የማዕከላዊ የግድግዳ ላይ “ሚስጥሮች”

0
842

የ28 ዓመቱ ወጣት መሐመድ ኑሪ ያለአስጎብኚ ለስድስት ቀናት ክፍት ሆኖ የነበረውን በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራውን የፌደራል ፖሊስ የቀድሞ የምርመራ እና ማረፊያ ጣቢያ በመቶዎች ለሚቆጠሩት ጎብኚዎች ሲያስጎበኙ ከነበሩ የቀድሞ እስረኞች መካከል አንዱ ነው። ለአምስት ወራት በማዕከላዊ ውስጥ የቆየው መሐመድ በስተግራ ጎድጎድ ብለው በተሠሩት እና በእስረኞች ዘንድም ጣውላ ቤት ተብለው በሚጠሩት እስር ቤቶች ነበር የእስር ቆይታው።

“ስገባ አሞኝ ስለነበረ ጣውላ ቤት ነበር ያስገቡኝ፣ ነገር ግን እስክወጣ ያገኘሁት ሕክምና አልነበረም” የሚለው መሐመድ በ2004 በተነሳው ‘የድምፃችን ይሰማ’ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ምክንያት ነበር ለእስር የተዳረገው። “አብዛኛው ምርመራ ይካሔድ የነበረው ጣውላ ቤት ላይ ባሉ የመርማሪዎች ክፍል ውስጥ ስለነበረ ሊመረመሩ የሚመጡ ሰዎች ሲመላለሱ አይ ነበር” የሚለው መሐመድ ከምንም በላይ የሴት እስረኞች ጩኸት ግን ከአዕምሮው እንደማይጠፋ ይናገራል።

በእስረኞች ዘንድ ጣውላ ቤት፣ ሳይቤሪያ እና ሸራተን ከሚባሉት ኹለቱ የእስር ቤት መደቦች ሻል ያለ ነበር የሚባለው በሩ እንደሌሎቹ የማይዘጋ በመሆኑ እስረኞች የተወሰነ ብርሃን ለማግኘት ቢችሉም ከክፍሎቹ ሥር ስለተንጣለለው ውሃ ግን የሚያውቁት ነገር እንደሌለ መሐመድ ይናገራል። አዲስ ማለዳ እስር ቤቱን በጎበኘችበት ወቅትም የተሰበረው ጣውላ ሥር በግምት ግማሽ ሜትር ርቀት ውሃ መመልከት ችላለች።

በፈገግታ ሆኖ ገለጻውን ያካሒድ የነበረው መሐመድ “አንድ ከእኛ ጋር የታሰረች ልጅ ወደ ምርመራ እየተራመደች ስትገባ አይቻት ነበር፣ ከዛም ምርመራውን ጨርሳ ከመርማሪዎች ክፍል ስትወጣ ግን ራሷን ስታ በፖሊሶች ተይዛ ነበር” ሲል በድንገተኛ የሐዘን ስሜት ተውጦ ትውስታውን አጋርቷል። በተመሳሳይም ከአንድ የአፍሪካ አገር መጥታ የታሰረች ልጅ ከድብደባ አልፎ መደፈሯን ለኀላፊዎች ስትናገር መስማቱን የሚናገረው መሐመድ በጣውላ ቤት ቆይታው በሴት እስረኞች ላይ ሲፈፀም የነበረው በደል እጅግ የከፋ እንደነበረ ይናገራል።

ይህ የቀድሞው የተጠርጣሪዎች ማቆያ ታዲያ በተደረገለት እድሳት የተለያዩ አስተያየቶች በሰፊው እንዲነሱበት ያስደረገ ሲሆን የግድግዳ ላይ ታሪኮቹ በቀለም እንዲጠፉ በመደረጋቸው በቦታው በእስር ያሳለፉ እንዲሁም እንደአዲስ ለመጎበኘት የመጡ ሰዎች ብስጭት ውስጥ ከትቷል።

በቦታው ታስረው የቆዩ ብዙዎች በግድግዳዎቹ ላይ የጻፏቸውን ትውስታቸውን ለማግኘት ባይችሉም መሐመድ ግን በጣውላ ቤት ግድግዳ ላይ የፃፋቸውን ኹለት ጽሑፎች ከቀለም አምልጠው እና የተወሰነ ፈዘውም ቢሆን ሊያገኛቸው በመቻሉ ደስተኛ ነበር።

ታስሮባት በነበረችው ጠባብ ክፍል በሚተኛባት የግድግዳው ጥግ “ድምጻችን ይሰማ” ሲል የሞነጨራት መፈክር በነጭ ቀለም ለማጥፋት ብትሞከርም በቦታዋ ላይ ግን ትገኛለች። በዚች ክፍል ከበሩ በስተግራ በኩል ባለው ግድግዳ ላይ የፃፈውን “ነፃ ያልወጡ ነፃ አውጪዎች” ስለሚለው ጽሑፍ ትውስታው ሲያስረዳም “የግንቦት 20 በዓል በግቢው ውስጥ በሚከበርበት ቀን የጻፍኳት ነች” ሲል ጽሑፎቹ አለመጥፋታቸው በፈጠረበት ፈገግታ ታጅቦ ያስረዳል።

አንዳንድ ሰዎች ግድግዳው ላይ “ከሞትኩ እከሌ እባላለሁ፣ ስትወጡ ለቤተሰቦቼ ንገሩልኝ” የሚሉ የስንብት መልዕክቶችን ያሰፍሩ እንደነበር መሐመድ ይገልጻል። የግድግዳ ላይ ጽሑፎቹና ምስሎቹ መጥፋት ሕግ ጥሰው በደል ያደረሱ ሰዎችን ወንጀል ከመደበቅ ባሻገር ብዙ ለተሰወሩ ሰዎች ቤተሰቦች መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ፍንጮችም እንዳይገኙ አድርገዋል፤ እውነተኛውን የማዕከላዊን ገጽታ አያሳዩም ሲል መሐመድ በከፍተኛ ቁጭት ተናግሯል።

የቀድሞ ማዕከላዊ ባልደረቦች የት ናቸው?
በድል አድራጊነት ወኔ ውስጥ በሚታይ ትህትና በወቅቱ የግቢው ሠራተኞች የነበሩ ግለሰቦችንም እየዞረ በደማቅ ፈገግታ የሚያናግረው መሐመድ ታስሮ በቆየባቸው ጊዜያት የግቢው ጠባቂ ፖሊስ የነበሩትን ቢኒያም አለባቸው (ሥማቸው የተቀየረ) የሞቀ ሰላምታ ሰጣቸው። እሳቸውም ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ማጋራት ጀመሩ። እስረኞች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ በሙሉ ፖሊሶች ላይም ይደርሳል የሚሉት የቀድሞው አባል፣ በተለይም መረጃ ታወጣላችሁ፣ በእስረኞች እና ውጪ ባሉ ሰዎች መካከል ድልድይ ትሆናላችሁ በሚል ፖሊሶች ታስረው እንደሚሰቃዩ እና ከዛም እንደሚባረሩ ይገልፃሉ።

“እኔ እንኳን አንድ ዓመት ብቻ ነው እዚህ የቆየሁት በኋላ ለቅቄ ሔጃለሁ፣ ያው ይፈፀማሉ ስለሚባሉ ነገሮች ከመስማት ውጪ ግን በዓይኔ ምንም አይቼ አላውቅም” ሲል ይናገራል።

እንደመሐመድ ገለጻ በመርማሪዎች ከሚፈፀሙ ድርጊቶች ባሻገር በተለይ በሐኪሞች ሲፈፀሙ ስለነበሩ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ቀላል የማይባሉ እንደነበሩ እና ሐኪሞቹም ሕክምና ከመስጠት ይልቅ ከእስረኞች መረጃ የሚቀበሉ መሆናቸውን ይናገራል። “አንድ የማስታውሰው ሰው ከክሊኒኩ መድኀኒት ይታዘዝለትና ይዞ ሲገባ አንድ ሕክምና የተማረ እስረኛ መድኀኒቱን አንብቦ ይህንን ቢውጥ ከተባለው በሽታ ማዳኑ ቀርቶ፣ ለባሰ ችግር እንደሚዳርገው በነገረው መሰረት ልጁ መድኀኒቱን አልውጥም ይላል፣ በኋላ ሐኪሙ አድማ በማስተባባር በሚል ብዙ ደብደባ እና ስቃይም ደርሶበታል።”

በግቢው ውስጥ ያገኘናቸው የፌደራል ፖሊስ አባል እንደሚሉት የቀድሞው የማዕከላዊ ሠራተኞች አብዛኛው በእስር ላይ ሲሆን ሌሎች ያሉበት አይታወቅም።
ጎብኚዎች ምን ይላሉ?

ኹለት በዐሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ እና ከማዕከላዊ ፊት የሚገኘው የቤተልሔም ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎች ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ጉንጮቻቸው ቀልተው፣ ፊታቸው ተጨማዶ እና እንባም ተናንቋቸው ነበር አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው። በዚህ ግቢ ውስጥ እስረኛ እንዳለ እንጂ እንዲህ ዓይነት ግፍ እንደሚፈጸም እንደማያውቁም ወጣቶቹ ይናገራሉ።

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባት ፈተናዋን ወስዳ የመሸጋገሪያ ውጤቷን የምትጠብቀው ምህረት “ወደ ፊት ሕግ እማራለሁ የሚል ሐሳብ ነበረኝ” ትላለች ማዕከላዊን ከጎበኘች በኋላ ግን የስሜት መደበላለቅ እንዳጋጠማት እና የሕግ ሰዎች ይህንን ይፈጽማሉ ብላ አስባ እንደማታውቅም ትናገራለች። “እኔ ግን እንደዚህ ዓይነት ሳይሆን የተሻለ የሕግ ሰው ሆኜ በደልን አስቀራለሁ” ትላለች።

ሙሉ ግቢውን ከኹለት ታዳጊ ወንድ ልጆቻቸው ጋር በመሆን ጎብኝተው ሸራተን ከሚባለው የእስር ቤቱ ክፍል የሚወጡት ባለ ሽበት ፀጉር ጎልማሳም “አያችሁ ልጆቼ! መንግሥትን መቃወም እንደዚህ ያስደርጋል፣ እዚህ ታስረው እንዲህ የተሰቃዩ ሰዎች መንግሥትን ስለተቃወሙ ነው” እያሉ ልጆቻቸውን መንግሥትን የመቃወም ተሳትፎ ውስጥ እንዳትገቡ የሚል መልዕክት ያዘለ ምክር የሚሰጡ አባት ከዙሪያቸው ተቃውሞ ገጥሟቸውም አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። “ይረፉ እንጂ! ልጆቾትን እንዲህ አያስፈራሩ፣ አሁን እንደድሮ አይደለም ከፈለጉ ይቃወሙ” የሚል መልስ ከተለያዩ ጉብኝቱን ከታደሙ ሰዎች የሰሙት አባት ልጆቻቸውን አፈፍ አርገው ግቢው ጥለው ወጥተዋል።

አስጎብኚ ያለመኖሩን ተከትሎም አስጎብኚ ነን በማለት ገንዘብ የሚሰበስቡ ሰዎችንም አዲስ ማለዳ ታዝባለች። አንድ መርካቶ ውስጥ ዕጣ በማዞር የሚተዳደር ወጣትም ግቢውን እያዞረ ከኋላው እየተጋፉ የሚከተሉትን ሰዎች የተሳሳተ መረጃ እየሰጠ እና በየመሐሉም “ከላይ ያሉት ቢሮዎች መከፈት አለባቸው፣ እነሱ ካልተከፈቱ ሌለው ምን ዋጋ አለው” በሚል ሐሳቡንም ጭምር እያጋባ ከላይ ታች ሲል ይታያል።

እንዳጋጣሚ እዚህ ታስሬ ነበር የሚል ሰው ሲገኝ ቁጥሩ ቀላል የማይባለው ጎብኚ ይከበውና መተንፈሻ ሲያጣ እና በአብረን ፎቶ እንነሳ ጥያቄ ሲጨነቅም ይታያል።
“እንዲህ ቀብተው ምኑን ሙዚየም ይላሉ። ይልቁንስ ሥራ ፈትቶ ከሚቀመጥ ያከራዩን” የሚሉ የተለያዩ አዝናኝ አስተያየቶችም በጆሮ ደጋግመው ይሰማሉ።

የግድግዳ ላይ ጽሑፎቹንና ምስሎቹን መመለስ ይቻል ይሆን?
አዲስ ማለዳ ባደረገቸው የተወሰነ ዳሰሳም በዓለም ላይ የተለያዩ የወንጀል ማስረጃዎችን ለማጥፋት ግድግዳዎችን በቀለም መሸፈን የተለመደ ድርጊት መሆኑን ተከትሎ በተለይም በአሜሪካ እና በጣሊያን አገሮች በተሠሩ የተለያዩ ጥናቶች ከቀለሞቹ በስተጀርባ ያሉ ምስሎችን መመልከት እንደሚቻል ያስረዳሉ።

ክራይም ሲን ኢንቨስቲጌተርስ ኔትወርክ የተባለው እና በዓለም ላይ የወንጀል ምርመራ ምርምሮችን እና ዘዴዎች ላይ የሚሠራው ጥምረት በ2002 ቶማስ አዴይር በተባሉ የወንጀል ተመራማሪ የታተመው ምርምርም ይህንን ያረጋግጣል። በአሜሪካን አገር ዴንቨር ግዛት በተፈጸመ ግድያ ወንጀል አማካኝነት ወደ ምርመራ የገቡት ቶማስ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ የተቀባው ግድግዳ ሥር ያለውን የደም ፍንጥቅጣቂዎችን ለማግኘት ችለዋል።

የደም ፍንጥቅጣቂዎቹን ከማግኘት ባለፈ የደሙን ዘረመል መርምረው የማን መሆኑ ለማወቅ መቻሉን በጥናታቸው አረጋግጠዋል። አጥኚዎቹ አራት በአራት ሜትር የሆነ የግድግዳውን መልክ ከመረጡ በኋላ አራት ዙር ኹለት ዓይነት ቀለም በመቀባት ቀለሙ በአንድ ሌሊት ደርቆ እንዲያድር በማድረግ ከጎን የሚታየው ምስል ላይ ያለውን ውጤትም ለማግኘት እንደተቻለ ጥናቱ ያመለክታል።

ቀለምን ከመጠቀም ባሻገርም የሰማያዊ ጨረርን በመጠቀም በቀለም፣ በሻጋታ ወይም ለዓመታት በቆየ አቧራ የተደመሰሱ የግድግዳ ላይ ስዕሎች እና ጽሑፎቹን መመልከት እንደሚቻል የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ። አዲስ ማለዳ ላይት ፎር አርት የተሰኘውን የጣሊያን የጥገና ቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር ባደረገቸው የኢሜይል መልዕክት ልውውጥም የጨረር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተለያዩ የጠፉ ወይም የተሰወሩ ምስሎችን ከግድግዳ ላይ መመለስ እንደሚቻል አረጋግጣለች። በተለይም የጥንታዊ የጥበብ ውጤቶችን ሳይጎዱ ወደ ቦታቸው ለመመለስ እና ሽፋናቸውን ለማንሳት የሚውሉ የተለያዩ የጨረር እና መብራት ዘዴዎችም በዓለም ላይ የተለመዱ ናቸው።

ሌላው የማዕከላዊን ግድግዳ ለመመለስ እና ጽሑፎችን ለመሰብሰብ እንብዛም አያስቸግርም የሚሉት መሐመድ አብዛኛው እስረኛ መጻፊያ ቀለሞችን ስለማያገኝ ግድግዳውን በመቦርቦር መልዕክት ስለሚያስቀምጥ ከቀለሙ ባሻገር ያለውን መልዕክት ለማግኘት የሚሞክር አካል ካለ አያስቸግርም ይላሉ።

