መንግሥት ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ለምን ይፈራል?

0
1194

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የአዲስ አበባ አገር ስብከትን ጨምሮ ስድስት የተለያዩ አደረጃጀት ያላቸው ኅብረቶችና ማኅበራት፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና አማንያን ላይ እየደረሱ ያሉትን የተለያዩ ዓይነት ጥቃቶችን አስመልክቶ መስከረም 4/2012 ሊደረግ የነበረው ሰላማዊ ሠልፍ መንግሥት ችግሩን ለማስተካከል ቃል በመግባቱ መተላለፉን ከማኅበራቱ አደራጆች መካከል ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ማኅበራቱ ሰላማዊ ሠልፉን የጠሩት ለእሑድ፣ መስከረም 4/2012 የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት የሰልፉን ጥሪ ተከትሎ ከማኅበራቱ ጋር አስቸኳይ ውይይት ለማድረግ ጥሪ አስተላልፏል። ከጳጉሜን 1/2011 ጀምሮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ጋር ውይይትና ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ጳጉሜን 2/2011 ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውንም ታውቋል። ከክልል ብሔራዊ መንግሥታትና ተወካዮቻቸው ጋር ውይይት በማድረግ፣ ጥያቄያቸው ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ሰላማዊ ሠልፉን ጥቅምት 30/2012 እንደሚያደርጉም አደራጆቹ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ፣ “የአዲስ አበባ ባላአደራ ምክር ቤት” ተቋቋመ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ሦስት ሕዝባዊ ስብሰባዎችና አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ሞክሮ፣ ሁሉም በአዲስ አበባ መስተዳድር ተፅዕኖ ተደርጎባቸው፣ ኹለቱን ለመሰረዝ ተገዷል። አንዱ ጋዜጣዊ መግለጫም ቢሆን፣ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ክልከላ እንደተደረገበት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ ተናግረዋል።

ይህ ሁሉ መንግሥታዊ ሕገ ወጥነት አግባብ እንዳልሆነ፣ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማና እስክንድር ነጋ በተገናኙበት ጊዜ ቢተማመኑም፣ ስምምነቱ ሰኞ፣ መጋቢት 30/2011 ዕለት ተደርሶ፣ በማግስቱ፣ ማክሰኞ፣ ሚያዚያ 1 ለመስተዳድሩ በገባ ደብዳቤ፣ በቀጣዩ ቅዳሜ፣ ሚያዚያ 5 መገናኛ በሚገኘው ኮከብ አዳራሽ የቦሌና አቃቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ሕዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን፣ ለዚህም የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግ ጠይቀው ምላሽ አለማግኘታቸውን እስክንድር ተናግረዋል። ሆኖም፣ እስከ ዓርብ ድረስ የመስተዳድሩ ምላሽ በመጥፋቱ፣ ለራሳቸው ለምክትል ከንቲባው በጽሑፍ መልዕክት እንዲያውቁት ተደርጓል። በመጨረሻም፣ ዓርብ፣ ሚያዚያ 4 በተሰጠ የቃል ምላሽ፣ በሕጉ መሰረት ስብሰባ ለማድረግ እንደማይከለከል ተጠቅሶ፣ የፖሊስ ጥበቃ ለማድረግ ግን መስተዳድሩ ፈቃደኛ አለመሆኑ መገለጹን ያወሳሉ።

“በዚህ ተስፋ ባለመቁረጥ፣ አዳራሽ ስብሰባውን በራሳችን ኀይል እያስጠበቅን ለማከናወን ወስነን በቦታው ላይ የተገኘን ቢሆንም፣ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት በመኪና ተጭነው የመጡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ወጣቶች፣ በቡድን በቡድን ተደራጅተው በአካባቢው ከመሰማራታቸውም በላይ፣ ወደ ስብሰባው በመምጣት ኹከት ለመቀስቀስ ሞክረዋል። ይህንን ለፖሊስ ብናሳውቅም፣ በመጨረሻ ላይ፣ “ጥበቃ አይደረግላችሁም” የሚል እጅግ አሳፋሪና ኀላፊነት የጎደለው ምላሽ ተሰጥቶናል” ሲሉ በሰላማዊ መንገድ ሊደረግ የታሰበው ስብሰባ እክል እንደገጠመው እስክንድር ለአዲስ ማለዳ ሁኔታውን በዝርዝር አስረድተዋል።

ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የማድረግ መብት
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 3/1983 መሠረት ሰላማዊ ሰልፍ ማለት “ብዙ ሕዝብ በአደባባይ፣ በመንገድ ወይም በሌላ ለሰላማዊ ሰልፍ ምቹ በሆነ ሥፍራ፣ የጦር መሣሪያ ሳይዙና የኅብረተሰቡን ሰላም ሳያውኩ ሐሳባቸውን በንግግር፣ በዘፈን፣ መፈክር በማሰማት፤ ጽሑፍን በማንገብ ወዘተ በስርዓትና በይፋ የሚገልጹበት ሒደት” መሆኑን ይገልጿል።

በተመሳሳይ መልኩ ሕዝባዊ የፖለቲካ ወይም ሲቪል ስብሰባ ምን ማለት እንደሆነ አዋጁ ሲደነግግ፣ “ሕዝባዊ ስብሰባ ማለት ብዙ ሕዝብ በቤት፣ በግቢ፣ በአደባባይ ወይም በሌላ ለስብሰባ ምቹ በሆነ ሥፍራ የጦር መሣሪያ ሳይዙና የኅብረተሰቡን ሰላም ሳያውኩ፣ ካስፈለገ በድምፅ ማጉሊያ መሣሪያም ጭምር እየተጠቀሙ ፖለቲካዊና ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በይፋ ውይይት የሚያካሒዱበት ስብሰባ” ነው ሲል በይኗል። እነዚህ ኹለት ድንጋጌዎች፣ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የማዘጋጀትና በእነዚሁ የመሣተፍ መብቶችን አመላካች ናቸው።

አዋጅ ቁጥር 3/1983 በአንቀጽ 6 (2) ሥር ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ለማድረግ የሚፈልግ አካል የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ከሚካሔድበት ጊዜ ቢያንስ ከ48 ሰዓታት በፊት በጽሑፍ ማሳወቅ እንዳለበት ይናገራል።

መስፍን ወልደማሪያም (ፕሮፌሰር) ግንቦት 2005 በተለይ ለዞን 9 ጦማሪያን ላይ ባወጡት ጽሁፍ፣ በሥራ ላይ አለ የሚባለው በ1987 የወጣው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 30 እና 31 የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የመደራጀት መብትን እንደሚደነግግ ገልጸው፤ ነገር ግን ኹለቱም አንቀጾች እያሉ መፍረሻውን ወይም ማርከሻውን አብረው ያስቀምጣሉ፤ “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” እንደሚባለው ሲሉ ክፍተት መኖሩን አመላክተዋል። ይህ ዘዴ በአጼ ኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ሕገ መንግሥቶች ውስጥ የሚታይ ነበር ሲሉ ሕጉ ክፍተት እንዳለበት ይናገራሉ።

አንቀጽ 30 “ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸውሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፤ በማለት የአንቀጹን ዋና ርዕስ ያደበዝዘዋል ያሉት መስፍን፣ ያውም ምንም ትርጉም በሌለው ማመካኛ ነው፤ መሠረታዊ የሆነ የዴሞክራሲ ማሙያዎች የሆኑትን የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍን የማድረግ መብት “ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ” በሚል በተምታታና ግልጽ ባልሆነ አስተሳሰብ ዋናውን መብት ለመገደብ “ሕጋዊ” የሚመስል ማመካኛ ፈጠሩ፤ በዚህም ምክንያት በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ የሚመስሉት አንቀጾች በተግባር ታግተዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ በበኩላቸው፣ የሕጉ አወዛጋቢነት እንዳለ ሆኖ ያለውም ሕግ በግልጽ እየተጣሰ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሕዝባዊ ስብሰባ ሲደረግ መንግሥትን ማስፈቀድም ሆነ መጠየቅ እንደማያስፈልግ የገለጹት እስክንድር፣ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ሕዝባዊ ስብሰባ ሊያደርግ ሲል ፈቃድ አምጡ እየተባልን ነው ብለዋል። በሕውሓት የሥልጣን ዘመን መግለጫ ተክልክሎ እንደማያውቅ ገልጸው፣ የባሰ ስርዓት መምጣቱን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሕግ ማውጣት እንጂ መተግበር ላይ ገና ብዙ እንደሚቀር በማከል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር መሰንበት አሰፋ (ዶ/ር)፣ “ማሳወቅ ነው፣ ወይስ ማስፈቀድ” የሚለው የሕጉ ክፍል አከራካሪ መሆኑን በመግለጽ፣ ሰዎች፣ ቡድኖች ወይም ማኅበራት በሆነ ጉዳይ አዝነው ድንገት ሰልፍ ቢወጡ፣ “ስላላስፈቀዱ” በሚል መንግሥት እርምጃ መውሰድ እንደማይችል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። መንግሥት ሆደ ሰፊ ካልሆነ አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገሩት መሰንበት (ዶ/ር)፣ መንግሥት ጥበቃ የመስጠት እንጂ ሰልፍ እንዲካሔድ የመፍቀድ ሥልጣን የለውም ባይ ናቸው።

በአንቀጽ 6 (2) የማሳወቂያው ጽሑፍ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ በከተማ ከሆነ የሚደረገው ለከተማው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፤ ከከተማ ውጭ ከሆነ ለወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት መሆን እንዳለበትም አስቀምጧል። በመሆኑም ማንኛውንም ዓይነት ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ከመደረጉ በፊት፣ በአቅራቢያቸው ለሚገኝ አስተዳደር ስለጉዳዩ በጽሑፍ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል ይህ የሚሆነው ደግሞ ስብሰባው ወይም ሰልፉ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ታስቦ ነው።

በጽሑፍም ጉዳዩን ሲያሳውቁ ስድስት ነጥቦችን የያዘ ዝርዝር መረጃዎችን አብረው ማቅረብ እንዳለባቸው ሕጉ ይደነግጋል ያሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ እነዚህም፣ የሰላማዊ ሰልፉ ወይም የሕዝባዊ ፖለቲካ ስብሰባው ዓላማ፤ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው የሚደረግበት ቦታ፤ ሰላማዊ ስልፉ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር ከሆነም የሚተላለፍባቸው መንገዶችና አደባባዮች፤ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው የሚደረግበት ቀንና ሰዓት፤ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው የሚወስደው ጊዜ ግምትና የተሳታፊው ሕዝብ ብዛትና ማንነት ግምት፤ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው በሚደረግበት ጊዜ ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ ከመንግሥት የሚፈለገው ዕርዳታ፤ እና የሰላማዊ ስልፉ ወይም የሕዝባዊ ፖለቲካ ስብሰባ አደራጅ ግለሰብ ወይም ቡድን ሙሉ ሥም፣ አድራሻና ፊርማ፤ በድርጅት ሥም የሚዘጋጅ ከሆነም የድርጅቱ የአመራር አካል ተወካዮች ሦስት ተጠሪዎች ሥም፣ አድራሻና ፊርማ መኖር እንደሚጠበቅበት መቀመጡን ያብራራል።

አዋጁ ከወጣበት አንዱ ምክንያት ዜጎች የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙባቸው ማስቻል እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት መሰንበት፣ ይህንን መሠረታዊ መብት ዜጎች እንዲጠቀሙበት ለማስቻል ደግሞ ኀላፊነት ከተጣለባቸው አካላት አንዱ በየአካባቢው ያሉ የአስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች ናቸው። እነዚህ አካላት የሰላማዊና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ጥያቄ በጽሑፍ ሲቀርብላቸው ጥያቄውን በመቀበል የዜጎችን ጥያቄ በግልጽ ማስተናገድ እንዳለባቸው ሕጉ በግልጽ ደንግጓል ብለዋል።

መንግሥት ሰላማዊ ሰልፍን ለምን ይፈራል? ሰልፍ የማድረግ ጥቅሙስ
እንደ መስፍን ገለጻ፣ በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚነሱ መንግሥታት ሰልፍን ይፈሩ እንደነበር አስታውቀው፣ ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው በሚሠሩት ሥራ በራስ የመተማመን ነገር እንደሌላቸውና የመልካም አስተዳደር እጦት የተጫናቸው በመሆናቸው ነው ብለዋል።

መንግሥት ሰላማዊ ሰልፍን የሚፈራው ዴሞክራሲያዊ ስላልሆነ ነው የሚሉት እስክንድር፣ አንድ ጊዜ ሥልጣን በእጃችን ገብቷል፤ አሳልፈን አንሰጥም የሚሉ ባለሥልጣናት በአደባባይ ድምጻቸውን እያሰሙ መሆኑን አስታውቀው፣ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ለአገርም ለመንግሥትም እንደማይጠቅም ይናገራሉ።
“ምን ያለበት ዝላይ አይችልም” እንደሚባለው፣ እነታከለ ዑማ የሚሠሩትን ስለሚያውቁና ሁሌም በሥጋት ስለሚኖሩ፣ ሕዝባዊ ስብሰባ ወይም ሰልፍ ሲጠራ ያ ነገራቸው የሚወጣ ስለሚመስላቸው ፈቃደኞች አይሆኑም ሲሉ የገለጹት እስክንድር፣ ይሁን እንጂ እነርሱ ቢከለክሉም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች መልዕክቶቹ ይዘታቸውን ቀይረው እንደሚተላለፉና ያም እራሳቸውን ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ያወሳሉ።

እንደፕሮፌሰር ገለጻ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብቶች የሕዝቡን ስሜትና ፈቃድ ለማወቅ ለሚፈልግ መንግሥት የእነዚህ መብቶች በተግባር መዋል በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም መንግሥትንና ሕዝብን ያቀራርባሉ፤ የእነዚህ መብቶች መታፈን የሚያሳየው በመንግሥት ፋንታ አገዛዝ መኖሩንና ሕዝቡን ያለፈቃዱ በኀይል ብቻ የሚገዛ መሆኑን ነው።

መሰንበትም በመስፍን ሐሳብ ይስማማሉ። ሰዎች በውስጣቸው ያለውን ነገር በአደባባይ ወጥተው ሲተነፍሱት በውስጣቸው ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ቅሬታ በብዙ መልኩ እንደሚያስወግዱ አስታውቀዋል። መንግሥትም በበኩሉ ኅብረተሰቡ በሆዱ የያዘውን ቅሬታ ስለሚረዳ አስችኳይ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚጠቅመውና የችግሮችን መደራረብ ቶሎ ቶሎ እንዲቀርፍ እንደሚረዳው ያወሳሉ።

እስክንድርም በበኩላቸው፣ የስብሰባ ጥቅሙ ቅሬታዎች ታፍነው ከሚያመጡት ችግር የሚገላግል መሆኑን ይናገራሉ። መንግሥትም ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣታቸው በፊት እርምጃ እንዲወስድ ጠቋሚ ነው ብለዋል። ባለፉት ስርዓቶች የሕዝብ ድምጽ ታፍነው በመቆየታቸው መጨረሻቸው ምን እንደሆነ አይተናል ሲሉ አስታውቀዋል።

እናም መንግሥት የሰላማዊ ሰልፍን ጥቅም ተረድቶ ዜጎች ሐሳባቸውን በአደባባይ መግለጽ እንዲችሉ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን፣ ማበረታታትም እንዳለበት መሰንበት ይናገራሉ። የሕዝቦች መታፈን የሚያመጣውን ችግር ባለፉት ሦስት መንግሥታት ተምረናል የሚሉት መስፍን፣ ከታሪክ መማር ያልቻለ መንግሥት ዕጣ ፈንታው እንደአቻዎቹ መሆን ነው ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here