የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተጨማሪ ኹለት ቋንቋዎች ኅትመት ሊጀምር ነው

0
691

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከመጪው መስከረም ወር 2012 መጀመሪያ አንስቶ በሶማሊኛ እና በትግሪኛ ቋንቋዎች ኅትመት ለመጀመር ቅድመ ዘግጅቱን አጠናቀቀ።
ድርጅቱ መረጃዎቹን በተለያዩ ቋንቋዎች ለሕዝብ ለማድረስ ኹለቱን ቋንቋዎች ጨምሮ ጋዜጦችን ለማሳተም የሰው ኀይል እና የፋይናንስ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን የይዘት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሄኖክ ስዩም (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

እነዚህ አዲስ የሚጨመሩት ጋዜጦች እያንዳንዳቸው ስምንት የገፅ ብዛት ይዘው የሚመሰረቱ ሲሆኑ በሳምንት አንዴ አንባብያን እጅ የሚደርስ ሲሆን በሳምንት ውስጥ መቼ እንደሚወጣ አልተወሰነምም ተብሏል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣን ለ1933 ዓመት ያለማቋረጥ ያሳተመው ፕሬስ ድርጅት በሳምንት ለስድስት ቀናት በእንግሊዘኛ “ዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ” የተሰኘውን ጋዜጣ ያሳትማል። በተጨማሪም በአፋን ኦሮሞ “በሬሳ” እና በአረብኛ “አል ዓለም” የተባሉ ጋዜጦችን በሳምንት አንድ ጊዜ በአርበ ጠባብ (‘ታብሎይድ’) መጠን ያሳትማል። በየኹለት ወሩ የምትዘጋጀው ዘመን መጽሔትም የድርጅቱ አምስተኛ የኅትመት ውጤት መሆኗ ይታወቃል።

የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስከያጅ ጨምረው እንደገለፁት የመንግሥት ባለበጀት ሚዲያ የሆነው ድርጅቱ ከዚህ በፊት በአራት የተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት እየሰጠ ቢቆይም ሁሉንም አንባቢ ያማከለ አለመሆኑን ይናገራሉ። ለዚህም እንደምክንያት የአገሪቱ ዜጎችን በያሉበት በቋንቋቸው አንባቢው መድረስ ያለመቻላቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

“ከአንባቢዎቻችን እንዲሁም ከአካባቢው ኃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ የሰው ኃይል አደራጅተን ወደ ሥራ ገብተናል” ብለዋል። “በመጪው መስከረም በኹለቱ ቋንቋዎች ለሕዝቡ ተደራሽ ይሁኑ እንጂ በሚቀጥሉት ዓመታት በሌሎች የአገር ውስጥ ቋንቋዎችም ሰፊ ሥራ እንሠራለን።”

የሶማሌ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሂባ አህመድ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት አዲስ በተጨመረው ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል። ምክንያቱም ደግሞ የአካባቢው ማኅበረሰቦች ብዙ ጊዜ የራሳቸውን ቋንቋ ይጠቀማሉ። ሆኖም በራሳችን ቋነቋ አዳዲስ ነገሮችን መመልከት መቻላችን ሚበረታታ ነገር ሲሆን ኅትመቱን በሶማለኛ ቋንቋ ማቅረብ መጀመሩ እንደግፈዋለን ብለዋል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሕዝብ እንደመሆኑ መጠን አገልግሎቱም ሁሉንም ኅብረተሰብ ያማከለ መሆን ነበረበት። ምክንያቱም በጀት ተመድቦለት የሚያገለግል የመንግሥት ሚድያ አሁን ካሉት ቋንቋዎች በተጨማሪ አብዛኛው ሕዝብ በሚጠቀምበት ቋንቋ ማሳተም ጥሩ ሆኖ ሳለ እነዚህ ቋንቋዎች እንዴት ተመረጡ በምን መስፈርት የሚባለው ግን ግልፅ አይደልም ሲሉ በሚድያ ጥናትና ምርምር የረጅም ዓመት ልምድ ያካበቱ ባለሙያ አስተያየት ሰጡ።

አያይዘውም ከዚህ በበለጠ ሰፊ የሆነ ሥራ እንዲሠራ ይጠበቃል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አገሪቱ ላይ ያሉት ቋንቋዎችን በሙሉ ማዳረስ ባይቻልም አንዳንድ እየተባለ መጨመሩ የሚደገፍ ነውም ብለዋል።

ከእነዚህ የኅትመት ጭማሪዎች ባሻገር ሳምንታዊ የሆነችው በሪሳ ጋዜጣ በሳምንት ሦስት ቀናት እንድትታተም ለማድረግ በስፋት እየተሠራ መሆኑን ድርጅቱ የአዲስ ዘመን ጋዜጣን 78ኛ ዓመት ባከበረበት ወቅት መጥቀሱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በ1933 የተመሠረተ የመንግሥት የኅትመት መገናኛ ብዙኀን ድርጅት ነው። ድርጅቱም አሁን ላይ ከ300 በላይ ሠራተኞች ያሉትና በራሱ ገቢ የሚተዳደር ተቋም ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here