የታሪክ እስረኞች

0
1255

ታሪክን እንደታሪክ ለታሪክ ጸሐፊዎች ብቻ መተው መቻል አለብን የሚሉት በፍቃዱ ኃይሉ፥ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች የተጫኗቸው ታሪክ አጻጻፎች ስለሚበዙ እውነቱ ላይ መድረስ አስቸጋሪ ነው በማለት ተጨባጭ ያሏቸውን ማሳያዎች ጠቅሰዋል። የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን ለመወሰን ባለፈው ታሪካችን ላይ የግድ መስማማት አይጠበቅብንም ሲሉ መፍትሔ ነው ያሉትንም ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

 

“ታሪክ በታሪክ ማንኛውም ነገር ሊረጋገጥ እንደሚችል አረጋግጧል” – ቮልቴር።
ከማኅበራዊ ሚዲያ ቡራኬዎች አንዱ በአጭር ገለጻ ግዙፍ መልዕክቶች ድንገት የሚተላለፉበት መድረክ መሆኑ ነው። አንድ ትዊት ለዚህ ማሳያ ይሆናል፤ “የሐሰት ዜና ካለ፣ ታሪክን አስቡት” (“If news is fake, imagine history”) የሚል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የታሪክ እስረኛ ነው። ፖለቲከኞቹም የታሪክ እስረኛ ናቸው። የጋራ ታሪክ የለንም፤ የጋራ ዕጣ ፈንታ ሊኖረንም አይገባንም የሚሉት ባንድ በኩል፣ የአንዳችን ማሸነፍ የሌላችን መሸነፍ (ዜሮ ድምር) ታሪክ ስለሆነ ሁላችንንም ዕኩል አያኮራንም፣ የጨቋኝ ተጨቋኝ ታሪክ ነው ያለን የሚሉት በሌላ በኩል የየራሳቸውን ትርክት ፈጥረው ከታሪክ ጋር ሥምም የሆነ መጪ ዘመን ለመተመን ይጥራሉ። ነገር ግን ሁሉም ወገን ስለሚያወራው ታሪክ እርግጠኛ መሆን አይችልም።

በአዲሱ ዓመት (2012) መባቻ ዋዜማ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የኩራት እና የአንድነት ቀን ሲያውጅ፥ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ጃዋር መሐመድ “በጋራ የምንኮራበት የከፍታ ታሪክ የለንም” የሚል ምላሽ አቅርቦ ነበር። የአንድነት ቀን በተባለው ጳጉሜን 6 ምሽት ከቤተ መንግሥት በቀጥታ በተላለፈው ፕሮግራም ደግሞ የሶማሊ ምክትል ፕሬዚደንት ሙስጠፌ ቀርበው ኢትዮጵያ ውስጥ የባሕል መቻቻል መኖሩን ከጠቀሱ በኋላ፥ የጎደለን የታሪክ እና አረዳድ ልዩነታችንን ማቻቻል እና መቀበል ነው። ለወደፊት አብረን ለመዝለቅ በታሪክ መሥማማት ግዴታ የለብንም የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ከመዓዛ ብሩ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎቹ ልዩነቶች የሚነጩት ከታሪክ ሳይሆን ከተረክ ነው ብለዋል። ጉዳዩ ይህንን ያክል አነጋጋሪ የሆነበት ወቅት ስለሆነ እኔም ብዙዎቻችን እርግጠኛ ልንሆን የማንችልበት ታሪክ እስረኞች እንደሆንን ለማውሳት ብዕሬን መዝዣለሁ።

