በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ የተጋረጠው የፖለቲካ አደጋ

አዲስ አበቤ በኹለት ሁኔታዎች ውስጥ ተወጥሯል የሚሉት ዳንኤል ፀሀይ ሰዋሰው (ዶ/ር)፣ በአንድ በኩል ራስን የመሆን፣ መብትና ጥቅምን የማስከበርና የመታግል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ የፖለቲካ ኀይል ፍላጎትና መስፋፋት የመዋጥ ስሜት ውስጥ ይገኛል ሲሉ ሐሳባቸውን የሚያጠናክሩ ተጨባጭ ያሏቸውን አስረጅ ዘርዝረዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪ (አዲስ አበቤ) የፖለቲካ ውክልና አልባነት አጭር ታሪክ
አዲስ አበባ (አአ) የኢትዮጵያ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ኹነቶች መገለጫ አስኳል ስትሆን፤ ባለፉት አንድ መቶ ኻምሳ ዓመታት ባስተዳደሯት መንግሥታት እና ሕዝቦቿ ጥረትና ትጋት የተገነባች ብርቅዬ ከተማ ነች። ከተማዋ ባለብዙ ገጽ እና ኅብረ ብሔራዊ፤ በዘመናት መካከል በተፈጠረ ሕዝባዊ መስተጋብር የተፈጠረች፤ የራሷ ማንነት፣ መለያ፣ ወግና ባሕል ያላት የመላው ኢትዮጵያውያን ከተማ ነች።

በዘመናዊ ኢትዮጵያ ከ1889 ጀምሮ አአ የአገሪቱ ዋና መናገሻ፣ እንዲሁም የግዛቶች ሁሉ እምብርት ሆና እያገለገለች ትገኛለች። ከ1983 ጀምሮ የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ በሽግግር መንግሥቱ ከ1984 እስከ 1987 አአ በክልልነት ደረጃ ያስተዳደራት ቢሆንም። ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ኅዳር 1987 ከክልልነት ወደ ከተማ መስተዳደርነት ዝቅ ተደረገች። ከተማዋ በተወካዮች ምክር ቤት 23 መቀመጫ እንዲኖራት ቢደረግም፣ በፌዴሪሽን ምክር ቤት ግን ምንም ዓይነት የፖለቲካ ውክልና እንዳይኖራት ተደረገ። በመሆኑም ባለፉት ኻያ ሰባት ዓመታት፣ ከሰባት እስከ ዐሥር ሚሊዮን የሚገመተው ነዋሪ ቀጥተኛ የፖለቲካ ውክል እና የከተማ ባለቤትነት የለውም።

ይህ በፌዴሪሽን ምክር ቤት ተወካይ አልባነት ሆን ተብሎ አዲስ አበባን የማንም ላለማድረግ እና ከተማዋን በገዥ ፖርቲዎች ቁጥጥር ሥር ለማድረግ ያለመ የተጠና ሥሌት ሲሆን በፖለቲካ ቋንቋ የአአ ነዋሪን የከተማ ባለቤትነት የካደ መሰሪ አካሔድ ነው። በመሆኑም በአሁኑ የፌዴራል ሥርዓት፣ የአአ ከተማ ነዋሪ ያለው ምስለኔ የአስተዳደር ውክልና እንጂ ሀቀኛ የፖለቲካ ውክልና ባለቤትነት የለውም፣ በተለይም ባለፈው ኻያ ሰባት ዓመታት አአ በክልል ፖርቲዎች ግንባር (ኢሕአዴግ) እንጂ በእራሷ ልጆች ወይም ፓርቲ ተመርታ አታውቅም። ለምሳሌ አንድ አዲስ አበቤ በፖለቲካ አመራር ወደ ሥልጣን ለመምጣት እና የአአ ሕዝብ ለማገልገል ቢፈልግ፣ የግድ ከአራቱ የክልል ፓርቲዎች መካከል የአንዱ ፓርቲ አባል መሆን አለበት ማለት ነው።

በሥልጣን ባለቤትነት ደረጃም ብናይ፣ የአአ ከተማ መስተዳደር በቻርተር የምትመራ በመሆኗ ምክንያት፣ እንደ ሌሎች ክልል መስተዳደሮች በሕገ መንግሥቱ የተሰጠ ነጻና ቀጥተኛ የሆነ የሥልጣን ባለቤትነት የላትም፣ ይልቁንም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ አዋጅ ቁጥር 361/95 በውክልና ሥልጣን የተቋቋችና የምትተዳደር ከተማ አድርጓታል።

