“የሴቶችን መብት ለማሳነስ ሕገ መንግሥቱን እስከመተው?”

0
640

ቤተልሔም ነጋሽ በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ረቂቅ” በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን መነሻ በማድረግ፥ ከሴት ተወዳዳሪዎች ጋር በተያያዘ የተካተተውን አንቀጽ አግባብነት የለውም ሲሉ ተችተዋል። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35 የተዘረዘሩትን የሴቶች መብት አትንጠቁን ሲሉም ሞግተዋል።

 

 

በዜና እንደሰማችሁት ወይንም እንዳያችሁት ነሐሴ 18/2011 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር” ረቂቅ ሕግ አጽድቋል። እስካሁን ባየሁትና በገጠመኝ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ውጪ (ድሮ 1 ሺሕ 500 ፊርማ የነበረው አሁን ለምን 10 ሺሕ ሆነብን በሚል) ይህ ጎደለው ወይንም ትክክል አይደለም ብሎ የትኛውም አካል ጠንካራ ተቃውሞ ያቀረበበት አልነበረም። ምናልባትም በዚሁ ጋዜጣ ከሳምንታት በፊት የሴቶች ውክልናን ለሚጨምሩ ፓርቲዎች ማበረታታቻ አለማድረጉ ወይንም በቂ ኮታ በሴቶች እንዲያዝ አለመደንገጉ ተጠቅሶ ከተተቸው ውጪ ማለት ነው።

ባልተመለደ መልኩና ምናልባትም ሕገ መንግሥቱ ለሴቶች የሰጠውን መብት በሚጥስ ሁኔታ የሴቶች ውክልናን በፓርላማዎች መቀመጫ ማሳደግ የሚችል የተካተተ አንቀጽ በምክር ቤቱ በድምጽ ብልጫ ውድቅ ተደርጓል። በእነማን ብትሉ በድምጽ ብልጫ ውስጥ ባሉት ብቻ ሳይሆን ትክክል አይደለም ብለው ባሰቡ ሴት የፓርላማ አባላት ጭምር። እኩልነት ማለት ይሔ አይደለም ብለው ባመኑ፣ ኢሕአዴግ በሰጠው 30 በመቶ ኮታ ምክንያት ምክር ቤቱ በገቡ ሴት የፓርላማ አባላት ጭምር።

አንቀጹ ምን ነበር ሴትና ወንድ እኩል ውጤት ቢያመጡ ሴቷ እንድታሸንፍ ይደረጋል። ቢበልጣት አልተባለም፣ ቦነስ ይሰጣት አልተባለም፣ እኩል ቢያመጡ። በሌላ አነጋገር በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው የውድድር ሜዳው እስኪደላደል (ለሴቶች በብዙ መልኩ አሁንም ረባዳ ላይ የቆሙ ናቸውና) ነጥቡ እኩል ቢሆን ይህቺ ቅድሚያ ትኑራቸው ነው። በነገራችን ላይ በሲቪል ሰርቪስ ቅጥር ለሴት እኩል ብታመጣ ቅድሚያ መሰጠት ያለ አሠራር ብቻ ሳይሆን በደረጃ ዕድገት ጭምር ተጨማሪ ነጥብ ያሰጣል። በዩኒቨርሲቲዎች መግቢያም እንደምታዩት ለሴቶች የተወሰነ ድጋፍ ይሰጣል፣ በእኩል ዓይን እየታዩ መጫወቻ ሜዳው ተስተካክሎ አላለቀምና።

ሌላው ጥርስ አልባ ሆኖ ለዓመታት ቆይቶ አሁን መነቃቃት ያሳየው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሕገ መንግሥቱን እንደማያውቁትና በተለይም የሴቶች መብቶችንና የሥርዓተ ፆታ እኩልነት መርሆዎችን በሚመለከት ገና ግንዛቤ የሚያሻቸው መሆኑን ያሳየ ውሳኔ መሆኑን መጥቀስ ያሻል እዚህ ላይ።
እስቲ ከላይ ያነሳሁት ሕግ፥ በሕግ ባለሙያዎች አንጻር በምን መልኩ እንደታየና ዜናውስ ምን እንደሚል እንመልከት።