ፖለቲከኞች ታሪክን ለምን ያጦዛሉ?
ጆርጅ ኦርዌል በሚለው የብዕር ሥሙ የሚታወቀው ደራሲ 1984 በሚል በሰፊው በሚታወቅለት ልቦለዱ “ኦርዌሊያን” የሚባለውን ጠቅላይ ገዢ አምባገነናዊ አስተዳደር ምሥል ሰጥቶታል። እዚህ መጽሐፉ ላይ “የወደፊቱን ጊዜ መቆጣጠር የሚፈልግ፣ ያለፈውን ጊዜ መቆጣጠር አለበት፣ ያለፈውን ጊዜ ለመቆጣጠር ደግሞ አሁንን መቆጣጠር ያስፈልጋል” የሚል ተጠቃሽ ዓረፍተ ነገር አኑሯል። ፖለቲከኞች ታሪክን የሚያጦዙት ለዚህ ዓላማ ሲባል ነው። ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትም “የታሪክ መንታ ተግባር፥ የሰው ልጅ ያለፈውን ዘመን በቅጡ እንዲረዳ እና ባሁኑ ዘመን ላይ ያለውን ቁጥጥር እንዲያዳብር መርዳት ነው” ሲሉ በሌላ አማርኛ ይህንኑ ይደግሙታል።

በኢትዮጵያም ታሪክ የሚጠቀሰውም ይሁን የውዝግብ መንሥኤ የሚሆነው ስላለፈው ጊዜ ተብሎ አይመስለኝም። የወደፊቱን ዕጣ ፈንታ የመወሰን ዕድልም ስላለው ነው። በፖለቲካ ትርክታችን ተቀናቃኝ የሆኑትን ኹለት ኀይሎች ወስደን ነገሩን እንተንትነው። እነዚህን ኀይሎች ‘ተገንጣይ ኀይሎች’ እና ‘የአንድነት ኀይሎች’ እንበላቸው። ተገንጣይ ኀይሎች የኢትዮጵያ ታሪክ የቅኝ ገዢዎች እና ተገዢዎች ነው ይላሉ፤ ስለዚህ መፍትሔው መገንጠል (“ነጻነትን ማወጅ”) ነው ይላሉ። በተቃራኒው የአንድነት ኀይሎች ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉንም ያሳተፈ የከፍታም፣ የዝቅታም ነበር ይላሉ። ስለሆነም፣ መፍትሔው በጋራ መጪውን ጊዜ ማስተካከል ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ።

በታሪክ መተማመን ይቻላል?
እንግዲህ የተለያየ ብሔር፣ ቋንቋ እና/ወይም ሃይማኖት ያላቸውን ሕዝቦች አንድ ላይ የሚያኖሩ ወይም ደግሞ የተለያየ አገር እንዲገነቡ የሚገፋፉ ትርክቶች በታሪክ ገበታ ለዚህ የኢትዮጵያ ትውልድ እየቀረቡ ነው። ይሁንና ታሪክ እና ትርክቶች ላይ ምን ያህል እንተማመናለን?
ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት “ተረትና ታሪክ በኢትዮጵያ” በሚለው ታዋቂ እና አጭር ጥናታዊ መጣጥፋቸው ስለኢትዮጵያ ታሪክ የምናውቀው የሚመስለንን በሙሉ እንድንጠራጠር ያደርጋሉ። በማስቀደም “ታሪክ በእምነት አይጻፍም” ሲሉ የሚመክሩት ታምራት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ዋነኛ ምንጮች የሆኑት ዜና መዋዕሎች የተጻፉበት አጻጻፍ የአስተማማኝነት ደረጃቸው “በጥንቃቄ መገምገም አለበት” ብለዋል። እንደ እርሳቸው እንኳን በብዙ ወገንተኝነት የሚታሙት የኢትዮጵያ ጸሐፍት የዘገቡት ቀርቶ የትኛውም “የታሪክ ትንተናና ጽሑፍ ዘለአለማዊ እውነት የለውም። አዳዲስና አስተማማኝ መረጃዎች ሲገኙ፥ በነሱ መሠረት ይስተካከላል፤ ጨርሶም ሊለወጥ ይችላል።” በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የታሪክ ትርክት ግን ታሪክ የቅዱስ ቃል ያህል የማይደፈር ይመስላል።

