም ልኂቃኑ የወደዷቸው ዕጩዎች የሚመረጡበት፣ ሌሎቹ ደግሞ የሚገለሉበት ዴሞክራሲ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ዴሞክራሲ ለዘብተኛ አውቶክራሲ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ እንደማሳያ
የአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ፣ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት መወሰን (‘ብሬግዚት’)፣ እንዲሁም በአውሮፓ የቀኝ ዘመም አክራሪ ብሔርተኞች ማቆጥቆጥ የማኅበራዊ ሚዲያ ምፅዓት ያስከተለው እንደሆነ መግባቢያ ላይ ተደርሷል። እንደ ወትሮው ቢሆን ትራምፕ ትውፊታዊ ብዙኀን መገናኛዎች እና ልኂቃን የሚደግፏቸው ዓይነት ሰው ስላልሆኑ፣ የመመረጥ ዕድላቸው ጠባብ ነበር። ምንም እንኳን እንደ ‘ፎክስ’ ያሉ የሚደግፏቸው ትውፊታዊ ብዙኀን መገናኛዎች ቢኖሩም፥ የሚበዙት ግን የሚቃወሟቸው ናቸው። ሆኖም የትራምፕ መራጮች በመባል የሚታወቁት መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነጮች እና የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች በተለይ በፌስቡክ በተደረገው ዘመቻ ዶናልድ ትራምፕን ከልኂቃኑ ተቃውሞ አትርፎ አብላጫ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል። የብሬግዚት ውጤትም ተመሣሣይ ነው። ይህ የአሜሪካን እና የእንግሊዝን አማካይ ብዙኀን ፍላጎት እና ማንነት ገላጭ ውጤት ነው ብለው የሚከራከሩትን ያህል በተቃራኒው የማኅበራዊ አሳሳች ሚና ውጤት ነው ብለው የሚሞግቱም ሞልተዋል።

ልኂቃኑ እና ትውፊታዊ ብዙኀን መገናኛዎች ቀድሞ የነበራቸውን የመወሰን ዘመን በማኅበራዊ ሚዲያ ምፅዓት ተነጥቀዋል። በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያ ተደራሽነት ከፍተኛ በሆነባቸው አገራት በቀጥታ፣ በሌሎቹ ደግሞ በሥማ በለው ዜጎች ስለሚደግፉት ዕጩ ወይም ቡድን ወይም ሐሳብ የፈለጉትን ዓይነት መረጃ የሚያገኙበት፣ ምሥጢር የማይደበቅበት ወይም ፕሮፓጋንዳ እና ቅስቀሳ ዜጎች ለዜጎች የሚያራምዱበት ዘመን ነው። ሆኖም ይህንን ሕዝቦች በልኂቃን እና በኮርፖሬቶች የተደራጀ ቅስቀሳ የሚመረጡ ዕጩዎችን በር ሊዘጋባቸው ቢችልም፥ ለሌሎች የዜጋ ለምድ ለለበሱ ተኩላዎችም በሩን ከፍቷል። ለፖለቲካ ዓላማ የተፈለፈሉ የሐሰት እና አሳሳች ዜናዎች መራጮችን በተሳሳተ መረጃ፣ ድምፃቸውን ለማይጠቅሟቸው ዕጩዎች እንዲሰጡ እያደረጋቸው ነው።

ሐሰተኛ እና አሳሳች ዜናዎች
በርካታ እንግሊዛውያን “የብሬግዚት አሳዛኝ ፍፃሜ በራሽያ የማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ ዜናዎች የተፈጠረ ነው” ብለው ይከራከራሉ። አሜሪካውያንም ራሺያ ዶናልድ ትራምፕ እንዲመረጡ በአሜሪካውያን ሥም በተፈጠሩ ሐሰተኛ የፌስቡክ ገጾች ተቀናቃኞቻቸው ላይ የሐሰት እና አሳሳች ወሬዎችን በመልቀቅ ቅስቀሳ አድርጋለች ብለው ያስባሉ። በተለያዩ አገራት ፖለቲከኞች ምርጫን ለማሸነፍ በርካታ ሴራዎች ተጎንጉነዋል። ካምብሪጅ አናሊቲካ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ በመውሰድ እና የተጠቃሚዎቹን ባሕሪ እና ዝንባሌ በማጥናት ፖለቲከኞች የምርጫ ቅስቀሳዎችን በዚያ መልኩ እንዲያሰናዱ አድርጓል። በብራዚል ምርጫ ወቅት በዋትሳፕ ብቻ ከተለቀቁ መቶ ሺሕ ምሥሎች ውስጥ ግማሹ (ሃምሳ ሺሕዎቹ) ሐሰተኛ እና አሳሳች ምሥሎች እንደነበሩ በጥናት ተረጋግጧል። በአጭሩ ስለምንመርጣቸው ዕጩዎች እና ስለተቀናቃኞቻቸው ያለን መረጃ ትክክለኝነት ላይ እርግጠኛ መሆን የማንችልበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ሆኖም ብዙኀን እነዚህን የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ያለጥርጥር አምነው ይቀበላሉ።

ኢንተርኔት መዝጋት እንደ መፍትሔ
አውቶክራት መንግሥታት የማኅበራዊ ሚዲያ ምፅዓት ያስከተለባቸውን ዕዳ በሳንሱር መሻገር ነው ምኞታቸው። በ1990ዎቹ፣ ኢንተርኔት ብርቅ በነበረበት አፍላ ጊዜ ኢንተርኔትን በጥርጣሬ ይመለከቱት የነበሩት የቻይና ኮሙኒስቶች ነበሩ። ምዕራባውያን የቻይናን ጥርጣሬ እና የማገድ ሙከራ በስላቅ ነበር የተመለከቱት። በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ቢል ክሊንተን አንድ መድረክ ላይ “ቻይና ኢንተርኔትን መቆጣጠር ያምራታል” ይሉና ሳቃቸው ያመልጣቸዋል፤ ከዚያም “መልካም ዕድል” ሲሉ በስላቅ የማይቻል መሆኑን በማመልከት አጀንዳውን ይዘጉታል። ከዚያ በኋላ ቻይና “ግሬት ፋየርዎል” የተባለ የኢንተርኔት ማጥለያ ሶፍትዌር ገንብታለች። ከማኅበራዊ ሚዲያ ዕድገት ጋር አብራ እየገሰገሰች ከሥር ከሥር ፖለቲካዊ የተቃውሞ ቃላትን ማጥለሏን ቀጥላለች።

ዛሬ ቻይናውያን ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ እና ዩቱዩብ የመሳሰሉትን እንዳይጠቀሙ ታግዶባቸዋል። ሆኖም የራሳቸውን እንደ ‘ባይዶ’ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ፈጥረው ዜጎቻቸው የሚያነጥሱትን ሳይቀር ይሰልላሉ። በቻይናውያን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚጻፉትን ነገሮች መንግሥት ካልወደደው ያጠፋቸዋል። የተጠቃሚዎችን አካውንት ሙሉ ለሙሉ እስከማጥፋት የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይችላል። ይህንን ቻይና ብታደርገውም የሁሉም አውቶክራቶች ምኞት ነው።
ይሁንና ቻይናውያንም ቢሆኑ አርፈው አልተቀመጡም። የመንግሥት የተቃውሞ ድምፆች ማጥለያ ማሽኖች እንዳያገኙባቸው የሰውኛ ብልሐታቸውን በመጠቀም ያሻቸውን መጻፋቸውን ቀጥለዋል። ምሥሎችን በፎቶሾፕ በማንጋደድ እንዲሁም ቃላትን በመግደፍ የሳንሱር ማሽኑ ሳያውቅባቸው መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ተፈጥሮ ያጎናፀፈቻቸውን ሐሳብን የመግለጽ መብቶቻቸውን ይተገብራሉ።

የራሺያ መንግሥት ደግሞ ብሎገሮችን እና የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን በመቅጠር ትርክት ለመቆጣጠር ይሞክራል። ሁሉንም የማድረግ አቅሙ የሌላቸው የአፍሪካ አውቶክራቶች ደግሞ ኢንተርኔትን ከናካቴው በመዝጋት በመረጃ ዳፍንት ውስጥ ምርጫዎችን ያካሒዳሉ። ለሁሉም ችግር ማኅበራዊ ሚዲያን መውቀስ ከሚወዱ መንግሥታት መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት አንዱ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የቀጣዩ ዓመት ምርጫ እየቀረበ ሲመጣ ግጭቶችን በማስወገድ ሰበብ ማኅበራዊ ሚዲያን ብቻ ሳይሆን፥ ኢንተርኔትን ማገድንም ጭምር መፍትሔ አድርጎ እንደሚወስደው ለመገመት ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም።

የመድረኩ ገለልተኝነት
አውቶክራት መንግሥታት ሊረዱት የማይፈልጉት ነገር ቢኖር የማኅበራዊ መድረኮች በራሳቸው ገለልተኛ መሆናቸውን ነው። የሚያጠፉትም፣ የሚያለሙትም የሚጠቀሙባቸው ሰዎች ናቸው። ለጥፋት የሚጠቀሙባቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ለልማት የሚጠቀሙባቸው ግን ቁጥራቸው የበለጠ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ሐሰተኛም ይሁኑ አሳሳች መረጃዎች ዛሬ ለም መሬት አግኝተው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቢፈሉም፣ ነባር የዓለም ታሪክ አካል ናቸው። ‘LikeWar’ በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ርዕሰ ጉዳዩን የዳሰሱት ሲንገር እና ኤመርሰን ብሩኪንግ የተባሉ ደራሲዎች፣ ሐሰተኛ ዜናዎች ከኅትመት መጀመር እኩል ዕድሜ ጠገብ እንደሆኑ ይናገራሉ።

በ18ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው አጋማሽ ሲጽፏቸው የነበሩትን ነገሮች ጠቅሰው፣ የአሜሪካ መሥራች አባቶች ከሚባሉት መካከል ቤንጃሚን ፍራንክሊንን “የአሜሪካ ሐሰተኛ ዜና መሥራች አባት” (“Founding father of American fake news”) ብለው ይቀልዱባቸዋል። ቁም ነገሩ፣ ሐሰተኛ ዜናዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ስለመጡ ወይም ስለሔዱ የሚመጡ እና የሚሔዱ ነገሮች ሳይሆኑ፣ ነባር መሆናቸውን ማመልከት ነው። የመረጃ ልውውጥ ዘዴዎች በተቀላጠፉ ቁጥር፣ በስህተትም ይሁን ለእኩይ ዓላማ የሚፈበረኩ ሐሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች መብዛታቸው አይቀሬ ነው።

የማኅበራዊ ሚዲያን አደገኛ ጎን ለመቀነስ ሁነኛው መፍትሔ ማገድ አይደለም። የመንግሥታትን ግልጽነት መጨመር፣ የዜጎች የሚዲያ ግንዛቤ ማደግ፣ የፖለቲከኞች ሐቀኝነት፣ የብዙኀን መገኛዎች ገለልተኝነት እና ሞያተኝነት ናቸው። ዴሞክራቶቹ እየተከተሉ ያሉት ይህንን መንገድ ነው።

በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here