“በአገራችን አርዓያ እንዳይኖር፣ በታሪክ እንዳናምን ተደርጓል። ”

0
715

ኦባንግ ሜቶ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ወላጆቻቸው ካፈሯቸው ስድስት ወንድ ልጆች መካከል ሦስተኛ የሆኑት ኦባንግ፣ ውልደትና እድገታቸው ጋምቤላ ነው። በ16 ዓመታቸው ኢትዮጵያን ለቅቀው ወደ ካናዳ በማምራት የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ምዕራብ ካናዳ ከሚገኘው ሳስካችዋን ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ከኻያ ዓመታት ቆይታ በኋላ 1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ጋምቤላን በጎበኙበት ወቅት እርሳቸው በነበሩበት ጊዜ የነበሩ መሰረተ ልማቶች ባሉበት መሆን ብሎም አንዳንዶቹ ከነጭርሱ አለመኖር ኦባንግን ክፉኛ አሳስቧቸው፣ በካናዳ መንግሥት ድጋፍና በበጎ ፈቃድ ግለሰቦች የገንዘብ ልገሳ የጋምቤላ ልማት ደርጅት (Gambella Development Agency) የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት አቋቁመው የልማት እንቅስቀሴ በንጹሕ ውሃ አቅርቦት፣ በትምህርት ቤት እና ሆስፒታል ዘርፍ ጀምረው ነበር።

ይሁንና በታኅሣሥ 1996 ከአራት መቶ በላይ የአኝዋክ ማኅበረሰብ አባላት በመንግሥት ታጣቂዎች ግድያ መፈጸም ፊታቸውን ከምግባረ ሠናይ ድርጅት ሥራ ወደ መብት ተሟጋችነት እንዲለውጡ እንዳስገደዳቸው ኦባንግ ይናገራሉ። በተለያየ መልኩ ከተለያዩ አካላት ጋር ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጨምሮ በመፍጠር በሰፊው ተሳትፈዋል፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አጋልጠዋል፤ በወቅቱ በነበረው መንግሥት ላይ ዓለም ዐቀፍ ተጽዕኖ እንዲበረታ ግፊት አድርገዋል።

ለሰብኣዊ መብት መከበር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚናገሩት ኦባንግ፣ “በጋራ የሚያስተሳስረን ኢትዮጵያዊነት ነው” ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያሰማሉ፤ የብሔር አክራሪነትንም አምርረው ይቃወማሉ።

በተለይ ከሰብአዊ መብት ተሟጋችነታቸው ጋር በተያያዘ የተለያዩ ዕውቅናና ሽልማት ያገኙት ኦባንግ፣ በቅርቡ የበጎ ሰው ሽልማት እንዲሁም በ2007ም ተቀማጭነቱን ሰሜን አሜሪካ ካደረገው ማኅበረ ግዮራን ኢትዮጵያ ወይም በምኅፃረ ቃሉ ሲድ (SEED Award) ያገኟቸው ሽልማቶች በልዩነት ተጠቃሽ ናቸው።
የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከኦባንግ ሜቶ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የሲቪል ማኅበራት አዋጁ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?
የአዲሱ ሕግ መውጣት ትልቅ ነገር ነው። በትምህርት፣ በልማትም ወይም ሰዎች መብታቸውን እንዲያውቁ ይረዳል። ከዚህ በፊት ግን መተማመን የሌለበትና ፍርሃት የነበረበት ጊዜ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው ስርዓት ለየትኛውም ማኅበረሰብ አይመችም ነበር። ሕጉ በነጻነት እንድንንቀሳቀስ ረድቶናል ማለት ይቻላል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ድርጅታዊ አቋም እንዴት ነው?
በመጀመሪያ ጋምቤላ ግድያ የነበረ ጊዜ ስለ አኝዋክ መብት ስንከራከር ነበር። ከዛ በኋላ የተማርነው ምንድን ነው፣ ጋምቤላ ብቻውን ነጻ ሊወጣ አይችልም፤ መላው ኢትዮጵያ ፍትሕ ካላገኘ በቀር። በሌላ በኩል ከአንድ ኢትዮጵያዊ ወንድማችን ጋር ስንገናኝ እኔ በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በብሔሬ ነው የማምነው አለን። እኔም የኢትዮጵያ ችግር የብሔር ሳይሆን የአስተሳሰብ ችግር ነው አልኩት።

ሁላችን ነጻ ካልወጣን አንድ ሰው ብቻውን ነጻ ሊወጣ አይችልም። በኢትዮጵያ ሰው በሰውነት ከተከበረ ያለውን ነገር ማስተካከል እንችላለን።
አሜሪካ በነበርን ጊዜ ስብሰባ ሲጠራ በብሔር ሥም ሲሆን አዳራሽ ይሞላ ነበር፤ በአገር ደረጃ ግን ሰው የለም። እናም አሠራሩ እዛ ጋር ትክክል እንዳልሆነ አወቅሁ። ይሔ ራሱ ሆነ ተብሎ የተደረገ ነው፤ በሕገ መንግሥቱም ቢሆን በአብሮነት እንዳንሆን ነው የተደረገው። ሕገ መንግሥቱ ብሔር ብሔረሰቦች እንጂ ዜጎች አላለም፤ አብሮነትን ስለማይፈለግ። ይህ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጪ አገር ጭምር መከፋፈል ፈጥሯል፤ እያንዳንዱ ለብሔሩ እንጂ ለአገሩ አልቆመም።
እኛም ከዚህ ለየት ያለ ድርጅት ማቋቋም አለብን ብለን ነሐሴ 24/ 2000 የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄን መሠረትን። ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ማለት አዲስ አስተሳሰብ፣ ሰው በሰውነቱ የተከበረበት፤ በብሔሩ ሳይሆን ሁሉም አንድ የሚሆንበት አገር ማለት ነው። ለዛም ተሰባሰብንና ድርጅቱን አቋቋምን። አወቃቀሩ ላይ የተካተቱ ሰዎች ከተለያዩ ብሔሮች የመጡ ናቸው፤ ነገር ግን ብሔር ወክለው ሳይሆን ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ነው።

በዚህም መሰረት ከ46 አገራት በላይ ቋሚ ቢሮዎች ከፍተናል፤ 105 አገራት አባል ናቸው። የእኛን ድርጅት የሚደግፉ ሰዎች አንድ መመሪያ አላቸው፤ ከብሔር ይልቅ ሰብኣዊ መብት ጥሰትና ሁሉም ነጻ ካልሆነ አንድ ሰው ነጻ ሊሆን አይችልም የሚል። በዚህም እኛ ብዙ ሰዎችን ረድተናል፤ እኔም 21 አገራት ሔጃለሁ፤ ሜክሲኮ፣ ኖርዌይ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ጃፓን፣ እስራኤል፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች ብዙ ኢትዮጵያውያን ያሉባቸው አገራት ለተቸገሩ ሰዎች ደርሰናል። የተደፈሩ ሴቶችም ካሳ እንዲያገኙ አድርገናል። በአሜሪካም ጭምር ሦስት ሚሊዮን ዶላር የተከፈላቸው አሉ።

በዚህም ብዙ ኢትዮጵያውያን አወቁንና ደጋፊዎቻችን እየጨመሩ መጡ። ኦባንግ ከፊት ይታያል እንጂ የቦርዱ አባላት አውስትራሊያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይና ሌሎች አገራት አሉ። ከዚህ በፊት አገር ቤት ስንመጣ 16 ሆነን ‘ቲም ኢትዮጵያ’ ብለን ሲሆን ሁላችንም ከየክልሉ የተውጣጣንና የተለያየ ቋንቋ የምንናጋር ነን። መሪ ሐሳባችንም “ለመተማመን እንነጋር” የሚል ነው። ምክንያቱም በመካከላችን መተማመን እንዳይኖር ተደርጓል። ባንስማማ እንኳን በአገር ላይ አንድ እንሁን በሚል ነው፤ በአገር ስለማንለያይ።

ዐሥራ ስድስታችን በመጀመሪያ በቀጥታ ወደ ጋምቤላ በመሔድ 5 ሺሕ ሰዎች ሰበሰብን፤ የመጣነው ለይቅርታና እርቅ እንጂ ለጥላቻ እና ለበቀል እንዳልሆነ ነገርናቸው። ከዛም አዲስ አበባ ስንመጣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኘን።

ቀጥሎም በየቦታው ግጭቶች ነበሩ፤ በተለይ በትምህርት ቤቶች። ዲግሪ ለማግኘት ትምህርት ቤት የሚገቡ አሉ፤ ግን ሬሳቸው ነው የሚወጣው። እኛም ወደዛ ሔደን ለቡድኑ እንዲሁም ለድርጅታችን አባላትን መመልመል ጀመርን።

አዲስ አበባ ላይ ጽሕፈት ቤት ከፍታችኋል?
አዎን! አስፈላጊ የቢሮ ቁሳቁሶችን በማሟላት ሒደት ላይ ነን። በቅርቡ ፈቃድ አግኝተናል።

በአገራችን አሁን የሚታዩ ሥጋቶች አሉ፤ ለወጡም መጀመሪያ ላይ እንደነበረው አይደለም፤ በዚህም የሲቪል ማኅበራት ጋር በተያያዘ ማኅበራቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ባለመቻላቸው ነው ይባላል። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
እኛ’ኮ አገር መገንባት ላይ ነን፤ ከዜሮ እንደመጀመር ነው። ሕገ መንግሥቱ ራሱ አገር ለመገንት የተሠራ አይደለም፤ ሕዝቡ እርስ በእርስ እንዲባላና እነርሱ በፈለጉበት መንገድ ሕዝቡ እንቢ ሲል አገር እንዲፈርስ የሚፈልግ ነው። ኢሕአዴግና ሕገ መንግሥትን ያቋቋሙ ሰዎች ጫካ የገቡ፣ ኢትዮጵያን የማይወዱ፣ ሁሉም ነጻ አውጪና ተገንጣይ ነበሩ። በዛም ላይ በአቋማቸው አልቀጠሉም። በአቋማቸው ቢቀጥሉ እንደዛ አይሆንም ነበር። የሰው ልጅ መጀመሪያ በተነሳበት አቋም መቀጠል አለበት፤ እነዚህ ግን በተነሱበት ዓላማ አልቀጠሉም።

ደርግ ከወደቀ በኋላ አቋም አልነበራቸውምና አገርን ትተው ትንሹ ላይ አተኮሩ። ባለፈው 27 ዓመታት የተገነባው በብሔር የተደራጀ አገር ነው፤ በኢትዮጵያዊነት አንድነት ላይ አይደለም። በሌላ አገር እንዳለው ብሔራዊ ፍላጎት ሳይሆን የብሔር ፍላጎት ነው ሲጠበቅ የኖረው።

ስለዚህ የሲቪል ማኅበራት ሥራቸውን አልሠሩም፣ ብዙዎቹ በእስር ላይ ነበሩ። ብዙዎቹም ተዘግተዋል። ከማስተማርና ማነቃቃት ጀምሮ ብዙ ይሠሩ ነበር። እቁብና እድር ተዳክሟል። በሌላው ዓለም ማኅበራት ይሠራሉ፤ እኛ አገር እንዳይሠሩ ተደርጓል። ስለብሔር ማደግ እንጂ ስለአገር ማደግ ስላላሰቡ ነው። እኛም መስዋዕትነት እየከፈልን ነው እየሠራን የነበረው። ይህን ነገር ለማስተካከልም ጊዜ ወስዷል።

እናንተስ ወደ ሥራ ለመግባትና ሚናችሁን ለመወጣት ምን እያደረጋችሁ ነው?
ዋናው ወጣቶች ናቸው። ብዙ ቦታ ስንቀሳቀስ ብዙ ወጣቶች ነው መንገድ ላይ ያየሁት። በአገራችን ሰባ በመቶ አካባቢ ወጣቶች ናቸው። ችግሩ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲወዱ፤ አገራቸውን ግን እንዳይወዱ ተደርጓል። እነዚህን ልጆችን ማካተት ከተቻለ መንግሥት ላይ ያለው ጫና ይቀንሳል።

እኛ የምናስበው ወጣቶችን ማብቃት ላይ ነው፤ የተወሰደባቸውን ለራስ የሚሰጡትን ክብር (self esteem) እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ለራሱ ክብር የማይሰጥ ሰው ባዶ ነው የሚሆነው። በሌላ በኩል እኛ ተከፋፍለናል፤ ክልል የሚባለው ነገር ራሱ አንድ በሽታ ነው። በፊት በአንድ ክብ መሶብ ነበር የምንበላው፤ በዛ ክልልና ድንበር የለም፤ የተለየ የሚባል ሰውም የለም። አሁን ግን እንደ እንስሳ ተከልለናል። ልጆችም ለሥራ ወደ ሌላ ክልል እንዳይንቀሳቀሱ ሆኗል። እነዚህን ለመለወጥ እንደ ዘመቻ ዓይነት ነገር ያስፈልጋል።

በዋናነት ግን ሕገ መንግሥት መለወጥ አለበት፤ ይህ ካልሆነ ችግሩ ይቀጥላል። ይህን ለማስተካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ስብእናን እንትከል፣ የአገር ፍቅርን እንትከል።

ባለፈው መስቀል አደባባይ የኩራት ቀን ተከብሯል፤ ይህም ግን አዲስ አበባ ብቻ ነው። በብሔር የሰከሩ ሰዎችን ካላዳንን ራሳችንን እንመታለን፤ እውነተኛ ለውጥም አይደለም።

ችግኝ ተክለናል፤ ዛፉ ሥር በአብሮነት ለመኖር ወይስ ለመባላት? ስለዚህ ፍቅርም አብሮ መተከል አለበት ማለት ነው። ኢትዮጵያዊነትን፣ ስብእናን ክብርን በየአንዳንዱ ልጅ አእምሮ ሊተከል ይገባል።

የእኛ አንዱ ሥራ የትምህርት ዘመቻ ነው። በቅርቡ የምናገኘው ፈንድ አለ፤ ወጣቶችን ከተለያዩ ክልሎች አምጥተን እናስተምራለን።
እርስ በእርስ አንተዋወቅም አንነጋገርም። ለሌላ ከምናወራት ይልቅ እርስ በእርስ እንነጋገር ነው፤ የመኮራረፍ ፖለቲካ አይጠቅመንም አገርም በዛ መኖር የለባትም።
ወጣቶችን ሰብስበን የዛሬ ወጣቶች የነገ መሪዎች ናችሁ። ኢትዮጵያ እንደ አገር የምትቆየው እናንተ ሰላም ስትሆኑና በእናንተ መካከል ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ብለን እንነግራቸዋለን። እርስ በእርስም ታሪካቸውን እንዲለዋወጡ እንዲነጋገሩ እናደርጋለን። ከሩዋንዳ የምንጋብዘው ሰውም አለ፤ እርሱም ብሔርተኝነት ምን ዓይነት ችግር እንደሚያመጣ፣ አገር እንደሚያፈርስ እንዲነግራቸውና እንዲነጋገሩ እናደርጋለን። በመጨረሻም መድረኩን ለመገናኛ ብዙኀን ክፍት እናደርገዋለን። ልጆቹ ወደየመጡበት ሲመለሱም ሰብሰብ ብለው የሚቋቋሙበትን ድርጅት እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው።

ከትምህርት ሚኒስቴር ጋርም እየተገናኘን ነው። ካሪኩለም መቀየርን በተመለከተ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የትምህርት ሥርዓት ጥሩ አልነበረም። በትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይም ሐሳብ ሰጥተናል።

በተለይም ስብእና እና ኢትዮጵያዊነትን እንድናስተምር፣ ስንወለድም ሆነ ፈጣሪ ሲፈጥረን ብሔር ሳይሆን ሰው ነውና የፈጠረው፤ እያንዳንዱ ልጅ ከጎረቤቱና ከአጠገቡ ሰው ሲያገኝ፤ ወንድምና እህቴ የአገሬ ልጅ ነው ብሎ እንዲያስብ ከአንደኛ ክፍል እስከ ኮሌጅ እንድናስተምር፤ ሌላም ዝም ብሎ በቃል ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን በምሳሌ ማሳየት ነው። ለምሳሌ የተወሰነ በጀት ተመድቦ የጋምቤላ ልጅ ትግራይ የአክሱም ሐውልትን ቢያይ፣ የአፋር ልጅ ፋሲል እንዲይይ፣ የሶማሌ ልጅ እንጦጦ ተራራን እንዲያይ፣ የጉሙዙ የአፋርን አፍዴራ እንዲያይና የመሳሰለውን ማድረግ ኢትዮያዊነትን ያሳያል።

ሌላው ከሰላም ሚኒስትር ጋር ተገናኝተናል። ለእነርሱ ያልነው ችግሮችን የምንፈታበት እሴቶች አሉ፤ ባሕልም አለን። የሚከሰቱ ችግሮችን የምንፈታው በመንግሥት ፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን በዛፍ ሥር መሆን አለበት። ለሰላም ሚኒስቴር ያልነውም ሽማግሌዎችና እናቶችን እናሳትፍ የሚል ነው። ይህንንም ለማገዝ ጥረት እያደረግን እንገኛለን።

የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመሔድ ቅስቀሳ አድርገዋል፤ ባለሥልጣናትና የአገር ሽማግሎችንም አናግረዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ተጨባጭ ለውጥ መጣ?
በአገራችን አርዓያ እንዳይኖር፣ በታሪክ እንዳናምን ተደርጓል። የታሪክ ትምህርት ክፍል እንኳን ተዘግቶ ነበር። በራሴ ምሳሌ ልስጥ፤ ውጪ አገር የኹለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ከሦስት ሺሕ ተማሪዎች አንድ ጥቁር እኔ ብቻ ነበርኩ። ያስተናገዱኝ ግን በቋንቋ እና በቀለሜ ሳይሆን ሰው በመሆኔ ብቻ ነበር። እንዲህ ዓይነት ወጣቶች ጋር ጥሩ ተስፋ አለ።

በየቦታውና በየሔድኩባቸው የትምህርት ተቋማት ግብረ መልሱ ጥሩ ነው፤ ልጆቹም መድረኩ እንዲቀጥልና እንዲደገም ይፈልጋሉ። እኛም ጋር ይኽው እቅድ አለ፤ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሔደን እንዲሁ ያለ ውይይት ለማድረግና እነርሱም እንዲነጋገሩ ለማድረግ አስበናል። ውጤታማነት እንዳለው ከልጆቹ እየሰማን ነው። ችግር እንዳለ ደግሞ ይናገራሉ። በመካከል ሆነ ብሎ የማናውቀው ሊያጣላን የሚፈልግ አካል ደግሞ አለ። አብሮነት ያለውን ጥንካሬ ስለሚያውቅ በትምህርት ቤትም ገብተዋል።

ጥቂት የሆኑ የተማሩ የተባሉ ብሔር የሚያቀነቅኑ ሰዎች ከሌላ ቦታ የመጡ ናቸው። የብሔር ውክልና የላቸውም። ሌላው አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው 28 በመቶ ኢትዮጵያውያን ከኹለት ብሔር የተወለዱ ሰዎች ናቸው። እነዚህ የት ልናስገባቸው ነው?
ችግሩ ከሕዝቡ ሳይሆን ጥቂት የፖለቲካ ልኂቃን ናቸው። ሕዝቡ እንደሆነ ተጋብቶ አብሮ የኖረ ነው። አንዱ ትልቁ ከተማሪዎች የምንሰማው እነርሱ ራሳቸው ነገሮች የሚለወጡበትን መንገድ ያውቃሉ። የእኛም ትኩረታችን እዛ ላይ ነው።

በተደጋጋሚ በሚሰጡት ቃለመጠይቆች በኢትዮጵያ በተጀመረው ለውጥ ኹለት መሠረታዊ ነገሮች መደረግ አለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል። ሕገ መንግሥታዊ እና ተቋማዊ ማሻሻያ፤ አሁንስ ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ የማምጣት ተስፋ አለ?
እኔ ስለ አገሬ ስጋት አለኝ። የዛሬ አንድ ዓመት ስመጣ በየቦታው የነ ዐቢይ፣ የለማ፣ የገዱ እና የደመቀ ፎቶ በየቦታው አያለሁ፤ አሁን አታገኝም። በውጪም እንደዛው ነው፤ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደውም እንደ ዐቢይ የተደገፈ የለም። እኔም ዐቢይ መሪዬ ነው ብዬ ነበር። ምክንያቱም የመጀመሪያ ንግግሩ ልቤን ነክቶታል። ምክንያቱም እኔ የምመኘው ነው። ኢትዮጵያ ተብሎ ሥም መጥቀስ የማይወዱና የማይፈልጉ ነበሩ ከእሱ በፊት የነበሩት። እርሱ ደፍሮ ኢትዮጵያን ከኻያ ጊዜ በላይ ሲጠራት መስማቴ ትልቅ ነገር ነው።

በዛም ላይ “የመለስ ርዕይ” እና “ታላቁ መሪ” የሚሉ ቃላትን አለመጠቀሙ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ምክንያቱም ኃይለማርያም ደሳለኝ የራሱ ርዕይ አልነበረውም፤ በሞተ ሰው ርዕይ ነበር የቆየው፤ በመለስ ሥም ነበር የሚኖረው። እናም ዐቢይን መሪዬ ነው ያልኩበት ምክንያት የራሱ ርዕይ ስላለው ነው።

የደገፍኩት ኦሮሞ ስለሆነ ወይም በፓርቲውን አይደለም፤ በኢትዮጵያዊነቱ ነው። ሐሳቡም ትልቅ ስለነበር ነው። አሁንም እንደመሪ እደግፈዋለሁ፤ ግን እየሔደበት ያለው አቅጣጫ፤ ከጠበኩት አንጻር ስጋት ፈጥሮብኛል። ትልቁ ስጋቴ በሕገ መንግሥት ላይ ነው። ሕገ መንግሥቱ ከዚህ በፊት እርስ በእርስ እንድንባላ፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲጠፋ፣ ከኖርንበ እንድንፈናቀል፣ ሰላም እንዳይኖር ያደረገ ነው። በዚህ ሕገ መንግሥት ከቀጠለ ነገሮችን እናስተካክላለን ብንል ራስን ማታለል ነው የሚሆነው።

በእኔ አመለካከት ዐቢይ እንደ ዐቢይ እየሠራ ነው ግን ሕገ መንግሥት አለመነካቱ ላይ ነው ስጋት ያለኝ። ለምን ቢባል ታሪክን መድገም ማለት ነው። የትም ዓለም እንደ እኛ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር መጀመሪያ ሕገ መንግሥት መለወጥ አለበት። እኛ ግን የምንነጋገረው ስለ ምርጫ እንጂ ሕገ መንግሥት አይደለም፤ ትልቁ ሥጋቴ ይሄ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ መንግሥት እንደሚሻሻል ተናግረው ያውቃሉ። በአንጻሩ ለአንድ ክልል ብለን ሕገ መንግሥት አንለውጥምም ብለውም ነበር። ይህን ተቃርኖ እንዴት ያዩታል?
ይህ ነው ትልቁ የአገራችንም የለውጡም ሥጋቴ። እኛ የምንፈልገው ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሔ ነው። ይሔ የእኔ ሥጋት ብቻ አይደለም፤ ፎቶዎቹ ከየቦታው መነሳታቸው የሰዉን ሥጋት ያንጸባርቃል። ትክክለኛው መንገድ ላይ አይደለም ብዬ ነው የማምነው። ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ ካልተቀየረ ሌላ ችግር ውስጥ እንገባለን፤ ወደ ኋላም እንመለሳለን።

ወደ ኋላ መመለስ ግን የለብንም። በአገራችን እየጠበቅን ያለነው እውን እንዲሆን ሕገ መንግሥቱ መለወጥ ወይም መሻሻል አለበት። ምድራችን መፈናቀል የበዛው ሕገ መንግሥቱ ስለፈቀደ ነው። አንድ የብሔር ፖለቲካ ፓርቲ ሌላ ክልል ሔዶ ቅስቀሳ የማያደርጉት በሕገ መንግሥቱ ስላልፈቀደ ነው።
እናም ዋናው ችግር ሕገ መንግሥቱ ነው። ፓርላማ ውስጥ ያለው መቶ በመቶ የዐቢይ ደጋፊ ነው። ዐቢይ ከፈለገ ሕገ መንግሥቱ ለመለወጥ ማን ያቆመዋል፤ ይህን ማለፍ ከፈለገ ማለፍ ይችላል፤ ለምንድን ነው ማለፍ ያልቻለው።

መሬት ላይ ያለው እውነት ሕገ መንግሥት ወደ መለወጥ የሚወስድ ነው?
እሱ እየታየኝ አይደለም። ቢለወጥ ኖሮ አሁን አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሆኗል። እስከአሁን ስለ ሕገ መንግሥቱ እየተነጋገርን አይደለም። ሥጋቴ እዚህ ጋር ነው። እስከዛሬ በዚህች አገር መከራ ያመጣው ይሔ ሕገ መንግሥት ነው። ይህንኑ ሕገ መንግሥት እየተጠቀምን ለወጥ ይመጣል ማለት ራሳችንን ማታለል ነው። ሕገ መንግሥቱ የሚጠቅመውና እንዲለወጥ የማይፈልጉ ደግሞ ከተለወጠ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚሉትም ራሳቸውን ማታለል ነው።

ምርጫ ካልተካሄደ ኢትዮጵያ ትፈረሳለች ይላሉ፤ እውነተኛ ምርጫ እስከዛሬ ድረስ መቼ ነው የተካሔደው? እንዲህ ዓይነት ሰዎች በሰው ሕይወት ላይ ቁማር እየተጫወቱ ነው። ለዚህ ነው ሕገ መንግሥት መለወጥ አለበት ያልኩት።

ሌላው እውነተኛ ተቋማት ነው፤ ዝም ብሎ አርቴፊሻል አይደለም። ሌሎች ለውጦች በሕገ መንግሥት አይደለም የመጡት። ሕገ መንግሥት አይደለም ዐቢይ ኤርትራ ሔዶ ስምምነት ያስፈጠረው፤ ሕገ መንግሥት አይደለም ቡርቱካን ሚደቅሳን ለምርጫ ቦርድ ያስመረጣቸው። ሕገ መንግሥት ሳይሆን ራሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠራው ነው።

በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበራቸው ተቀባይነት ከፍተኛ ነበር፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አንዳንዶች ወደ አምባገነንነት እየሔዱ ይሆን እያሉ ይሰጋሉ። ጸረ ሽብር ሕጉም ተግባራዊ እየሆነ ይመስላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ አምባገነንነት የመሔድ አዝማሚያ እያሳዩ ነው?
ሕገ መንግሥት ካልተለወጠ ወደዛ የማይሔድበት ምክንያት የለም። አምባገነንነት የመጣው በዚህ ሕገ መንግሥት ምክንያት ነው። ካልተለወጠ ወደ አምባገነንነት እንደማይገባ ምንም ማስተማመኛ የለም። ሁሌ እንደምለው ሹፌር ተለወጠልን እንጂ መኪናው አልተለወጠም። ከዚህ በፊት የነበረውን ኃይለማርያምን ትተን ዐቢይ የሚባል ሹፌር መጣ። ሕዝቡ የሚወደው ሹፌር ነው፤ መኪናው ግን ገና አልተለወጠም። መኪና ትክክለኛ ካልሆነ፣ ፍሬን የማይሠራ ከሆነ ማንም ይሁን ማን መኪናው ገደል ይገባል። እንደዛ እንዳይሆን ግን መኪናው በጥንቃቄ መለወጥ አለበት።

አሁን ባለው የፖለቲካ እንቅስቃሴና ለውጥ በአዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ተስፋ ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ ተስፋ ሕዝቡ ነው። ሕዝቡ ደግሞ እምቢ ባይ መሆን አለበት። የምናየው ትክክል ካልሆነ አምቢ ማለት አለብን።
ሕዝቡ ከዚህ በፊት እንደነበረው እንደ ከብት መነዳት የለበትም። ምክንያቱም በራሳችንም ሆነ በልጆቻችን ሕይወት ቁማር መጫወት የለብንም። በየእያንዳንዱ የምንሠራው፤ ከተራው ግለሰብ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ የሚሠራ ራሱን መጠየቅ አለበት።