በሌላ በኩልየሕዝብ አገልግሎት መሥሪያ ቤቶችን አወቃቀር እንኳን ብናይ፤ የከተማ ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው በድርጅት (ኢሕአዴግ) አሠራርና አደረጃጀት መሠረት ብቻ ነው። ለምሳሌ አአ የራሷን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ የፀጥታ ኀይል (የፖሊስ ኀይል መመልመል) ብትፈልግ በራሷ ብቻ የማትችል በመሆኑ፣ከ1997 ጀምሮ ከእራሷ ልጆች ይልቅ በብሔረ ተዋፅዖ መሠረት ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ማዕከል ያደረግ ምልመላ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል። ይህ ተግባር በብዙ ጉዳይ ከተማዋን በፌዴራል ተጽዕኖ ውስጥ እንድትውል አድርጓታል፤ እንዲሁም በፌዴራል መቀመጫነት ሥም ብዙ የፖለቲካ መብቶችን መግፈፍና ጣልቃ ገብነት ትልቁ የኢሕአዴግ በደል ነው። በአጠቃላይ ሕዝቦቿ በፖለቲካ በራሳቸው መወከልና ማስተዳደር የዘመናት ጥያቄ ሆኖ አሁን ላይ ደርሷል።

በአአ ዙሪያ የተኮለኮሉ የፖለቲካ ኀይሎችና ፍላጎቶች
አአ የአገሪቱ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ኹነት ሁሉ እምብርት በመሆኗ፣ በከተማዋን የተመረጠ ፖርቲ ሁሉንም የአገሪቱን አውታር የመቆጣጠርና የመግዛት ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ብዙ የፖለቲካ ኀይሎች አአ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ያሳያሉ። ነገር ግን እነዚህ የፖለቲካ ኀይሎች የከተማ ነዋሪዎችን ጥያቄ አውቆ አጀንዳ በመቅረፅ ለመመለስ ከመትጋት ይልቅ፣ የራሳቸውን ዓላማና ፍላጎት ለመጫንና ለማስፋፋት ብቻ የሚተጉ በመሆኑ ሕዝቧ ግራ ተጋብቶ ይገኛል። የአአ ጉዳይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኀይሎች መካከል ትልቅ አጀንዳ ቢሆንም በአለመተማመን የተሞላ በመሆኑ መጨረሻው የማይተነበይ አድርጎታል። በዚህ ምክንያት የተለያዩ የፖለቲካ ኀይሎች በአአ ነዋሪ ላይ ቀጥተኛ ይሁን ተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ለመፍጠር ትግል ሲያድርጉ ይታያል፣ የበለጠ ለመረዳት ዋና ዋና የከተማዋን የፖለቲካ ተዋናዮችን እንመልከት።

1) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና አዲስ አበባ
የአአ ሕዝብ የዐቢይን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ፣ ከፍተኛ ድጋፉ በሰኔ 16/2010 በማድረግ ያለውን ይሁንታ ያሳየ ቢሆንም ቅቡልነቱ የዘለቀው ለጥቂት መጀመሪያ ወራት ብቻ ነበር። የአአ ሕዝብ የዐቢይን ፍላጎት ጥርጣሬ ውስጥ እንዲያነሳ ካደረጉት ኹነቶች ውስጥ፤ የአአ መስተዳደር ምክትል ከንቲባን ታከለ ኡማ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ በፖርላማ አፀድቆ የከተማ ምክር ቤት ተመራጭ አባል ሳይሆን መሾሙ፣ በአአ ዙሪያ ለተፈጠሩ መፈናቅል ያሳያው ለዘብተኛ ምላሽና አያያዝ፣ በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሿሚ ታከለ በየጊዜ በአአ የሚሠሯቸው ሥራዎች የከተማ ነዋሪን ያላማከለ ሥልታዊ አካሔድ መሆኑ፣ የዐቢይ ለባልደራስ ምክር ቤት ያሳዩት በቁጣና ስሜት የተሞላ ምላሽና ንግግር “ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባልን” ማለታቸው፣ በቃሊቲ ክፍለ ከተማ ብዛት ላላቸው ከአንድ ክልል ለመጡ ወጣቶች የመኖሪያ መታወቂያ መሰጠቱ የአደባባይ ሚስጢር መሆኑ እየታወቀ በኹለተኛው የሚዲያ ጥያቄና ምላስ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የክህደት ምላሽ መስጠት እንዲሁም በጊዜ ሒደት አአ ላይ ለተፈጠሩ የተለያዩ ኹነቶችና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋምና መግለጫ ለዘብተኝነት እና ዝምታ መታየቱ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።

በሌላ በኩል የሕዝብን ቀልብ ለመግዛትና የቀጣይ ምርጫ የቤት ሥራ ለመሥራት ዐቢይ በተለያዩ የበጎ አድራጎቶች (ጽዳት፣ ችግኝ ተከላ፣ ብሔራዊ የኩራት ቀን፣ ወዘተ….) ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ይገኛል። እነዚህ ሥራዎች በራሳቸው በጣም መልካም ቢሆኑም መንግሥትን ከዋናው ኀላፊነት ተግባርና የወቅቱ የአገሪቱ ችግር ላይ ትኩረቱን እንዳቀይሱት ያሰጋል፣ በተቃራኒዊም ሕዝብን በአጀንዳ የመያዥያ ዘዴ ሊሆኑ ይችላል የሚል መላምንት ይነሳል።

የዐቢይ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ ጥቂት ወራት በኋላ ከታዩ ተግዳሮቶች በመነሳትና በመማር፣ በአአ ጉዳይ ንቁና ቀጥተኛ ተሳታፊ ከመሆን ይልቅ በተዘዋዋሪ ተጽዕኖውንም በታከለ ኡማ በኩል በማድረግ ዓላማና ጉዳዩን የማስፈጽም አካሔድ እየተከተሉ ይገኛል። ለዚህ ማሳያ፣ አንደኛ የእራሱ ተሿሚ ታከለ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ብዙ ስህተቶች ሲሠራና የከተማዋን ነዋሪ ግራ ሲያጋባ፣ በዝምታ ድጋፍን መስጠታቸው፤ ኹለተኛ ደሴ ላይ በተደረገ ሕዝባዊ ስብሳባ መድረክ ላይ በስፋት እየተሠራበት ስላለው ኢፍትሐዊ የሥራ ስምሪትና ምደባ ዙሪያ ለቀረበላቸው የሕዝብ ጥያቄ፣ “ያለፉ ኢፍትሐዊ አሠራሮች ስለነበሩ ያንን ለማመጣጠንና ለማካካስ እንደሚሠራ” ያስረዱበት አካሔድ አአ ላይ በአሁኑ ሰዓት እየታየ ላለው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቶችን በአንድ አካባቢ በመጡ ሰዎች የመሙላት ዕቅድ ግልጽ ድጋፍና ማሳያ ነው። ይህን አካሔድ በተጨባጭ የሚያጠናክር ሰሞኑን የአዴፖ የአአ ጽሕፈት ቤት የግምገማ መግለጫ ማየት ይቻላል። የታከለ ኡማ አስተዳደር በሥራ ስምሪትና ምደባ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በሚዲያ አጠቃቅም እንዲሁም በአመራር ምደባ ላይ ትልቅ ኢፍትሐዊ አሠራር እንዳሰፈነ መግለጫው ያትታል። በአጠቃላይ የዐቢይ አያያዝና አካሔድ፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያን በአዲስ መልኩ በኦሮሞ ተጽዕኖ የመቃኝትና መቅረጽ ወሳኝ አካል ሲሆን በታከለ በኩል የሚሠሩ ሥራዎች በሙሉ በኦሮሞ አሻራ አአን እንደገና የመሥራት ውጥን አንዱ ፕሮጀክት እንደሆነ ልብ ይሏል።

2) ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማና አዲስ አበባ
ታከለ ኡሞ ከሹመታቸው ጀምሮ ሕገ ወጥ ሲሆን በከተማ ነዋሪ ምርጫ ያልተመረጠና የምክር ቤት አባል ያልሆነ ነገር ግን በፖለቲካ ውሳኔና አካሔድ የመጣ ከንቲባ ናቸው። ታከለ በዋናነት የዐቢይን ተልዕኮና ዓላማ ለማስፈጸም የተሾሙ መሆኑን ለማወቅ ከተለያዩ ኹነቶች ማወቅ አያዳግትም። በተለይም የታከለ አስተዳደር በዋናነት ከዚህ በፊት በነበረው ስርዓቶች “ኦሮሞ በልኩ የሚባገውን አላገኝም” የሚለውን መነሻ በመያዝና የአአ ላይ ልዩ ጥቅም አሁን መከበር አለበት ብሎ በጥብቅ እየሠራ ያለ አስተዳደር ነው። አአን በኦሮሞ ተጽዕና አሻራ ለመቅረጥ፣ ታከለ በዋናነት የነዋሪውን አመለካከት ለመቀየርና ለመግዛት እንዲሁም ፖለቲካውን ለመቆጣጠር የተለያዩ አካሔዶች በተጠና መልኩ ይተገብራሉ፤ ከብዙ በጥቂቱ፡-

