መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛከልካዩ የተገላበጠበት ባንዲራ

ከልካዩ የተገላበጠበት ባንዲራ

ከሠሞኑ መነጋገሪያ ሆነው ከተሰሙ አጀንዳዎች መካከል ብዙዎችን አጀብ ያስባለው “የኦነግ ባንዲራ”ን የተመለከተው የክልከላ ደብዳቤ ቀዳሚው ነበር ማለት ይቻላል። እንደሕዘብ ባንዲራ ተደርጎ ይገለጽ የነበረ፣ እንዲሁም ለረጅም ዓመታትም የትግል ምልክት ተደርጎ ይወሰድ እንደነበረ የሚነገርለት ባንዲራ የአንድ ፓርቲ ነው መባሉ ግራ አጋብቶ ነበር የሰነበተው።

ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ባህል መገለጫ ተደርጎ የሚወሰደው የኦዳ ዛፍ አጠቃቀም ላይ እስከ ክስ የደረሰ ውዝግብ እንደነበር ቢሰማም፣ ይዘቱም ሆነ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ ሳይደረግ ተድበስብሶ የቀረ ነበር። የሰሞኑ ግን ሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩነታቸው ምን እንደሆነ የማይረዳቸው ቡድኖች በባንዲራ ይገባኛል ሳይሆን አይገባህም በሚል በደብዳቤ ተካሰዋል።

የባንዲራው ቀዳሚ ባለቤት ነኝ የሚለው የፖለቲካ ቡድን፣ ባንዲራው የግሌ ስለሆነ የሌላ ፖለቲካ ቡድን አመራርም ሆነ አባል መጠቀም እንዳይችል የሚከለክል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤን ልኳል። የክስ መንደርደሪያ የሆነ የክልከላ ወረቀት የተላከለት አካል እምቢም ይሁን እሺ ስለማለቱ ምንም የተባለ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ ግን ስለሁኔታው ያለውን አስተያየት ባገኘው አጋጣሚ ሰንዝሯል።

አትጠቀሙብን የተባለውን ባንዲራ ከሦስትና አራት ዓመት በፊት በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ይዞ መገኘት በራስ ላይ እንደመፍረድ የሚቆጠርበት ጊዜ ነበር። ባንዲራውን መያዝ የሚከለክለው መንግሥት የነበረው ቡድንና ባለሥልጣናቱ እንጂ፣ ለሥልጣንም ሆነ ለነፃነት እንታገላለን የሚሉ ማናቸውም አካላት እርስ በእርስ ሲከላከሉት አይሰማም ነበር።

በእርግጥ በባንዲራው ባለቤቶች በደል ተፈፅሟል ብሎ የሚያምን የኅብረተሰብ ክፍል ባይወደውም፣ አትጠቀሙ ብሎ በገሐድ ስለመናገሩ ተሰምቶ አይታወቅም። ታዲያ መንግሥት ብቻ ይከለክለው የነበረውን ይህን ባንዲራ፤ ባለቤት ነኝ የሚለው አካል በፊት በፊት የቻለ ሁሉ እንዲይዝለት በነፃም ያደለበት ጊዜ ነበር።

አሁን ግን ጊዜው ተገልብጦ ራሱ ሲያሰራጭና ሲያስተዋውቅ የነበረውን ባንዲራ ሌላ እንዳይጠቀመው እንደቀደመው መንግሥት ከልካይ መሆኑ ብዙ አስብሏል። አንዳንዶች ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀምበት ፓርቲ ቢሮ ውስጥ እንዲገደብና ቀስ በቀስ እንዲከስም ስላሰቡ ነው ቢሉም፣ ሌሎች ደግሞ ለባንዲራው ፍቅር ያለውን ኅብረተሰብ ለማታለል እንዳይጠቀሙበት ነው በሚል የማኅበረሰብ ንቃተ ሕሊና ላይ ያነጣጠረ አስተያየት ሲሰጡ ታይተዋል።

ያም ተባለ ይህ፣ የባንዲራው ውዝግብ ከልካዩን ገልብጦ እንደመጣው፣ ገዳይና ተገዳይንም እንዳያፈራ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ ማስጠንቀቂያም የሰጡ አሉ። አንዳንዶች ደግሞ የክልሎችንም ባንዲራ ለይቶ ለመያዝ ባስቸገረበት በዚህ ወቅት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲህ ዓይነት የባንዲራ ፉክክር ላይ ከገቡ የዋናው ሠንደቅ ዓላማችንን ትኩረት እንዳያደበዝዘው ሲሉ የአገር መገለጫው የቡድን እንዳይሆን ይመክራሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች