ወተት በሊትር ከ40 ወደ 60 ብር ከፍ ብሏል

0
2296

ከአንድ ወር ወዲህ የወተት ዋጋ በአንድ ሊትር ከ40 ብር ወደ 60 ብር ከፍ ማለቱን አዲስ ማለዳ ከተጠቃሚዎችና አከፋፋዮች አረጋግጣለች። አንድ ሊትር ወተት ከወር በፊት ከ30 እስከ 40 ብር ድረስ እየተሸጠ የነበረ ሲሆን፤ ሰሞኑን ግን ወደ 60 ብር ከፍ ማለቱን በአዲስ አበባ የሚገኙ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከተለያዩ ቦታዎች በመረከብ አንድ ሊትር ወተት በ30 ብር ለማኅበረሰቡ ያከፋፍሉ እንደነበር የገለጹት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዓለሙ ተሻገር ሲሆኑ፤ ሰሞኑን ግን በ60 ብር እያከፋፈሉ መሆናቸውን አልደበቁም።

ለዋጋ ጭማሬው ዋነኛ ምክንያት የመኖ መወደድ ነው የሚሉት ዓለሙ፤ ይህን ተከትሎም ተኮናታሪዎች ኮንትራት እንዳቆሙ ጠቅሰዋል። ተጠቃሚዎቹ በበኩላቸው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የዋጋ ጭማሬውን ተከትሎ በተለይም ለሕጻናት ሲኮናተሩ የነበሩ እናቶች ከሌላው ኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ መቋቋም ስላልቻሉ ኪራይን ለማቆም መገደዳቸውን ነው።

አለምነሽ ይርዳው የተባሉት እናት ለልጃቸው የሚሆን ወተት በወር አንድ ሺሕ 200 ብር ተኮናትረው እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ወደ አንድ ሺሕ 800 ብር ከፍ በማለቱ ኮንትራቱን እንዳቆሙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እንደ አለምነሽ ገለጻ ከሆነ፤ ኮንትራቱን ለማቆም የተገደዱት ከአሁን በፊት ሲኮናተሩ ሲያወጡት ከነበረው ወጭ ስደስት መቶ ብር ጭማሪ ስለተደረገባቸው ነው። አዲስ ማለዳ ከተጠቃሚዎቹ የደረሳት መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፤ በሊትር ብቻ ሳይሆን ዋጋ ጭማሪው የተስተዋለው በእሽግ የወተት ዓይነቶች ጨምሮም ነው።

ማማ፤ ሾላ፤ ሎሚ፤ ሐርሜና የመሳሰሉት እሽግ የወተት ዓይነቶች ከፋሲካ በዓል በፊት እስከ 20 ብር ድረስ ሲሸጡ የነበረ ቢሆንም፣ የፋሲካ ጾም ከተፈታ ወዲህ ዋጋቸው ወደ 30 ብር ከፍ ማለቱን አዲስ ማለዳ በከተማው ተዘዋውራ ተመልክታለች። አንዳንድ ቦታዎች ላይ 28 ብር ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ 30 ብር ሲሸጥም መመልከት ተችሏል።

በእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርት መኖ ቅንብርና ጥናት ምርምር አስተባባሪ ታሪኩ ተካ ለጭማሬው ምክንያቱ የመኖ መወደድና ወቅታዊ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል። ፍሩሽካ፤ ፋጉሎ፤ በቆሎ የተሰኙት የመኖ ዓይነቶች ከዘይት እና ከዱቄት ፋብሪካ ነው የሚገኙት ያሉት ታሪኩ፤ በፋብሪካዎች ላይ የሚስተዋለው የጥሬ ዕቃ ዕጥረት ለወተት ዋጋ መወደድም መንስኤ እንደሚሆን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አስተባባሪው በተያያዘም፤ ጊዜው አጭር ከመሆኑ አንጻር የመኖው መወደድ የወተትን ዋጋ በምን ያክል መጠን እንደጨመረ በቁጥር ለመግለጽ ሙያዊ ጥናት ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል። ገበያ ላይ በቂ መኖ አቅርቦት ተማልቷል ለማለት እንደማይቻልና እጥረት ካለም የወተቱ ዋጋ መጨመሩ አይቀሬ መሆኑ ተብራርቷል።

በሌላ በኩል በተለይም በሚያዚያ ወር የወተት ዋጋ መጨመር የተለመደ ነው ያሉ ሲሆን፤ የፋሲካ በዓልና በዓለ ሀምሳን ተከትሎ ኹሉም ሰው ተጠቃሚ የሚሆንበት አጋጣሚ ስላለ ነው ተብሏል። እንደ አስተባባሪው ገለጻ ከሆነ፤ በዚህ ወቅት አርሶ አደሮች ሰርግ ስለሚሰርጉ ወተትን ወደ ቅቤ፤ አይብ እንደሚቀይሩት አንስተው፤ ይህን ተከትሎም ወደ ኢንዱስትሪው የሚመጣው አቅርቦት ስለሚያንስ ነው ብለዋል።

ችግሩ ወቅታዊ ነው ያሉት ታሪኩ፣ ላለፉት ስድስት ዓመታትም በዚህ ወቅት የወተት ምርት አቅርቦት እጥረት ተስተውሏል ነው ያሉት። በመሆኑም ዝርያቸው የተሻሉ እንስሳትን ማርባት፤ የእንስሳትን ክትባት ማሻሻል፤ መኖን በመጠንና በጥራት ማቅረብ እንዲሁም የግብይት ስርዓቱ የተሻለ እንዲሆን ማድረጉ ለችግሩ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ሲሉ ታሪኩ ምላሽ ሰጥተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 186 ግንቦት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here