የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግሥት 114 ባለሀብቶች ጠፍተዋል አለ

1
1675

• በዚህም ክልሉ 100 ሚሊዮን ብር ግብር አጥቷል

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 114 የፕሮጀክት ባለቤቶች መጥፋታቸውን ተከትሎ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር ማጣቱን የክልሉ መንግሥት የገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት የገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመት ቢሮ ኃላፊ አመንቴ ገሽ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በክልሉ በእርሻ፣ በማዕድን እና በሌሎች ኢንቨስትመንቶች ከዘጠኝ መቶ በላይ ፕሮጀክቶች በሥራ ላይ ይገኛሉ።

ከእነዚህ መካከል ከ2010 ጀምሮ እስከ 2014 ባለው ጊዜ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኹለት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በመውሰድ ወደ ሥራ ገብተው የነበሩ 114 የኘሮጀክት ባለቤቶች ጠፍተዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት በክልሉ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት መሥራት አልቻልንም በማለት እና በፍላጎታቸው ሥራ አቁመው መጥፋታቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።

በዚህም ምክንያት የክልሉ መንግሥት ከምርት ግብር፣ ከእርሻ ግብር፣ ከመሬት ኪራይ ግብር ማግኘት የነበረበት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ ግብር አለማግኘቱ እና የክልሉ መንግሥት ያጣውን ግብር ለማስመለስ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ውይይት ተደርጓል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መሬቱን የሚያስተዳድር ከሆነ የክልሉን ግብር እንደሚከፍል ያነሳ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት በክፍያው ቢስማማም ነገር ግን መሬቱ እንዲመለስና ለሌላ ልማት እንዲውል በማሰቡ ተጨማሪ መግባባት ላይ የሚያደርስ ምክክር እንዲደረግ መጠየቁን ኃላፊው አስረድተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለያዩ ወቅቶች የጸጥታ ችግሮች በተፈጠሩበት ወቅት እና በመሠረተ ልማት እጥረት ምክንያት፣ የክልሉ ኢንቨስትመንት በሚጠበቀው ልክ እድገት እያስመዘገበ ነው ለማለት እንደማይቻል ኃላፊው ጠቁመዋል። አሁን ላይ የጸጥታ ለውጦች መምጣታቸውን ተከትሎ፣ በማዕድን እና በእርሻ ዘርፍ የተሻለ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።

በክልሉ በተለይም በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለአርሶ አደሩ ተሞክሮ ከማካፈል ጀምሮ ግብር በአግባቡ በመክፈል የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
አክለውም፣ የክልሉ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ማንኛውንም የፀጥታ ችግር ማረጋጋት እየቻለ በመምጣቱ ባለሀብቶች በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ አስተላልፏል።

በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ሀብት አቅምን በጥናት በመለየት ለክልሉ ብሎም ለኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረውን የክልሉን ኢንቨስትመንት በማስፋፋት እና በማበረታታት የአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን አቅም በማሳደግ እየተሠራ ነው ተብሏል።

ለክልሉ ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ እንዲሁም አሰራሮችን በማዘመን የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተወስቷል።
በተጨማሪ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት መብት ዋስትና በማረጋገጥ ዘርፉ የሚያስገኛቸውን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትሩፋቶችን እውን ለማድረግ እየተሠራ መሆኑም ተነግሯል።

የክልሉ መንግሥት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የገጠር መሬት ቅየሳና ምዝገባ በሰፊው እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ በርካታ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በመስጠት የመሬት ባለቤትነት ዋስትና ለማረጋገጥ መቻሉም ታውቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

አስተያየት

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here