“ሻይ በጤና ሔዋን?!”

0
873

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሁሌ ዕቃ ለመግዛት በሔድኩበት ሱቅ ግድግዳ ላይ ተሰቅላ ከማያት አባባል የምታስቀኝ “ዱቤ ዛሬ የለም፤ ነገ ይመለሱ” የምትለው ስትሆን የምትገርመኝ ደግሞ “ደንበኛ ንጉስ ነው” የምትለው ናት። ምንም እንኳን ልማዳዊ በሆነችው ጾታን መሰረት ያደረገች የሥራ ክፍፍል ብዙ ጊዜ ወደ ገበያም ሆነ ሱቅ የሚያቀኑት ሴቶች ቢሆኑም የንግሥና ክብር ያገኙት ግን ወንዶቹ ብቻ ናቸው። በርግጥ ወንድሞቼ ባገኙት የንግስና ክብር ደስተኛ ነኝ። ጥያቄዬም ሆነ ግርምቴ የምትመነጨውም ለምን እነርሱ ንጉሥ ተባሉ ከምትለው ሐሳብ ተነስቼ አይደለም። ነገር ግን ሴት ደንበኞችስ ምንድን ናቸው? ንግሥት አይደሉምን? ከምትለው ነው። በርግጥ ይህቺን ጥያቄ ስጠይቅ ቋንቋ መግባቢያ ነው። ስለዚህ መልዕክቱ ላይ ብቻ ለምን አታተኩሪም የምትል ክርክር የሚገጥሙኝ ሰዎች አይጠፋም። ለዚህ መሰሉ ክርክር ቋንቋ መግባቢያ ብቻ ሳትሆን የማኅበረሰብን አስተሳሰብ የምታንጸባርቅ መሣሪያም ጭምር ናት የምትል ጽኑ እምነት እንዳለችኝ ለመግለጽ እወዳለው። እንዲሁም ቋንቋ አንዲት ማኅበረሰብ ባሕሏን፣ እምቷን፣ ልማዷንና ታሪኳን የምትገልጽበት ነው። ሶሾሊንግዊስቲክ (sociolinguistic) የተባለችው የጥናት ዘርፍም ይህንኑ ታረጋግጣለች። በዚሁ የትምህርት ዘርፍ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነም አንዲት ማኅበረሰብ በአባባሎቿ፣ በቅኔዎቿ፣ በጥቅሶቿ፣ በዘፈኖቿና መሰል ድርጊቶቿ ቋንቋን በመጠቀም እንዲሆንላት የምትፈልገውን ወይንም መሆን አለበት ብላ የምታስበውን ነገር ትገልጻለች። እናም የምንኖርባት ዓለም የወንዶች የበላይነት የሚንጸባርቁባት በመሆኗ ብዙ ጊዜ ወንድን የሚያሞግሱ ሴትን ጥገኛ የሚያደርጉ የሚያንቋሽሹ፣ ስፍራዋን የሚመርጡና መሰል አባባሎች በርካታ ናቸው።

ሴት በማጀት ወንድ በችሎት፣ የሴት ሞቷ በማጀቷ፣ ሚስትና ዳዊት በብብት፣ የሴት አገሯ ባሏ ማደሪያዋ አመሏ፣ አለባል ሴት ወይዘሮ አለማንገቻ ከበሮ፣ ሴት ለቤት ወፍጮ ለዱቄት፣ አህያና ሴት ቢረግጥዋት አይከፋት፣ የድንጋይን ጦርነት የሽሮን ቀለብነት የሚስትን ባርነት፣ የምታሸንፈውን ምታ ቢባል ወደ ሚስቱ ሮጠና ሴት አግብቶ ሴት ቢወልዱ የት አለ ንግዱ የሚሉት አባባሎች ቋንቋ ምን ያህል አስተሳሰብን ገላጭ እንደሆነች ማሳያ ናቸው። ከአባባሊቱም ባለፈ ለምሳሌ ከመንገድ ላይ ምልክቶች አንዷ የሆነችውን ቁም የምትለውን ብንመለከት ገላጭነቷ ኹለቱንም ጾታ አታመለክትም። ይህችን መሰል ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን የአባታዊ ስርዓት ነጸብራቅ የሆኑ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ግን ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም አይደል የምትባለው? የሆነው ሆኖ ከላይ ላነሳኋት የቋንቋ አጠቃቀም አካታችነት እንከን መፍትሔዋ መሰረታዊ የሚባሉት ነገሮች ላይ አካታች ገላጮችን መጠቀም ነው የምትል እምነት አለችኝ።

“ደንበኛ ንጉስ ነው” የምትል ጥቅስ ከተጻፈችበት ካፌ ውስጥ ቁጭ ብዬ በውስጤ ደንበኛ ንግሥትም ናት እያልኩና ከላይ የገለጽኳትን ዓይነት የቋንቋ አጠቃቀማችንን እየታዘብኩ እያለ አስተናጋጁ ምን እንደምፈልግ ጠየቀኝ። እኔም ሻይ በጤና-ሔዋን ብዬ በሐሳብ ከራሴ ጋር መሟገቴን ቀጠልኩ።

ኪያ አሊ

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here