አበባ

ሰሞኑን መነጋገሪያ ከሆኑ አገራዊ ጉዳዮች አንዱ አዲስ አበባ ቀለሟ ግራጫ እንዲሆን መወሰኑ ነው። አበባ የተባለች ከተማ ግራጫ ትሁን መባሉ ምን ዓይነት ግራጫ አበባ ቢያውቁ ነው በሚል ሐሳቡ ለትችት ተዳርጓል።

ከተማዋ ካሏት ሕንፃዎች አብዛኞቹ ግራጫ ስለሆኑ ሌሎቹም እንደነሱ ይምሰሉ በሚል፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ሕንፃዎች ለወጪ ቁጠባ ተብሎ ቀለም እንዲቀይሩ መባሉ ብዙዎችን ያስደነቀ ተግባር ሆኖ ነበር። አገሪቷ እንዲህ በኑሮ ውድነትና በተለያዩ ችግሮች በተወጠረችበት ሰዓት ማስቀየሻ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ማንን ስለጎዱ ነው ቀለም ቀይሩ የሚባሉት በሚል ሕንፃ ካላቸው ሰዎች ይልቅ የሌላቸው ናቸው እሪታቸውን በጽሑፍ ያቀረቡት።

የቀለም ባለሙያዎች ምንም ብዙ ሕንፃ ግራጫ ቢቀባም ሳይንሳዊ በሆነ ጥናት የቀለሙን ጎጂነት ለማመላከት ጥረዋል። ግራጫ ቀለም ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጠፉ ይጋብዛል በሚል ምርጫው ተገቢ አይደለም በሚል ቢደረግ እንኳን ጠቃሚ ቀለም ይሁን ብለዋል። የግለሰቦችን አስተያየት ተንተርሰው አንዳንዶች መንግሥት ምን ዓላማ ቢኖረው ነው በማለት ሐሳቡን የተቹ ሲሆን፣ ሕዝቡ በሰው እጅና በተፈጥሮ አደጋ እየሞተ አላልቅ ቢላቸው፣ ራሱን እንዲያጠፋ ብለው እንዲህ ዘየዱ በሚል በለውጡ ሐሳብ ላይ ተሳልቀዋል።

አንዳንዶች የተዥጎረጎሩ ውብ ከተማዎችን በምስል እያስደገፉ ነዋሪዎቻቸው በተድላ እንደሚኖሩም በማመላከት፣ ማን ይሆን ይህን የመሰለ ሐሳብ የሚያመጣው በሚል ዓላማው ይጣራ ሲሉ ጠይቀዋል። ድሃ አገር ሆነን ሳለ ሀብታሞቹ እንኳ ያላደረጉትንና አስፈላጊ ያልሆነን ተግባር ለማከናወን ለጥናቱ ጭምር ወጪውን ያስወጣው አካል ሀብትን በማባከን መጠየቅ አለበት ያሉም አሉ።

የከተማው አስተዳደር በወራት ውስጥ ሞዴል የሚሆን ሠርቶ ማሳያ አካባቢ እለያለሁ ማለቱም ግራ አጋብቷል። በምን ሂደት አካባቢው የሚመረጥ መሆኑ ይፋ ባይደረግም፣ ወጪውን ባለሀብቱ እንዲሸፍን መታሰቡ ለትችት በር ከፍቷል።

የከተማዋ ዝብርቅርቅ ቀለም ወጥ መሆን አለበት ያለው መንግሥት፣ ለዐይኔ አላማረኝም እያለ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ላይ መድረሱና አሳቢ መስሎ ሳያፍር ማቅረቡን የኮነኑ በርካቶች ናቸው። መንግሥት በዚህ አስተሳሰቡ ከቀጠለ ሐዘን ላይ ያለ ሕዝብ አብዛኛው ጥቁር ስለለበሰ አልያም በቤቱ ጥቁር ልብስ ስለማያጣ ሁሉም ጥቁር ለብሶ ይውጣ ማለቱ አይቀርም ሲሉ የጨርቁንም ዓይነት እንደቀደመው ዘመን ካኪ ሳይሉ በፊት አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ የመከሩ አሉ።

ባለሥልጣናቱ የሕንፃዎቹ ቀለም ካጥበረበራቸው ወይም ከተዘበራረቀባቸው፣ አንዱን ከሌላው ለመለየት የሚያስቸግር ተመሳሳይ ግራጫ ቀለም ከማስደረግ ይልቅ አጎንብሰው ለምን አይሄዱም፣ አልያም ግራጫ የሚያሳይ መነፅር ለምን አይገዙም እያሉ ሐሳቡ ላይ የቀለዱም ብዙ ናቸው። የማን ዘመድ የቀለም ፋብሪካ ከፍቶ ለማበረታታት ታስቦ ነው ሲሉ ሴራ እንዳለበት የታያቸውም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች