መነሻ ገጽዜናትንታኔአፋር ከሰብዓዊ ቀውስ እስከ “ጦርነት በቃን”

አፋር ከሰብዓዊ ቀውስ እስከ “ጦርነት በቃን”

ጦርነት የሰላማዊ ሕይወትንና ኑሮን ዋጋ በሚገባ የሚያስረዳ አንዱ ክስተት ነው። ይህንን አንድም መሬት ላይ ወርዶ በአፋር ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪ በሆኑ፣ አስቀድሞ የነበራቸው ሕይወት ተመሰቃቅሎ ሌላ መልክ ይዞ በተገኘባቸው ሰዎች ሕይወት በግልጽ መመልከት ይቻላል። ሠርቶ መብላት በአንድ ጀንበር ወደ ተረጂነት ሲቀየር፣ የሞቀ ቤትና የተሻለ ኑሮ ቀርቶ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ መገኘት የግድ ሲል፤ የጦርነት ክፉ ገጽታ በግልጽ ይታያል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ወደ አፋር ባቀናበት ወቅት በአፋር የተለያዩ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎችን ቃኝቶ፣ ከባለታሪኮች አንደበት እውነትን ቀድቶ እንደሚከተለው አሰናድቶታል።


ኢድሪስ አሊ አሕመድ በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን (ዞን-2) የበርሃሌ ወረዳ አርብቶ አደር ሲሆኑ፣ የአራት ሚስቶች ባለቤትና የ12 ልጆች አባት ናቸው። የአፋሩ አርብቶ አደር ራሳቸውን ጨምሮ 17 ቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው። ኢድሪስ ብርቱ አርብቶ አደር ሲሆኑ፣ ኑሯቸውን የሚገፉት በእንስሳት እርባታ ነበር።

ይሁን እንጂ የብርቱው አርብቶ አደር ቤተሰብ መተዳደሪያ የነበሩት እንስሳት ዛሬ ላይ በአርብቶ አደሩ ቀዬ የሉም። ከኢድሪስ መንደር የሌሉት የ17 ቤተሰብ መተዳደሪያ የነበሩ የቤት እንስሳት ብቻ ሳይሆኑ፣ የኢድሪስ አራት ሚስቶችና 12 ልጆችም ተወልደው ባደጉበትና የልጅነት ጊዜያቸውን ካሳለፉበት አካባቢ አሁን አይገኙም። ሚስቶችና ልጆቻቸው ከቀያቸው የሌሉት ለሽር ሽር ወይም ዘመድ ጥየቃ ወደ ሌላ ቦታ አቅንተው ሳይሆን፣ ከሰላሙ ቤታቸው የሚያስወጣው አስከፊ ጦርነት ገጥሟቸው እንጂ።

የ17 ቤተሰብ አስተዳዳሪውና አርብቶ አደሩ ኢድሪስ ሕይወት፣ ከአራት ወራት በፊት በዞኑ በተጀመረው ጦርነት ምክንያት ከአርብቶ አደርነት ወደ ሌላ ገጽ ተቀይሯል። ሕይወታቸው የተቀየረው ከአርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነት ወይም ወደ ነጋዴነት ሳይሆን፣ ከብርቱ አርብቶ አደርነት ወደ ተረጂነት ነው። በሰላሙ ጊዜ በተለይ በፍየል እርባታ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩት ኢድሪስ፣ አሁን ላይ ቤተሰቦቻቸው በመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ። የኢድሪስ ሚስቶችና ልጆች በጦርነቱ ተፈናቅለው ከሰመራ ከተማ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አሳይታ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ናቸው።

ኢድሪስ በጦርነቱ ቀኝ እግራቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የአፋር ክልል ዋና ከተማ ከሆነቸው ሰመራ ከተማ በ11 ኪሎ ሜትር ርቅት ላይ በሚገኘው ዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ሕክምና ሲከታተሉ ነው፤ አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው። ጠጋ ብላም ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በሕክምና ላይ የሚገኙትን አርብቶ አደር ስለደረሰባቸው ጉዳትና እንዴት ከአካባቢው እንደወጡ ለጠየቀቻቸው ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹ጁንታ የሚባል የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ጦርነቱን ጀምሮ በከባድ መሣሪያ ሁላ እየተኮሱ ሲመጡ፣ ያንን ጦርነት ለመመከት ወደሄድኩበት አካባቢ ላይ ያጋጠመኝ ችግር ነው።” አሉ።

