መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበዘጠኝ ወራት 2 ሺሕ 822 የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች የምዝገባ አገልግሎት ተሰጥቷል

በዘጠኝ ወራት 2 ሺሕ 822 የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች የምዝገባ አገልግሎት ተሰጥቷል

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን በዘጠኝ ወራት ውስጥ ባደረገው የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች የምዝገባ አገልግሎት፣ በፈጠራ ሥራ ባለቤትነት (Patent)፣ በንግድ ምልክት እና በቅጅ መብት 2 ሺሕ 822 የባለቤትነት መብት መስጠቱን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ880 ወይም 45 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው ተቋሙ ያሳወቀው።

በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ታምሩ ታዬ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የአእምሯዊ ንብረት መብቶች የምዝገባ አገልግሎት በፈጠራ ሥራ ባለቤትነት (Patent)፣ በንግድ ምልክት እና በቅጅ መብት ለ2 ሺሕ 246 ተገልጋዮች የባለቤትነት መብት ለመስጠት ዕቅድ ተይዞ፣ ለ2 ሺሕ 822 ተገልጋዮች መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።
በቅድመ ምዝገባ አገልግሎትም ከሦስት ሺሕ በላይ ተገልጋዮችን ማስተናገድ እንደተቻለ ነው የተናገሩት።

እንዲሁም በንግድ ምልክት፣ በፓተንት እና በቅጅ መብት ዘርፎች ለሚሰጡ አገልግሎቶች የአገልግሎት ክፍያ በመሰብሰብ፣ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 18 ሚሊዮን 73 ሺሕ 971 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 18 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ13 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንዳለው ገልጸዋል።

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በንግድ ምልክት፣ በፓተንት፣ በቅጅ መብት በሚሰጠው የምዝገባ አገልግሎት ቅሬታ ያለው ማንኛውም ተገልጋይ ይግባኝ የሚልበት የአእምሯዊ ንብረት የትሪቡናል ስርዓት ያለው ሲሆን፣ በዚሁም መሠረት በበጀት ዓመቱ 9 ወር የቀረቡ አቤቱታዎች፣ የተደረጉ ችሎቶች፣ የተዘጋጁ የውሳኔ ሐሳቦችና የተሰጡ ውሳኔዎች ስለመኖራቸው ተጠቅሷል።

በዚህም ተቋሙ 48 የይግባኝ ማመልከቻዎችን የተቀበለ ሲሆን፣ ከቀረቡት አቤቱታዎች መካከል የ37ቱን ማመልከቻ በመመርመር ችሎት ማስቻል ተችሏል ነው የተባለው። ከ2013 በጀት ዓመት የተንከባለለ መዝገብን ጨምሮ 44 መዝገቦች ላይ የውሳኔ ሐሳብ መዘጋጀቱና የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጣቸው ለ42 መዝገቦች መሆኑ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ በፊልም፣ ሙዚቃ፣ መጽሐፍ እና ሌሎች ከአዕምሯዊ ንብረት ጋር በተያያዙ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ከፍተኛ የሆነ ሊለማ የሚችል አቅም ቢኖራትም የምታገኘው ጥቅም ግን ከበርካታ አገራት ያነሰ መሆኑ ነው የተመላከተው።
በተለይ የቅጅ መብት ጥበቃ ከሚያስገኘው ከፍተኛ አገራዊ ጥቅም አንፃር እስከ አሁንም ድረስ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ነው የተገለጸው።

በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የቅጅ መብት ጥበቃና ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወሰን ሙሉ፣ እንደ ሕንድ፣ ናይጄሪያ እና ሲንጋፖር ያሉ አገራት አዲስ የእድገት ምዕራፍ የከፈቱት የቅጅ መብታቸውን (Copy right) በአግባቡ በመያዛቸው መሆኑን ጠቁመው፣ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የቅጅ መብት ፅንሰ ሐሳብ በማኅበረሰቡ ዘንድ ገና በሰፊው ሰርፆ አልገባም ብለዋል።

በዚህም ጃማይካ ሙዚቃ፣ ናይጄሪያ ደግሞ ፊልምና ሙዚቃ ለውጭ ገበያ በማቅረብ (Export) ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኗን አመላክተዋል። እንዲህም ሆኖ ዘርፉ ለአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚው (GDP) ከ4 ነጥብ 5 በመቶ በላይ አስተዋፅኦ ያበረክታል ነው ያሉት።

አጠቃላይ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶች ምዝገባ መረጃን በተመለከተም፣ 17 ሺሕ 111 ንግድ ምልክት፣ 101 በፈጠራ ሥራ ባለቤትነት፣ 1 ሺሕ 56 ግልጋሎት ሞዴል፣ 242 አስገቢ ፈጠራ ሥራ ባለቤትነት (Patent)፣ 948 ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ እንዲሁም 6195 የቅጅ መብት በአዕምሯዊ ንብረት መብቶች የምዝገባ አገልግሎት የባለቤትነት መብት መሰጠቱ ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች