የጋራው ቤተመንግሥት

በኢትዮጵያ ባለፈው ምዕተ ዓመት ውስጥ ከተገነቡት አራተኛ የሆነው ቤተመንግሥት ግንባታ መጀመሩ እየተነገረ ይገኛል። ከእንጦጦው ቤተመንግሥት ቀጥሎ የተሠራውና አሁንም የመንግሥት መቀመጫ የሆነው የአፄ ምኒልክ ቤተመንግሥት በመባል የሚታወቀው የ4 ኪሎው ግቢ፣ ከሞላ ጎደል ወደ ሙዝየምነት እየተቀየረ ይገኛል። ውስጡ ያሉት በሙሉ ወደ ቅርስነትም ሆነ ወደ ታሪክ ከመቀየራቸው በፊት ግን ቅያሪ ቤተመንግሥት አስፈልጓቸዋል።

የስድስት ኪሎው የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ቤተመንግሥት በንጉሠ ነገሥቱ ፍላጎት ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በተለገሰ ወቅት፣ እንደ አዲስ የሚኖሩበት ቤተመንግሥት ስላስፈለጋቸው፣ እዮቤልዩ ቤተመንግሥት እየተባለ የሚታወቀውን በከፍተኛ ወጪ አስገንብተው ነበር። ይህ ከጊዮን ሆቴል ተጎራብቶ የተሠራውና በተንጣለለ ስፍራ ላይ ያረፈው ቤተመንግሥት ከአቀማመጡ አኳያ ስጋት ላለባቸው ለቅርቦቹ መንግሥታት መቀመጫ መሆን ስላልቻለ ዋናዎቹ ገዢዎች አይቀመጡበትም።

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የፕሬዝዳንቶች መቀመጫ ሆኖ የሚያገለግለው ይህ ቤተመንግሥት፣ አሁን ባዶውን እንደሆነም እየተነገረ ይገኛል። ማን እንደሚኖርበትም ሆነ ለምን ዓይነት አገልግሎት እንደሚውል ሕዝብ መረጃ እንዲኖረው ስለማይደረግ ከነአካቴው እንደሌለም ተደርጎ ይወሰዳል። ታሪካዊነቱም ያን ያህል እምብዛም ስለሆነ ጎብኚዎች ይበልጥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን አልያም የምኒልክ ቤተመንግሥትን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው ነው የሚነገረው። ይህ ግምት ግን እዮቤልዩ ቤተመንግሥቱ እንደሌሎቹ ለጎብኚዎች ክፍት ቢሆን ሊቀየር እንደሚችል መገመት ይቻላል።

እነዚህ ቀደምት ቤተመንግሥቶች አገልግሎት መስጠት ሳያቆሙ፣ አሁን ያለው የብልፅግና መንግሥት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ለሕዝብም ሆነ ለተወካዮች ምክር ቤት ሳያሰማ፣ እንደነፍሰጡር አማረኝም ሳይል አዲስ ቤተመንግሥት እየተገነባ ይገኛል።

በ50 ቢሊዮን ብር ገደማ መገንባት ጀመረ የተባለው አዲሱ ቤተመንግሥት፣ አሁን አገሪቷ ካለችበት አጠቃላይ ችግር አኳያ እጅግ የተጋነነ ቅብጠት ነው በሚል ብዙዎች ሲተቹት ተደምጧል። ቦታው አዲስ አበባ ውስጥ መሆኑ ደግሞ የተባለውን ያህል ሰፊ መሬት እንዴት ሊገኝ ነውም ሲያስብል ነበር። 5 ሺሕ ያህል ነዋሪዎች ለቤተመንግሥቱ ይነሳሉ መባሉም ሌላ መነጋገሪያ የሆነ ጉዳይ ነው።

ቤተመንግሥቱ ይሠራል የተባለው በተለምዶ “የካ ጋራ“ ተብሎ በሚታወቀው፣ በደን ተሸፍኖ በነበረ ከፍታማ ስፍራ ላይ ነው። ቦታው የካ ክፍለ ከተማ ውስጥ ያለ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጀርባ፣ ከቀበናዋ ደብረ እንቁ ልደታ ቤተክርስቲያን በስተምሥራቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በስንት ልፋት የበቀለ ጥቅጥቅ ደን ተመንጥሮም የሚገነባ ነው።

ምን ያህል ሄክታር ላይ እንደሚያርፍም ሆነ መግቢያና መውጫው በየት እንደሆነ ባይታወቅም፣ አስፋልት ሥራው ከቀበና በኩል ተጀምሯል። በፊት ባህር ዛፍ ተቆርጦ ለማመላለሻ እንዲውል ተብሎ አልፎ አልፎ ይጠረግ የነበረ መንገድን ተከትሎ ሰፊ አውራ ጎዳና እየተሠራ ቢሆንም፣ ብዙዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል። በደፈናው ሥራው ተጀምሯል ተብሎ ቢነገርም ቁርጡ እስኪታወቅ አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡ በርካቶች ናቸው።

በቀበና ልደታ ቤተክርስቲያን አድርጎ በተለምዶ ዋሻ ተክለሃይማኖት እየተባለ የሚታወቀውን 1 ሺሕ 600 ዓመት ያስቆጠረውን አፄ ኢዛናና ሳይዛና የተባሉት መንታ ነገሥታት ያሳነፁትን ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍሎ የነበረና በጣሊያን ከፊሉ የወደመውን ጥንታዊ ደብር አቋርጦ ወደ ኮተቤ 02 የሚሄድ በአንቆርጫ የሚያልፍ መንገድ አለ። ይህ መንገድ የ77ቱን ድርቅ ሸሽተው መጥተው ጋራው ላይ የሰፈሩና 37 ዓመት ያህል እያረሱና ከተማ ተመላልሰው እየሠሩ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን ያቋርጣል። ወሎ ሠፈር እየተባለ የሚታወቀው ይህ አካባቢ፣ ለዋሻ ተክለሃይማኖት ቅርብ ከመሆኑ አንፃር ለቤተመንግሥቱም ቅርብ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።

አሁን ቤተመንግሥቱ ይገነባበታል ተብሎ ረጃጅም የብረት አጥር እየቆመበት የሚገኘው ቦታ፣ ወደ ወሎ ሰፈር አቋርጦ ከሚሄደው መንገድ በስተሰሜን ያለ ነው። አጥሩን አሻግረን ስንመለከት ቤላና ፈረንሳይን ጨምሮ ጉራራ የሚባሉት ሰፈሮች ቁልቁል ከጋራው በስተጀርባ የሚታዩበት ነው።

ቀጥ ያለ መስመር የያዘው አጥር መገንባት ገና መጀመሩ ስለሆነ ቤተመንግሥት የተባለው ከአጥሩ ኋላ ይሁን ከአጥሩ ወዲህ ለማወቅ ያስቸግራል። ነባሩ መንገድ እየተሠራ ስለነበርም ሌላ ቅያሪ በጀርባ ያለን መንገድ ተከትለን ወደ ወሎ ሰፈር ስለተጓዝን ሥራውም ገና እየተጀመረ እንደመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ያስቸግራል። ከመንገዱም ሆነ ከአጥሩ ወደ ደቡብ ማለትም ወደ መዲናዋ መሀል አቅጣጫ ያለ ሰፊ ደን የነበረ ቦታ መጨረሻውን መለየት እስኪያስቸግር ድረስ እየታረሰ በደረጃ መልክ ሲቆፈር ተመልክተናል።

በቀናት ልዩነት ወደ ቦታው ድጋሚ ስናመራም ከ12 ሰዓት በኋላ ጭምር እስኪጨልም ግንባታውና የመሬት ጠረጋው ያለማቋረጥ ሲካሄድ መመልከት ይቻላል። ይህ ሁሉ ጥድፊያ ለምንድን ነው እስኪያስብለን ድረስ በዘመቻ መልክ እንዲህ ሲያፋጥኑት ማየት ይገርማል።
ቦታውን ከልጅነት ጀምሮ በተደጋጋሚ ለሚያውቀው የተጨፈጨፈው ደን ብዛት እጅግ ያሳዝናል። እሱን የሚተካ ምን ሊደረግ ነው ብሎ ለመጠየቅም፣ የነበረውን ማስታወሻ ምስል ስለመቅረት አለመቅረቱ ማወቅ አይቻልም። ጥቂት የሚባሉ አበባዎችና ዛፎች ተተክለዋል፣ የተወሰኑም ተደርድረው ተመልክተናል። ቦታውን ማልማቱ በጎ ሐሳብ ቢሆንም ተፈጥሯዊነቱን ሳይለውጥ በጥቂት ደቂቃ ያለምንም ችግር የሚደረስበት ቦታ መሆኑን እንዳያሳጣው የብዙዎቻችን ስጋት ነው።

መንገድ መሠራቱን ማንም የሚቃወመው ባይኖርም፣ ለዓመታት ከኖሩበት ቦታ መነሳቱ ግን ግርታን የፈጠረ ነው። አንዳንዶች ከጅብ ጋር እየተጋፋን ከተማ ከምንመላለስና ለማምሸትም ሆነ ማልደን ለመውጣት ከምንሰጋ ወደ መሃል ከተማ መቅረባችን ሊጠቅመን ይችላል ሲሉ ይናገራሉ። የት ቦታ ቅያሪ እንደሚሰጣቸው ባለማወቃቸው ግን ቦታው የባሰ እንዳይሆንና ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ እንዳይሆን የሚል ስጋትም ገብቷቸዋል።

ስለተነሺዎቹ ያለ ምልከታ እንደሚነሱት ሰዎች ብዛትና አስተሳሰብ የተለያየ ቢሆንም፣ ቤተመንግሥት መገንባቱ ያሳሰባቸው ግን ነዋሪዎቹ ብቻ አይደሉም። ይገነባበታል የተባለው ቦታ ታሪካዊነት፣ ሃይማኖታዊ ቅርስነትና አቋርጦ የሚያልፈውና የሚወስደው ቦታ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮችን ይበልጥ እንዳሳሰበ ይሰማል።

ስለኅብረተሰቡ ስጋትም ሆነ ጥያቄ መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ፣ “ንቆ ትቶታል” በማለት ምንም ምላሽ አለመሰጠቱን እንደተጨማሪ ስጋት አድርገው የሚያዩትም አሉ። የቤተመንግሥት ግንባታ ምስጢራዊ ስለሆነ ሕዝብ ዝርዝር መረጃውን ማወቅ አይገባውም ቢባል እንኳን፣ መሠረታዊ የሆኑ መረጃዎችን የተወሰነው ስጋት ያለበት የማኅበረሰብ ክፍል ማወቅ ይፈልጋል።

ሌላው ቅርስን በተመለከተ ስጋት ያሳደረው ለገንቢዎቹ እቃ ማከማቻና ማረፊያ ተብሎ የተገነባ ካምፕ አቅራቢያ የሚገኝን ጥንታዊ ፍርስራሽን የተመለከተ ነው። ቦታው በተለምዶ የጣሊያን ግንብ እየተባለ የሚታወቅና አልፎ አልፎ ወታደሮች በካምፕነት የሚጠቀሙበት ቦታ አቅራቢያ የሚገኝ ነው። ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመግዛት አስበው በከተማዋ በቆዩባት ጊዜያት ለጥበቃ ማማነት ያሠሩትና በከፊል ቆሞ የሚገኘው ፍርስራሽ ከጥንቱ ፍርስራሽ የሚለይ ነው።

የጥንቱን ፍርስራሽ ድንጋይ እያነሱ እላዩ ላይ ሌላ ስለገነቡበት ታሪኩም ሆነ ቅርሱ አንዲፋለስ አድርጓል። ጥንታዊውና ከስር ያለው ቅርስ የቤተመንግሥትና የቤተክርስቲያን ፍርስራሽ እንደሆነና በግራኝ አህመድ ዘመን የፈራረሰ እንደሆነ ታሪኩን የሚያውቁት ይናገራሉ። ስለጥንት ኢትዮጵያውያን ግንባታ የሚያውቅም ከጣሊያኖች አገነባብ የሚለይበትንም ሆነ ከነአፄ ፋሲለደስ ቤተመንግሥት የሚያመሳስለውን መመልከት ይችላል።

- ይከተሉን -Social Media

ይህ ጥንታዊ ቅርስ በመንግሥት በኩልም ሆነ በተለያዩ አካላት ትኩረት ተነፍጎት የቆየ ነው። በአንድ ወቅት የዘርፉ ባለሥልጣን ተጠይቀው፤ ‹እኛ የምናጠናውና በቅርስነት የምንፈርጀው ዝም ብለን አይደለም› በማለት ጥያቄ ቀርቦ ከገመገምነው በኋላ ነው ቢሉም፣ ያኔ ከቀረበላቸው ጊዜ በኋላም እስከ አሁን ምንም ዓይነት ጥናትም ሆነ ቁፋሮ አለማድረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በሌላ በኩል፣ ጥንት የተቀበረ ታቦት አለበት በማለት የቦታውን አወዛጋቢነት በማንሳት የሰሙትን አፈታሪክ በመናገር አካባቢው ላይ የግንባታም ሆነ የምርምር ቁፋሮ ማድረግ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ሐሳባቸውን የሰነዘሩም አሉ።
አሁን ቤተመንግሥት የሚሠራበትንም ሆነ ስለአካባቢው ፓርክ የሚገልፅ ካርታ መሳይ ጠቋሚ ታፔላ በቀበና በኩል ተሰቅሎ ቢታይም ለመረዳትም ሆነ ኅብረተሰቡ ተመልክቶ ለመገንዘብ አዳጋች ነው።

ለቤተመንግሥት ቦታ ሲመረጥ፣ ጠላት ቢመጣ ተብሎ ከሩቅ የሚታይበት ከፍታማ ቦታ አሊያም በጥልቅ ውሃ የተከበበ ማድረግ የተለመደ ነው። የጋራው ቤተመንግሥት የተመረጠበትን እርግጠኛ ምክንያት ማወቅ ባይቻልም፣ መገመት ግን ይቻላል።

በነዋሪ ያልተያዘ ሰፊ ቦታ መኖሩ፤ ጫካ መሃል መሆኑና በአንፃራዊነት ከፍታማ ቦታ መሆኑ ሊጠቀስ ይችላል። የሕዝብ አመፅ ቢነሳ ራቅ ብሎ ለማምለጥም ሆነ ለመከላከል እንዲመችም ታስቦ ይሆናል የሚሉ አሉ። የተለያዩ አማራጭ ማምለጫ መንገዶች በሌሉበት የስርቆሽ ማለፊያም ለማዘጋጀት በሚያስቸግርበት ሁኔታ፣ እንዲሁም ባለጉዳዮችና እንግዶች በሚቸገሩበትና በሚለዩበት አኳኋን ቦታውን መነጠሉም ተገቢ አይደለም የሚሉም ተደምጠዋል።

በአጠቃላይ፣ ለሕዝብ መረጃው ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ ቤተመንግሥቱ ይሠራበታል የተባለው ቦታም ሆነ ወጪ፣ ድጋፍም ሆነ ትችትን አስተናግዷል። በበርካቶች ለወደፊት ይመጣል ተብሎ ከጥንት ጀምሮ እንደተተነበየለት የሚነገርለት ቴዎድሮስ የሚባለው ንጉሥ፣ አገሪቷን በብረት በትር ቀጥ አድርጎ ይገዛበታል የተባለ ቦታ ላይ በብልፅግና መንግሥት ቤተመንግሥት መገንባቱ ብዙዎችን አስገርሟል።

“የተነገረልኝ እኔ ነኝ” ለማለት ይሁን ወይስ ደጃች ውቤ ደረስጌ ማርያምን ለመንገሻቸው አዘጋጅተው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እንደነገሡበት ታሪክ፣ የአሁኑም መንግሥት አዘጋጅቶ ለመጠበቅ ይሁን ባይታወቅም፣ እውነታው ያስገረማቸው መጨረሻውን ለማየት መጓጓታቸውን ይናገራሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች