መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳ786 ቢሊዮን ብር ተስፋ ወይስ ስጋት?

786 ቢሊዮን ብር ተስፋ ወይስ ስጋት?

ጊዜው በብርሀን ፍጥነት እየተጓዘ ይመስላል። በምጣኔ ሀብት የዘመን አቆጣጠር የ2015 በጀት ዓመት ሊገባ ቀናትን እየጠበቀ ነው። መንግሥትም ከወዲሁ የቀጣይ ዓመቱን እቅድ እያሰናዳ፣ ረቂቆችን እያቀረበ ውይይት እንዲደረግባቸው እያደረገ ይገኛል። በዚህ መሠረት የ2015 በጀት ዓመት 786 ቢሊዮን ብር በጀት ቢመደብለትስ ተብሏል። ነገር ግን ይህ በጀት ጉድለት እንዳለበት ተጠቅሶ፣ ይህን ጉድለት ለመሙላት ይሆናሉ የተባሉ አማራጮች ሁሉ ቀርበዋል።

አገራት የበጀት ጉድለት የሚያጋጥማቸው በዋናነት የሚሰበስቡት ገቢና ወጪ ሳይመጣጠን ሲቀር ነው ይላሉ፤ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች። ጦርነትን ጨምሮ በርካታ ጫናዎችን ከአቅሙ በላይ ተሸክሞ ያለው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት፣ ለ2015 ጉድለቱ ተሞልቶ ሸክሙም ከዜጎች ትከሻ ላይ ቀለል እንዲል ለማስቻል፤ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች የተለያዩ ምክረ ሐሳቦችን እየሰጡ ይገኛሉ። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ ጨምሮ፣ የተለያዩ ዘገባዎችን በማጣቀስ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል። መንግሥትም የኢኮኖሚውን ፈተና ውስጥ መግባት አሁን አሁን እያመነ መምጣቱን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ባለፈው ሳምንት ስለ 2015 ረቂቅ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰጡት ማብራሪያ መረዳት ይቻላል።

በውስጣዊና በውጫዊ ችግሮች የተወጠረው ኢኮኖሚ፣ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲባባስ ከማድረጉ ባለፈ የዜጎችን ኑሮ እየተፈታተነ ከመጣ የሰነባበተ ሲሆን፣ ይህም ያስከተለውን የኑሮ ውድነት ግስጋሴ ማስቆም አልተቻለም።

መንግሥት ለ2015 በጀት ዓመት በጀት እንዲጸድቅለት ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ አቅርቧል። ለምክር ቤቱ የቀረበው የ2015 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 786 ቢሊዮን ብር ነው። በጀቱ በመጠናቀቅ ላይ ከሚገኘው ከ2014 በጀት ጋር ሲነጻጸር 102.7 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን፣ የ2014 በጀት 683.7 ቢሊዮን ብር ነበር።

የበጀት ድልድሉ ለመደበኛ ወጪ 345.1 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ፕሮጀክት 218.1 ቢሊዮን ብር፣ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ 209.4 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 14 ቢሊዮን ብር ሆኖ ተደልድሏል። የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የ2015 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ መንግሥት ከያዘው 786 ቢሊዮን ብር በጀት 231.4 ቢሊዮን ብር የተጣራ የበጀት ጉድለት እንዳለበት ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።

መንግሥት የገጠመውን የበጀት ጉድለት በዋናነት ከአገር ውስጥ ብድር ለመሙላት እቅድ እንዳለው ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። ያጋጥማል ተብሎ ከተገመተው የበጀት ጉድለት 224.5 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን የታደቀ ሲሆን፣ ቀሪውን 6.9 ቢሊዮን ብር ከውጭ ብድር ለማግኘት ታቅዷል።

ይሁን እንጂ፣ የአገር ውስጥ ብድር የዋጋ ግሽበትን እንዳያባብስ ስጋት እንዳላቸው የምክር ቤት አባላት በጥያቄ አንስተዋል። የምክር ቤት አባላት ያነሱትን ስጋት በምጣኔ ሀብት ባለሙዎችም በስፋት እየተገለጸ ነው። መንግሥት የበጀት ጉድለቱን በአገር ውስጥ ብድር ለመሙላት በሚያደርገው ጥረት፣ የዋጋ ግሽበት እንዳይባባስ ጥንቃቄ አደርጋለሁ ቢልም፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ስጋታቸውን በስፋት እየገለጹ ነው።

ገንዘብ ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዕቅድ ሲያዘጋጅ፣ የሚገጥመውን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን ከውጪ የሚገኘው ሀብት በታሰበው መጠን ላይገኝ ስለሚችል፣ መንግሥት ከአገር ውስጥ ከሚመነጨው ሀብት ማለትም ከግምጃ ቤት ሰነድና ከሌሎች የሀገር ውስጥ ምንጮች ለሟሟላት እንደታሰበ ይፋ አድርጓል።

ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ የቀረበበት ሌላኛው ጉዳይ የመከላከያ በጀት ከፍተኛውን በጀት መያዙ ሲሆን፣ የምክር ቤት አባሉ ክርስቲያን ታደለ “የአገር ደኅንነት የሚረጋገጠው ዜጎች በልተው ማደር ሲችሉ ነው” በማለት ለመከላከያ የተመደበውን ከፍተኛ ወጪ ተችተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ረቂቅ በጀት፣ በ2015 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት በጀቱን ለመሸፈን ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ የቀረበ ሲሆን፣ የበጀት ዓመቱ ጠቅላላ የፌዴራል መንግሥት ገቢ የውጭ እርዳታን ጨምሮ 477.8 ቢሊዮን ብር ይሆናል ተብሎ በእቅድ መታሰቡን አብራርተዋል። ከታቀደው ገቢ ውስጥ 92 በመቶ ያክል ከአገር ውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፣ 84 በመቶ ያክሉ ወይም 400 ቢሊዮን ብር ከግብር ምንጭ ለመሰብሰብ የታቀደ ነው።

በ2015 በጀት ዓመት መንግሥት ለመሰብሰብ ያቀደው ግብር በ2014 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ካቃደው 294 ቢሊዮን ብር አንጻር፣ የ36 በመቶ ዕድገት ይኖረዋል ተብሎ የታቀደ ሲሆን፣ በበጀት ከታወጀው 334 ቢሊዮን ብር አንጻር ደግሞ የ19 በመቶ ዕድገት አለው።

የፌዴራል መንግሥት የበጀት ወጪውን ለመሸፈን ያቀደው ግብር ነክ ካልሆኑ ገቢዎች ሲሆን፣ ግብር ነክ ካልሆኑ ምንጮች የሚሰበሰበው ገቢ በዋናነት ከብሔራዊ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከሌሎች ተቋማት የሚገኝ የዘቀጠ ትርፍ ገቢ፣ በባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ከሚሰጡ የአገልግሎት ክፍያና ከመንግሥት ዕቃዎች ሽያጭ የሚገኝ ነው። መንግሥት ግብር ነክ ካልሆኑ የገቢ ምንጮች 38.6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታውቋል።

የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ጉድለትን በአገር ውስጥ አማራጭ ለመሙላት መታሰቡ የዜጎችን ሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው የዋጋ ግሽበት እንዳይባበስ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከወዲሁ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። የምጣኔ ሀብት ተንታኙ ዋሲሁን በላይ፣ መንግሥት ያጋጠመውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ከሚወስዳቸው አማራጮች መካከል ገንዘብ ማተም አንዱ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ዋጋ ግሽበት ላይ ገንዘብ ማተም ችግሩን ከዚህ በላይ እንዲባባስ አቀጣጣይ ምክንያት መሆኑ እንደማይቀር ከወዲሁ መገመት እንደሚቻል ተንታኙ ሳይጠቅሱ አላለፉም። መንግሥት 36 በመቶ የደረሰውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ እሠራለሁ ይበል እንጂ የማይቻል መሆኑንም ነው ዋሲሁን ያመላከቱት።

የገንዘብ ሚኒስትሩ በ2015 የዋጋ ንረቱ አሁን ካለበት 36 በመቶ ወደ 11 በመቶ ለማውረድ መንግሥት ይሠራል ብለዋል። ይሁን እንጂ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ አሁን ባለው ሁኔታ የዋጋ ንረት መቀነስ ከባድ መሆኑን ነው። ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚነሳው ጦርነቱና አገራዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች መሻሻል አለማሳየታቸውና አሁንም ተባብሰው መቀጠላቸው ነው።

- ይከተሉን -Social Media

በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት መንስኤ ናቸው ተብለው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል፣ የብር የመግዛት አቅም መዳከም፣ የማምረቻ ወጪ መጨመር እና ከውጪ የሚገባ እቃ ዋጋ ንረት ናቸው። የብር የመግዛት አቅም መዳከም ደግሞ ከብር ስርጭት ጋር የሚገናኝ ሲሆን፣ በገበያ ላይ ከፍተኛ ጥሬ ብር በሚንቀሳቀስበት ወቅት የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ የዋጋ መናርን እንደሚያስከትል ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የበጀት ጉድለት መንስኤው ምንድን ነው?
አገራት የበጀት ጉድለት የሚያጋጥማቸው በዋናነት የሚሰበስቡት ገቢና ወጪ ሳይመጣጠን ሲቀር መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ። ስተዲ የተሰኘ ተቋም በድረ ገጹ ስለ በጀት ጉድለት ባሰፈረው ጽሑፍ፣ የበጀት ጉድለት መንስኤዎች ቀላል እና ውስብስብ ሊሆኑ ይችላሉ ይላል። በዋናነት ግን አንድ መንግሥት ከግብር ከሚሰበስበው በላይ ወጪ ሲያወጣ የበጀት ጉድለት ይከሰታል ይላል።

የገቢ መቀነስን ግምት ውስጥ በማስገባት ወጪው ካልተቀነሰ የግብር ተመኖችን መቀነስ የበጀት ጉድለትን ሊያስከትል እንደሚችልም የሚያትተው የስተዲ ጽሑፍ፣ የኢኮኖሚ ውድቀት አንድ መንግሥት ወጪውን ለመሸፈን በሚያስችለው አቅም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል ይላል።

ሌሎችም ጥናቶች እንደሚሳዩት ደግሞ፤ የበጀት ጉድለት በዋናነት ከመጠን በላይ የመንግሥት ወጪዎች ወይም የገቢ ወጪ አለመመጣጠን እና ወጪዎችን የማይሸፍኑ ዝቅተኛ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ይከሰታል። የግብር ቅነሳ የሚያስከትለው የገቢ ማሽቆልቆልን፣ የበጀት ጉድለትን ሊያስከትል የሚችልበት ዕድልም ቀላል የሚባል አይደለም።

መንግሥት ከግብር ቅነሳ አንጻር በ2014 በጀት ዓመት፣ የድጎማ በጀት በመመደብ ሸቀጦቹ ከቀረጥ ነጻ ከውጭ እንዲገቡ ፈቅዶ፣ 29 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማጣቱንም መግለጹ የሚታወስ ነው።

የምጣኔ ሀብት ተንታኙ በበኩላቸው፤ የፌዴራል መንግሥት የገጠመው የበጀት ጉድለት ዋናው ምክንያት የወጪና ገቢ አለመመጣጠን መሆኑን ያነሳሉ። የመንግሥት በጀት ከገቢ ጋር የተመጣጠነ ካልሆነ፣ የበጀት ጉድለት ማጋጠሙ የማይቀር ነው የሚሉት ተንታኙ፣ መንግሥት የተለያዩ የገቢ ምንጮችን አስፍቶ ገቢውን ከወጪው እኩል ካላሳደገ ችግር ያጋጥማል ይላሉ።

“ወጪ የገቢ ጥገኛ ነው” የሚሉት ተንታኙ፣ የፌዴራል መንግሥት የሚሰበስበው ግብር ከበጀት ወጪው ጋር የተመጣጠነ አለመሆኑን እንደሚያሳይ ጠቁመዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ መንግሥት ስለገጠመው የበጀት ጉድለት ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥት የገጠመውን የበጀት ጉድለት ለማስቀረት በከፍተኛ ጥረት የግብር ማሻሻያዎችን በቀጣይነት እንደሚሠራ ጠቁመዋል። የምጣኔ ሀብት ተንታኙ በበኩላቸው ደግሞ መንግሥት የበጀት ጉድለትን ለመሙላት የተለያዩ የገቢ ግብር ምንጮችን ማስፋት እንዳለበት ይጠቁማሉ።

በኢኮኖሚው ላይ ምን ያስከትላል?
የበጀት ጉድለት በተለይ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ሲያጋጥም በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። በምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው ቦይሴ ዋየር የተሰኘ ድረ ገጽ፣ ስለ በጀት ጉድለት ያሰፈረው ሰፊ ጽሑፍ፣ የበጀት ጉድለት የሚፈጥራቸው ችግሮች የሕዝብ አገልግሎቶችን እስከ ማስተጓጎል የሚደርስ መሆኑን ያትታል።

- ይከተሉን -Social Media

የበጀት ጉድለት አጠቃላይ የመንግሥት ዕዳን እንደሚጨምር የሚያትተው ጸሑፉ፣ መንግሥት ብዙ ሲበደር ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እንደሚቸገርም ይገልጻል። ለዚህም እንደ ምክንያት የተነሳው የመንግሥት የብድር ጫና ሲጨምር የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ አስቸጋሪ መሆኑ ነው።

የበጀት ጉድለት የመንግሥትን የብድር ጫና የሚጨምር መሆኑ የማያጠራጥር መሆኑን የሚገልጹት የምጣኔ ሀብት ተንታኙ፣ የአገር ውስጥ ብድር በራሱ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ አለመሆኑን ያነሳሉ። የመንግሥት የእዳ ጫና በጨመረ ቁጥር የውጪ አበዳሪዎች ብድር ለመስጠት ወደኋላ የሚሉበት ሁኔታ እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።

ሌላኛው ኢንቨስቶፔዲያ የተሰኘ ትኩረቱን ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ላይ አደርጎ የሚሠራ ደረ ገጽ፣ የበጀት ጉድለቶች ሊያስከትሏቸው ከሚችሉ አደጋዎች መካከል የዋጋ ንረት አንዱ ነው ይላል።

የበጀት ጉድለት ከሚያስከትላቸው ቀዳሚ አደጋዎች አንዱ የዋጋ ንረት መሆኑን የሚገልጸው የኢንቨስቶፔዲያ ጽሑፍ፣ የበጀት ጉድለት የዋጋ ጭማሪን ለመግታት እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ያብራራል። የፌዴራል መንግሥት የበጀት ጉድለት ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዲለቅ ሊያደርግ እንደሚችል የሚገልጸው ኢንቨስቶፔዲያ፣ ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚ ሲለቀቅ የዋጋ ግሽበትን እንደሚያባብስ ይተነትናል።

መንግሥት ምን ሊያደርግ ይችላል?
መንግሥት የበጀት ጉድለትን ለመቀነስ የበጀት ፖሊሲውን ተጠቅሞ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስፋፋት የተለያዩ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚችል ጥናቶች ያመላክታሉ። ከዚህ አንጻር መንግሥት የገጠመውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት የተለያዩ የገቢ አማራጮችን እንደሚያሰፋና የግብር ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ አሕመድ ሽዴ ለምክር ቤቱ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ መንግሥት ገቢውን ከማሳደግ በተጓደኝ የበጀት ጉድለትን ለመሙላት የመንግሥት ወጪን መቆጠብ እንደ አማራጭ ሊጠቀም ይችላል።
አገራት የኢኮኖሚ እድገትን የሚያመጡ ፖሊሲዎች በማስተዋወቅ የመንግሥት ወጪን በመቀነስ እና ታክስን በመጨመር የበጀት ጉድለትን መከላከል እንደሚችሉ ጥናቶች ያመላክታሉ። የኢትዮጵያ መንግሥትም የገጠመውን የበጀት ጉድለት አዳዲስ የግብር ስርዓቶችን በመዘርጋትና ቦንድ በመሸጥ የበጀት ጉድለቱን ሊፈታ እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን ይጠቁማሉ።

በገቢ አሰባሰብ እና በሰነድ ገበያ ላይ ያሉ መቀዛቀዞች እንዲሁም ከጸጥታ ጋር ያለው ሁኔታ በአስተማማኝ ካልተፈታ የቀጣይ ዓመት በጀት የሚሞላበትን መንገድ የዋጋ ንረትን ሊያባባስ የሚችል እንደሚሆን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርሄ ( ዶ/ር) ይገልጻሉ። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አክለውም፣ ለሥራ ማስኬጃ፣ ለክልሎች በጀት፣ ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች እና ለሌሎች ሥራ ማስኬጃ እንዲውል ታስቦ የፌዴራል መንግሥት ያሳወቀውን በጀት ተንተርሶ በጀቱ ከባለፈው ዓመት አንጻር እድገት እንዳለው የሚነሳ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት ከ30 በመቶ በላይ በሆነበት በዚህ ወቅት የሚጠበቀውን ለማከናወን ብዙ ለውጥ አይኖረውም ባይ ናቸው።

በሰሜኑ ያለው ጦርነት መፍትሄ የሚያገኝበት እድል ከተፈጠረ ሰብአዊ ድጋፉ ሌሎች አገራት እና የተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች የሚሸፍኑበት እድል ሰፊ በመሆኑ እና መንግሥት ለሰብአዊ ድጋፍ ለመበጀት ያሰበውን ለበጀት ጉድለቱ ማዋል እንደሚችል የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጠቁመዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በተጨማሪ ሌሎች አገራትም ቢሆኑ፣ ከአገር ውስጥ ብድር የሚሞሉበት ሂደት እንዳለ እና የፌዴራል መንግሥትም የቀጣይ ዓመት በጀት ጉድለቱን በብድር የሚሞላበትን ሂደት ቢፈጥርም ጥሩ ነው ባይ ናቸው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አክለውም፣ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ካላገኘ በቀጣይም ቢሆን፣ ዜጎች ይፈናቀላሉ፣ መሠረተ ልማቶች ይፈርሳሉ፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ተረጂዎች ቁጥርም የሚጨምርበት ሂደት እንደሚፈጠር እና መንግሥት በቀጣይም ቢሆን ውጥረት ውስጥ ከመግባት እንደማይላቀቅ አሳስበዋል።

አክለውም፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ከሚሰበስበው ታክስ፣ ርዳታ እና ብድር ለግሉ ሴክተር ተቋማትን በፐርሰንት በመሸጥ ከሚገኘው ገቢ አንፃር የመንግሥትን በጀት በጥሩ ሁኔታ እያቀረበ መሆኑ የሚበረታታ ነው ያሉት ባለሙያው፣ በጀት የሚለቀቅላቸው ተቋማትም በጀቱን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በወቅቱ ኮቪድ-19፣ የሰሜኑ ጦርነት እና የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት መንግሥት አምኗል። ከ2011 እስከ 2013 በጀት ዓመት ድረስ ምጣኔ ሀብቱ በአማካይ በ7.1 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ቢባልም፣ በእቅድ ከተያዘው በታች መሆኑንም መንግሥት አስታውቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች