ሚናዬ!

0
811

ግዜው ወደ ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ ይሆናል። ታክሲ ለመጠበቅ ረጅም ሰዓት ስለፈጀብን እየተማረረ ነው። ታከሲ ውስጥ ገብተንም፤ ቀናቱን ያማርራል። ተራ አስጠባቂዎችን ይተቻል። መንግስትነ ይራገማል። ህዝብና ሀገርን ይሳድባል፤ በወር ገቢ ማነስ ያጉረመርማል። ዐብሮት ያለው ጓደኛው ከጥቂት ፈገግታ ጋራ ግድ ባልሰጠው መንገድ እየሰማው የእጅ ስልኩን ይነካካል። ታክሲ ውስጥ ከመግባታችን በፊትም አሁንም ታከሲ ውስጥ ቢያንስ ላለፉት ሰላሳ ደቂቃዎች ያህል ያወራል፤ አይሰማውም። የጓደኛው ቸልተኝነትም፤የሰውየው ጨዋታ ሁኔታም ስለሳበኝ ታክሲ ውስጥ አጠገባቸው ተቀመጥኩ። በማማረሩ ቀጥሎ ታክሲው ሲንቀሳቀስ ‹እነዚህ ዶማዎች› አለ ተራ አስጠባቂዎቹን። ረጅም ሰዓት ስሰማው ስለነበረ አኔም አስቲ ለምን አላወራውም ብዬ አጋጣሚውን ተጠቀምኩ ‹ የሰው ልጅ ዶማ አይባልም› አልኩት።

ገላመጠኝና ለአፍታ ያህል ዝም አለ። ረጅም ሰዓት ስለሰማሁት ነው መሰለኝ ‹እንዴት?› አለኝ። በሰው ጨዋታ መሃል ዘው ብሎ መግባት ስላልለመደብኝም፤ለት ጓደኞችም ስለሆኑ፤ ከሱ ሁኔታም ተነስቼ ከሰደበኝ ብዬ ቆዳዬን አወፍሬ ስለነበር ቀለለኝ። ስለዚህ መለዘብ ነበረብኝ። ‹ ይሄውልህ ወንድሜ የሰው ልጅ ህይወት አለው አይደል?› ስለው ‹አዎ› አለኝ። ‹ዶማ ግን ህይውት የለውም አይደል?› አልኩት ጫን ብዬ። አላመነታም ተስማማ። በውስጤ አስተማሪነቴ ሳይጠቅመኝ አልቀርም አልኩ። ‹ስለዚህ ሰው የተቀደሰ የተከበረ ፍጡር ስለሆነ ዶማ አይባልም› ሰለው ተስማማ።

‹ዶማ ዶማ አለመሆኑንና ዶማ ጉድጓድ ለመቆፈር፤ ለመደምደም ወዘተ እንደምንጠቀምበትና እህልና እጽዋትን ለመኮትኮት እንደምንጠቀምበትና ሕይወት እንደሚሰጥ› አወጋን። ዶማ ሕይወት ባይኖረውም ሕይወትን ለመንከባከብ እነደሚጠቅም አውርተን ልብ ለልብ ተግባባን። መፈራራት ቀረ።ከዛማ የባጥ የቆጡን ማውራት ቀጠልን ።

አሱም ‹እሱስ አውነትህን ነው ተናድጄኮ ነው እንጂ ሰው ከቡር ነው› ብሎኝ ፡- ስለሃይማኖተኛ ማነስ፤ ባህል ስለመበረዙ፤ መተማማን ስለመቀነሱ፤ ሥነ ምግባር ሰለመሳሳቱ፤ የሃገራችን መከራ ስለመብዛቱ፤ የጦርነቱን አስከፊነት፤ የኑሮ ውድነቱ ነዋሪውን ስለማማረሩ፤ የታክሲ ሰልፍ ሰለመርዘሙ፤ ታከሲ ውስጥ የጠፋብህን ዕቃ ድሮ መልሰህ የምታገኘውን ያህል አሁን እኝደማታገኝ፤ ሰልፍ ዐስከባሪዎችም እንዳስቸገሩ፤ ሌባ አንደ በዛ፤ ሱስና ሱሰኛ ስለመብዛቱ፤ ጓደኛውም ዝም ብሎ ሞባይል ስልኩን እየነካካ እኔና እሱ እየተጨዋወትን የሃያ አምስት ብሩን የታክሲ መንገድ ሰናጋምስ አንድ ጥያቄ ጣል አደረኩለት ‹ ለመሆኑ አንተ በዚህ ሁሉ መከራ መሃል የችግሩ አካል ነህ ወይስ የመፍተሄው አካል? › አልኩት። ‹ መሆንማ ያለብን የመፍተሄው አካል ነው› አለኝ።

አኔም በፍጥነት ብዙ ውይይቶችን የመሳተፍ ድል ነዳገኘሁና አንዳንድ ጉዳዮችም ሲገጥሙኝ ራሴን ደጋግሜ የምጠይቀው ‹ እኔ የየትኛው አካል ነኝ ? በዚህ ሁሉ መሃል የችግሩ አካል ነ? ወይስ የመፍተሄው አካል ?› የሚለውን ጥያቄ ነው ብዬ ልምዴን አካፈልኩት። በእውነቱ አዳማጫ ነበረ።

እዚህ ዓለም ላይ ስንኖር በአንድም በሌላም መንገድ ሚና (role) አለን። ሚና የሌለው ፍጥረት አልተፈጠረም። ሚናውን የማወቅ ያለማወቅ በራሱ ቢወሰንም ቅሉ። ሚናችንን ሁልጊዜ ብናስብ አጅግ ተጠቃሚ እንሆናለን። ያ ሚናችን ሁለት ጎን ይኖረዋል። ማለትም ሚናችን በጎ ወይም አሉታዊ ሊሆን ይችላል። ይሄ እንደ አስተሳሰባችን፤ እንደ አስተዳደጋችን፤ እንደ አነጋገራችን፤ እንደ አዋዋላችን፤ እንደ ባህላችን፤ እንደ ስራችን፤ እንደ ሞያችን፤ እንድ የትምህርት ደረጃችን፤ እንደ ሓማኖታችንና እንደ አለንበት ሁኔታ ይወሰናል። ያ ሰው ሚናው በጎ ነው አልያም አሉታዊ ነው የሚባለው የበለጠ የትኛውን ነው የሚያደርገው ነው በሚለው ይወሰናል።

ይሄ የሰው ልጅ ሚና ይጠናል። ይመረመራል። በሚናችን ልክ እንጠናለን እነመረመራለን፤ እንገመገማለን፤ እንመዘናለን። አዚህ ውስጥ አራት ተዋናዮች አሉ። መዛኝ፤ ተመዛኝ፤ መመዘኛና የመመዘኛ ስርዓት። ይሄንን ነው የሲሶ ዓመት፤ የግማሽ ዓመት፤የዓመት ምዘና የምንለው። ለተማሪም፤ ለአስተማሪም፤ለሰራተኛም። ከላይ እስከታች በሚታይም በማይታይም መልኩ፤ የግም የመንግሰትም ተቋማት፤ የታች የመሃልም የበላይ የአስተዳደርና የማኔጅመንት ሰዎች ይሄን Role Analysis ‹የሚና ቅምራና ትንተና› ይሰሩታል።ሪፖርት ያቀርባሉ። የሚና ግምገማ ውጤት ያሸልማል። በአንጻሩም የሚና ግምገማ ውጤት ካነሰ ያስቀጣል። ለዚህ ሲባል የሚና ግምገማ እጅግ ጥንቃቄ በተሞለበት መንገድ መሰራት እንዳለበት በለሞያዎች ያብራራሉ።

በዚህ መሰረት የአንድ ሰራተኛ ሚና በአጠቃላይ መስሪያ ቤት ውስጥ፤ ወይም በአንድ ፐሮጀክት ውስጥ ምንድን ነው ብለው የገመግማሉ። ወይም ምን ያህልና ምን ምን አበርክቶ እንዳለው ይጠናል። እኛም እንደ ግለሰብ፤ እንደ ማህበረሰብ፤ እንደ አደግንበት ባህልና ሃይማኖት፤ እንደምንኖርበት ሃገር የራሳችን ሚና ይኖረናል። ጥያቄው ሚናችን ምንድን ነው የሚለው ነው? ስለዚህ ለምሳሌ እርስዎ ባሉበት ሰፈር፤ በሚሰሩበት ቦታ፤ በጓደኞችዎ ልብ ውስጥ፤ በትዳር አጋርዎ ፊት፤ በቤትዎ ውሰጥ፤ በማህበረሰቡ ውሰጥ፤ በሄሞት አስተምሮዎ ውሰጥ እንዲሁም አሁን በገጠመን ሀገራዊ ውጥንቅጥ ሁኔታ ውስጥ የእርስዎ ሚና ምንድን ነው ? ባለሞያዎቹ የሞያን ትንታኔ በተለያየ መልክ መተንተን እንደሚቻል ያብራራሉ። ለምሳሌ በዚህ መንገድ ጥናቱን መጀመር ይቻላል ይላሉ ። የመጀመሪያው አጠቃላይ መረጃዎች ናቸው። ከአጠቃላይ መረጃ እስከ ዝርዝር ጉዳዮች በማየት።

እኔ ለምሳሌ እንደ አንድ ኢትዮጵያ ዜጋ ለሀገሬ ሚናዬ ገንቢ ነው ወይስ አፍራሽ። ባለፉት አራት ዓመታት እንደ ሀገር በተፈጠረው ምስቅልቅል ውስጥ የኔ ሚና በአስተሳሰብ ፤ በሥነ ምግባር፤ በሞራል፤ ሕብረተሰባዊና ሓማኖታዊ ባህልና እሴቶችን ከመጠበቅ አንጻር ብቻ እንኳን ቢለካ ምን ነበር ብለን ብንጠይቅ አብዛኛዎቹ አሉታዊ መሆናቸው አሌ አይባልም። ለራሳችን፤ ልፍቅረኛና ለትዳር አጋር፤ ለቤተሰብና ለህብረተሰብ በመጨረሻም ለሃገር ያለን አመለካከት ጥሩ ዓይመስልም። የውስጣችን መልካም ያልሆነ አመለካከት ደግሞ ወደ ውሰጥም ወደ ውጭም ይንጸባረቃል። ወደ ውስጥ ሲንጸባረቅ አኛኑ መልሶ ይጎዳናል። ወደ ውጭ ከተንጸባረቀ ደግሞ ሌሎቹንና ኣባቢያችንን በአሉታዊ መንገድ ይጎዳል። የውስጥ ኔጋቲቭ ኢነርጂ ደግሞ ውጭውን ነጌቲቭ ያደርገዋል። የውስጥ ሰላም ልንለው እንችላለን።

የውሰጥ ሰላም የሌለው ሰው ለውጩ ሰለም ሊሰጥ አይችልመና። እንደ ተጨማሪ ምሳሌ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ 14 ዓይነት የሚና መለኪያዎች እንዳሉ ይብራራል። ስለዚህ በየሥራ መስካችን የተለያዩ መለኪያዎች አሉ ማለት ነው። ለማስታረቅ ተቀምጠን አጣልተን አልለያንም? ሚናችን አልተደበላለቀብንም? አልተምታተብንም? በብዙ ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ሚናችን ምንድን ነው ብንል ለማህበረሰብ ግንባታ የምናበረክተው አስተዋጽዖ ቀላል አይሆንም ብላችሁ ታስባላችሁ ? ስለዚህ እባክዎ አሁን በዚህ ቅጽበት እየሰሩ ባሉት ነገር ውሰጥ ላንዳፍታ ሚናዬ ምንድን ነው ይበሉ እስቲ ? ገንቢ ነው ወይስ አፍራሽ ?


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here