“ብርሃን ስታይ ተከተል፤ ወደ ጨለማ እንዳይወስድህ መርምር”

0
897

ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (አአዩ) የፍልስፍና መምህር ናቸው። ውልደታቸው ደሴ ይሁን እንጂ ዕድገታቸው አዲስ አበባ ነው። የአንደኛ እና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ በወቅቱ የነበረውን የቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አሁን አአዩ) ለከፍተኛ ትምህርት ተቀላቅለው ለአንድ ዓመት ተከታትለዋል። በወቅቱ በነበረው የተማሪ እንቅስቃሴ ውስጥም ተሳታፊ ነበሩ።

የመጀመሪያ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወደ ሰሜን አሜሪካ በማምራት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የማስትርስና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከቦስተን ኮሚውኒቲ ኮሌጅ በፍልስፍና አግኝተዋል።

በአሜሪካ ቆይታቸው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፍልስፍናን ያስተማሩት ዳኛቸው፥ ከ12 ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚወዱትን የማስተማር ሥራቸውን ቀጥለዋል።

ከብዙዎቹ የአገራችን ምሁራን በተለየ ዳኛቸው፥ ሐሳባቸውን አደርጅተው እና በድፍረት በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም በተገኙባቸው ሕዝባዊ መድረኮች ላይ በመንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ በይበልጥ ይታወቃሉ።

ከአራት ዓመት በፊት ትችታቸው ያልወደዱት የወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ከነበሩት አድማሱ ፀጋዬ (ፕሮፌሰር) በተጻፈ ደብዳቤ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር ከነበሩት መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ጋር መባረራቸውን ያስታወሱት ዳኛቸው፥ “በወቅቱ ከምወደው ሥራዬ በመሰናበቴ በጣም አዝኜ ነበር” ብለዋል።

ይሁንና ከዩኒቨርሲቲው መባረራቸው በጎ ዕድልን ይዞላቸው እንደመጣም ይናገራሉ። “ተጋባዥ መምህር በመሆን በ14 ዩኒቨርሲቲዎች ተዘዋውሬ አስተምሬያለሁ” የሚሉት ዳኛቸው፥ አንዳንድ ወዳጆቻቸው ሲቀልዱባቸው “ልክ እንደጠበል ተረጨኽ” ይሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ዳኛቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት ደስተኛ እንደሆኑና ለውጥንም እንዳዩ በግልጽ ይናገራሉ። “ዐቢይ ወደምወደው የቀደመ ሥራዬ ስለመለሱኝ ባለውለታዬ ናቸው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩን አወድሰዋቸዋል።

ከአዲሶቹ የመንግሥት ሹማምንት ጋር ያላቸውን ቅርበት በተመለከተ ለሚተቿቸው “አሸናፊ ሆኑ [ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ] ብዬ ከውጪ ተመልክቼ አላውቅም። ከዐቢይ በፊት ከሕወሓት ጋር ስታገል የቆየሁ ሰው ነኝ። ልታሰርም እችል ነበር፤ ጽሑፎቼን ማየት ይቻላል” የሚሉት ዳኛቸው ሹመት እንደማይፈልጉ ሲገልጹም “ባጣ ባጣ የአንድ አፍሪካ አገር አምባሳደር መሆን አላጣም፤ አልፈልገውም እንጂ። ተማሪዎቼ ተሹመውልኛል” ብለዋል።

ዳኛቸው አራት ወንድምና ኹለት እህት ሲኖራቸው አንድ ወንድምና አንድ እህታቸውን በሞት ተነጥቀዋል፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና አቋማቸው ተቃራኒ የሆኑት የቀድሞዋ የትምህርት ሚኒስትር በኋላም አምባሳደር ገነት ዘውዴ (ዶ/ር) ወንድምም ናቸው።

ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት የሆኑት ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) በተለይ የኢሕአዴግን ውሕድ ፓርቲ (“የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ”) ሆኖ መምጣት በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ በሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም በአገር ደረጃ ሊኖረው የሚችለውን አንድምታ በተመለከተ ከአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አዲስ ማለዳ፡ ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ወጥ ፓርቲነት መዋሐድ ያለው አንድምታ ምንድን ነው?
ዶክተር ዳኛቸው፡ ውሕደቱ አዲስ ሐሳብ አይደለም። የዛሬ 20 ዓመት ገደማ እነ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ አንድ ጉባዔ አዘጋጅተው፥ እዛ ላይ በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትልቁ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሐንቲገተን መጥቶ ነበር፤ እርሱም የመከረው ይህንን ነው። ወደ አንድነታችሁ ብትሔዱ፤ ለዲሞክራሲውም ሲባል ግንባሩ አንድ ፓርቲ ቢሆን ጥሩ ነው ብሎ ነበር።

በአንድ አቅጣጫ ከሕወሓት ክፍፍል በፊት [ከ1993] ይህ ጉዳይ ተነስቶ ነበር። ነገር ግን ክፍፍሉና ጠቡ መጣና የመለስ ቡድን አሸንፎ ከወጣ በኋላ በመድከማቸው፤ በዛው ቀጠሉ።

አንድ ወጥ ፓርቲ መሆናቸው ጥሩ ነገር ይመስለኛል፤ የብሔር እና የነገድ አካሔድን ትንሽ ይገታዋል ብዬ እገምታለሁ። አንድ ማረሚያና የሚያርቅ ጥሩ መንገድ ይመስለኛል። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ነገር ሲያደርግ ለወገኑ አገዘ አይባልም፤ ከውህደቱ በኋላ ግን ፓርቲው ነው ይባላል። ወደ ኢትዮጵያ አንድነት የሚደረግ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ነው፤ የእነርሱን አንድ መሆን በበጎ ነው የማየው። እንዴት አድርገው ውሕደቱን እንደሚያደርጉት ግን የምናየው ይሆናል። ያጣነውን ኢትዮጵያዊነት መልሰን የምናገኝበት አንድ መሠረታዊ መንገድ ነው።

በኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል መዘላለፎች ታይተዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም አለመቀበል አዝማሚያ ታይቷል። ይህ ወደ ውሕደት የመምጣትን ነገር አጠራጣሪ አድርጎት ነበር። ይህ መሆኑ ምን የሚያስከትል ይመስልዎታል?
የውሕደቱ ትልቁ መሰናክል የሕወሓት ነው። [ይሁንና] ሔዶ ሔዶ አዲስ የአመራር ትውልድ ከሕወሓትም ሆነ በአካባቢው ይወጣል የሚል እምነት አለኝ። አሁን የያዙት መንገድ የሚያዋጣም አይደለም። የትግራይን ሕዝብና ሕወሓትን ለይቶ ማየት ያስፈልጋል። እኔ ደጋግሜ እንደተናገርኩት የትግራይ ሕዝብ መምረጥ ካለበት ኢትዮጵያዊነቱን ያስቀድማል የሚል አቋም አለኝ። ሕወሓት ግን የሚተባበር ኀይል አይደለም። ከወልቃይትና ከራያ በቀር ኢትዮጵያ ውስጥ በተነሱ ጥያቄዎች ጀርባ ሕወሓት አለበት፤ ይህ ማለት ግን ጥያቄዎቹ ትክክል አይደሉም ማለት አይደለም። [ሕወሓቶች] ሁሉም ቦታ ገመድ እየሳቡ ነው።

ይህንን የማፍረስ ሥራ ትተው ቢተባበሩ፤ እኛኮ የጥፋት ኀይል ብቻ አይደለምን እንዲህ አድርገናል ብለው ሊከራከሩ የሚችሉባቸው ጉዳዮች አሏቸው። ይሁንና እዚህ ውሕደት ላይ በሥነ ልቦና እንኳን የተዘጋጁ አልመሰለኝም። በመጀመሪያም የፌደራል መንግሥቱን የተቀበሉ አልመሰለኝም። እንደ አንድ ነጻ የሆነ [አገር] እየመሩ ነው ያሉት።

ኹለተኛ አሁን ምርጫ ምርጫ ይላሉ፤ ግን ለምርጫ የሚሆን ከባቢ አይፈቅዱም። ምርጫ ማለት ጠዋት 12 ተከፍቶ 2 ሰዓት ሲዘጋ ሳይሆን ሙሉው የፖለቲካ ሒደት ነው። ምርጫ የማይፈልግ ፓርቲ ምርጫ መደረግ አለበት እያለ መጮኹ ይገርማል። ለጥያቄውም ትብብር ያሳያሉ የሚል እምነት የለኝም።

የሕወሓት አለመተባበር ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ምን ያህል ተግዳሮት ይሆናል?
የምናወራው ስለ ትልቅ ክፍፍል ነው። ትግራይ ውስጥ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚወጡ ፓርቲዎች ቢወጡ ከእነርሱ ጋር ውሕደት መፍጠር ይቻላል። የትግራይ ሁኔታ አሳሳቢ ነው፤ በጣም በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ነው። እንደ ግብጽ ዓይነት አገራትም እዚህ ላይ ነው የሚያነፈንፉት። ሕወሓት ራሳቸውን አድሰው በአዲስ ትውልድ የሚመጡ ይመስለኛል፤ ግን ትንሽ ጊዜ ይፈጃል። ጦርነት መቼስ የሚታሰብ አይደለም።

የኢሕአዴግ መዋሐድ የብሔርና ጎሳን ፖለቲካ ያበርደዋል ብለዋል። አንዳንዶች ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ አሰላለፍ ይወስናል እያሉ ነው። ይህን እንዴት ያዩታል?
ባለፉት 27/28 ዓመታት የፖለቲካ ማዕከሉ የያዘው አካሔድ የነገድና የጎሳን ስብስብ የሚያበረታታ ነው። በብሔር፣ በጎሳ፣ በነገድ መደራጀትን የፈቀደ ነው። አሁን በአንጻሩ ሕብረ ብሔራዊ ሆኗል። ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ችግር እንደ ገጠማቸው ምክንያቱን ማከም የሚያበረታታው ሌላ ነገር ነው። ወደ ሕብረ ብሔራዊ ሲሆን ወደዛ የሚፈስ ነገር ይኖራል። አሁን ችግር የሚፈጥርባቸው የነገድና ጎሳ ፓርቲዎች ናቸው።

አሁን የተጀመረው ወሳኝ አካሔድ ነው። ብዙ ሰዎች የሰው ለውጥ ነው እንጂ የስርዓት ለውጥ የለም ሲሉ ነበር፤ ይሄ እንደውም ቀድሞ መጣ ማለት ነው። በኢሕአዴግ አሁን መዋቅራዊ ለውጥ እየመጣ ነው። ለኢትዮጵያዊ አንድነት ለሚለው ኀይል ይሔ ትልቅ አሸናፊነት ነው።

አብሮ ይዞት የሚመጣው የፖለቲካ አሰላለፉ እንዴት ሊሆን ይችላል?
ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አለ። ሁላችንም አንድ ወጥ መንገድ እንይዛለን ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። አሁን ለእንደዚህ ዓይነት ፍጥጫ ገላጋዩ ዴሞክራሲ ነው። ሁሉም መድረክ ይሰጣቸዋል። አብንም ኦነግም ሌሎቹም የነገድና የጎሳ የበላይነት [አለ] ብለው ለሚነሱትም ማለት ነው። ምኅዳሩ በጣም መስፋት አለበት። የመናገር ነጻነት ይኑር፤ እንደፈለጉ ፕሮፓጋንዳ ያቅርቡ። እነርሱ ልክ አይደሉም ብሎ ሌላ ዓይነት ጫና ውስጥ መግባት የለብንም። ሁሉም ሕግ እስካልጣሱ ድረስ ይንቀሳቀሱ፤ ውጥረቱ ጥሩ ነው።

ለምሳሌ የአብን መኖር እንደ አዴፓ ዓይነቱን እንዳያንቀላፋ፣ የኦነግ መኖር ኦዴፓ እንዳይተኛ ያደርጋል። ይህም ሞራል ለመሆን ተጨማሪ ግብዓት ይሆናል። ስለዚህ ይህን እንደ ችግር አላየውም። ዋናው መያዝ ያለብን ነገር ግን ትክክለኛ ነን በሚል የሌሎች ድምጽ ማፈን የለብንም። ከዛ ወደ ምርጫ ሔዶ ሕዝቡ የፈለገውን ይምረጥ። በጠረጴዛ ዙሪያ ይህን መርጠናል ብለን የምንጫነው አይደለም።

ለምሳሌ የሕብረ ብሔራዊ ነገር ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ነው። ሌሎች ኀይሎች ደግሞ አሉ። የማንነት ፖለቲካውም የራሱ ምክንያት አለው የሚል እምነት አለኝ። በዓለም እንደተደረሰበትና ፍራንሲስ ፉክያማም በመጽሐፉ ሊበራሊዝ ሊያቀርብ ባልቻለው ነገር ላይ ነው የማንነት ፖለቲካ የመጣው፤ አብርሆቱ (ኢንላይትመንቱ) ሊሸከመው አልቻለም። አብርሆቱ የሚያወራው ስለኢኮኖሚ ብልጽግና፣ ስለሰዎች ነጻነት፣ ስለሕዝብና ስለዜግነት ነው። ስለማንነት ምንም አይልም። በኋላ የማገናዘብ ነገር መጣ፤ እኔ እንደ አንድ ነገድ ተበድያለሁ፤ እውቅና አልተሰጠኝም። ይሔን ሊበራሊዝም ሊያስተናግደው ስላልቻለ አውሮፓም ካናዳም አሜሪካም አገር የፈነዳ ነው፤ እኛም አገር እንደዛው ነው። እናም ውጥረት መኖሩ ጥሩ ነው።

የጎሳ ፖርቲዎቹ ከሕወሓት ጋር ቢሰለፉ ለአገሪቱ ጥሩ ነው። ተፎካካሪነት ይጨምራል፤ ተገዳዳሪ ሆኖ የመውጣት ነገርም ሊያመጣ ይችላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሸገር ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተደጋጋሚ መደመርና ብልጽግናን ሲያነሱ ነበር። ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አንጻር መደመርን እንዴት ያዩታል?
አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው የምንከተለው ነበር የተባለው፤ ግን ግልጽ የሆነ ጽሑፍ አግኝቼ አላውቅም። አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንደ አያ ድቡልቡሌ ነገር ነው፤ በተፈለገ ጊዜ የሚጠቀሙበት ስንል አንዳንዴ እንቀላለዳለን። አንዳንዶችም አብዮታዊም አይደለም፤ ዲሞክራሲያዊም አይደለም ይላሉ።
የዐቢይ መደመርና ፍልስፍና ብልጽግና የሚለው ነገር፤ መቼም አንድ ፓርቲ የሆነ አቅጣጫ ይዞ ይመጣል? እኔ ገና አላጠናሁትም።

ስለመደመር የጻፉትን መጽሐፍ አንብቤአለሁ፤ ግን ያለኝን ለራሳቸው ለመንገር ስላሰብኩ ብዙ ለማውራት አልፈቅድም። መጽሐፉ ተሰጥቶኝ በጥሞና አንብቤዋለሁ። መጽሐፉ በጣም የሚስብ ነው። እንደውም ካነበብኩት በኋላ በስልክ ዊልያም ጀምስ የሚባል ሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ያስተምር የነበረ ፈላስፋ፤ የሐርቫርድን የፍልስፍና የዶክትሬት ጥናታዊ ጽሑፍ (ፒኤችዲ ዲዘርቴሽን) ባነበብኩ ቁጥር ብዙ ይህቺ አገር ብዙ ገበሬ እንዳጣች አውቄአለሁ ብሏል አልኳቸው። እያለ ያለው ነገር ወደ ፍልስፍና መግባት የሌለባቸው ሰዎች ገብተው ፒኤችዲ አገኙ ነው። የእርሶን መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ ይህቺ አገር ጥሩ ፕሮፌሰር አጣች ብያቸዋለሁ።
ሌላ ደግሞ አንድ መፈክር ነው ያለኝ፤ ብርሃን ስታይ ተከተል፤ ወደ ጨለማ እንዳይወስድህ አደራህን መርምር። ይሔን የወሰድኩት ከመቶ ዓመት በፊት አንድ ታላቅ ሰው ከተናገሩት የተማርኩት ነው። ብርሃን ሳይ መከተል ብቻ አይደለም፤ ወደ ጨለማ እንዳንሔድ የመመርመር አቅም አለን ብዬ እገምታለሁ።

ይህ የመደመር ፍልስፍና ወዴት ይወስደናል?
እንደፍልስፍና ተማሪ አንድ አቅጣጫ አይመቸኝም፤ ትናንት አብዮታዊ ዴሞክራሲ፥ ዛሬ ደግሞ መደመር።
በፍልስፍና ‘ሞኒዝም’ የሚባል ነገር አለ፤ ይህም አሃዳዊ አስተሳሰብ ነው። ይህ ደግሞ ከፕሌቶ ጋር ያያይዙታል። አንድ ትክክለኛ ጥያቄ አለ፤ አንድ መልስ አለ። ዴሞክራሲ አብዝሃ (ፕሉራሊዝም) ላይ ነው፤ አንድ ትክክለኛ ጥያቄና አንድ መልስ የለም። ትላንት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ታንቀን እንደነበር፤ አሁንም ቀጣይ ኻያ ዓመት በመደመር እንድንታነቅ አልፈልግም። ኻያ ዓመት እኖራለሁ ማለት ግን አይደለም። እናም ኻያ ዓመት ስል ለወጣቶች ማለቴ ነው። አንድ ነገር ብቻ ተጭኖ የዛ ተጽዕኖ መኖር የለበትም፤ ገና ደግሞ ይፈተሻል። አሃዳዊ አካሔድ ጥሩ አይደለም።

ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ ለውጦች ሲመጡ አገረ መንግሥትም ይወድቃል። የገዢው ግንባር ወደ ፓርቲነት መለወጥ የአገረ መንግሥቱ ህልውና ላይ ሥጋት አይፈጥርም?
ችግር የሚያመጣ አይመስለኝም። መሪ ሲወድቅ ስርዓት የሚወድቀው ተቋማዊ አሠራር አልነበረም ማለት ነው። ለምሳሌ ሠራዊቱን ውሰድ፤ መከላከያንም ውሰድ፣ ረጅም ጊዜ የተገነባ ተቋም ነው። ትልቅ የኢትዮጵያዊነት ዋልታ ነው። ባለፈው ያቀረብኩት አንድ ወረቀት ላይ አገሪቱ በመደብ ትግል ስትናወጥ ወታደሩ አንድነት ኀይል ሆኖ ሲዋደቅ ነበር። አሁን አገሪቱ በነገድና ጎሳ ስትናወጥ ይሔው ተቋም ኢትጵያዊነቱን ይዞ ነው ያለው።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይህን ንግግሬን ሰምተው ትክክል ነህ፤ ኢትዮጵያ ሠራዊቷ ዋልታዋና ዋናው ምሰሶ ነው። ግን አንድ ነገር ረሳህ አሉኝ። ምንድን ነው የረሳሁት፤ አርሶ አደሩን ረስተሃል፤ ኢትዮጵያ የቆመችው በወታደሯና አርሶ አደሯ ነው። እኛ እናወራልን አርሶ አደሩ ግን ተስተጓጉሎ አያውቅም። ይህ የወደድኩት እርማት ነው።
ስለዚህ ፓርቲ ተዋሐደ፣ እንዲህ ሆነ እንዲያ ሆነ፤ እንደተቋም ጠንካራ ስለሆነና አብሮ ዥዋዥዌ ስለማይል አንዱ ተስፋዬ እሱ ነው። እንደውም ህልውናው ይጠናከራል ብዬ ነው የማምነው።

እና በእንግሊዝ አገር ኹለቱን ስርዓት ላለመጣል ሰር እና ሎርድ ይላሉ፤ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን፣ ሰር አይዛክ ኒውተንን ማንሳት ይቻላል። ለይተው ቁጭ ብለዋል። በትውልድ ያገኘው እንዳይከፋው ‘ሎርድ’፤ በሥራ ያገኘውም እንዳይከፋው ‘ሰር’። እናም ስለዐቢይ የመደመር ፍልስፍና ክፍት ሆኖ እንደምንወያይበት ተስፋ አደርጋለሁ።

ከሕገ መንግሥት አንጻር የፓርቲው መለወጥ ያለው አንድምታ?
ሲጀመር ሕገ መንግሥቱ ውል (ኮንትራት) ነው፤ በመንግሥትና በዜጎች መካከል የሚደረግ ነው። እኛ ጋር ግን ዜጎች ሳይሆን እኛ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው የሚለው። ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ኹለት ሦስት ቦታ ዜግነት የሚለው ቃል አለ፤ የውጪ ዜጋ ያገባ ኢትዮጰያዊነቱ አይገፈፍም የሚልና ሌላ ከውጪ ጋር የሚገናኝ ቦታ ላይ ተጠቅሷል።

መንግሥት እኛን የሚያውቀን እንደዜጋ አይደለም፤ እንደብሔር፣ እንደነገድ ነው። ለዚህ ነው የማስወጣት/የማፈናቀል ነገር የመጣው። የሚያስወጡ ሰዎችም ሕገ መንግሥታዊ መሠረት አላቸው፤ ምክንያቱም ዜጋ አይደለንም።

እና የሕገ መንንግሥት መሻሻል መኖሩ ጥርጥር የለውም። መሻሻል ያለባቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። አሜሪካውያንም እያሻሻሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በሽግግር ላይ ነች ይባላል፤ አሁን ደግሞ ገዢው ግንባር ተዋሕዶ ወደ ፓርቲነት ራሱን ሊለውጥ ነው። ይህ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ከመወሰን አንጻር እንዴት ይታያል?
አሁን ለየት ያለ መንፈስ እየመጣ ነው። ለሩብ ምዕት ዓመት ሲወስኑ የነበሩት አንዲት ከተማ መሽገው ተቀምጠዋል። በአንጻሩ አሁን ወጣቶች መጥተዋል። በሰላምና በበጎ መንገዱን ይዞ ቢሔድ ጥሩ ይመስለኛል። ካልሆነ ኢትዮጵያ ከአሁን ወዲህ ምንም ዓይነት ግጭት የምትሸከምበት ትከሻ ያላት አይመስለኝም፤ በጣም አደገኛ ነው። አዳዲስ ተጠሪ ነን የሚሉ አሉ፤ ተልዕኳቸው አንዳንዴ አደገኛ ነው። ተረጋግቶ መነጋገር ያስፈልገናል፤ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ኀላፊነት ስላለብን።

እነዚህ ‘በጎ ፈንድ ሚ’ (በድረ ገጽ ገንዘብ በሚሰበሰብ ድጋፍ) የሚጽፉ ዳያስፖራዎች ግጭት ነው የሚሸጡት። ዐሥር ሰው ከሞተ መቶ ሰው ሞተ ይላሉ። ከራማቸው ሞቅ ሲል ገበያቸው ሞቅ ይላል፤ በጣም ያሳዝናሉ። እንዴት ወሬ እየሸጥክ ትኖራለህ? ሰው ተወልዶ፣ አድጎ ዕድሜ ልኩን ሐሜት የሚሸጥ!?
ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ አላት ብዬ ነው የምገምተው። ብዙ መንገድ መጥታለች፤ ሽግግሩ ከደርግ የጀመረ ነው። ያኔ ጀምሮ መንገድ እየፈለገ ሲቃጠል ሰብሰብ እያልን፤ ሲያንሸራትተን ሰብሰብ እያልን። የዴሞክራሲ ባሕላችንን እናበለጽጋለን። ሌላው የሚያስፈልገው የመሪዎች ፍላጎት ነው። እኔ ፍላጎት ያለ ይመስለኛል። መጀመሪያ እንዳልኩት ብርሃን ስታይ ተከተል፤ ወደ ጨለማ እንዳይወስድህ መርምር ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here