ሀ) የአቀራረብ ለውጥ በማድረግ በብዙ በጎ አድራጎትና (ለምሳሌ፣ የአረጋዊያን የክረምት ቤት እድሳት፣ የተማሪ ደብተር ስብሳባ፣ ጽዳት፣ ማስ ስፖርት፣ ችግኝ ተከላ፣ ወዘተ….) ሕዝባዊ የገጽ ግንባታ ላይ በማተኮር እንዲሁም በሚድያ ላይ የተጋነነ ሽፋን በመሥራት ድብቅ ዓላማን የማሳካት አካሔድ። በተለይም የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኅንን የከተማዋን ነዋሪ ድምጽና ስሜት ከማስተናገድ ይልቅ የአመራርን ሥም ዝናና ስብዕና በመገንባት ላይ ያተኮረ ሥራ ላይ መጠመድ ዋናው ሲሆን ይህ አካሔድ ሕዝበኝነትን የሚያነግስ መሆኑን ማውቅ ይገባል።

ለ) ሥውርና ሥልታዊ በሆነ መልኩ የዲሞክራፊክ ለውጥ ማምጣት። ይህ አካሔድ ኹለት ዓይነት መልክ አለው፣ አንደኛ በዘላቂነት አአ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠርና ለመቆጣጠር የሥነ ሕዝብ ለውጥ እስከ 40 በመቶ ማምጣት፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በተቻለ መጠን በአአ ዙሪያ ሕዝብ የማስፈርና የማመጣጠን ሥራ መሥራት (ይህን ስትራቴጂ በግልጽ በኦሮሞ ልኂቃና ሹመኞች የሚቀነቅን ነው፣ ለምሳሌ አዲሱ በአሜሪካ ሉስ አንጀለስ ቆንስላ ዳሬክተር ብርሃነመስቀል (ዶ/ር) በቅርቡ በሚድያ መግለጻቸው ይታውቃል)፤ ኹለተኛ በመካከለኛና አጭር ጊዜ ዕቅድ መሠረት በተለያዩ ክፍለ ከተማዎች በገፍ የነዋሪነት መታውቂያ ካርድ እዳላ ማድረግና አዳዲስ ወጣቶች ወደ ከተማዋ ማስገባት እንዲህም በመጪው ምርጫ አስተማማኝ የድጋፍ መሠረት መፍጠር ዕቅድ ናቸው።

ሐ) በከተማ አስተዳደር አገልግሎት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ብዛት ያለው የሰው ኀይል ቅጥር በመፈፀም፣ የመንግሥትን ቢሮክራሲ መቆጣጠርና ማመጣጠን። ባልተገባ ድጋፍ እና እርዳታ በእውቀትና በአቅም ተወዳድሮ የሚይዝ የሰው ኀይል ከመቅጠር ይልቅ፣ ሲቪል ሰርቪስ ከሚፈቅደው ውጭ ልዩ ምደባ መፈፀም። እነዚህ ዓላማዎችን ለማሳካት በስውር ሆነ በግላጭ የታከል ኡማ አስተዳደር በሙሉ አቅሙ እየሠራ ይገኛል። በዚህም ውጤታማ ሲሆን ማንኛውም ዜጋ የአንድ ክፍለ ከተማ ቀበሌ በመሔድና መጎብኘት ያለውን አዲስ የባለሙያ ስብጥር መመልከት ይችላል። ምን አልባትም ይህ ሒደት በዚህ ከቀጠለ በቅርብ ጊዜ መሠረታዊ የሚባል የባለሙያ ለውጥ በአአ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች እንደምናይ መገመት አያዳግትም።

መ) መሬትን ባልተገባ መልኩ መያዝ። በከተማይቱ አአ ውስን የሆነው የመሬት ሀብት ሕጋዊ ባልሆነ አግባብ እየተወረረና ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈጸመበት ይገኛል። ያልተያዙ እና ልማት ላይ ያልዋሉ መሬቶች ወደ መሬት ባንክ አገልግሎት መግባት ሲገባቸው፣ ሥልታዊ በሆነ አካሔድ ለቡድንና ግለስብ መጠቀሚያ እየሆነና ግልጥ ባልሆነ አሠራር ለተጠቃሚ እየተላለፋሉ ይገኛል።

ሠ) ፍትሐዊ ያልሆነ መኖሪያ ቤት ድልድል። አአ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ችግር አንዱ ሲሆን ይህንን ለመፍታት የተዘረጋው የቤቶች ልማት ፕሮግራም በሚፈለገው ፍጥነት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያላረጋገጠ ነው፤ ይልቁንም የከተማ ነዋሪዎች ለዘመናት በቁጠባ ያገኙትን የቤት ዕጣ ዕድል እንዳይጠቀሙና ቤት እንዳይረክቡ ሲደረግ፣ ምንም ዓይነት መፍትሔ ሳይሰጥ የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የከለከለ አስተዳደር ሆኗል።

ረ) በግለሰብ ይሁንታ የአመራር ምደባና ሽግሽግ ማድረግ። የአአ መስተዳድር፣ በመሪ ድርጅቱ ኢሕአዴግ አሠራር መሠረት የአመራር ምደባ፣ ስምሪትና ሽግሽግ የሚያደረግ ቢሆንም ይህን ድርጅታዊና ተቋማዊ አሠራር በመጣስ በግለስብ ፍላጎት ይሁንታና አድራጊ ፈጣሪነት የአመራር ምደባና ሽግሽግ እያከናውነ ይገኛል፣ የታከለ አስተዳደርም አምባገነናዊነት እንዲሰፍን እየሠራ ይገኛል።

ሰ) ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የአዲስ አበባ ምክር ቤትን ቆይታ ለአንድ ዓመት ማራዘም። የአዲስ አበባ ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ያለው የቆይታ ጊዜ አምስት ዓመት ብቻ ሲሆን ታከለ ኡማ ሕገ ወጥ በሆነ አካሔድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት አስወስነው ተጨማሪ አንድ ዓመት ያለ ሕዝብ ፈቃድ ወይም ይሁንታ ሥልጣን ላይ ይገኛሉ። አንደኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዲስ አበባ ምክር ቤት ውስጥ ገብቶ ሕዝባዊ ተሳትፎና ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሥልጣን የለውም፤ ኹለተኛ በአዲስ አበባ ምክር ቤት ይሁን በሌላ የክልል ምክር ቤቶች ላይ፣ የምክር ቤት ሥልጣን ማራዘም በሕግ መንግሥት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያልተሰጠ መብት በመሆኑ ድርጊቱ ትልቅ ጣልቃ ገብነትን የሚያሳይ አካሔድ ነው።

መሆን የነበረበት የአዲስ አበባ ምክር ቤት የቆይታ ጊዜው ሲያልቅ በሌላ ሕዝባዊ ምርጫ የመተካት እንጅ በተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ሥልጣን ማራዘም ሕገ ወጥ አሠራር ነው። እንደዚህ ዓይነት የሥልጣን ክፍተቶች ሲፈጠሩ በዋናነት የስምምነት መንግሥት በመመሥረት ዋናውን የሕዝብ ሥልጣን ይሁንታ ከምርጫ በኋላ ማረጋገጥ ትክክለኛ ሕጋዊ ሒደት ነው። ነገር ግን በአዲስ አበባ ላይ ታከለ ኡማ እያደረጉት ያሉት አካሔዶች የሕዝቡን ፖለቲካዊና ዲሞክራሲዊ መብት የጣሱ፣ የሕዝቡን ዘላቂ ጥቅም አሳልፎ የሚሰጡ፣ የሚጎዱና የፖለቲካ ውክልና የሚከለክሉ ናቸው።

ሸ) በመጨረሻም፣ የታከለ አስተዳደር ምንም ዓይነት የተቃዋሚ ኀይሎች እንዳይኖሩ ማድረግና የዐቢይን ቅቡልነት በመጠቀም ኢሕአዴግን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ የማቅረብና የማመቻቸት ሥራ በስፋት እየሠራ ይገኛል። በዚህ ረገድ በአንድነት ኀይሎች ጎራ፣ የአአ ነዋሪን ለመብቱ ያታግሉታል ተብለው የሚታሰቡት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ፣ አሁን ላይ የዐቢይ ደጋፊ ሲሆኑ፣ የሕዝብን ጥያቄና ፍላጎት ችላ በማለትና ሥልጣን ብቻ ግብ በማድረግ የታከለን አስተዳደር ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ እየተባበሩ ይገኛሉ።

ከላይ የተዘረዘሩት መሰሪ አካሔዶች በአጠቃላይ መላው የአአ ነዋሪ የፖለቲካ ፍላጎትና ጥቅም ግምት ውስጥ ያላስገቡ ሲሆን የታከለን አስተዳደር የሚደግፍ ነዋሪ (የተደመረ) ብቻ አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኙ ያለሙ ናቸው። እንደማሳያ ከወራት በፊት ለሥራ ፈጠራ እና ብድር አገልግሎት ወጣቶች እንዲደራጁ በማድረግ አብዛኛው ካንድ አካባቢ ለመጡ ወጣቶች የብድር አገልግሎት ቢሮክራሲ የሚጠይቀውን ሒደት በመዝለል እስከ ሦስት መቶ ሺሕ ብር ያበደረ ሲሆን ለአአ ወጣቶች (አዲስ አበቤ) ግን በቀድመ ሁኔታ ለተደመሩና ለታመኑ ብቻ አድርጎታል።

3) የአንድነት ኀይሎች እና አዲስ አበባ
ኢዜማ በተለይም የቀድሞው ግንቦት 7 ከለውጡ በኋላ ወደ አገር ሲገባ በዋናነት የድጋፍ መሠረት ባለባቸው አካባቢዎች (አዲስ አበባ፣ ደቡብና የአማረ ክልል) የአንድነት ኀይሉን ያንቀሳቅሳል ያታግላል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም። አገር ቤት ከገባ በኋላ ለውጡን ለመደገፍ ቅድሚያ እንስጥ በሚል፣ በሕዝቦች ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ከመቆም ይልቅ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የዐቢይን አስተዳደር የመደገፍና የመከላከል ሁኔታ ውስጥ የገቡ ሲሆን በሚደግፋቸው ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ብዥታ የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል።

በተለይም መሠረታዊ በሚባሉ የአገሪቱ ፖለቲካ ኹነቶች ላይ ያሳዩት መለሳለስ፣ አንዳንዴም የመደግፍ አዝማሚያ፣ የቆሙት ለሥልጣን ነው ወይስ ለፖለቲካ ትግል የሚል ጥያቄ ያስነሳል። እንደማሳያ፣ አምስት የኦሮሞ ፖርቲዎች በአአ የባለቤትነት ጉዳይ በሰጡት አደገኛ መግለጫ ላይ ያሳዩት ዝምታ፣ በሕገ ወጥ መንገድ በገፍ ሰለሚሰጡ የነዋሪነት መታወቂያ እና በአአ ልዩ ጥቅም ጉዳይ ምንም ዓይነት የአቋም መግለጫ አለማውጣት፣ የታከለ አስተዳደር የሚወስዳቸውን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ላይ እንዳላይና እንዳልሰማ ማለፍ ይገኙብታል።

ተለዋዋጭ በሆነው በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኢዜማ እያሳየው ያለው የአድርባይነት እና የመለጠፍ አካሔድ ከኢሕአዴግ በላይ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የሚማራውን የአንድነት ኀይል አደገኛ ቅርቃርና የቅቡልነት ምስቅልቅል ውስጥ የከተተ መሆኑን ልብ ይላል። መሆን የነበረበት እራስን ችሎ አጀንዳ ይዞ ከሕዝብ ጎን በመቆም ልክ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲነት የዐቢይ አስተዳደርን በመገዳደርና ማስጨነቅ ኢሕአዴግን ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ ነበር። በመሆኑም ለአንድነቱ ጎራ ከዚህ ቀደም በቀላል የሚያገኙትን የድጋፍ መሠረት አሁን በቀላል እንደማያገኙት ልብ ይላል።

በሌላ በኩል ኢዜማ፣ ለዐቢይ እና ለታከል በአአ ጉዳይ ከሚያሳዩት ተለጣፊነት በላይ በትልቅ የመመረጥ ዕድል ባላቸው አአ ላይ ከመሥራት ይልቅ፣ የአማራ የፖለቲካ ኀይሎችን (አብን፣ አዴፓ) የማጥቃት እንዲሁም እስጣ ገባ ውስጥ መግባት ኹለት ዓይነት እንደምታ ይሰጣል። አንደኛ አማራ በኢትዮጵያነት ስለሚያምን ከተቻለ የአንድነት ኀይሉ በአማራ ክልል ውስጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ የአማራ ፖለቲካ ኀይሎችን በምርጫ በማሸነፍ አማራን ማዳከምና ለኦሮሞ የበላይነት አሳልፎ የመስጠት፤ ኹለተኛ ከሌላው በተሻለ አማራ ክልል የመመረጥ ዕድል ስላለ አጋጣሚው ከተገኘ አማራ ላይ በመሥራት ወደ ሥልጣን መውጣጫ መንገድ ማድረግ ናቸው።

በተለይም ሰሞኑን በታከል ኡማ አስተዳዳር ላይ ያሉትን ውስጣዊ ችግሮችና ልዩነቶች በማጋለጥ ረገድ የአዴፓ አአ ጽሕፈት ቤት ባደረገው ግምገማና ያወጣው ጠንካራ ባለዐሥራ አንድ አቋም መግለጫ፤ የእነ ብርሃኑ ነጋ መሰሪ አካሔድን ያመላከተ እንዲሁም ለአአ ሕዝብ ደንታ ቢስነታቸውን፣ ለታከለ አስተዳደር መሸፋፈን ውስጥ መግባታቸውን ያሳየ ትልቅ ክስተት ሆኖ አልፋል። በአጠቃላይ የአንድነት ኀይሉ ከዐቢይ አስተዳደር በተለየ የሕዝብን ጥያቄ ወደ አጀንዳ ቀይሮ ለፖለቲካዊ ትግል አለመዘጋጀቱ፤ አንደኛ የቅቡልነት ችግር በራሱ ላይ ፈጥራል። ኹለተኛ የአአ ሕዝብ ትክክለኛ አታጋይና ጥቅሙን የሚያስጠብቅለት የፖለቲካ ኀይል በትክክለኛ ሰዓትና ቦታ አሳጥቶታል።