ከዚህ በፊት ከእንጦጦ ተራራ ስንመጣ በጀርባቸው እንጨት ይዘው ተሸክመው የሚሔዱ ሴቶች አሉ፤ እውነት በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ነው ቁማር የምንጫወተው? ደግሞ መስቀል አደባባይም ቤንዚን የሚስቡ ታዳጊ ልጆች አሉ፤ በእነዚህ ነው የምንቆምረው? ሴተኛ አዳሪ በየመንገዱ የሚወጣው ወዶ ነው? እውነት የእነዚህን ሰዎች ሕይወት ለማሻሻል ነው የምንሠራው?
ሴተኛ አዳሪዎች የሚሆኑት፣ ጎዳና ወጥተው የሚተኙት ሁሉም ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ነው። እስከመቼ እንደዚህ እንኖራለን? ለአገራችን በጀት ለምነን ነው የምንኖረው። በቀን ብዙ ጊዜ ይዘንባል ግን ምግብ የማይበላበት አገር ነው። በዓመት አንድ ጊዜ የሚዘንብበት አረብ አገር መብራት ሆነ ምግብ ጠፍቶ አያውቅም። እስከመቼ በሕይወታችን እና በትውልድ እየቆመርን እንኖራለን? እናም ለእኔ ተስፋው በሕዝብ ላይ ነው። በመሪና በፖለቲካ ፓርቲና ሳይሆን በሕዝብ ነው። ሕዝቡም ኀላፊነት መውሰድ አለበት፤ በልጆቼና የልጅ ልጆቼ ሕይወት አልጫወትም የሚል እንቢ ባይ መሆን አለበት። እምቢ ካላልን አምባገነንነት ሊደገም ይችላል።

ለምሳሌ በኢትዮጵያ ታሪክ ኀይለ ሥላሴ በወደቁ ሰዓት ትልቅ ቀዳዳ ነበር፤ አልተጠቀምንበትም፤ ዕድሉ አመለጠን። ደርግ ከወደቀ በኋላ የተገኘ ክፍተት ነበር፤ እነዚህ ኢትዮጵያን የማይወዱና የማይፈልጉ ሰዎች ኢትዮጵያን ያዙ። በ97 ቅንጅት የነበረ ጊዜም ትንሽ ቀዳዳ ነበር፤ ሕዝቡ ከወጣ በኋላ ወደ ቤቱ ተመለሰ። አሁን ዐቢይ መጣ፤ በየቦታው የሆነው ሁሉ እየታየ ነው። ነገ ደግሞ ማን ያውቃል ቁጭ ብለን የማንነጋገርበት የባሰ ወቅት ይመጣ ይሆናል።

ይህ እንዳይሆን ግን እንደ ሕዝብ ጆሮዎችና ዐይኖቻችንን ከፍተን፤ በትክክል እንደቤተሰብ መነጋገር አለብን። በሐሳብ ልንለያይ እንችላለን፤ በአገር ግን አንለያይም፤ አንድ አገር ብቻ ነው ያለን። ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፤ ነጮች ጭስ ባለበት እሳት አለ ይላሉ፤ ዝም ብለው አይደለም ይህን የሚሉት።

አያቶቻችን በሕግ አምላክ እያሉ በሰላም ነበር የሚኖሩት። በሕግ አምላክ ማለት መከላከያ ወይም ፌዴራል መለዮ የለም ነበር። አሁን ግን በአንጻሩ ሕግ የለም፤ አምላክ የለም። በአሁኑ ሰዓት ወንጀል የሠራና ሕይወት ያጠፋ ሰው በብሔሩ እየደበቅን ነው።

እንደዚህ ያለ ችግር እንዳለ እያወቅንና ዝም ካልን ተጠያቂ ነን። እውነት ከሆነና እውነት ካለ ሰዎች መደማመጥ ይችላሉ፤ በመደማመጥ መተማመን ይኖራል፤ ከዛም በአብሮነት መሥራት አለ፤ በዚህም አገር መገንባት ይቻላል፤ ሰላምም ይመጣል።

እውነት ከሌለ እና ማታለልና ማስመሰል ከሆነ ትክክል አይመጣም፣ መተማመን፣ አብሮነት መሥራትም ሆነ ሰላምና ብልጽግና አይመጣም። ስለዚህ ተስፋው ሕዝቡ ላይ ነው እንጂ በመሪ ላይ አይደለም።

ሕዝብና ፖለቲከኞች በሚመኙት መንገድ አገርን ዴሞክራሲያዊና መብቶች የሚከበሩበት አገር ለማድረግ በትክክለኛ መንገድ ላይ ነን?
በአንድ በኩል በትክክለኛው መንገድ ላይ አይደለንም፤ ገና መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን። በየትኛው አቅጣጫ መሔድ እንዳለብን አላወቅንም። ምርጫውም ቢሆን ለእኔ አቅጣጫ አይደለም። አቅጣጫ ማለት አንድ መንገድ ሲያዝ ነው። መስቀለኛ መንገድ ላይ አራት አቅጣጫ አለ፤ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ፣ ወደ ኋላ ወይም ወደ ፊት። የትኛውን እንደምንወስድ አላውቅም። ለእኔ ትክክለኛው አካሔድ ሰዎች ተደራጅተው የትኛው ነው ትክክለኛው መንገድ ማለት አለባቸው።

የብሔርተኛነት አቅጣጫ ከሆነ አለ፤ ልንመርጠው እንችላለን። እርስ በእርስ እንዳንባላ የሚያደርግ መንገድም አለ፤ እሱንም መምረጥ እንችላለን። ወደ ኋላም ለመሔድ ከፈለግንም ይቻላል፤ አቅጣጫ አለ። ሰው በሰውነቱ የሚኖርባት አገር፤ የዘር የበላይነት ሳይሆን የአገርና የሕግ የበላይነት ያለበት አገር የሚወስደን አቅጣጫ መያዝም እንችላለን።

ትልቁ ጥያቄ ግን በአብሮነት መኖር እንፈልጋለን ወይ የሚለው ነው። የምንፈልግ ከሆነ መንገዱን መፈለግ አለብን። ይህም ለሁላችንም የምንመኘው ነው። ግን ለጥቂት ለሆዳቸው ያደሩና በአቋራጭ መንገድ መክበር የሚፈልጉ፣ የብሔር የበላይነት የሚያምኑ ወይም ተረኛ እኛ ነን ብለው የሚያስቡ ሰዎች ምክንያት፤ መስቀለኛ ነን ብዬ ነው የማምነው። ትክክለኛ መንገድን ለመያዝ መደራጀት ያስፈልጋል። በአሁኑ ሰዓት ብሔርተኝነት የሚያቀነቅኑ ሰዎች ድምጽ ያላቸውና የተደራጁ የሚመስሉት እነርሱ ናቸው፤ የእኛ ግፊት ደግሞ እነርሱ ላይ ነው። በመካከል ዝም ያሉ አሉ። ግን ዝም የምንልበት ወቅት አይደለም ብዬ አምናለሁ።

ምክንያቱም እነርሱ ጠንካራ ሆነው አይደለም። ብሔርተኝነት ቢያሸንፍ 27 ዓመት ቆይቷልና ነው። እንዲህ የጠሉበት ምክንያትም የወሰዳቸው መንገድ ትክክለኛ ባለመሆኑ ነው። እኛ የምንፈልገው ሰው በሰውነት የሚከበርበት አገር ከሆነ ሁሉም ለትክክለኛ መንገድ መደራጀት ነው።

አሁን የምንኖረው የተከፈተው የብሔር ሚድያ ጎረቤትን ከጎረቤት እንዲያባላ፤ ይሄ ክልል የእኔ ክልል መባባል እንዲኖርና ስለአገር የሚያስቡ ቡድኖች ድምጻቸው እየቀነሰ ነው። ያ ግን ጥሩ አይደለም። የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሲናገሩ “የትም አገር ብሔር አለ፤ አገር ሲቀድም ነው ሰላም የሚኖረው። ብሔር በቀደመበት አገር፤ አገር ይፈርሳል” ብለው ነገሩን። እኛም እንደዜጋ እንደሕዝብ ፈተና ላይ ነን።

ከወራት በፊት ጋምቤላ ላይ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ተሰምተዋል። አሁን ያለውን የጋምቤላ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?
ጋምቤላ ክልልን የሚመሩት የሕዝብ መሪ አይደሉም። ስለ ክልሉም ሆነ ስለአገር ርዕይ የሌላቸው ናቸው። ከዚህ በፊት በሕወሓት ጥቅም የተያዙ ናቸው። በእኔ አመለካከት በጋምቤላ ለውጥ የለም። ሌላ አካባቢ የታየው ለውጥም ሆነ ልማት በጋምቤላ የለም። መሪዎቹ ስለ ሰው ልጅ የማያስቡና የማይቆረቆሩ ናቸው። እዛ በነበርኩ ጊዜ እንዳየሁት ትምህርት ቤት የሌለበት፣ ደሞዝ እንኳን የማይከፈልበት ነው።

ይህን ሳይ በጣም ነው ያዘንኩት። ያንን የመሰለ ቦታ የምግብ ችግር የማይኖርበት ቦታ ሊሆን ሲገባ በአመራር ደካማነት ምክንያት ችግር አለ። በዛም ላይ ሕዝብ የሚፈልጋቸው ሳይሆኑ ከዚህ ቀደም ሕወሓት መርጦ ያስቀመጣቸው ናቸው። አገርና ክልል ማስተዳደር ቀርቶ ራሳቸውን እንኳን ማስተዳደር የማይችሉ ሰዎች ናቸው።

በእኔ አመለካከት ጋምቤላ ገና ፈተና ላይ ነው። የጋምቤላ ሕዝብና ነዋሪ የሚወደው፣ ሕዝቡ አኝዋክ፣ ኑዌር፣ መሃል አገር፣ ሙስሊም፣ አማራ ወይም ሌላ ብሎ ሳይሆን እንደራሱ ቤተሰብ የሚመለከት መሪ እስከሚገኝ ድረስ፤ ለጊዜው ያለን ምንም ነገር የለም። እኔ ደግሞ አንድ ቀን ጋምቤላን የሚወድ መሪ ከሕዝቡ ይመጣል፤ ሕዝብም የሚወደው መሪ ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here