በማዕከላዊ ግቢ ውስጥ የጥበቃ ሥራ ሲያስተባባሩ አዲስ ማለዳ አግኝታ ያነጋገረቻቸው አንድ የፌደራል ፖሊስ አባልም “ቀለሙ የተቀባው በ2010 የበጀት ዓመት መጠናቀቁን ተከትሎ እንጂ በተደጋጋሚ እንደሚባለው የታራሚዎችን መልዕክት ለማጥፋት አይደለም” ይላሉ። “ቀለሙ ሲቀበባ እስረኞች ራሳቸው እዚህ ነበሩ” የሚሉት ግለሰቡ “በራሳቸው በእስረኞች ጥያቄ የተቀባ ነው፣ ተባይ እና ቆሻሻ አስቸገረን የሚሉት ራሳቸው ናቸው።”

በዚህ የማይስማማው መሐመድ ማዕከላዊ የነበረበት ወቅት እንደሚያስታውሰው እስር ቤቱ በየዓመቱ ቀለም የሚቀባ እንደማይመስል ይናገራል።
“የውስጥ እግራቸውን የሚገረፉ ሰዎች የእግራቸውን አሻራ በግድግዳው ላይ ያደርጉ ነበር፣ ፊታቸውን ተደብድበው እየደሙ የሚመጡ ሰዎችም በደማቸው ግድግዳው ላይ የተለያየ ነገር ይጽፋሉ፣ ብዙ በደም የታተሙ አሻራዎችም በግድግዳው ላይ ነበር” ሲሉ ይናገራሉ።

በተለይም በምርመራ ላይ ያሉ ሰዎች የሚቆዩበት የሳይቤሪያ ማረፊያ ክፍል ግድግዳ በደማቁ የተቀባ ሲሆን ጣውላ ቤት እና ሸራተን በስሱ የተቀቡ ሲሆን ጽሑፎቹን ግን መመልከት ይቻላል።

በነሐሴ 2011 የተከበረውን የፍትሕ ወርን ካስተባበሩት ተቋማት መካከል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ባለሞያ የሆኑት ዝናቡ ቱኑ እንደሚሉት እስር ቤቱ የተቀባው ኢሕአዴግ ማዕከላዊ እንዲዘጋ መወሰኑን ተከትሎ በነበሩ የሽግግር ወቅቶች እንደሆነ ቦታውን ለጎብኚ ለማስከፈት ሲሞክሩ እንደተረዱ ይናገራሉ።

“የላይኛው የምርመራ ክፍሎች ግን የፖሊሶች ማደሪያ ከመሆን ባለፈ ተመሳሳይ እድሳት አልተደረገላቸውም” የሚሉት ዝናቡ ምናልባትም በችኮላ የተቀባ እንደሚመሰል እና ለጎብኚዎች ክፍት ሲሆን እንደተቀባ የሚሰራጩ መረጃዎች ግን ስህተት ናቸው ሲሉ ያስተባብላሉ።

መሐመድም ምናልባት የግድግዳ ምስሎቹ ቢወጡ ዛሬም ድረስ በነፃነት እየኖሩ ስላሉ የቀድሞው አባላት መረጃ ይገኛል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ። መንግሥትም የማዕከላዊ የግድግዳ መልክቶችን ረስቶ መተው እንደሌለበት እና ማስተማሪያ እንዲሆን ካሰፈለገ መልዕክቶቹን በባለሞያ አስመርምሮ ማግኘት አለበት ይላሉ።

በጳጉሜን ወር ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ የነበረው ማዕከለዊ አሁን የተዘጋ ሲሆን ቋሚ ሙዚየም የማድረግ ሐሳብ እንዳለ ዝናቡ ቢገልጹም ዝርዝር ዕቅዶች ግን ለማጋራት ጊዜው ገና ነው በማለት ከአዲስ ማለዳ ጋር የነበራቸውን አጭር ቆይታ አጠቃልለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here