ማሳያ አንድ፦ “ዮዲት ጉዲት”
ታደሰ ታምራት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለውን “ክብረ ነገሥት” ይጠቅሱና፥ “የንግሥተ ሳባና የቀዳማዊ ምኒልክ ተረት መልክ ይዞ የተቀናበረበት” ይሉታል። ይህ ግን በነባራዊዋ ኢትዮጵያ በአደባባይ በተነገረ ቁጥር አነታራኪ መሆኑ ግልጽ ነው። ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ ታሪክ እና ትርክት ውስጥ “ዮዲት ጉዲት” የምትባል ሴት ትጠቀሳለች፤ ይሁን እንጂ ሴቲቱ “ከሌላ ዘመን፣ ከሌላ ሕዝብ፣ ከሌላ አካባቢ ተወስዳ በአክሱም ታሪክ ላይ የተወረወረች ጎበዝ መሪ ናት” በማለት ስለርሷ የሰማነው ሁሉ ውሸት መሆኑን ያረዱናል።

ማሳያ ኹለት፦ የደርግ ፕሮጀክት
ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ “ያልተቀበልናቸው” በሚል ርዕስ ሰብስቦ በመጽሐፍ ያሳተማቸው መጣጥፎች አሉት። ከመጣጥፎቹ አንዱ “ታሪክ፣ ተራኪና አስተራኪ” የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል። ዕውቁ የታሪክ ጸሐፊ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ “ዐፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” የሚለውን መጽሐፋቸውን ያሳተሙት በደርግ መንግሥት ስፖንሰርነት ነበር። እንዳለ ጌታ ይህንን ካስፈፀሙት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻለቃ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ሰማሁት ብሎ የተረከልን ነገር ብዙዎቻችን የማንገምተውን ነበር። ለዚህ የመጽሐፍ ፕሮጀክት የተመረጡት ተክለ ጻድቅ ዐፄ ቴዎድሮስን ጨካኝ እና አምባገነን አድርጎ የሚያሥል የታሪክ መጽሐፍ ይዘው በመምጣታቸው ፍቅረሥላሴ ተናደዱባቸው።

“ለእኔ እርሳቸው [ዐፄ ቴዎድሮስ] አርአያ ናቸው – ብርቱ ጦረኛ፣ አገር ወዳድ፣ የአንድነት ታጋይ፣ የኢትዮጵያዊ ጀግንነት ተምሣሌት፣ እኔ እንዲህ እንዲቀሩልኝ ነበር የሚፈልገው” በማለት መጽሐፉ በምናባቸው ያለውን ምሥል ይዞ እንዲከለስ አዘዙ። ተክለ ጻድቅም “ጠንካራ ጎናቸውን አጉልቼ፣ ጨካኝነታቸውን አሳንሼ እቀርፃቸዋለሁ” ብለው እንደልቦለድ ሥራ አዲስ መጽሐፍ ይዘው ተመልሰው መጡ። መላው የዘመኑ ትውልድም ያንን መጽሐፍ እያነበበ በዚያ ምሥል ንጉሡን እንዲያስታውሳቸው መንግሥታዊ ሥራ ተሠራ ማለት ነው። በተመሣሣይ መንገድ “ዐፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” እንዲሁም “ዐፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” የሚሉ መጽሐፍት ታትመዋል።

ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ምን ይላሉ?
ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ከላይ ከጠቀስናቸው መጽሐፎች አስቀድመው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጊዜ ከጻፏቸው መጽሐፍት መካከል “የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከዐፄ ልብነ ድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ” በሚል ርዕስ በ1961 ያሳተሙት ይጠቀሳል። በዚህ መጽሐፋቸው መቅድም ላይ “የቀድሞ አጻጻፍ” በሚል ያሰፈሩት ትችት አለ። የቀድሞ ጸሐፍት የነገሥታትን ታሪክ ሲጽፉ “የንጉሡን ታሪክ ንጉሡ ከሚወደው ሰማዕት ወይም መልአክ ጋር እያነጣጠሩ፣ እያቁላሉ ይጽፉታል” ይላሉ። ጸሐፍቶቹ “የንጉሡ ጠላቶች የተባሉት ያልተናገሩትን የፍርሐት ንግግር እንደተናገሩ እያስመሰለ ባንድ ፊት በማጋነን እና በማዳነቅ (በቃለ አጋኖ ወ አንክሮ) የዠግንነቱን እና የኀይሉን፣ የሥልጣኑን፣ በሌላ ፊት የደግነቱን፣ የመሓሪነቱን፣ የጸሎቱን፣ የትሩፋቱን ታሪክ በቤቱ ወይም በቤተ መንግሥቱ ቀን ቀን ሲጽፍ ይውልና ማታ ማታ ከግብር በኋላ ወይም ከጉዞ ባደረበት ከተማ ያነብለታል።” በዚህ መልኩ የተጻፈ ታሪክ፣ ታሪክነቱም፣ እውነትነቱም አጠራጣሪ ነው።

አሕመዲን ጀበል የተባሉት ደራሲ “ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከ615-1700 የጭቆናና የትግል ታሪክ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ መግቢያ ኢብራሒም ሙሉሸዋ ያሰፈሩት መቅድም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንዱን አጉልቶ ሌላውን ለማንኳሰስ ሦስት ስልቶች አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህም “መረጣ (selection)፣ መዝለል ወይም መተው (Omission) እና ማጠልሸት (Demonization) ናቸው።”

ታሪክ ክለሳዎች እና ዳግም መውደቅ
የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ እንከን የተሞላበት እንደሆነ የተረዱ ሰዎች ታሪክ ክለሳ ውስጥ ገብተዋል። ዋነኛው ሙከራ ታሪክን በነገሥታቱ ዓይን እና የጊዜ ተፋሰስ ከመጻፍ ይልቅ በሕዝቦች ዓይን እና ከሕዝቦች አንፃር ለመጻፍ መሞከር ነው። ሌላው ደግሞ በብሔርተኞች እየተሞከረ ያለው ሙሉ ለሙሉ የነገሥታቱን ታሪክ በመቃወም ለእያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ የየራሱን ታሪክ ለመጻፍ መሞከር ነው። ይህንኛው ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የላቸውም የሚል ዕሳቤ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በራሱ ከችግር የነጻ አይለደም። በሌላ በኩል የቀድሞውን የታሪክ አንብሮ (thesis) በሌላ የታሪክ ተፃርሮ (anti-thesis) ለመሻር የሚደረግ ሙከራም አለ።

የተስፋዬ ገብረአብ ልቦለድ እና አፈታሪክ ላይ የተመሠረቱት የአኖሌ ጡት ቆረጣ ታሪኮች ይሄ ነው የሚባል ታሪካዊ ማስረጃ ያልተገኘላቸው ለዚህ ነው። እሾህን በእሾህ የተሰኘው የአንብሮ-ተፃርሮ አቀራረብ ለሌላ ታሪካዊ ጥፋት ሊዳርግ ይችላል።

ከዚህ ሁሉ መፍትሔ የሚሆነው ታሪክን እንደታሪክ ለታሪክ ጸሐፊዎች ብቻ መተው መቻል ነው። በእስከዛሬው አካሔድ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች የተጫኗቸው ታሪክ አጻጻፎች ስለሚበዙ እውነቱ ላይ መድረስ ቀርቶ መጠጋትም አስቸጋሪ ነው። የታሪክ እስረኛ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካም በሚያሳዝን ሁኔታ የውሸት ታሪክ እስረኛ ነው። የቅድሚያ ትኩረታችን ከዚህ የውሸት ታሪክ እስረኝነት ነጻ መውጣት መሆን ይኖርበታል።

ሁሌም እንደማደርገው ለመውጪያ ያክል ተጨማሪ መፍትሔ ልጠቁም። ይኸውም የምክትል ፕሬዚደንት ሙስጠፌ ምክርን መቀበል ነው፦ የወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታችንን ለመወሰን ባለፈው ታሪካችን ላይ የግድ መሥማማት እንደማይጠበቅብን ሥምምነት ላይ መድረስ መቻል። ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ቋንቋ እና ባሕል እንዲሁም ሃይማኖት ልዩነታችን የተለያየ የታሪክ አረዳድ አለን። የየራሳችንን አረዳድ ለራሳችን ይዘን የወደፊቱን በመፈቃቀድ እና በመከባበር ላይ ለመገንባት መሞከር ዋነኛው ከታሪክ እስረኝነት የመውጪያ መንገድ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here