‹‹የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሄጄ ብጠይቅም የለም ብለውኛል››፦ የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ጠበቃ አዲሱ አልጋው

0
1944

ዕረቡ ሚያዚያ 26 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ከመኖርያ ቤቱ ባሳለፍነዉ እሁድ በመንግስት አካላት ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብሎ ቢወሰድም እስካሁን ያለበትን ለማወወቅ አለመቻላቸውን ጠበቃው አዲሱ አልጋው ገለፁ፡፡

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ሚያዝያ 23/2014 ጠዋት 4 ሰዓት ላይ በአዲሰ አበባ ከተማ አሰተዳደር ሀያት ባቡር ጣቢያ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በመንግሥት የፀጥታ ሀይሎች መወሰዱንና የት እንዳለ ማወቅ እንዳልተቻለ ጠበቃዉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የራዲዮ ጣቢያ ተናግረዋል፡፡

ስምንት የሚሆኑ ሲቪል የለበሱ የመንግስት አካላት ነን ብለው የመጡ ሰዎች ለጥያቄ ነው የምንፈልገው ብለው መወስዳቸውን አስታውሰው፣ የት እንደታሰረ ባላውቅም ምናልባት ፍ/ቤት ሊያቀርቡት ይችላሉ በሚል ተሰፋ ትላንት ሚያዚያ 25/2014 ጠዋት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ ከሆነ በሚል ለማጣራት ከ3 ሰዓት እስከ 5 ሰዓት ድረስ ቆይቼ ነበር ብለዋል ጠበቃዉ፡፡

‹‹ነገር ግን አንድም መርማሪ ፖሊስ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን በችሎቱ አላቀረበውም›› ሲሉ የጋዜጠኛው ጠበቃ የሆኑት አዲሱ አልጋው ለራዲዮ ጣቢያው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ይህ አልሆን ሲል ‹‹የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሄጄ ብጠይቅም የለም ብለውኛል›› ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሥራ ባልደረቦቹ ወደ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቅሬታ ለማቅረብ መሄዳቸውን አስታውስው፤ ያንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ጉዳዩን አጣርቶ መግለጫ አውጥቷል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በበኩሉ ጋዜጠኛው ያለበትን ሁኔታ እና የታሰረበትን ቦታ ለማወቅ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ መረጃ ማግኘት ባለመቻሉ የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ጉዳይ እንዳሳሰበው መግለፁ ይታወሳል፡፡

መንግስትም ጉዳዩን በአፅኖት ተመልክቶ ምላሽ እንዲሰጥበት ማሳሰቡን በማንሳት መንግስትም በፍጥነት ምላሽ ይሰጥበታል ብለው እንደሚምኑ አንስተዋል፡፡

የጋዜጠኛው ጠበቃ አክለውም እነዚህ አማራጮችን ተጠቅመው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ ካልታወቀ፣ ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር መሄዳቸው እንደማይቀርም ገልፀዋል፡፡
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here