መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበአማራ ክልል በዘጠኝ ወራት 471 ሴቶች ተጠልፈዋል ተባለ

በአማራ ክልል በዘጠኝ ወራት 471 ሴቶች ተጠልፈዋል ተባለ

በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 471 ሴቶች መጠለፋቸውን የአማራ ክልል ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የአማራ ክልል ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ስማቸው ዳኘ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በክልሉ ያለው ጠለፋ እና ያለእድሜ ጋብቻ እንደቀጠለ ነው። በ2013 ሐምሌ ጀምሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 471 ሴቶች ካለፍላጎታቸው ተጠልፈዋል ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም በተያዘው ዓመት በክልል ያለው ያለዕድሜ ጋብቻ እንደጨመረ እና ለዚህም በባለፈው ዓመት በነበረው የሰሜን ጦርነት ኢኮኖሚያቸው ላይ ተፅዕኖ ያደረባቸው ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ያለዕድሜያቸው ለመዳር እንደተገደዱ እና መንግሥትም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መወጠሩ ለችግሩ መጨመር በምክንያትነት ተጠቅሳል።

ኃላፊው አያይዘውም ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት የሕወሓት ቡድን ወደ ክልሉ በገባባቸው በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ፣ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ የሰሜን እንዲሁም ደቡብ ጎንደር አና ሌሎች አከባቢዎችን ጨምሮ አንድ ሺሕ 936 ሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፣ አንድ ሺሕ 800 በላይ ሴቶች እንዲሁ ለሥነ ልቦና ጉዳት መዳረጋቸው ተጠቁሟል።

በተጨማሪ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በግንዛቤ እጥረት እና በተለያዩ ምክንያቶች እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ 415 ሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት እንደተፈጸመ እና በአጠቃላይ ኹለት ሺሕ 351 ሴቶች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከተደፈሩት ሴቶች መካከል ለእርግዝና የተጋለጡ ሴቶች ያሉ ሲሆን፣ መረጃውን በቁጥር ላይ የተደገፈ ለማድረግ የአማራ ክልል ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በጋራ ሪፖርት የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ ፆታዊ ጥቃት ለተፈፀመባቸው ለ969 ሴቶች እና አንድ ሺሕ 328 ለሚሆኑት እንዲሁ የሥነ ልቦና ሕክምና መስጠት እንደተቻለ እና በአገልግሎት ተደራሽ ባለመሆን፣ በበጀት እጥረት፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ባለመደረጉ እና በበጀት እጥረት ምክንያት ከ900 በላይ ሴቶች የሕክምና አገልግሎት አለማግኘታቸው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በበኩሉ ባለፈው ወር በአፋር እና አማራ ክልሎች ባደረገው ጥናት በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከአንድ ሺሕ 200 በላይ ሰዎች ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው መግለጹ የሚታወስ ነው።

የክልሉ መንግሥት በጦርነቱ ወቅት የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ አደረግኩት ብሎ ከኹለት ሳምንት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሰረት፣ የሕወሓት ታጣቂዎች አንድ ሺሕ 782 የአስገድዶ መድፈር ጥቃት መፈጸማቸውና፣ በቡድን በመሆንም በቤተሰብ አባላት ፊት አስገድዶ የመድፈር ድርጊት በመፈጸም አሰቃቂ ጉዳት ማድረሳቸው ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

አስተያየት

  1. ያለ እድሜ ጋብቻ, አስገድዶ መድፈር ወይም ጠለፋ የሴቶችን በተለይም የወጣት ሴቶችን ሰብአዊ መብት ከመጋፋት አልፎ ቀሪ ህይወታቸው ላይ የማይወጡት ጫና መፍጠሩ ሀላፊነቱ ከግለሰብ, ቤተሰብ እና ማህበረሰብ አልፎ ከፍተኛዉ ሀላፊነት በመንግሥት ላይ ይወድቃል ምክንያቱም ከማህበረሰብ አልፎ በሀገር ላይ የሚያስከትለው ቀውስ ከአንድ ትውልድ አልፎ በተከታታይ ትውልድ ላይ ጫና ሚፈጥር በመሆኑ በዚህ ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ አካሎች በህግ ማእቀፍ አስተማሪ የሆነ, ሌሎች በዚህ ተግባር እንዳይሳተፉ ገደብ የሚጥል ቅጣት ተግባራዊ ማድረግ አንዱ የመንግስት ዋናዉ ሀላፊነት ሆኖ በሌላ በኩል መንግስት ለዚህ ማህበራዊ ችግር ይመለከታቸዋል የሚላቸውን አካላት በማሳተፍ ማህበረሰቡን ማስተማርና ማንቃተ የቀን በቀን ተግባርና እንቅስቃሴ መሆን ችላ የማይባል የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ተግባር ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች