ለክልሉ አርሶ አደር 769 ሺሕ ኩንታል ብቻ ተሰራጭቷል
በዘንድሮው የምርት ዘመን ለአማራ ክልል የሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ በዕቅድ የተያዘው 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የነበረ ቢሆንም፣ እስከ አሁን የገባው 29 በመቶ ብቻ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ ከሚያስፈልገው 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የተገዛው 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የገባው 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታሉ ብቻ ነው ብለዋል። ቀሪውን እየጠበቅን ነው፣ ችግር ካልተፈጠረ በስተቀር እስከ ሰኔ 30 እንዲገባ እንፈልጋለን ነው ያሉት።
እስከ አሁን ለአርሶ አደሮች የተሰራጨው 769 ሺሕ ኩንታል መሆኑን ጠቅሰውም፣ በኩንታል ከ4 ሺሕ 600 እስከ 4 ሺሕ 700 አማካይ ዋጋ እየተሰራጨ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የመግዛት አቅም ለሌላቸው አርሶ አደሮችም የዋጋውን የተወሰነ መጠን ከፍለው በዱቤ እንዲወስዱ የተመቻቸላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹ልንገዛ ካቀድነው 58 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ነው የገዛነው። በዚህም ዐስር ኩንታል የሚፈልግ አንድ ገበሬ አምስት ኩንታል ብቻ ገዝቶ ሌላውን በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመሸፈን ይገደዳል።›› ነው ያሉት። ከዚህ በኋላም የአቅርቦት መጠኑ እንደማይስተካከልና በመንግሥት በኩልም አዲስ ነገር ሊኖር እንደማይችል ነው የጠቆሙት።
በዶላር እጥረትና በዋጋ መናር ምክንያት የዋጋ መናርና እጥረት መፈጠሩን ጠቅሰውም፣ ችግሩ በመላ አገሪቱ የተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩሪያ የተሰኘውን የአፈር ማዳበሪያም እስከ አሁን ኹለት መርከብ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን፣ ቀሪ ሰባት መርከብ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
‹‹ገበሬዎች ዋጋው ይቀንሳል የሚል ተስፋ የሰጧቸው አካላት ስለነበሩ አድማ አድርገው ነበር። አሁን ግን፣ ችግሩ ተነግሯቸው እየገዙ ነው።›› ብለዋል። ድጎማ ይኖራል ብሎ የሚጠብቅ አካል ሊኖር እንደማይገባም አክለዋል።
ሆኖም በአማራ ክልል ያለው የአፈር ማዳበሪያ ከፍተኛ ዋጋ እና እጥረት በርካታ አርሶ አደሮች መሬታቸውን እንዳያርሱ እንዳደረጋቸው ነው የሚነገረው። አዲስ ማለዳ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ባደረገችው ማጣራት፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ባሉ የተወሰኑ ቀበሌዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ የሚሰጣቸው በመሬታቸው ልክ ሲሆን፣ ለሌሎች ደግሞ መሬታቸው ቢያንስም ቢበዛም አንድ ከረጢት ብቻ ተሰጥተው ጠብቁ እንደተባሉ ተገልጿል።
በሰሜን ወሎ ዞን ከሚገኙ አርሶ አደሮች በተገኘ መረጃም ከሳምንት በፊት ብዙዎች የአፈር ማዳበሪያ መግዛት ቢፈልጉም ማግኘት እንዳልቻሉ ነው።
የጎጃም ገበሬዎች እንዲሁ ከፍተኛ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ያጋጠማቸው ሲሆን፣ ከቦታው አንድ ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የግብርና ባለሙያ እንደገለጹት፣ በጥቁር ገበያ አንድ ከረጢት ማዳበሪያ በ3 ሺሕ ብር እየተሸጠ ይገኛል። ‹‹ከየት እንደሚመጣ አይታወቅም። ሆኖም በማኅበራት ሠራተኞች በኩል በሕገ ወጥ መንገድ እንደሚወጣ ይነገራል።›› ብለዋል።
‹‹ዩሪያ የለም›› ሲሉ አክለውም፣ በዋጋ ውድነቱ እና በእጥረቱ የተነሳ በርካታ አርሶ አደሮች መሬታቸውን እያረሱ እንዳልሆነና ሌሎችም ለሌላ እንዳከራዩት ተናግረዋል።
ብዙ አርሶ አደሮች ችግሩ እንደሚፈጠር ቀድሞ እውቅና ስላልተፈጠረላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዳላዘጋጁም ተነግሯል። በዚህም አንዳንዶች ጓሯቸውን ያለማዳበሪያ እየዘሩ ሲሆን፣ ያለ አፈር ማዳበሪያ የሚያበቅል ባለመሆኑ፣ ትንሽ ከጠበቅን ሊመጣ ይችላል በሚል የዘር ወቅት እያለፋቸው ነው ተብሏል።
የአፈር ማዳበሪያ ችግሩ በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ መሆኑ ይነገራል። ይህንንም በሚመለከት አዲስ ማለዳ ከግብርና ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014



