በሕገ ወጥ ተግባር ተሳትፈዋል የተባሉ 830 ጫት ላኪዎች ፈቃድ ተሰረዘ

0
2780

በሕገ ወጥ መንገድ ወደተለያዩ አገራት የጫት ምርት የሚልኩ 830 ጫት ላኪ ድርጅቶች ፈቃድ መሰረዙን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የወጪ ምርት ንግድ ዙሪያ የሚደረገው ሕገ ወጥ ንግድ እና የኮንትሮባንድ ሥራን ለመከላከል በኢትዮጵያ የተደነገገውን የንግድ ሕግና ደንብ በመተላለፍ በሚሠሩት ላይ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ መረጃን በማጥራት እና ግብረ ኃይል በማደራጀት ምርቱ በሚወጣባቸው የኢትዮጵያ መውጫ በሮች ወይም በድንበሮች ላይ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ አስተማሪ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል ተብሏል።

ሚኒስቴሩ በጥናቱ ሂደት በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሳትፎ ያላቸው በተለይ ሕጋዊ አሠራርን ወደ ጎን በመተው፣ ለጫት ምርት የላኪነት ንግድ ሥራ ፈቃድ ያላሳደሱ 830 የጫት ምርት ላኪ ድርጅቶች በመገኘታቸው የንግድ ሥራ ፈቃዳቸው መሰረዙን ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ የሆኑ የአዲስ ማለዳ ምንጭ ጠቁመዋል።

ለጫት ምርት የላኪነት ንግድ ሥራ ፈቃድ ያላቸው ቢሆኑም፣ በሕወጥ መንገድ የምርት መላኪያ ፍቃድ ለሦሰተኛ ወገን አሳልፈዉ የሰጡ 40 የጫት ምርት ላኪ ድርጅቶች የንግድ ሥራ ፈቃዳቸው በጊዜያዊነት እንዲታገድ ተደርጓል ተብሏል።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሕገ ወጥነት እየተንስራፋ በመምጣቱ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጪ ምንዛሬ ከማሳጣቱም ባሻገር፣ የአገርን ሀብት ለጎረቤት አገራት ሲሳይ በማድረግ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መገኘቱም ተጠቁሟል።
ችግሩን ከስር መሠረቱ መፍታት እንዲቻል ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የሚወጡ ማናቸውንም የጫት ምርት ዓይነት በየጊዜው በመመዝገብ የመላኪያ ፍቃድ ለመስጠት የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ ዝግጅት መጨረሱን ተናግሯል።

የጫት ምርት ላኪ ድርጅቶች የሚልኩትን የጫት ምርት የግብይት ውል የባንክ የመላኪያ ፍቃድ ከመውሰዳቸው በፊት፣ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በማቅናት እንዲያስመዘግቡ እና ሕጋዊ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ምን ያህል መጠን ያለው የጫት ምርት መጠን እና ወደየት አገራት እየላከች እንደሆነ አዲስ ማለዳ የጠየቀች ቢሆንም፣ ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት በኩል መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም።

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ምንጭ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከጫት ምርት የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እና ሕጋዊ የንግድ ስርዓትን ለማሳለጥ ብዙ ጥረቶች በመደረግ ላይ ነው ተብሏል።
የጫት ምርት በኢትዮጵያ ባለፉት ኹለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋቱ በዓለም ደረጃ ኢትዮጵያን ከፍተኛ አምራች ከሆኑት አገራት ተርታ ያስቀምጣታል።

በአሁኑ ወቅት በሰፊ የመሬት ይዞታ ላይ በብዛት ከሚተከሉ ተክሎች መካከል አንዱ የሆነው ጫት፣ አገሪቱ ለውጪ ገበያ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል አንዱ ነው። በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችም እጅግ ጠቃሚ የገቢ ምንጭ ነው።

ጫት በአብዛኛው የሚመረተው ትንንሽ እርሻዎች ባሏቸው እና ምርታቸውን ለቀጣይ ስርጭት ወይም ለውጪ ገበያ በንግድ ማዕከላት በሚሸጡ ገበሬዎች ነው። የአገር ውስጥ ፍላጎት መኖሩ ከፍተኛ መጠን ያለውን የጫት ምርት በአገሪቱ ውስጥ በጥቅም ላይ እንዲውል ያደረገ ሲሆን፣ ተክሉ ከብዙ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ልምምዶች ጋር በጥልቅ የተሳሰረ መሆኑንም ጥናቶች ያሳያሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here