የሕፃናቱ መተጫጨት

0
1038

ሰሞኑን መነጋገሪያ ከነበሩ አንኳር ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ ትምህርት ቤት አንድ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ዩኒፎርም የለበሱ ተማሪዎች ሲተጫጩ የታዩበት ምስል ነው። ወንድየው ተንበርክኮ ለሴቲቱ የጣት ላይ ቀለበት ሲያጠልቅ (የወርቅ ይሁን የዘንባባ መሆኑ በግልፅ ባይታይም) ተመልክተናል።

አንዳንዶች ለቀልድ የተደረገ አስመስለው ሲዝናኑበት የታየ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ የትውልድ ዝቅጠትን ያሳያል ሲሉ ተመሳሳይ ምስሎችን በማጋራት እርግማን ቀረሽ ትችታቸውን ሰንዝረዋል። ነገሩን ልዩ ያደረገው ደግሞ እንደፋሽን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መደረጉ ሲሆን፣ ልጆች የሆኑ ተማሪዎቹ በፉክክር ተጫጭተው እንዳያልቁ ሲሉ የተዘባበቱባቸውም አሉ።

ተደብቀው ወይም ከትምህርት ገበታቸው ርቀው አለማድረጋቸውን ያስተዋሉም፣ እግረመንዳቸውን ቀለበት አግኝተው የሚያስቀምጡበት አጥተው እንዳይሆን ሲሉም ቀልደዋል። የሚተጫጩት ተማሪዎችን ከበው የሚታዩት እኩዮቻቸው፣ እየተንጫጩ ፎቶ እያነሱ ታሪኩን በምስል ለማስቀረት ሲራወጡ ማየት ነገ ተረኛ ለመሆን አሰፍስፈው የሚጠብቁ ያስመስላቸዋል።

የተማሪዎቹ ሁኔታ ከፍቅር የመነጨ ሊሆን ይችላል ብለው ሐሳባቸውን የሰጡት ላይ አስተያየታቸውን የሰነዘሩቱ እንዳሉት፣ ዓላማቸው የቀለም ትምህርት እንጂ ከትዳር ትምህርት የሚወስዱበት በፈተና የሚያልፉበት ተቋም አይደለም።

በሌላ በኩል ልጆቹ እንዲህ ሲያደርጉ የሚያሳየውን ምስል ወላጆቻቸው ቢያዩ ምን ይላሉ እያሉ እንዳይሰራጭ የሚጥሩትን አሳቢዎቻቸውን ያህል፣ ቤተሰቦቻቸው ይዩትና ጉዳቸውን ይወቁ ያሉም ነበሩ። በባህላችን መሠረት መሆኑ ቀርቶ አጉል ጥራዝ ነጠቅ ለመሆን መሞከራቸው፣ ሕፃናቱ በፊልም ዓለም ላይ እንዳሉ አመላካች ነው ሲሉ ሂደቱ ከወዲሁ እንዲታረም ምክራቸውን የለገሱም በርካቶች ናቸው።

ይህ የተማሪዎች መተጫጨት የገረማቸው ሰዎች እንዳሉት፣ ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ተግባርን በአደባባይ ማድረጉ አልበቃ ብሏቸው፣ ምስሉን ለሕዝብ ለማጋራት ካልጨነቃቸው፣ እንግዲያው በስውር ስንት ነገር ውስጥ ገብተው ይሆን ሲሉም ስጋታቸውን ጠቅሰዋል። ይህ አይነት አስተያየት መሰጠቱን ተከትሎ አንዳንዶች በዐይናቸው ያዩትን የተማሪዎች ተግባር በመጥቀስ የትውልዱን አካሄድ የኮነኑም አሉ።

ወላጆች በድሮ ጊዜ ልጆቻቸው ሲያድጉ የሚያገቡትን መርጠው፣ “ልጅህን ለልጄ” ተባብለው በተዋዋሉት መሠረት ሲያድጉ አልያም ቀድመው ያጋቡ እንደነበር ይነገራል። ይህ አሁንም በከተማ ጭምር ያልቀረ አጉል ባህል ነው ተብሎ እየተወገዘ ባለበት ሰዓት፣ ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው ሊድሩ ራሳቸውን ሳይችሉ ሲተጫጩ ማየት ያሳዛናል ሲሉ አስተያየት የሰነዘሩም አሉ።

ይህ አይነት ድርጊት በሌሎች አገራት እንደሚደገፍም ይወራል። ተማሪዎች ካደጉ በኋላ በፍቅር ዓለም ባርቆባቸው እንዳይጎዱ ከልጅነታቸው እንዲለማመዱት የሚመክሩም አሉ። ይህ ማለት ግን ትዳር ይያዙ ሳይሆን ተቃራኒ ፆታ ጋር ያላቸው ቅርርብ ጤናማ እንዲሆን ያግዛል ይላሉ።
የተማሪዎቹን መተጫጨት ያዩና ድርጊቱን የኮነኑት፣ ትምህርት ቤቶች እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ሊቆጣጠሩ ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል። በምን መንገድ ብለው የሚጠይቁና፣ ለማወቅም ሆነ ለመቆጣጠር ከባድ እንደሚሆን የሚሞግቱም አሉ። ያም ተባለ ይህ፣ ለሁሉም ጊዜና ቦታ አለው በሚለው መስማማቱ የተሻለ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here