4) የባልደራስ ምክር ቤት እና አዲስ አበባ
የባልደራስ ምክር ቤት አመሠራረትና አመጣጥ በዋናነት የኦሮሞ ፖለቲካ ኀይሎችና ታከለ ኡማ በአአ ላይ በሚያራምዱት አቋምና አያያዝ ጋር የተገናኘ ነው። በተለይም በአአ ልዩ ጥቅም ጉዳይ አምስት የኦሮሞ የፖለቲካ ኀይሎች ያወጡት የአቋም መግለጫ፣ ጃዋር መሐመድ በየጊዜ የአአ ጥቅምና የነዋሪ መብት የሚጋፋ አካሔድና ዘመቻ፣ እንዲሁም በታከለ ኡማ በኩል ለአንድ ክልል ለመጡ ወጣቶች በስፋት የአአ መኖሪያ መታወቂያ እደላ ዘመቻ ተከትሎ የተመሠረት ሕዝባዊ እንቅስቃሴነው።
የባልደራስ ምክር ቤት፣ በባልደራስ አዳራሽ ከአምስት ሺሕ በላይ የአአ ነዋሪ ይሁንታ መሠረት በ2011 የተቋቋመ የሲቪክ እንቅስቃሴ ሲሆን የማንም ፓርቲን የማይወክልና የማይደግፍ፣ እንዲሁም ለፖለቲካ ሥልጣን የማይወዳደር (Non-Partisan) ነገር ግን የአአ ሕዝብ መብትና ጥያቄ አንግቦ የሚንቀሳቀስ የሕዝባዊ ድምፅ ነው።

የባልደራስ ምክር ቤት የከተማን ነዋሪ መብት ወደ ፖለቲካው ሜዳ ይዞ መምጣት በአአ ዙሪያ ለተኮለኮሉ የፖለቲካ ኀይሎች ትልቅ ራስ ምታትና ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ ነበር። አስገራሚው ነገር አንድም የፖለቲካ ፓርቲ በአአ ዙሪያ ከባልደራሱ ጋር አብሮ ለመሥራት ፍላጎትን የገለፀ ወይም ያሳየ አለመኖሩ ነው፣ እዚህ ላይ የባልደራስ ጥያቄዎች ሕዝባዊ እንደሆኑ ልብ ይሏል። በሌላ በኩል የባልደራስ መምጣት የአንድነት ኀይሉ ለምን ዓላማ እንደ ቆመ ሕዝቡን ያሳየ ትልቅ የመፈተሻ ኹነት ሆኖ አልፎል። በተለይም ብርሃኑ ነጋ የባልደራሱ እንቅስቃሴን ማውገዝ አስገራሚ ሲሆን ተገዳዳሪነት በመፍራት ይሁን ለዐቢይ ድጋፍ በመስጠት አይታውቅም።

የባልደራስ ትልቁ ፈተና ከዐቢይ እና ከታከለ ኡማ አስተዳደር የመጣ ሲሆን ዋናው ስትራቴጅ ደግሞ ባልደራሱን ሥር ሳይሰድ እንቅስቃሴውን መቆጣጠር እና ማዳከም ነው። እንደማሳያ ምንም ዓይነት ስብሰባና መግለጫ እንዳይሰጥ ማድረግ እንዲሁም እንቅስቃሴውን ፀረ-ኦሮሞ አድርጎ በኦሮሞ ሕዝብና የፖለቲካ ኀይሎች እንዲታይ ማድረግ። እነዚህ ዘዴዎች በተወሰነ መልኩ ውጤታማ ሲሆኑ፣ ብዙ የኦሮሞ የፖለቲካ ማኅበረስብ ባልደራሱ ላይ አሉታዊ አመለካከት እንዲኖረው አድርጓል።

ሌላው አማራጭ ደግሞ የተለያዩ ኹነቶችን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የባልደራስ እንቅስቃሴ ማዳከምና መቆጣጠር። ለምሳሌ፣ የሰኔ 15 የባሕር ዳር ኹነት ተከትሎ፣ በተለይም ከሰኔ 17/2011 ጀምሮ ከፍተኛ የሚባል አፈሳ በአዲስ አበባና ባሕር ዳር እንዲሁም በተለያዩ የወረዳ ከተሞች የተፈፀመ ማድርግ፤ በተለይም የአስራት ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች፣ የባልደራስ አባላት፣ በአስራት ቴሌቪዥን ቀርበው ከሰኔ 15 በፊት አስተያየት የሰጡ ሰዎችን ሰብስቦ በሽብር ሕግ መክሰስ እንደምን አድርጎ ተያያዥ እንደሆነ ማሰብ አስገራሚ ነው።

የተጠርጣሪዎች አያያዝም ሰብአዊነት የጎደለው ነው፣ ገና ማጣራትና ምርመራ ላይ እያሉ መደበኛ ክስ ሳይመሰርት፣ መርማሪዎች በፀረ ሽብር ሕግ አዋጅን በመጠቀም፣ ሽብረተኛ ብሎ መጥራት/መበየን፣ እንዲሁም ማንገላታትና ማሸማቀቅ የዕለት ተዕለት ተግባር እንደሆነ ከተጠርጣሪዎች የሚቀርቡ ስሞታዎች ናቸው። በምርመራ ከሚነሱ ጥያቄዎች ወይም ምክንያቶች ውስጥ ለምን አብንን ትደግፋላችሁ፣ ባላአደራው አይጠቅማችሁም፣ ለምን ታከለ ኡማን አትደግፉም፣ ለምን በሞባይል መልዕክት ትላላካችሁ፣ ወዘተ የሚሉ ከሰኔ 15ቱ ኹነት ጋር ግንኙነት የሌላቸው ናቸው። እስካሁን ባለው መረጃ በአአ በአዲስ ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ብቻ ዘጠና አንድ ሰዎች ሲታሰሩ፤ በክልል የታሰረው በቁጥር እስከ አሁን በውል አይታወቅም።

በአጠቃላይ በአአ ከተማ መመረጥ የሚፈልጉ የፖለቲካ ኀይሎች ከባልደራስ ምክር ቤት ጋር ለመሥራትና ያነሱትን የሕዝብ ጥያቄ አጀንዳ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ፣ ዐቢይና ታከለን ላለማስቀየም በሚመስል መልኩ ዝምታና ባላየ ማለፍን የመረጡ ሆኗል። ለአአ ነዋሪ ግን ተቃዋሚዎች እየሔዱበት ያለው አካሔድ፣ የነዋሪዎችን ፍላጎትና ጥቅሙን አሳልፎ እንደ መስጠት የሚቆጠር ነው። ምክንያቱም በዚህ ጊዜ አታጋይ የፖለቲካና ማኅበራዊ አደረጃጀት በሚያስፈልገበት ወቅት ራስን መደበቅ፣ በኋላ ላይ ዋጋ እንደሚያስከፍልና በምርጫ የሕዝብ ይሁንታ ማግኘት አዳጋች እንደሚያደርግ ልብ ይሏል። ነገር ግን በተቃራኒው አሁን ያለው የአአ የፖለቲካ ሁኔታ የተወሰኑ አደረጃጀቶች ብቻ ለሕዝቡ ተቆርቋርና ድምፅ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ የባልደራስ ምክር ቤትን በአአ ነዋሪ ዘንድ እውቅና ተቀባይነትን በቀላሉ ጨምሮለታል።

ማጠቃለያ
የአአ ነዋሪ በኹለት ሁኔታዎች ውስጥ ተወጥሯል፤ ባንድ በኩል ራስን የመሆን፣ መብትና ጥቅምን የማስከበርና የመታግል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ የፖለቲካ ኀይሎች ፍላጎትና መስፋፋት የመዋጥ ስሜት ውስጥ ይገኛል። የአአ ነዋሪ እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ እንዲገባ ያደረግው፤ በዋናነት አአን በተመለከተ የአንድነት ኀይሎች በግልጽ አቋም ወደ ፖለቲካ ሜዳው አለመቅረብና ሕዝብን አለመታገል እንዲሁም ወቅቱ የሚፈልገውን የፖለቲካ ቁመና ላይ አለመገኘታቸው ነው። በመሆኑም ሕዝቡ አማራጭ በማጣቱ ምክንያት በሒደት እንደ ባልደራስ ያሉ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በፍጥነት እንዲቀበልና እንዲደግፍ አድርጎታል። በሌላም በኩል አአ ነዋሪ በሚያስዝን ሁኔታ ከሌሎች ክልል አስተዳደሮች ባነሰ ሁኔታ ላለፉት ኻያ ሰባት ዓመታት የፖለቲካ ውክልና ተነፍጎ እየኖረ ይገኛል። የአዲስ አበቤ አንኳር ችግሮችና ጥያቄዎች ውስጥ 1) ራስን በራስ ማስተዳደር፣ 2) በራስ ሀብት ላይ ወሳኝ መሆን፣ 3) ፍትሕና አገራዊ ውክልና (በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና ማግኘት)፣ 4) ማንነትን፣ ባሕልን፣ ሥነ ጥበባዊ እሴቶችን መጠበቅ ማበልጸግ ናቸው።

ዳንኤል ፀሀይ ሰዋሰው (ዶ/ር) የሥነ ልቦና መምህርና ተማራማሪ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው sewsewdaniel@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here