“አገር በቀል” የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወይስ “የዋሽንግተን ስምምነት” በሽታውን ያልተናገረ መድኀኒት አያገኝም

0
1225

ይህ ጽሑፌ የመንግሥትን ስህተት ነቅሶ ነጋሪና ከአገራችን ብሔራዊ ጥቅምጋ ወጋኝ እንጂ መንግሥቴ ተቃዋሚ ወይም ጠላት አድረጎ እንደማያስወስደኝ ተስፋዬ ነው። ዕውቁ ምሁራችን ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የዛሬ 100 ዓመት ግድም እንዳለው “መንግሥቱን የሚወድ ሰው ያ ቅዱስ ቅዱስ የሚለው አይደለም፥ ጥፋቱን የሚገልፅለት እንጂ።“

 

 

1. “አገር-በቀል” የተባለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲን በጥልቀት ለመረመረው፣ “ዋሽንግተን-በቀል” እንጂ በፍፁም አገር-በቀል አይመስልም። እንዴት? ምክንያቱም ለታዳጊ አገሮች ከተዘጋጁትና ገበያችሁን ለኛ ክፈቱልን፣ ንብረቶቻችሁንም እኛ እንግዛቸው ከሚሉትና ዋሽንግተን ከተማ ዋና መሥርያ ቤታቸው ከሆነው የምዕራብ አገር ዋንኛ ጥቅም አሰከባሪ ከሆኑ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ፕሮግራም መመሪያዎች ጋር በጣም ተመሳሳይ ስለሆነና ከዛም የተቀዳ ስለሚመስል ነው (ለአብነትም “IMF Pamphlet No. 47, 2019”ን ይመልከቱ)።

ፖሊሲው አገር-በቀል እንዳልሆነ ማሳያው የኢትዮጵያን እውነተኛ የኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምን እንደሆኑ ከመረዳት አይጀምርም። በዚህ ምክንያት በፖሊሲው ውስጥ ያለው የችግሮቻችን ግምገማ እና የምርመራው ውጤት በመሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ጉዳይ ይልቅ የእነዚህ “የዋሽንግተን ድርጅቶች ስምምነት” በሚባለው የፖለሲ አቅጣጫ ላይ የተመሠረተ ነው።

ይህም ማለት፤ በመጀመሪያ፣ የእስከዛሬው የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ ምን ነበር የሚለው የሰነዱ ትንታኔ አሳሳች ነው። ምክንያቱም የዕድገቱ አብዛኛው ምንጭ የካፒታል ክምችት ነው ይላል (በመሆኑም ከ10 በመቶ ዕድገት ውስጥ የካፒታል ማከማቸቱ ድርሻ 5.6 በመቶ ነው፣ ቴክኖሎጂ ወይም ምርታማነትን ማሳለጥ በ 2.6 በመቶ ይከተለዋል)። ሃቁ ግን የካፒታል አስተዋፅዖ 1.6 በመቶ ብቻ ሲሆን የሠራተኛው አስተዋፅዖ 2.4 በመቶ እና የቴክኖሎጂ/ምርታማነት ማሳለጡ ከ1 በመቶ የማይበልጥ እንደነበረ እናውቃለን። የቴክኖሎጂ አስተዋፅዖ፣ እንኳን እኛ አገር የአደጉ አገሮችም ቢሆን ወደ 2 በመቶ ያህል ነው። ይህ የተሳሳተ የመንግሥት የዕድገቱ ምንጭ አረዳድ “አገር-በቀል” የተባለው ፖሊሲውን የትኩረቱ አቅጣጫ ምርትን ወደ መፍጠር ሳይሆን የምርት ሁኔታን ወደ ማሳለጥ እንዲሔድ አድርጎታል። ለዚህም ሳይሆን አይቀረም የዚህ ዓይነት ፖሊሲዎች በሰነዱ ውስጥ የበዙት።