ማርታ ካሳ የተባሉ የሕግ ባለሙያ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው እንዲህ ብለዋል፤
“የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ለሴቶች ልዩ ድጋፍ የሚያደርገውን አንቀጽ ውድቅ ያደረጉበት አግባብ ሕገ መንግሥቱ ታሪካዊውን ሴቶች ወደ ኋላ የቀሩበትን ሒደት ለማካካስ ለሴቶች ልዩ ድጋፍ እርምጃ ይወሰዳል የሚለውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ የሚፃረር ነው። የምርጫ ቦርድም ይህንን የተመጣጠነ ውክልና ለሴቶችና ለወንዶች ሊደረግ የሚችልበትን አንድ መንገድ በሕግ ለማጸደቅ የተሻለ ትግል ማድረግ ይጠበቅበት ነበር”
“በእውነቱ ፓርላማችን የፆታ እኩልነት ፅንሰ ሐሳብ ዘልቆታል! ማፈሪያዎች!” ከሚል አስተያየት ጋር ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ የሆኑት ቁምላቸው ዳኜ የተባሉ ባለሙያ በፌስቡክ ያጋሩት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ዜና እንዲህ ይላል።

“አዲሱ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ ፀደቀ
ተሻሽሎ የቀረበውን የኢትዮጰያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ረቂቅ አዋጅን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ አፀደቀው።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ክርክር ካደረገ በኋላ ነው በሙሉ ድምፅ ያፀደቀው።

ይሁን እንጂ ወንድ እና ሴት ተወዳዳሪዎች እኩል ድምጽ ቢያገኙ ሴት ተወዳዳሪዋ እንደምታሸንፍ በረቂቅ አዋጁ ላይ ቢቀመጥም ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ ውድቅ አድርጎታል። ምክንያቱ ደግሞ የፆታ እኩልነትን መርህ የሚፃረር የሚል ነው።

ዛሬ በፀደቀው ረቂቅ አዋጅ የመንግሥት ሠራተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ በምርጫ ቅስቀሳና በውድድር ቢሳተፍ ያለ ደሞዝ ፈቃድ ማግኘት እንደሚችል ይደነግጋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ከአባልነት ለመሰረዝ ቢፈልጉም ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ ማሰናበት እንዲችሉም ፈቃድ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
በፀደቀው ረቂቅ አዋጅ መሰረት ለግል ለተወዳዳሪዎች መንግሥት ድጋፍ እንደሚሰጥም ተደንግጓል።”

አንቀጽ 35 – የሴቶች መብት
ሴቶች ይህ ሕገ መንግሥት በአረጋገጣቸው መብቶችና ጥበቃዎች በመጠቀም ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው።
ሴቶች በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሠረት በጋብቻ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው።
ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው። በዚህ በኩል የሚወሰዱት እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግሥት እና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው።

ሴቶች ከጎጂ ባሕል ተጽዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግሥት ማስከበር አለበት። ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሮአቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶች የተከለከሉ ናቸው።
ሀ) ሴቶች የወሊድ ፈቃድ ከሙሉ የደሞዝ ክፍያ ጋር የማግኘት መብት አላቸው። የወሊድ ፈቃድ ርዝመት ሴቷ የምትሠራውን ሥራ ሁኔታ፣ የሴቷን ጤንነት፣ የሕፃኑንና የቤተሰቡን ደኅንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕግ ይወሰናል።

ለ) የወሊድ ፈቃድ በሕግ በሚወሰነው መሠረት ከሙሉ የደመወዝ ክፍያ ጋር የሚሰጥ የእርግዝና ፈቃድን ሊጨምር ይችላል።
ሴቶች በብሔራዊ የልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በኘሮጀክቶች ዝግጅትና አፈጻጸም፣ በተለይ የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ኘሮጀክቶች ሐሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው።

7) ሴቶች ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት አላቸው። በተለይ መሬትን በመጠቀም፣ በማስተላለፍ፣ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው። እንዲሁም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት አላቸው።

8) ሴቶች የቅጥር፣ የሥራ ዕድገት የእኩል ክፍያና ጡረታን የማስተላለፍ እኩል መብት አላቸው።

9) ሴቶች በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመከላከልና ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት መረጃ እና አቅም የማግኘት መብት አላቸው።

እንግዲህ ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ ሳይቀር የሴቶች መብት የሚሸራረፍ ከሆነ ምንድነው ጉዳዩ? ያደለው (ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳደረጉት) ሕግ ድጋፍ ሳይጠብቅ 50 በመቶ ካቢኔ ይሰጣል – በሕግና በተቋማዊ አሠራር ሊደገፍ የሚገባው መሆኑ እንዳለ ሆኖ – ሌላው ደግሞ ተሰብሰቦ “አይ እኩል ናችሁ ከተባለ በቃ የምን ድጋፍ ነው” ብሎ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይገናነኝ የሴቶችን እኩል የመሳተፍ ተስፋ የሚገድል ሕግ ያወጣል። የሕጉን ውጤት ለማየት እንግዲህ ብዙ መሔድ አያስፈልግም፣ በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ 38 በመቶ ደርሷል የተባለው የሴት ፓርላማ አባላት ቁጥር ተጠብቆ ይቆይ እንደሆን ማየት ነው። ለነገሩ ለሴቶች የሚበጅ ፖሊሲ ለማውጣት ካልሆነ አደረግን ከማለት ውጪ ቁጥር ምን ይጠቅማል?

እንደምታውቁት ከትምህርትና የሥራ ቋንቋ ጀምሮ እስከ አከላለልና ሌሎች በርካታ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ መፈፀም አይችሉም እየተባለ በሕገ መንግሥቱ ዘበኝነት ሲጠበቁ እያየን ነው። ታዲያ የሴቶችን መብት ለማሳነስ ሲሆን መጣሱ ብለን ብንጠይቅ ተሳሳታችሁ እንባል ይሆን?

ይህንን ያስባለኝ ሌላም ብዙ ነጥቦች አሉ። ይኸውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35 ከተደነገጉት 9 ዋና ዋና መብቶች የማይጣረስ የለም በሚያስችል መልኩ ሴቶች ሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው የተለያዩ ሕጎች (ሁሉንም የአገሪቱ ሕግ አካል አድርጋ መቀበሏ ይጠቀሳል ሆኖም ለአፈፃፀም የሚረዳ መዋቅርና የአሠራር ሥርዓት ባለመዘርጋቱ የወረቀት ላይ ነብር ሆነው ብቻ ቀርተዋል።) ያረጋገጡላቸውን መብቶች በልማዳዊና ሃይማኖታዊ ሕግና አሠራሮች ሲጣሱና ሲወሰዱባቸው ይስተዋላል። ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ሕገ መንግሥቱና የቤተሰብ ሕጉ አንዲት ሴት 18 ዓመት ሳይሞላት ማግባት እንደሌለባት ሲደነገግ አገራችን ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን በየዓመቱ እንደምትድር ባለፈው ሰሞን የአገሪቱ ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የተነደፈው ፍኖተ ካርታ ይፋ በሆነበት ወቅት ተጠቅሷል። በዚሁ ወቅት አንዲት ከአፋር የመጡ ተሳታፊ አስተያየት ሲሰጡ “በአፋር ያለውን ነገር እንዴት አያችሁት፣ በሸሪዓ 15 ዓመት ነው የሴት የጋብቻ ዕድሜ፣ ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት አፋር ካልሠራችሁ ድምር ውጤቱ ያው ነው” ብለው ነበር።

በዚሁ አንቀጽ 35 (2) ላይ ሴቶች በጋብቻ ውስጥ እኩል መብት አላቸው የሚለውን ብናይ እኩልነትና መብት ቀርቶ ከጥቃት መጠበቅም በሆነላቸው የሚሰኝ ነው እውነታው። “ሴቶች በብሔራዊ የልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በኘሮጀክቶች ዝግጅትና አፈጻጸም፣ በተለይ የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ኘሮጀክቶች ሐሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው።” የሚለውን ቁጥር 6 ለማየት በሕግ መሻሻልና ማርቀቅ ሥራ ላይ የሚዋቀሩ ኮሚቴዎችን የፆታ ተዋጽዖ ማየት ይበቃል። አብዛኛው ሴት የአገሪቱ ነዋሪ በዚህ ላይ ምንም ድምጽ የለውም ለማለት ይቻላል። ሌሎቹንም እንዲሁ ብዙ ለማለት ይቻላል። በቅርቡ ራሴ በተሳተፍኩበት ከሴቶች መብት ጋር ተዛማጅ ያልሆነና በሐዋሳ ለወጣት የኹለተኛ ደረጃ ተማሪ ሴቶች በተዘጋጀ ሥልጠና ማብቂያ ላይ ወላጆቻቸው ተጋብዘው ነበርና ተወክለው ንግግር ያደረጉት ሴቶች ከመሃል ከተማ (ከፌደራል) የሔድነውን ጭምር ልብ አድርጉ ብለው ለወላጆቻቸው የተናገሩት “እኛም ልጆቻችሁ ነን፣ ሴቶች ስለሆንን ብቻ ውርስ አትንፈጉን ገንዘብ ለእኛም ያስፈልገናል” የሚል ነበር። በበኩሌ በክልሉም ባይሆን በሐዋሳና አካባቢዋ ሴቶች ልጆች አይውረሱ የሚልና የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 7 የሚጥስ ልማዳዊ ማኅበረሰቡ የተቀበለው አሠራር መኖሩን አላውቅም ነበር። ብንጠይቅ ከዚህም የባሰ የመብት ጥሰት በየአካባቢ ሊፈፀም እንደሙችል እሙን ነው። ቢያንስ ግን እንደው በአደባባይ በፓርላማ ደረጃ በሕግ አምላክ የተሰጠንን መብት አትንጠቁን ለማለት ያህል ነው ይህን ጽሁፍ መፃፌ።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here