ዕረቡ ግንቦት 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ፈረንሳይ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገሯ የገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ልትመልስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከ15ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ጅማሮ ባሉት ዓመታት ውስጥ የተሰሩት ቅርሶቹ ከሦስት ዓመታት በፊት በሕገ-ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወደ ፈረንሳይ ከተጓጓዙ በኋላ በፓሪስ ሮይሲ አውሮፕላን ማረፊያ የተያዙ ናቸው ተብሏል፡፡
በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ባለስልጣን ጋር በጉዳዩ ላይ የተወያየ ሲሆን፤ ቅርሶቹ በመጪው ሰኔ ወር እንደሚመለሱ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 125ኛ ዓመት በሚያከብሩበት በዚህ ወቅት፤ የቅርሶቹ መመለስ የኹለቱን አገራት በባህል ዘርፍ ያላቸውን ጠንካራ ትስስር የሚያመላክት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
በተጨማሪም የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑዌል ማክሮን በሕገ-ወጥ መንገድ የተጋዙ የአፍሪካ ቅርሶችን ለመመለስ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ የፈረንሳይ መንግስትን በጉዳዩ ላይ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑም ተገልጿል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n