ኹለተኛ፣ በፖሊሲ ሰነዱ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው የተጋነነ የአገራዊ ምርት ወይም የ“GDP” ዕድገት በእርግጠኝነት መንግሥትን የተሳሳተ የገቢ አሰባሰብ ችሎታ እንደሚኖረውና የተሳሳተ ዕዳ የመሸከም አቅም እንዳለውም ሊያመላክተው ይችላል። (ለምሳሌ፣ ሰሞኑን በአፍሪካ የታየው ከፍተኛ የዕዳ ጫና ቀደም ብሎ የተደረገ የእንደዚህ ዓይነቱ አብረቅራቂ የዕድገት ትንበያ ውጤት ነው።) እኔ እንደማስበው፣ ከዚህም በተጨማሪም በፖሊሲው ላይ የተሰጠው የቁጠባ መጠንም በዕጥፍ የተጋነነና የድህነቱም መጠን ከእውነታው በብርቱ ያነሰ ነው። እነዚህ በመሬት ላይ ያሉ ሀቆችና ተዛማጅ ጉዳዮች በዚህ የፖሊሲ ሰነድ ውስጥ እንዲገቡ አለመደረጉ ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት ተብለው የወጡ እቅዶች ፣ ፖሊሲዎች እና አፈፃፀማቸው እውን መሆናቹውን እንድንጠራጠር የሚያደርጉ ናቹው።

2. “ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች” የተባሉትን የሰነዱን ፖሊሶዎች በተመለከተ፣ የሰነዱ አዘጋጆች የአገሪቱን የማክሮ (ዐቢይ) ኢኮኖሚያዊ ችግሮችና መሠረታዊ ምንጮች የተረዱት አይመስልም። እነዚህ መሠረታዊ ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፡-

ሀ) የየዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አለመጣጣም፤ ይህ በመሠረቱ ማለት የታቀደው ዕድገት አገሪቱ ልትከውነው ከምትችለው የምግብ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ የማፍራት አቅም ጋር የማይዛመድ ነው፣

ለ) የልማት ወጪ አሸፋፈኑ በውጭ ዕዳ እና በገንዘብ ማተም ላይ ጥገኛ መሆኑ እና

ሐ) በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የመካከለኛ ጊዜ ዕቅዱና በዓመታዊ በጀት እንዲሁም በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባሉት የረጅም ጊዜ ዕቅዶች መካከል መኖር የነበረበት መስተጋብር አለመኖሩ ናቸው።
“አገር-በቀል” የተባለው የፖሊሲ ማስተካከያም የተወጠነው እነዚህን የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች መሰረታዊ ምንጮች መጀመሪያ ሳይለይ ነው ። ችግሩ ሳይለይ መፍትሔ ሰጥቶ ጉዳዩ ይከወናል ማለት ደግሞ የዋህነት ነው።

3. ወደ “አገር-በቀሉ” የፖሊሲ ሰነድ “መዋቅራዊ እና ክፍለ-ኢኮኖሚያዊ/የሴክተር” ፖሊሲዎች ስንመጣ፣ የሰነዱ አዘጋጆች የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ችግሮች በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የተረዱት አይመስለም። በዚህም ምክንያት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የታቀዱት ፖሊሲዎቹም ለችግሩ መፍትሔ የሚሆኑ አይደሉም።

አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከታሪካቸው የወረሷቸው ለየት ያሉ መዋቅራዊ ችግሮች አሏቸው። ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በፊት እንዲህ ዓይነቱን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ችግሮች የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ሲዘረዝራቸው “በመሰረታዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መሠረተ ልማት ያሉ ጉድለቶች፣ የምርምር አቅም አለመኖር፣ ደካማ ምርታማነት፣ ኢ-መደበኛና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኢኮኖሚ ገጽታ፣ የቴክኖሎጅ ዕውቀት መሠረት አለመኖር፣ በውጪው የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ መሆንና ተያያዥ የሶሻልና የፖለቲካ ችግሮችና ደካማ የሰው ኀይል ልማት” ብሎ በይኗቸው ነበር። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የዋጋ ንረት (ግሽበት)፣ የክፍያ ሚዛን ጉድለት፣ የዕዳ ጫና የእነዚህ መዋቅራዊ ችግሮች ውጤቶች ናቸው። ኮሚሽኑ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ቀውስ ለማስቀጠል ያሴሩ መዋቅራዊ ችግሮች ብሏቸውም ነበር።
በእኔ አስተያየት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዛሬ የሚያሳየው ይህን መዋቅራዊ ችግር ነው። ስለሆነም መፍትሔውም መዋቅራዊ ባሕሪዎች ያሉዋቸው ፖሊሲዎች ናቸው። እነዚህ ከአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽኑ አረዳድ የተመዘዙ የኔ የመዋቅራዊ ችግሮች መረዳት ከዚህ በታች ባለው ሠንጠረዥ ውስጥ በቀኝ በኩል ከተሰጡት “የአገር-በቀሉ” ማሻሻያ ፖለሲ አረዳድ ጋር በንጽጽር (በግራ በኩል) ተሰጥቷል፡-
የኢትዮጵያ መዋቅራዊ ችግሮች ምንድን ናቸው? ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስፈልጉት ፖሊሲዎችስ?

4. ከላይ በተሰጠው ሰንጠረዥ ውስጥ የተጠቀሰው የ“አገር-በቀሉ” የፖሊሲ ሰነድ የኢትዮጵያ መዋቅራዊ ችግሮች አረዳድ ትክክል ነው እንኳን ብለን ብንወሰድ (ይሔ መቼም ለሰነዱ ከመጠን በላይ ደግ መሆን ነው)፣ ችግሮቹን ለመፍታት በታለሙት በማክሮ ፖሊሲ እና በመዋቅራዊ እና የሴክተሩ ፖሊሲዎች መካከል የማይናወጥ ግጭት አለ። እኔ ከላይ የገለጽኳቸውን የኢትዮጵያን መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት የሚወጠኑ የመፍትሔ ሐሳቦች ሦስት ጉዳዮችን ልብ ሊሉ ይገባል።
በመጀመሪያ፣ ይህንን የሚከውኑ ኀይሎች ሊታወቁ ይገባል (ይህም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጅ፣ አካባቢያዊ፣ ባሕላዊ እና ማኅበራዊ መልክ ይይዛል)፤

ኹለተኛ፣ ለዚህ ጉዳይ ያሉንና ሊገኙ የሚችሉ ሀብቶች (የሰው እና የተፈጥሮ ሀብቶች፣ የሀገር ውስጥ ቁጠባ እና ከውጭ የሚገኙ የገንዘብ ሀብቶች)፤ እና
ሦስተኛ፣ ልናገለግለው የምንፈልገው የሕዝብ ፍላጎቶች (ማለትም ለምሳሌ እንደ የቅንጦት እና ከፊል የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ በተቃራኒው አስፈላጊና መሰረታዊ በሆኑ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ማተኮር)።

እንዲህ ዓይነቱ የትንተናና የአስተሳሰብ ማዕቀፍ “በአገር-በቀሉ” ሰነድ ላይ በፍፁም አይታይም። ከላይ የገለጽኳቸውን በኢትዮጵያ ያሉትን መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት በተጨባጭ የሚከተሉትን ዓይነት በርካታ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።

በመጀመሪያ፣ የማምረት አቅምንና ምርታማነትን ማሻሻል፣ በቁጠባ ሀብትን ማሰባሰብ እና እሱንም በውጤታማነት መጠቀም ፣ የሰው ሀብት ልማት፣ የሳይንሳዊ እና የቴክኖሎጂ መሠረትን ማጠናከርና፣ ወደ ፊትም ወደ ኋላም ተያያዥና ተመጋጋቢ የሆኑ ምርቶችንና አመራረትን አሰባጥሮ ማስፋፋት፤

በኹለተኛ ደረጃ፣ የሕዝቡን የገቢ ደረጃ እና የገቢ ስርጭት ማሻሻል፣ የግል ወይም የመንግሥት የሚል ፅንፍ ሳይዙ በመንግሥትና በግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ መካከል ልዩና ተገቢ ሚዛን መጠበቅ፣ ለዘላቂ ልማት የሚሆን የኢኮኖሚያዊ ማበረታቻዎች እና የፖለቲካ መረጋጋት ሁኔታዎችን ማስቻል፣ የሀብት ብክነትን ማሰወገድና በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን የገቢ ክፍፍል ማሻሻል፤

በመጨረሻም በጣም መሰረታዊና አስፈላጊ ሸቀጦች ላይ በማተኮር በተለይም በምግብ ራስን መቻል፣ በገቢ ንግድና በውጭ ፋይናንስ ላይ ያለንን ከፍተኛ ጥገኛነትን መቀነስና አጠቃላይ አገራዊ ፍጆታችንና የአገር ውስጥ ምርታችንን ማቀናጀት ናቸው።

እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች በሙሉ በሰነዱ ላይ አለመጠቃለላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከእነዚህ ጉድለቶች መካከል ዋነኛውና “አገር-በቀሉ” ፖሊሲ የረሳው ጉዳይ የሰለጠነ የሰው ኀይልና የባለሙያ ጉድለት ነው። ሆኖም እንደዚህ ያለውን ፖሊሲ ለማውጣት፣ ለመተግበር እና ለመቆጣጠር ይህ የሰለጠነ የሰው ኀይል መሠረታዊው ጉዳይ ነው።

5. ምንም እንኳን ከላይ እንደተጠቀሰው ሰነዱ መሰረታዊ ችግሮች ያሉበትና ፈረንጆቹ እንደሚሉት ሰይጣኖቹ ብቅ ብቅ የሚሉት ወደ ፊት በዝርዝር በሚወጣው ፖሊሲ ውስጥ ቢሆንም፣ የቀረቡት የማክሮ ኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፍ ፖሊሲዎች አንዳንድ ጥሩ ገጽታዎችም አሏቸው። እንደ ክፉ ዕጣ ሆኖ ግን ብዙ አይደሉም።
በዚህ የበጎ ፖሊሲዎች ዝርዝር ውስጥ ከውጭ ምንዛሪ ገበያጋ የተነሱ አንዳንድ ፖሊሲዎች፣ የመንግሥት ገንዘብ አስተዳደርን ለማስተካከል የታለመው ጉዳይ፣ የዕዳ አያያዝ እና ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ ምርት የመተካት ፖሊሲዎች ይካተታሉ። ሆኖም ከዚህ በላይ ከገለጽኩት የሰነዱ ድክመት አንጻር እነዚህንም ቢሆን እንደገና መመርመር እና የአጭር ጊዜ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲሁም የገንዘብ ፖሊሲዎች በረጅምና በመካከለኛ ጊዜ ከታሰቡት መዋቅራዊና ክፍለ-ኢኮኖሚያዊ (የሴክተሮች) ፖሊሲዎች ጋር የሚጋጩ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና ውጤቶችን ስለሚያሳይ ይህንን ለመፍታት መሞከር አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ፣ በሰነዱ ላይ ባሉ ቁጠባን ማበራታታትና በአነስተኛ ወለድ መዋዕለ ንዋይን ማበረታታትን በሚመለከቱ ፖሊሲዎች መካከል ተቃርኖ ማየት ይቻላል፣ የታሰበው ጥብቅ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲና የእስካሁኑን የኢኮኖሚውን ዕድገት ፍጥነት የማስቀጠል ፖሊሲ መሀልም ተቃርኖ ይታያል፤ ፖሊሲው ይፈልጋል የተባለው የ10 ቢሊዮን ዶላር ወጪና ከዕዳ ጫናና በዘላቂነት ከውጭ ፋይናንስ ጥገኘነት መውጣትም ተቀርኖ ይታይባቸዋል።

ጨቅላ ኢንዱስትሪዎችን በማሳደግ ተወዳዳሪ የማድረጉ ፖሊሲና ገበያውን በብርቱ የሚከፍተው የነፃ ገበያ ፖሊሲም ተቃርኖ ይታይባቸዋል፣ መንግሥት ድህነትን ለመቀነስና እነዚህን ግዙፍ ሥራዎች ለመሥራት የሚያስፈልገው አቅምና ይህንን አቅም የመገንቢያ ምንጮች የሆኑ ቁልፍ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ንብረቶችን፣ ኢትዮ-ቴሊኮምን ጨምሮ፣ ለመሸጥ ማቀድም ተቃርኖ ከሚታይባቸው ጉዳዮች ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው። ለአብነትም መንግሥት ከልማት ድርጅቶች ዘንድሮ ካገኘው 45 ቢሊዮን ብር ውስጥ የቴሌ ብቻ ድርሻ 60 በመቶ ሆኖ ቴሌ አይነቱን መሸጥ የመንግስት አቅምን ሊያኮስስ እንደሚችል ማየት ይቻላል።

6. ይህን የመሰለ ግዙፍ ድክመት ለማረም ምን ማድረግ ይበጃል የሚለው ጥያቄ መሰረታዊና በማጠቃለያ መልክ የማነሳው የምክረ ሐሳቤ መንደርደሪያ ነው። የምክረ ሐሳቡ የመነሻ ነጥብ ከላይ ከተዘረዘሩት ድክመቶች አንጻር ፖሊሲውን እንደገና መመርመር እና ተገቢ የእርምት እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል የሚለው ሲሆን፣ በተጨማሪም የሚከተሉትን አራት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል፡
ሀ. [1] (i) በታለመው የኢኮኖሚ ዕድገት እና በምግብ አቅርቦት ዕድገት፣ እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ የማፍራት አቅም መካከል ያለውን የዘርፎቹን ዕድገት አለመመጣጠን እንዴት እንደሚፈታ ዕቅድ ማውጣት፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአነስተኛ ወጪ ከፍተኛ የግብርና ምርት/የምግብ አቅርቦት መጨመር የሚቻለው አነስተኛ የመስኖ ልማት በማስፋፋት፣ የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት በማሳደግና በረዥም ጊዜ ደግሞ የመሬት ስሪቱን ተያያዥ ጉዳዮችን በመፈተሸ ነው።

(ii) በአጭር ጊዜ፣ በዝርዝር የውጪ ምንዛሪ ቁጠባና የማፍራት አቅም ላይ ያነጣጠረ ሥራ መሥራትና በረዥም ጊዜ ከቻይና እና ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በተፈበረከ የወጪ ንግድና የኢንዱስትሪው ዕድገት ላይ ማተኮር ነው። እነዚህ የፖሊሲ አቅጣጫዎች የማክሮ ኢኮኖሚውን የመናጋት ችግርን በአጠቃላይ እና የዋጋ ንረትን (ግሽበትን) በተለይ ለመፍታትም ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።

(iii) መሠረታዊ የሆኑትን የሸቀጣሸቀጦች አቅርቦት ሰንሰለት በማሳጠርና በማሳለጥ ምርቶቹን በአነስተኛ ዋጋ ለከተሞች ነዋሪዎች በቀበሌ ሱቆች ወይም የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ እቅዶችን በመጠቀም ወይም የግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚን በመቆጣጠር በአነስተኛ ዋጋ እንዲያቀርቡ በማድረግ የእነዚህን አቅራቢዎችንና ደላሎችን ተገቢ ያልሆነ የጠቅላይነት ጉለበት መቆጣጠር ያስችላል።

ለ.) [2] ይህ የመንግሥት ፖሊሲና ዕቅድ በዋና ዋና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች (ቴክኖክራቶች) የሌሉት ከሆነ፣ የምኞት ዝርዝር እንጂ በተግባር የሚገለጥ ዕቅድ አይሆንም። ስለዚህ

(i) መንግሥት በዋና ዋና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች “የፕሮጄክት ትንተና እና ግምገማ ጽሕፈት ቤት” አዘጋጅቶ ቢያንስ 10 በሚሆኑ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ኢኮኖሚስቶች፣ ኢንጂነሮች እና የኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ማደረጃት ያስፈልገዋል፣ ይህንን በአጭር ጊዜ የእቅድ ዘመን በተለይ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እና ፋይናንስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ቢያደርገው ጥሩ ነው። በመካከለኛው ጊዜ እቅዱ ደግሞ ከግሉ ዘርፍ በተሻለ የሚከፍልና አገራቸውን ለማገልገል የሚፈልጉትን ብሩህ ወጣቶች የሚስብ አደረጃጀት ያለው የመንግሥት ሠራተኛ አሰራር ስርዓት መተግበር አለበት።

(ii) በተያየዥም እንደዚህ ያሉትን የየሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ቢሮዎች በሙሉ ለመቆጣጠር እና የእነሱን የመተንተንና የማሰፈጸም አቅምም ለማሻሻል በፕላን ኮሚሺን ስር “የልማት ፕሮጄክቶች ትንተና እና የክትትል ክፍል” ማዘጋጀት፣

(iii) እንደ ምክትል ሚኒስትሮች (ሚኒስቴር ዴታዎችና) እና እንደ ሚኒስተር ባሉ የፖለቲካ ቦታዎች መካከል ልዩነቶች መፍጠር። የምክትሎቹ ቦታ በሙያተኛ እና በችሎታ በተመረጡ ብቻ እነዲያዝ ማድረግ። በብሔራዊ ባንክ የምርምር ክፍል ውስጥ የገንዘብ-ነክ ጉዳዮችን በዝዝር የሚያሳይ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሞዴልን (የሂሳብ ምስለ-ኢኮኖሚ) ማዘጋጀት ፣ በፕላን ኮሚሽን ውስጥ ደሞ ለበጀት አፈፃፀም አገልግሎት የሚውል ዝርዝር የፋይናንስ ብሎክ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ሞዴልን ማዘጋጀት (ስለ ኹለቱም ጉዳዮች ከኬንያ መማር)። እነዚህ ሞዴሎች ወይም ምስለ-ኢኮኖሚዎች ደግሞ ጠቋሚ እቅድ በማዘጋጂያ የኢኮኖሚ ዕድገት ሞዴል መታገዝ አለባቸው። አገሪቱ ያላትን ምርጥ ባለሙያዎችንና ምርጥ ጭንቅላቶችን ከአገር ውስጥም ከትውልደ-ኢትየጵያዊያንም ለመሳብና ያሉትንም ለመያዝ፣ በሒደትም ዘላቂ የሆነ የአቅም ግንባታ ለማካሔድ፤ ለዚህ ተብሎ ከበድ ያለ በጀት መመደብ አለበት።

ሐ [3] መንግሥት የፖሊሲ ምርምርንና ትንታኔን ከውጭ በቴክኒክ ድጋፍ ሥም ለሚመጡ፣ ስለ አገሪቱ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ሁኔታ የጠለቀ እውቀት ለሌላቸው እና ምናልባትም ለመጡበት አገርና ድርጅቶች ብሔራዊ ጥቅም ለሚሰሩ ሰዎች ትቶ ከኋላ ተመልካችና ሰሚ ብቻ መሆን የለበትም። በምትኩ አገራዊ የማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ምርምር ማዕከሎችን፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማኅበርን፣ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍሎችን በመጠቀም ፖሊሲውን በመቅረፅ እና በመተግበር መንግሥት የባቡሩ ዋንኛ ሾፋሪ እንጂ ተሳፋሪ መሆን የለበትም።

በዚህ ስሌት እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባነክ እና የሃርቫርድ ቡድን ያሉ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪዎች እንጂ አሁን እየተደረገ እንዳለው እነሱ የባቡሩ ዋንኛ ሹፌር መንግሥት ደግሞ ተሳፋሪ መሆን የለበትም። መንግሥት ከዚህ ሁኔታ ወጥቶ የአገሪቱን ምርጥ ተመራማሪዎች ከላይ ከጠቀስኳቸው ተቋማት በመያዝ ዋና ዋና በሚባሉ መሥሪያ ቤቶች (በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም ወዘተ) እና በፕላን ኮሚሽን ውስጥ ካሉና ስለእያንዳንዱ ዘርፍ እና በእያንዳንዱ ሚኒስቴር ውስጥ ጥልቅ ዕውቀት ባላቸው የመንግሥት ባለሙያዎች (ለምሳሌ በብሔራዊ ባንክ፣ ባንኮችን የመቆጣጠር ጉዳይ ላይ አቶ ጌታሁን ናናን፣ በብሔራዊ እቅድ ላይ አገሪቱ አላት የሚባሉ ቴክኖክራቶችን ለምሳሌም አቶ ጌታቸው አደም፣ አቶ መኮንን ማዬዘዋልና እና አቶ መዝገበ፤ አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም እና አቶ ግርማ ዋቄን ደግሞ በመንግሥት ኩባንያዎች አመራር ላይ እና ሌሎችንም ወዘተ) በመቀናጀት የልማቱና የዕድገቱ ቁልፍ ችግሮች ምን እንደሆኑ ለማወቅ ጥልቅ ጥናትና የዕድገቱ ማነቆዎችን የመለየት ሥራ ማካሔድ አለበት።

ይህ ጉዳይ ወደ ፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር በሚቋቋም እውነተኛ የባለሙያዎች ምክር ቤት መከናወን አለበት፣ አባላቱም በችሎታቸው እንጂ በርዕዮተ ዓለም፣ በፖለቲካዊ አቀቋማቸውና በዓለም የገንዘብ ድርጅቶች ተፅዕኖ መመረጥ የለባቸውም (ወደ ፊትም ለዘልቄታው፣ ይህንን ዓይነቱ ተቋም የሕገ-መንግሥቱ አካል ቢደረግ ጥሩ ነው፤ ለዚህም የደቡብ ኮሪያና የአሜሪካን አሰራር ማየት ጥሩ ነው)።

መ) [4] በመጨረሻም በሚቀጥሉት ከአምስት እስከ ዐሥር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከእርዳታ እና ከውጭ ፋይናንስ ጥገኝነት እንዴት እንደምትወጣም የሚያካትት ዘላቂ የልማት ወጪ አሸፋፈን ስልት ሊቀይስ ይገባል። ይህ ስልትም ቢያንስ የሚከተሉትን ጉዳዮች የሚያካትት መሆን አለበት፡

(1) የሀገር ውስጥ ሀብት/ቁጠባን ማሰባሰብ፣ (2) የሀዋላ ገቢን ማጎልበት፣ (3) መዋቅራዊ ሽግግር በማምጣት የውጪ ምንዛሪን በበቂ የማፍራትን ጉዳይ ከምዕራቡም ከምሥራቁም የልማት አጋሮችጋ በመተባበር መከወን፣ በተለይ የደቡብ-ደቡብ አጋርነትና ትብብርን (በተለይም የምሥራቅ ኤስያን፣ ቻይናን፣ ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካን) በማጎልበት ግንኙነቱን ለዚህ ጉዳይ በዕውቀት መጠቀም ሊታሰቡባቹው የሚገቡ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ናቸው። ለምሳሌ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ከቻይና መበደራችን በራሱ ችግር አልነበረም፤ እኔ ካካሔድኳቸው ብዙ የቻይናና አፍሪካ ጥናቶች ተነስቼ የተረዳሁት ጉዳይ ቢኖር፣ የቻይናን የአፍሪካ ስትራቴጂ ተረድተንና ኢትዮጵያ በዛ ላይ ያላትን ሚና ተገንዝበን በዕውቀትና ሳንሰርቅ ብንጠቀምበት ኖሮ፣ ቻይና ባለፉት ዓመታት የሰጠችን የልማት ዕድል በትውልድ አንዴ የሚገኝ ዕድል ነበር። በግብዝነታችን ግን አልተጠቀምንበትም፤ አሁንም ከገባን ጨርሶ የሞተ ዕድልም አይደለም።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here