“በዚያ ሰዓት አካባቢው ላይ ሴትም፣ ሕጻናትም፣ አዛውንትም ነበሩና ሕጻኖቻችን ላይ፣ ሴቶቻችን ላይ የሚደርስ ጉዳት የማይቀር ስለሆነ መመከት አለብን ብለን ፊታችንን ወደዚያ አዞርን” የሚሉት ኢድሪስ፣ ጦርነቱ ብዙ ዓይነት ጉዳት አስከትሏል ይላሉ። “ሴቶቻችን ተደፍረዋል፣ መንገድ ላይ ያገኙትን ከብት የሚጠብቁ አዛውንትና ልጆች ተገድለዋል” ይላሉ።

“በርሃሌ ንግድ ባንክ ነበር። በጥይት በማቃጠል እንዲሁም መስጊድን በማቃጠል ብዙ የሀይማኖት ተቋማትን አፍርሷል።” የሚሉት ኢድሪስ፣ በጦርነቱ የተፈናቀለው ማኅበረሰብ በመጠለያ ጣቢያዎችና በተለያዩ ከተሞች ተበታትኖ እንደሚኖር ይናገራሉ። በጦርነቱ የተፈናቀለው የማኅበረሰብ ከፍል “ምንም ይዞ አልወጣም፣ ተመልሶ ለመቋቋም ብዙ አይነት ነገር ስለሚያስፈልግም ምንም ተመልሶ የሚያርፍበት ቦታ ስለሌለ፣ እስከ አሁን እዚህ ላይ አለ” ይላሉ ኢድሪስ ለአዲስ ማለዳ ሲያብራሩ።

ኢድሪስ በደረሰባቸው ጉዳት ሕክምና ለመከታተል ዱብቲ ሆስፒታል ይኑሩ እንጂ፣ ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩት ከሰመራ 70 ኪሎ ሜትር በምትርቀው አሳይታ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ነው። በአሳይታ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ የሚገኙት የኢድሪስ ልጆችና ሚስቶች ከበርሃሌ ሲፈናቀሉ ምንም አይነት ንብረት አለመያዛቸውን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ ለተረጂነት ተጋልጠዋል።

በጦርነቱ ቤት ንብረታቸውን ጥለው የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተፈናቀሉት ኢድሪስ፣ ወንድማቸው በጦርነቱ ሞተውባቸዋል። በዚህም በጦርነቱ የሞቱትን ወንድማቸውን ኹለት ሚስቶችና ስምንት ልጆች ከራሳቸው አራት ሚስቶችና 12 ልጆች ጋር በጋራ የማስተዳደር ኃላፊነት እንዳለባቸው ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ከጦርነቱ በፊት ራሳቸውን ጨምሮ የ17 ቤተሰብ አስተዳደሪ የነበሩ ሲሆን፣ በጦርነቱ ወንድማቸውን በሞት ማጣታቸውን ተከትሎ ተጨማሪ 12 ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት ተቀብለዋል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ 29 ቤተሰብ የሚያስተዳደሩበት አቅም ስለሌላቸው 28 ቤተሰቦቻቸውን በአሳይታ መጠለያ አስጠልለው ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ነው።

ተፈናቃዮች እንዴት እየኖሩ ነው?
የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከ18 ወራት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ እስከ አሁን ሦስት ክልሎችን አካሏል። ጦርነቱ የተካሄደባቸው ትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልሎች ሲሆኑ፣ ጦርነቱ በሦስቱም ክልሎች ለዜጎች ሞት፣ አካል ጉዳት፣ መፈናቀልና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል።

ከሐምሌ 2013 መጀመሪያ ጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ከነበረው የሰሜኑ ጦርነት በኋላ፣ ሕወሓት ከኹለቱ ክልሎች ከአምስት ወራት በፊት መውጣቱ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ሕወሓት ከአማራ እና አፋር ክልሎች መውጣቱ ከተገለጸ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኹለቱም ክልሎች የትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች በሕወሓት ጥቃት በድጋሚ መፈናቀላቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል።

አዲስ ማለዳ በአፋር ክልል በተለይ ከዞን ኹለት በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎች የሚገኙበትን ሁኔታ በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች በመገኘት፤ በጸጥታ ሁኔታ በአካል መገኘት ባልቻለችባቸው ቦታዎች ደግሞ ተፈናቃዮችን በስልክ አነጋግራለች።
አዲስ ማለዳ በአሳይታ መጠለያ ካምፕ ተገኝታ ያነጋገረቻቸው ተፋናቃይ ዜጎች በተለይ በቂ የውሀ አቅርቦት፣ የሕክምና አገልግሎት፣ የሕጻናት አልሚ ምግብና የቤት ውስጥ መገልገያ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

በአሳይታ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አንዷ የሆኑት ሰአዳ መሐመድ ‹‹እጃችን ላይ ሳንቲም እስካለን እንታከማለን። ከሌለን ግን ያው ታመንም ቢሆን ችለን ነው የምናድረው። አካባቢው ላይ የማኅበረሰቡ ድጋፍ ስላለ፣ በዚያ አማካኝነት የተወሰኑ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት አሉ። እና በዚያ አማካኝነት ነው የምንኖረው። ሕዝቡ መደጋገፍ ባህላችን ስለሆነ፣ በዚያ ምክንያት ነው የምንኖረው።” ሲሉ ስለ ሕክምና አገልግሎቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሌላኛዋ በአሳይታ መጠለያ ካምፕ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እናት መሊካ ከድር ሲሆኑ፣ “በዋናነት ያለው ችግር የጤና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን፣ ውሀም የምንቀዳበት የእቃ ችግር አለ። በዋናነት የእቃ ችግር ነው ያለብን” ይላሉ። እንደ ምግብ፣ አልባሳት የሕጻናትና የእናቶች አልሚ ምግብ አቅርቦት ውስንነቶች እንዳሉ የሚናገሩት የአሳይታ መጠለያ ካምፕ ተፈናቃዮች፣ ችግሩን የተቋቋሙት በአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብርና ድጋፍ መሆኑን ይናገራሉ።

ጦርነቱ ከደረሰባቸው ከዞኑ ኹለት ወረዳዎች ጦርነት ወዳልደረሰባቸው አጎራባች ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም አለመኖሩን አዲስ ማለዳ በስልክ ያነጋገረቻው ተፈናቃዮች ጠቁመዋል። በጦርነቱ ከተጠቁ እንደ በርሀሊ፣ መጋሊ የመሳሰሉ ወረዳዎች ተፈናቅለው አጎራባች ወደሆነው አፍዴራ ወረዳ የተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥት ድጋፍ እያደረገላቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዱ የሆኑት ሰዲቅ አሕመድ፣ አብዛኛው ተፈናቃይ ከአካባቢው ርቆ መሄዱን ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ በተለይ አቅመ ደካሞችና አቅመ ደካማ ቤተሰብ ያላቸው ሰዎች ሰላም ወደ ሆነው አጎራባች መጠጋትን መርጠዋል ይላሉ። አፍዴራ አካባቢ የሚገኙ ተፈናቃዮች የሚገኙበት ሁኔታ አስከፊ ነው የሚሉት ሰዲቅ፣ “ተፈናቃዮች የምንበላው የምንጠጣው የለንም፣ የአርብቶ አደር ኑሮ በእጃችን ምንም የለንም” ይላሉ።

በሰላሙ ጊዜ ኑሯቸውን የሚገፉት በአርብቶ አደርነት እንደሆነ የሚናገሩት ሰዲቅ፣ በጦርነቱ ምክንያት የአርብቶ አደርነት ሕይወታቸውንም አጥተው ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ይጠቅሳሉ። “በባዶ ነው የተፈናቀልነው። ከዚያ እያለን በአህያ ከሩቅ ውሀ እየቀዳን ነበር የምንጠቀመው። አሁን በርሃብና በጥም ላይ ነው ያለነው” ይላሉ። “ረሀብና ጥሙ ከሙቀቱ ጋር ተባብሮ ሽማግሌዎችና ሕጻናት እየሞቱብን ነው፣ መጓጓዣም የለ፣ የበረታው ወጣቱ ወደ ሌላ ቦታ እየወጣ ነው” ብለዋል።

አፍዴራ የሚገኙ ተፈናቃዮች በረጂ ድርጅቶችም ይሁን በመንግሥት እርዳታ እያገኙ አለመሆኑን የሚገልጹት ሰዲቅ “የምንበላው ስናጣ በየቀኑ ፍየል አርደን እየበላን ነበር” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚተባበር ቢሆንም እየቆየ ሲሄድ ችግሩ የጋራ እየሆነ መምጣቱንም ይናገራሉ። በተለይ በዞን ኹለት በተከሰተው ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች የገጠማቸው ችግር “ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ” ሊባል የሚችል መሆኑን ሰዲቅ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“በረሃውን አቋርጠው አፍዴራ ሲደርሱ ብዙ ሕጻናት ሕይወታቸው አለፈ። በውሃ ጥም እና በረሃብ ምክንያት እዚህ የደረሱ እድለኞች ደርሰዋል። በሕይወት እያሉ በቂ ምግብ የለም፣ ምንም ዓይነት የጤና አገልግሎት የለም” የሚሉት ሰዲቅ፣ ችግሩን መንግሥት ወደ አፍዴራ እርዳታ የማይልከው በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ትግራይ ይገባል በሚል ስጋት እንደሆነ መስማታቸውን ይናገራሉ።

መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ ለተፈናቃዮች ካለማድረሱ በተጨማሪ ባለው የጸጥታ ሁኔታ ወደ አካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፣ አፍዴራ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ አሰባስበው ወደ አፍዴራ ለማጓጓዝ የጠየቁ የአፋር ተወላጆች “የኮንትሮባንድ ንግድ ነው በሚል ሰበብ፣ ከውጭ የሰበሰብነውን ድጋፍ ለወገናችን እንዳናደርስ ተከልክለናል” ይላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ቢሮ ከአንድ ሳምንት በፊት በጦርነቱ ተፈናቅለው አፍዴራ የሚገኙ ሕጻናት ከደረሰባቸው የረሃብና የጥም ጉዳት እንዲያገግሙ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። በማዕከሉ የሕክምና እንክብካቤ ያገኙ ሕጻናት ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዳቸውን የሚያሳይ ምስል ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ በትዊተር ገጹ አጋርቷል።

ሌላኛው አዲስ ማለዳ የተመለከተችው የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ከሰማራ ከተማ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ዱብቲ ከተማ የሚገኝ ነበር። አዲስ ማለዳ በቦታው በደረሰችበት ጊዜ ዱብቲ የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ አሳይታ የተዛወሩ መሆኑን ሰምታለች። ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ዱብቲ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ምንም ሰው ባይኖርም የተፈናቃዮች መጠለያው አልፈረሰም።

አዲስ ማለዳ በዱብቲ መጠለያ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ነገር ግን ወደ አሳይታ ሲዛወሩ የዘጠኝ ዓመት ልጃቸው ታሞባቸው ዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል እያስታመሙ የቀሩ እናት አግኝታ አነጋግራለች። እኚህ እናት ሥማቸውን ለመናገር ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ በዱብቲ ሆስፒታል በረንዳ ላይ ልጃቸውን እያስታመሙ ስላሉበት ሁኔታ ለአዲስ ማለዳ አጫውተዋታል።

- ይከተሉን -Social Media

“ባለቤቴ እዚያው ሞቷል። ልጆቼን ይዤ ብሸሽ ልጄ ታመመብኝ” የሚሉት እኚህ እናት፣ አምስት ልጆቻቸው በአሳይታ መጠለያ ካምፕ ይዘው እንደሚገኙ ይናገራሉ። ልጃቸውን ለማሳከም በእጃቸው ላይ ምንም ገንዘብ የሌላቸው በመሆኑ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር ጠይቀው በተደረገላቸው ድጋፍ ልጃቸው እያሳከሙ ነው።

አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ የተመለከተችው ዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ከበረንዳ እስከ አልጋ ከፍል በቁስለኞችና በሕሙማን ተጨናንቋል። በየበረንዳው የሚታየው የቁስለኛ እና ታማሚ ብዛትና የአስታማሚዎች ትካዜ በቦታው ሆኖ ለተመለከተው “አዬ ሰው!” ያሰኛል።
ዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል በሰሞኑ ጦርነት ምክንያት የጤና ተቋማት በመውደማቸው፣ ዜጎች ተፈናቅለቀው ወደ አካባቢው በማቅናታቸውና በጦርነቱ የሚቆስሉ ሰዎችን የማስተናገድ ኃላፊነት ተደራርቦበታል። በዚህም ከመድኃኒት እጥረት እስከ የሕክምና ባለሞያ እጥረት እንዳስተናገደ እና በዚህም ታካሚዎችን በሚፈለገው አግባብና ፍጥነት የሕክምና አገልግሎት እንዳይሰጥ እንቅፋት ሆኖበት እንደከረመ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በሆስፒታሉ የድንገተኛ ክፍል ሐኪም ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
የደንገተኛ ክፍል ሀኪሙ እንደሚለው ሆስፒታሉ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ታካሚዎችን እያስተናገደ ቢሆንም፣ አገልግሎቱ ከተገልጋዩ ብዛት አንጻር የአገልግሎት እርካታ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ጠቁመዋል።

በሰመራና ሎጊያ ከተማ ቤት ተከራይተውና ቤተሰብ ጋር ተጠግተው የሚኖሩ ተፈናቃዮች የእርዳታ ተጠቃሚ አይደሉም። ሎጊያ ሰመራ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች አዲስ ማለዳ ሰማራ በነበረችበት በኢድ አልፈጥር በዓል ከክልሉ መንግሥት የምሳ ግብዣ ሲደረግላቸው ተመልክታለች። ይሁን እንጂ ቋሚ ድጋፍ እንደማያገኙ ያነጋገረቻቸው ተፈናቃዮች ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ከሳምንት በፊት ባወጣው ሪፖርት፣ በአፋር ክልል ከ600 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች የምግብ ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል ብሏል። በክልሉ የዞን ኹለት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ አጋሮች ዝቅተኛ መሆኑንም የኦቻ ሪፖርት ያመላክታል።

በአፋር ክልል በዞን ኹለት በአንዳንድ አካባቢዎች ማለትም በኮኔባ፣ በርሀሊ እና አባላ ወረዳዎች አሁንም ሰላም አለመሆኑን የጠቆመው የኦቻ ሪፖርት፣ የሰብአዊ ድጋፍ ወደ እነዚህ አካባቢዎች ለማድረስ አስቸጋሪ ሆኗል ብሏል። “በአፋር ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰብዓዊ ሁኔታው አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል” ያለው ኦቻ፣ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት አሁንም በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ፍላጎቶች ለማሟላት በቂ አይደለም ብሏል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም በበኩሉ፣ ከአንድ ወር በፊት በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ አደረግኩት ብሎ ይፋ ባደረገው የዳሰሳ ቁጥጥር ሥራ፣ አሁን ላይ ከዞን ኹለት ከስድስት ወረዳዎች ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች 336 ሺሕ 582 ናቸው ብሏል። ከእነዚህ መካከል ወንድ 164 ሺሕ 925፣ ሴት 171 ሺሕ 657 ናቸው። ሕፃናቱ 175 ሺሕ 23፣ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት 70 ሺሕ 682 እንዲሁም ነፍሰ ጡርና አጥቢ የሆኑ እናቶች 16 ሺሕ 829 መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

ዕምባ ጠባቂ በሪፖርቱ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች (ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን) የሚደረግላቸው ሰብአዊና ቁሳዊ ድጋፍ በቂና ተመጣጣኝ አለመሆኑን ተመልከቻለሁም ሲል ጠቅሷል። ለአብነትም የሕጻናት አልሚ ምግብ፣ ለአጥቢ እናቶች ወተት አለመኖር፣ ለሴቶች የንጽህና መጠበቂያ አለመሟላት፣ አቅም ላጡ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ወገኖች እርዳታው ባሉበት ቦታ ያለማዳረስ ችግሮች ይስተዋላሉ ብሏል።

ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች፣ ለተመላላሽ ታካሚዎችና በቋሚነት መድኃኒት ለሚወስዱ የመድኃኒት አቅርቦቱ ሲታይ ውስንነት መኖሩና የመጠለያ ችግር መመልከቱንም ተቋሙ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

“ጦርነት በቃን”
አዲስ ማለዳ በአፋር ክልል በተገኘችባቸው ቦታዎች የተለያዩ ተፈናቀዮችን ሕይወት በቦታው በመገኘት ከመመልከት በተጨማሪ፣ በጸጥታ ስጋትና በትራንስፖርት ችግር መድረስ ያልቻለችባቸውን አካባቢዎች በስልክ አነጋግራለች። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ኑሯቸው ወደ ተረጂነት ከተቀየረ ከአፋር የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል፣ ወንድማቸውን በጦርነቱ ምክንያት ከማጣት እስከ ከፍተኛ አካል ጉዳት ችግር የደረሰባቸው የአፋሩ አርብቶ አደር ኢድሪስ አሊ አሕመድ የችግሩን አስከፊነት “የደረሰበት ያውቀዋል” ይላሉ።

በጦርነቱ ምክንያት ኑሯቸው ከአርብቶ አደርነት ወደ ተረጂነት የተቀየረው ኢድሪስ አሊ አሕመድ፣ ምንም እንኳን ከእነ ቤተሰባቸው የከፋ ችግር ቢያጋጥማቸውም፣ በጦርነቱ የደረሰባቸውን እያሰቡ “ጦርነት በቃ” ይላሉ። በጦርነቱ ኑሮው የተመሰቃቀለው የአፋር አርብቶ አደር ወደ ቀድሞ ሰላሙ ተመልሶ ኑሮውን በሰላም እንዲመራ መፍትሔ ያሉትን ሐሳብ ኢድሪስ ሲገልጹ፣

“እኔ በዋናነት እንደ መፍትሔ የሚታየኝ ነገር፣ ያው እርቅ ነው። ዋናው ነገር ወደ እርቅ መግባት፣ የአፋርና የጁንታውን ጦርነት አስቁመን በአገራችን ሰላም እንዲሆን፣ በዋናነት ኹለቱ ወደ እርቅ ወርደው መታረቅ ነው። መንግሥትም ወደ መሬት አውርዶ፣ ወደ አንድ መልሶ ሕዝባችን በሰላም እንዲኖር ስሜቴ ነው።

ጦርነት ደግሞ አስከፊ ነው። ጦርነትን ደግሞ የደረሰበት ነው የሚያውቀው እና ስለ ጦርነት መጥፎነት እኔም ስለማውቀው ምንም ሕዝባችንም ቢጎዳ፣ ንብረታችን ቢወድምም አሁንም ለሰላም ቅድሚያ እሰጣለሁ። ዋናው ሰላም ነው እና ሰላምን የመሰለ ነገር የለምና ወደ ታች ወርዶ ሁሉም አመራር፣ ሁሉም በመንግሥት ያሉት አካላት ወደ እርቅና ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ ማድረግ አለባቸው ነው የምለው።” ይላሉ።

አዲስ ማለዳ ይህን ዘገባ ለማዘጋጀት ወደ አፋር ክልል በተጓዘችበት ወቅት በጉዳዩ ላይ የክልሉ የመንግሥት አካላት መረጃ እንዲሰጧት ከአንድም ኹለቴ ቢሯቸው እየተመላለሰችና በስልክ እየደወለች ብትጠይቀም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰች በኋላም ይህ ዘገባ እስካጠናቀረችበት ሰዓት ድረስ ጥረት አድርጋ አልተሳካላትም።

ከፌዴራል መንግሥት በኩል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴ ምላሽ እንዲሰጧት አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄ፣ ሦስት ጊዜ ቀጠሮ ቢሰጧትም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።


- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች