ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲሚንቶ ቸርቻሪዎችን ተክተው ሊሠሩ ነው

0
1430

የሲሚንቶ ቸርቻሪ ነጋዴዎችን ሙሉ በሙሉ ከስርዓቱ እንዲወጡ በማድረግ በየክልሉ ያሉ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተክተው እንዲሠሩ ለማስቻል እየተሠራ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት በገበያው ላይ በቂ የሲሚንቶ ምርት ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ በገበያ ላይ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በአማካይ እስከ አንድ ሺሕ አንድ መቶ ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሆነ እና መንግሥት ሲያደርግ የነበረው የቁጥጥር ሥራ መነሳቱም እየታየ ላለው ችግር አባባሽ ሆኖ እንደተገኘ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቁምነገር እሸቱ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ኃላፊዋ የተጠቀሰውን ችግር ለመቅረፍ እና ኅብረተሰቡ የሲሚንቶ ምርቶችን በአግባቡ እንዲያገኝ እንደታሰበ እና በቀጣይ የሲሚንቶ ቸርቻሪ ነጋዴዎችን ሙሉ በሙሉ ከስርዓቱ እንዲወጡ በማድረግ በየክልሉ ያሉ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተክተው እንዲሠሩ ይደረጋል ብለዋል። እንዲሁም የጅምላ አከፋፋዮች ሚና ከፍ እንዲል በዋና ዋና ከተሞች አስፈላጊውን ሎጂስቲክ በማሟላት ምርቱን ቀጥታ ለተጠቃሚ የሚቀርብበት ስርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር የሲሚንቶ ምርት ግብይት እና የቅብብሎሽ ሰንሰለቱ ላይ የሚታየውን የምርት መደበቅን ጨምሮ ሌሎች ውስብስብ እና በስውር የሚካሄዱ አሠራሮችን በማስቀረት በመንግሥት ዋጋ የሚተመንባቸው መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ውስጥ በማስገባት ከፋብሪካ በር ጀምሮ እስከተጠቃሚው የመሸጫ ዋጋ በመተመን ስርጭትን የመምራት ሥራ እንደሚከናወን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ በተጨማሪ አምራች ፋብሪካዎች በሰፋፊ ከተሞች የሲሚንቶ ምርቱን የሚያሰራጩበት መጋዘን እንዲከፍቱ ከማድረግ ባለፈ ምርቱን ከከተሞች ውጭ ለሚኖሩ ሰዎች እንዲሁ ጅምላ አከፋፋዮች እና ሸማች ማኅበራት በቸርቻሪዎች አማካኝነት በቀጥታ ለተጠቃሚዎች የሚያደርሱበትን ስርዓት አመቻችቶ ይሠራል ተብሏል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የጸጥታ ችግሮች ሲፈጠሩባቸው በነበሩ አካባቢዎች ያሉ ፋብሪካዎች ምርት ማምረት ባለመቻላቸው ለሲሚንቶ ምርት እጥረት ተጠቃሽ ምክንያት ነው የተባለ ሲሆን፣ በቀጣይ ማምረት ያቆሙ ፋብሪካዎች ወደማምረት መመለስ እንዲችሉ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ማሽኖች ለመተካት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከፋብሪካዎቹ ጋር ውይይት ተደርጎ ለመፍታት እንደሚሠራ እና በተለይ ሀበሻ ሲሚንቶ እና ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ምርቱን ማምረት እንዲችሉ ያሉባቸው ችግሮች ተለይተው ይፈታሉ ተብሏል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተጀመረውን ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታውን አጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ልዩ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግም ተመላክቷል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዘርፉ ሊሰማሩ የሚችሉ ባለሀብቶችን ሊያበረታታ የሚችል የኢንቨስትመንት ድጋፍ በማድረግ አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን በተለይም የጥሬ ዕቃ ግብዓት ባሉባቸው አካባቢዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ረገድ የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ እንደሚሠራ ተጠቁማል።

አብዛኛው ፋብሪካዎች አምርተው ለገበያ ከሚያቀርቡት የምርት መጠን በላይ ቅድመ ክፍያ በመጠቀም የሲሚንቶ ግብይቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን በተደጋጋሚ ሚኒስቴሩ የሚገልጽ ሲሆን፣ ለአብነትም የሀበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከጅምላ አከፋፋዮች የሽያጭ ገንዘብ ተቀብሎ ከስምንት ወራት በላይ ምርት ሳያስረክብ ቆይቷል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here