የፔትሮዶላር ዘመን የማብቂያው መጀመሪያ ላይ እንገኝ ይሆን?

0
1329

ፔትሮዶላር ራሱን የቻለ መገበያያ ገንዘብ ሳይሆን የዓለም ድፍድፍ ነዳጅ የሚሸጥበት የአሜሪካንን ዶላር ጥቅም ላይ የማዋል ሥርዓትን የሚገልፅ መጠሪያ ነው። ይህ አገላለፅ ከፈረንጆቹ 1970ዎቹ ጀምሮ ለፖለቲካ ተፅእኖም ሆነ ለኢኮኖሚ ማብራሪያ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረ ነው።

ፔትሮዶላር እየተባለ አሁን ድረስ የሚገለፀው አሜሪካን በዋናነት ከሳውድ አረቢያ ጋር ነዳጅን በአሜሪካን ዶላር ብቻ እንዲሸጥ የሚያደርግ ስምምነት የተፈራረመችበትንም ሂደት ይገልፃል ነው። የዓለም አገራት የነዳጅ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲፈልጉ ድፍድፉንም ሆነ የተጣራውን ከገበያ የሚገዙበት መገበያያ የአሜሪካን ዶላር እንዲሆንና ተመን እንዲወጣበት የሚያደርግ ውል ነበር። በዚህ ስምምነት መሠረት አሜሪካ ለሳውድ አረቢያ የጦር ድጋፍ የምትሰጥበትና ምንም ብታደርግ ሁሌም ከጎኗ የምትቆምበት ነበር።

ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ጥቅም ላይ በዋለው በዚህ ሥርዓት፣ አሜሪካ ሌሎች አገራት በገንዘቧ ሲገበያዩ ቁጭ ብላ ተጠቃሚ ሆናለች። አንድ አገር ከሌላ አገር ለመገበያየት ሲፈልግ ግድ ዶላርን መጠቀም ስለነበረበት፣ ክምችት ከሌለው ዶላርን በውድ ገዝቶ ፍላጎቱን እንዲገዛበት ይደረግ ነበር። ይህ አሰራር ሌላውን የሚያቆረቁዝ አሜሪካንን ደግሞ ያለምንም ልፋት የሚያበለፅግ ነው።

ይህን አይን ያወጣ ኢ-ፍትሐዊነት የተቃወሙ በርካቶች ቢሆኑም አሜሪካ ረጅም እጇን እየላከች ስታጠፋቸው እንደነበር ይነገራል። የኢራቁ ሳዳም ሁሴን፣ የሊቢያው ሙአመድ ጋዳፊ እንዲሁም በርካታ የአሜሪካ ተቀናቃኝ አገራትና ታዋቂ ግለሰቦች ይህ አሠራር እንዲቀር ቢሞክሩም እርምጃ እንደተወሰደባቸው ይነገራል።

ፔትሮዶላርን የግድ ጥቅም ላይ ማዋል በሕግ ያልተቀመጠ ቢሆንም፣ እንደ መርህ ተደርጎ ጥቅም ላይ ሲውል እስከአሁን በጅምላ የተቃወመ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል ኢትዮጵያ ከሱዳን ነዳጅ ስትገዛ የኢትዮጵያንም ሆነ የሱዳንን መገበያያ ጥቅም ላይ ማዋል ሳይቻል ቆይቷል። ሱዳንም ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልንም ሆነ ሌላ ምርትን ስትገዛ ከዶላር ውጭ መጠቀም ስለማይቻላት ሁለቱም አገራት እጥረት ያለባቸውን ዶላር እየተበደሩም ሆነ ተለቅተው እንዲገበያዩበት ሲደረግ ተኑሯል።

እርስ በርስ በባርተር በለውጥ ለመቀያየርም ሆነ ለመገበያየት አልያም ሌላ መገበያያን እንዳይጠቀሙ አሜሪካ ውስጥ ሆና የምትዘውራቸውን የዓለም ባንክንም ሆነ ዓለም አቀፉን የገንዘብ ፈንድ ተጠቅማ አገራቱ እርዳታም ሆነ ብድር እንዳያገኙ፤ ይህም ካልሠራ ማዕቀብ ተደርጎባቸው ከዓለም ኢኮኖሚ እንዲገለሉ በግልፅም ሆነ በስውር ስትሠራ መኖሯን በርካቶች ይመሰክራሉ።

ለ50 ዓመታት የውዴታ ግዴታ ሆኖ አገራትን ሲያቆረቁዝ የኖረው የፔትሮዶላር ሥርዓት፣ ዶላር መገበያያ ብቻ ሳይሆን የአገራት የክምችት ምንዛሬ እንዲሆንም አድርጓል። ከዛ ቀደም የሀብት ማከማቻ መንገድ የነበረው ወርቅ ጥቅም ላይ መዋሉ እንዲቀር ያደረገ ነበር። በዚህም ምክንያት የዓለም አገራት ዶላርን እንደሀብት መለኪያቸው እንዲያደርጉት አስገድዷል። ይህ በመሆኑ አሜሪካ በድንበሯ ውስጥ ካለው የገንዘብ መጠን በውጭ አገራት ያለው ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉ ይነገራል።

ኢትዮጵያን የመሳሰሉ አገራት ገንዘባችን በጎረቤት አገራት ጥቅም ላይ ዋለ እያሉ በተቃራኒው ለመገደብ ዘመቻ በሚያደርጉበት ዘመን፣ አሜሪካ ደግሞ የበለጠ ጥቅም ላይ እንዲውልላት የማትቆፍረው ጉድጓድ እንደሌለ ይታወቃል። በዚህ ጥረቷም እስከ አሁን ሥርዓቱን የሚያናጋ አንዳችም ከባድ ተቃውሞም ሆነ እንቅስቃሴ ገጥሟት ሳታዳፍነው ቀርታ አታውቅም።

ከአሜሪካ ውጭ ያለው በወረቀት ያለው የዶላር መጠን በእርግጠኝነት ባይታወቅም፣ ከ40 በመቶው እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ውጭ አገራት ውስጥ እንደሚገኝ ይታመናል። ዚምባብዌና ፓናማን የመሳሰሉ 11 አገራት በሕጋዊ መንገድ ዶላርን እንደመገበያያ ገንዘባቸው አድርገው የሚጠቀሙ ሲሆን፣ 8 አገራት ብቻ ናቸው ብለው የሚሞግቱም አሉ። ምንዛሬው ጭራሽ አገራቸው እንዳይገባ የሚፈልጉ ቢኖሩም፣ በማዕቀብ ተከልክለው የማይጠቀሙበትን ያህል እንደማይሆኑ ይታወቃል። የራሳቸውን ገንዘብ ዶላር ብለው የሰየሙ ካናዳ፣ ላይቤሪያንና ሆንግኮንግን የመሳሰሉ 20 አገራት ቢኖሩም፣ ከስያሜው በስተቀር የራሳቸው ምንዛሬ ያላቸው ናቸው።

የአሜሪካኑን ዶላር ራሱኑ የሚጠቀሙ በዋናነት የመካከለኛው የአሜሪካ አገራት ቢሆኑም ዚምባብዌን የመሳሰሉ ምንዛሬያቸው በከፍተኛ መጠን ጋሽቦ የማይጠቅም የሆነባቸው አገራትም እንደራሳቸው ገንዘብ ይገበያዩበታል። በዚህ ሂደት አሜሪካን ምን ያህል ተጠቃሚ እንደምትሆን በእርግጠኛነት መናገር ባይቻልም፣ ወደውጭ ከምትልካቸው ምርቶቿ በጣም አትራፊው እንደሆነ ባለሙያዎች እንደሚናገሩ ቡሊዮን ስታር የተሰኘው ድረገፅ አስፍሯል።

የአሜሪካ ዶላር ይህን ያህል ጥቅም ላይ እንዲውል የሆነው አገራቱ በሙሉ ተገደው ነው ማለት አይቻልም። የአሜሪካንን ጉልበት መፈርጠም የተመለከቱ፣ የኢኮኖሚዋንም ጠንካራነት የተገነዘቡ በርካታ አገራት የክምችት አማራጫቸው እንዳደረጉት ይነገራል። በዓለም አቀፉ ፖለቲካ ውስጥም ሆነ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያላትን ተፅእኖ የተረዱ ዶላርን ተመራጭ ያደረጉትን ያህል፣ ተገደው የገቡበትና መውጣት የተሳናቸው በተለይ ድሃ አገራት በርካታ መሆናቸው ይታወቃል።

አቅም ያላቸው የአውሮፓ አገራት፣ አገር የሌለው የአውሮፓ ሕብረት መገበያያ ዩሮን ጥቅም ላይ ማዋል የጀመሩት ከብዙ ጭቅጭቅና ውጣውረድ በኋላ ቢሆንም፣ ገና ከመነሻው አንስቶ እስከ አሁን ተቀባይነት አግኝቶ ተፈላጊነቱ ከፍ እያለ ይገኛል። በሌላ በኩል የድሃ አገራት መከማቻ የሆነው የአፍሪካ አህጉር የራሱ መገበያያ እንዲኖረው የሊቢያው ሙሐመድ ጋዳፊን ጨምሮ የተወሰኑ ቢጠይቁም፣ ውጤታማ ከመሆን ይልቅ መጥፊያቸውን እንዳፋጠነላቸው ይታመናል።

የራስን ጠንካራ መገበያያ ተግባራዊ ከማድረግ በፊት ራስን መቻል ይገባል ሲሉ የነበሩት የዚምባብዌው የቀድሞ መሪ ሮበርት ሙጋቤ፣ ድጋፍንም ለመላክ ዶላር መግዛት የለብንም በሚል እሳቤ ለህብረቱ መዋጮዋቸውን ከብት በመስጠት እንዳከናወኑ ይታወሳል።
የዶላር ተፅእኖ ከአገር አገር የተለያየ ቢሆንም፣ በድሃ አገራትና ከአሜሪካ በተቃራኒ በተሰለፉ አገራት ላይ ከባድ እንደሆነ ይታመናል። የአትዮጵያ መንግሥት በዶላር እጥረት ሳቢያ የፈለገውን እንደተጠየቀው መጠን ለመስጠትና ለመጠቀም የቻለበት ወቅት በጣም ሩቅ እንደነበረ ማንም የሚያስታውሰው ነው። ከተለያየ አገር ለሚገባ አስፈላጊ ምርትም ከዶላር ውጭ ጥቅም ላይ የሚውል ምንዛሬ ባለመኖሩ ችግሩ እየገዘፈ እንጂ እየቀለለ ሲመጣ አይታይም።

ዶላርን ዓለም አቀፍ መገበያያ ያደረገውን ዋናውን ድፍድፍ ነዳጅ እንኳን ብንመለከት፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ የምታወጣው ገንዘብና የሚያስፈልጋት የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል። ይህም በየዓመቱ ስለሚያድግ እያደር እያቆረቆዛት እንደመጣና አካሄዳችን ላይ ለውጥ ካልተደረገ ለወደፊቱም እየባሰብን እንደሚሄድ የኢኮኖሚ ተንታኞች ሲናገሩ ይደመጣል።

ነዳጅ አቅራቢ አገራት ወርቅ የሀብት ክምችት ማሳወቂያ መሆኑ እንዲቀር ያደረጉት ሆነ ብለው ነው ወይስ አይደለም የሚለው የሚያወዛግብ ቢሆንም፣ የዓለምን የኢኮኖሚ እድገት ተከትሎ መለወጥ ስላልቻለ ወደ ዶላር እንደተቀየረ የሚናገሩ አሉ። በወቅቱ ዋና የነዳጅ ገዢ የነበረችው አሜሪካ ስለነበረች፣ የወቅቱ የድፍድፍ ነዳጅ ላኪ አገሮች ምርጫ እንዲሆን አድርጓል ብለው የሚሟገቱም አሉ።

ያም ተባለ ይህ የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር ላኪዎቹ ይበልጥ የዶላር ክምችታቸው እየጨመረ ሲመጣ፣ በተቃራኒው ደግሞ ተጠቃሚዋ አሜሪካ የገንዘብ እጥረት እያጋጠማት በብድር መኖር ከጀመረች በርካታ አመታት መቆጠራቸውን ኢንቨስቶፒዲያ ያስነብባል።
በሌላ በኩል፣ አሜሪካ በፔትሮ ዶላር ሥርዓት በቀጥታ ተጠቃሚ ከመሆኗ ባሻገር፣ የጦር መሳሪያ አምራች ትልልቅ ኩባንያዎቿ የ70ዎቹን ስምምነት ተገን አድርገው ምርታቸውን በገፍ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል። በአካባቢው የትጥቅ ፉክክር እንዲከሰትና አገራቱ ከአፍንጫቸው በላይ እንዲታጠቁ በማድረግ እርስ በርስ አለመስማማትን በማንገሥ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ተደርገዋል።

በዘመናዊ ጦር መሳሪያ እሽቅድምድም አሁንም ድረስ ከነዳጅ ገቢ ያከማቹትን ከፍተኛ የዶላር መጠን መልሰው ለአሜሪካ እንዲያስገቡ እየተገደዱ ነው። ይህ አካሄድ አሜሪካ የበላይነቷን በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በውትድርናውም መስክ እንደያዘች እንድትዘልቅ አድርጓታል።

የፔትሮዶላር ዘመን ማብቂያ መጀመሪያ
ፔትሮዶላር እየተባለ የሚገለፀው የአሜሪካ ዶላር ተጽእኖ ላለፉት 50 ዓመታት እየጨመረ መጥቶ ከሰሞኑ እየተንገራገጨ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል። የራሺያና ዬክሬንን ጦርነት ተከትሎ ምዕራባውያን ራሺያ ላይ የቻሉትን አማራጭ ሁሉ ተጠቅመው ጫና ለማሳደርና ሌሎች አገራትንም ለማሳደም ሲጥሩ፣ የምሥራቁ ዓለም ጎራ መሪ ተደርጋ የምትቆጠረው ሩስያም አጸፋውን ለመመለስ እየጣረች መሆኗን እየተመለከትን ነው።

ከዚህ ጦርነት በርቀት ያሉና የቅርቦቹ የአውሮፓ አገራት፣ በረዶ ሠርቶ የደረቀውን ቀዝቃዛውን ጦርነት ለማሟሟቅ ሲጣደፉ ይስተዋላል። የዚህ ጥረታቸው ማሳያ ደግሞ ማዕቀብ መጣላቸውና ማስታጠቃቸው ሲሆን፣ ራሳቸውን እስካልጎዳ ድረስ ሌላውን ሊጎዳ በሚችል ነዳጅንና ምንዛሬን በመሳሰለ ለስላሳ መሣሪያ ሲዋጉ እየተስተዋለ ነው። እነአሜሪካ ሩስያን ለማዳከም የተለያዩ ማዕቀቦችን በሚጥሉበት ወቅት ሩስያ በተለይ ለአውሮፓ የምትልከው የነዳጅ ምርት ክፍያን በተመለከተ በዶላር ሳይሆን በሩብል እንዲከፍሉ ቀነ ገደብ ማስቀመጧ ብዙዎችን አሳስቧል።

አሜሪካ ሩስያን የጎዳች መስሏት፣ ለዩክሬን አስባ በማስመሰል የሩስያ ነዳጅ አገሯ እንዳይገባ ብትከለክልም፣ ውጤቱ የኑሮ ውድነትንና ግሽበትን በዜጎቿ ላይ ማምጣት ሆኖ የምትይዘው የምትጨብጠው አጥታ መቸገሯን የሚናገሩ አሉ። አውሮፓውያንም ፈለጓን ተከትለው እንዲያግዱ ብትወተውትና እነርሱ በበኩላቸው ጥቅማቸውን አሳልፈው መስጠት ባይፈልጉም፣ መሣሪያ ለዩክሬን ከማቀበል አልቦዘኑም።

በሩስያ ነዳጅ እየተጠቀሙ እሷን መውጊያ ዘዴ የሚያፈላልጉት አገራት ጋር ያለ ግንኙነቷን እንዳታቋርጥ እሷም ገቢውን ትፈልጋለች። ነገር ግን፣ የሩቅ ጠላቷ እንዳትጠቀም ቢጎዳትም በሩብል ክፈሉኝ ማለቷን አንዳንዶች እያንገራገሩም ቢሆን ተቀብለውታል። ሀንጋሪን የመሳሰሉ አገራት አማራጫቸውን መዝነው ወዲያውኑ የተስማሙ ሲሆን፣ በሩስያ ነዳጅ የምትተማመነው ጀርመን በበኩሏ፣ ልምዷን ወደሌላ ለመቀየር ቢያንስ ኹለት ዓመት ቢያስፈልጋትም እያንገራገረች ትገኛለች።

በሌላ በኩል የምዕራባውያኑ አጋር ናቸው በሚል ይከዳሉ ተብለው ከማይጠበቁ አገራት መካካል ለፔትሮ ዶላር መከሰት ዋነኛዋ መንሰኤ የነበረችው የሳውድ አረቢያ ማፈንገጥ ዓለምን ሲያነጋግር ነበር። አሜሪካን በእውቁ ጋዜጠኛ ግድያ ቅራኔ ውስጥ ከገባች አንስቶ ግንኙነታቸው ከሮ የነበረው ኹለቱ አገራት፣ እንዲህ ይጨካከናሉ ብሎ የገመተ ባይኖርም፣ ቃልኪዳናቸው መፍረሱን የሚያመላክት ክስተት ተፈጥሯል።

ሳወድ አረቢያ ለቻይና በዶላር ድፍድፍ መሸጧን ትታ በቻይና መገበያያ ዩዋን ለማድረግ ማቀዷ ለአሜሪካን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል። ወደምሥራቁ ማዘንበሏን ይጠቁማል የተባለው የሳውድ አረቢያ ተግባር የታወቀው፣ አሜሪካን ብዙ ምርት ለገበያ እንድታወጣና በሩስያ እንዲወደድ የተደረገውን ሂደት እንድታስቆም ስትወተወት የነበረውን ችላ ማለቷን ተከትሎ ነበር።

ይህ የሚያሳየው የአሜሪካ ተፅእኖ የቀነሰው ጠላቶቼ በምትላቸው ሩስያና ቻይና ብቻ ሳይሆን፣ ወዳጄ በምትላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትም ጭምር መሆኑ ነው። በአውሮፓውያኑም መተማመን አለመቻሏን ያየችበት ወቅት እንደመሆኑ ሲጋሽብ የነበረው የዶላሯ ተፅእኖ ቁልቁል የሚወርድበት ይሆናል የሚል ግምት የሚሰጡ አሉ። በተቃራኒው አዲሱ ክስተት ተፅእኖ ቢኖረውም፣ ያን ያህል ወደታች የሚያወርዳት እንደማይሆን የሌላ አገራትን ሁኔታ ከግምት እያስገቡ የሚናገሩ አሉ።

በሌላ በኩል የኃያላኑን ሽኩቻ ተከትሎ ድሃ የሆኑ የአፍሪካ አገራት አጋጣሚውን ተጠቅመው የራሳቸውን ምንዛሬ በማውጣት ከተለመደው የበዝባዥ ስርኣት የሚላቀቁበት እንዲሆን ጥሪ የሚያቀርቡ አሉ። የዝሆኖች ልፊያና ውጊያ ሳሩን እንደሚጎዳው ቢታመንም፣ ለምግብ ይውሉ ለነበሩ ተክሎች ደግሞ ጥቂትም ቢሆን የእፎይታ ጊዜን ስለሚሰጥ ወቅቱን እንጠቀምበት ብለው የሚወተውቱም መኖራቸው ተሰምቷል። ተስፋ ቆርጠው መጨረሻቸውን መጠባበቁ ይሻላል ብለው የበዝባዥን መቀያየር የሚጠብቁ ተገቢ አለመሆናቸውን የሚናገሩ በበኩላቸው፣ ተረኛ መሆን ባንፈልገም ደጃፋችን ባለ ሞፈር ሞኝ መባላችን ማብቃት አለበት ብለው ያስባሉ።

በነዳጅ ስርጭትም ሆነ በዋጋ እንዲሁም በዶላር ላይ የሚከሰት ለውጥ ጥቅምም ጉዳትም ሊያስከትል ይችላል። ውጤቱ በጊዜ ሂደት የሚታይ ነው ብለው አስተያየት የሚሰጡ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ፣ ወገን ሳይዙ በመቆየት ሊገኝ የሚችለው ጥቅም ትልቅ ባይሆንም፣ ማስቀረት የሚቻለው ጉዳት ግን ከፍተኛ ነው ባይ ናቸው። ሩስያ ላይ ምዕራባውያኑ ማዕቀብ ለመጣል አልያም ከተለያዩ ተቋማት ለማባረር በሚወስዱት እርምጃ ከሚቃወሙት በላይ ድምፀ ተአቅቦ የሚያደርጉት በጣም ብዙ መሆናቸው የውስጥ ፍላጎታቸውን የሚያሳይ እንደሆነም የሚናገሩ አሉ።

በሌላ በኩል በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ወገን ላለመያዝ ተስማምተው የነበሩ ኢንዶኔዢያን የመሳሰሉ ያደጉና በርካታ የአፍሪካ አገራት አሁን ወገን መያዛቸው ብዙዎችን እያስገረመ ነው። አንዳንዶች አማራጭ አጥተው መፈናፈኛ ስላሳጧቸው ነው በማለት ሊያስተባብሉላቸው ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ ጥቅማቸውን በማየት እንዳይቀርባቸው አልያም ለወደፊቱ ውለታን ለማስመዝገብ አስበው ነው ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ እየወደቀ ያለ ዛፍ ላይ መንጠላጠል ስለማይጠቅም፣ ከየትኛውም ወገን ይሁን የማያዛልቅ ቡድን መያዙ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ሲሉ ይደመጣሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ገለልተኛ ከመሰለ አቋሙ ተለይቶ የምሥራቁ ጎራ ጋር መቀራረቡን የተመለከቱ በርካቶች ደስታቸውን ሲገልፁ ቢሰማም፣ ከጅብ የማያስጥል የአህያ ወዳጅን አጋር አድርጎ መያዙ ከመበላት አያስጥልም ያሉ ደግሞ ሂደቱን ተችተዋል። <ብቻችንን የትም መድረስ አንችልም> ብለው በራሳቸውም ሆነ በሕዝባቸው ተስፋ የቆረጡ ደግሞ፣ ምንም ቢሆን አንዱን መምረጥና መደገፍ አለብን ይላሉ። ሌሎች ደግሞ፣ ሌባ የሚጣላው ሰርቆ በሚከፋፈለው ስለሆነ፣ በሰረቀው አካል የይመለስልን ጥያቄ ከቀረበ ያስማማቸዋል እንጂ የዘረፉትን አይመልሱም በሚል አገላለፅ የተሰራቂዎች ማህበር እንዲፈጠር ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

በየትኛውም እይታ ቢሆን ሙግቱ ጉዳት ባይኖረውም፣ መታየት ያለበት አሁን ላለንበት ችግር ብቻ ሳይሆን፣ እኛ መውጣት የቸገረን ለልጅ ልጆቻችን ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን በማሰብ መሆን ይኖርበታል። የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ከየትኛውም ጫና ብቻችንን ሳይሆን ከሌሎች ተበዳዮች ጋር ተባብረን የምንነሳበት ጊዜ መሆን አንዳለበት ልንገነዘብም እንደሚገባ ምሁራን ይናገራሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here