5ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ በመካሄድ ላይ ነው

0
1144

ዕረቡ ግንቦት 3 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የምስራቅ አፍሪካ ፋይናንስ ጉባኤ በየአመቱ የሚካሔድና በውስጡም ከ300 በላይ የፋይናንሱ ዘርፍ ባለድርሻዎች የሚሳተፉበት የእውቀት፣ የሃሳብ እንዲሁም የልምድ ልውውጥን ያካተተ መድረክ ሲሆን፤ 5ኛው ዓመታዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

“የለውጥ ማዕበል በነገሰበት ዘመን የነገውን የፋይናንስ ዘርፍ እንደገና መቅረፅ በሚል ጭብጥ ሥር ፖሊሲዎችን እና አሰራሮችን መፈተሽ” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ የሚገኘውን የዘንድሮውን ጉባኤ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ድርጅት፣ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ማህበር (ACCA) እና የአይ-ካፒታል ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን አዘጋጅተውታል።

ጉባኤው የፋይናንስ ዘርፉን የወደፊት አቅጣጫ መቀየስንና እንዲሁም ህግና ደንብ ማጥራትን እንደ ዓላማ ይዞ መዘጋጀቱም በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተገልጿል፡፡

የአይ-ካፒታል ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ የኢንዱስትሪ መሪዎችን እና በፋይናሱ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ሌሎች ቁልፍ ተዋንያንን ለማሰባሰብ ያለው ብቸኛው መድረክ መሆኑን ገልፀው ኹሉም ተዋንያን በቁልፍ የፖሊሲ እና የአሰራር ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እና ለመከራከር ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲጠቀሙት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አክለውም “ያለንበት ጊዜ የለውጥ እና የነውጥ ጊዜ ነው። በዚህ አዲስ የንግድ ዓለም ውስጥ ደግሞ ነባሩን ሁኔታ ጠብቆ ማቆየት ምንም ቦታ የለውም። መማር እና መለወጥ ካልቻልን ህልውናችን አደጋ ላይ ይወድቃል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የተመሰከረላቸው የሂሳብ እና ኦዲት ባለሙያዎች ማህበር (ACCA) የአገር ውስጥ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዮዲት ካሳ በበኩላቸው፤ “…የፋይናንስ ዘርፍ በጣም ተለዋዋጭ በመሆኑ እንዲህ ባለው ውይይት ውስጥ በመሳተፍ እና እንዲህ ያለውን ውይይት በመምራት የሂሳብ ባለሙያዎች የሚጫወቱት ሚና በተለያዩ ኢኮኖሚዎች ውስጥ ዘላቂ ዕድገት መኖሩን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡

በጉባኤው ላይም የዘርፉ ምሁራንና የሚመለከታቸው አካላት የጥናት ወረቀቶችን በማቅረብ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በፋይናንስ ሴክተሩ ዙሪያ በምስራቅ አፍሪካና በውጭ የሚገኙ ግዙፍ ድርጅቶች ይመክራሉ፣ የፋይናንስ ሥርዓት ፖሊሲም በስፋት ይገመገምበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ በአጠቃላይ እሴት ሰንሰለቱ ላይ ባሉ እና በኢትዮጵያ እንዲሁም በአህጉሪቱ ውስጥ በፋይናንሱ ዘርፍ ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ወሳኝ ዘርፎች በተወጣጡ የኢንዱስትሪ ባለሞያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የባንክ ባለሞያዎች፣ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የመንግስት ኃላፊዎች መካከል በርካታ አካላትን ያሳተፈ ውይይት የመፍጠር ዓላማን ይዞ የሚከናወን ጉባኤ ነው።

ጉባዔው ቅንጅታዊ አሰራርን የማጠናከር፣ በወቅታዊ ተግዳሮቶች ላይ የመወያየት፣ የገበያ ስትራቴጂዎችን የመቅረጽ፣ ዕውቀትን የማጋራት እንዲሁም የነገውን የፋይናንስ ዘርፍ ለመቅረጽ የሚረዱ መላዎችን ለይቶ የማስቀመጥ ዓላማ ያለው ሲሆን፤ ከዚህ በፊት አራት ጊዜያት ተከናውኗል።

የዚህ ዓመቱን ጉባዔም ከፋይናንስ ዘርፉ የተለያዩ ክፍሎች የተወጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የታደሙበት ሲሆን፣ በጉባዔው ላይ ንግግር ከሚያደርጉ እና የፓናል ውይይት ተሳታፊ ከሚሆኑ ሰዎች ውስጥም ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከዓለም ዙሪያ የመጡ ሥመ ጥር እና ዝናን ያተረፉ የፋይናንስ ባለሞያዎች ይገኙበታል።

ጠንካራ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲኖር የሚያስፈልገው ፖሊሲ፣ ቁጥጥር እና አስተዳደር፣ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መሽጋገር፣ አካታችነት፣ ፈጠራ እና የፋይናንስ ተደራሽነት፣ እንዲሁም ልዩ የባንክ አገልግሎቶች እና ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መሽጋገር በጉባዔው ላይ ውይይት እየተደረገባቸው ከሚገኙ ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሾቹ ናቸው።

በእዮብ ውብነህ
___
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

  

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here