ጋዜጠኛና ደራሲ ገነት አየለ አንበሴ የወጣቱን የፍራንኮ-ርዋንዳዊውን የጋይል ፋይ ግለ ታሪክ [Autobiography] መጽሐፍ ‹Petit Pays›ን የፈረንሳይ ቋንቋ እውቀቷን በመጠቀም ‹ትንሿ ሀገር› በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተርጉማ ለአንባብያን ካደረሰች ከራረመች። በድሉ አበበ ይህን መጽሐፍ ቃኝተዉታል። መጽሐፉ በሩዋንዳ የነበረውን አሰቃቂ የእርስ በእርስ መጠፋፋት ያወሳል። ‹‹ሀገር ብታንስም ይሄን መከራ መቀበል የለባትም። የእኛ ትልቅ ሀገር ነውና ትልቅ ጠላት ገጥሞታል።›› ሲሉም መጽሐፉን በኹለት ተከታታይ ክፍል እንደሚከተለው ከትበዉታል።
በኢትዮጵያው የቀድሞ መሪና ብዙ ነገሮችን እንዲታዘብ ፈጣሪ እድል የሰጠውን የኮለኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ትዝታዎችን ኹለት ቅጾች፤ ‹በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ቆይታዬ› የሚል የትርጉም መጽሐፍ (ተከታታይ ኹለት ክፍል ያለው) እና በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ በጋዜጣና በድረገጽ የተጻፉ በርካታ ሥራዎችን አበርክታለች፤ ጋዜጠኛና ደራሲ ገነት አየለ አንበሴ። በቅርቡም የወጣቱን የፍራንኮ-ርዋንዳዊውን ጋይል ፋይ ‹Petit Pays› የተሰኘ ግለ ታሪክ [Autobiography] መጽሐፍ ከፈረንሳይ ቋንቋ ወደ አማርኛ በመመለስ ለአንባብያን አድርሳለች።
‹ትንሿ ሀገር› የታተመው በማንኩሳ ማተሚያ ቤት ሲሆን፤ መግቢያና ስለ ደራሲዋ እንዲሁም የመጨረሻውን መጨረሻ የዳዊት ወ/ጊዮርጊስን አስተያየት ሳያካትት፤ በ216 ገጾችና በሠላሳ አንድ ምዕራፎች ተቀንብቧል። የታተመው ሰኔ 2020 ሲሆን፣ እንደወጣ ሳምንትም ሳይሞላው እያነበብኩ እንደሆነ በማኅበራዊ ገጽ (Facebook) ካጋራሁ በኋላ፣ አንድ ነገር እንድል ጉምቱው ኢንጂነር ተስፋዬ ማሞ ወትውቶኛል።
በነገራችን ላይ ገነት ራሷ መተርጎሟን በማኅበራዊ ሚዲያ (Facebook) ነው ቀድማ የነገረችን። ከዓመት በላይ ቢዘገይም አንድ ነገር በለን ባልከው መሠረት፣ ይኸው ተስፍሽ።
እንደ ሀገራችን ሰው ራሱን ለመብላት እጅግ የተጋበት ዘመን ቢኖር ትልቁ ጊዜ ይሄ ዘመን መሆን አለበት። ዓለም ላትጨርስ እጀምራለሁ ስትል ጥርስም ለመሳቅ ጥርስ ታጣለች። ማንነት የጥል ምክንያት ሊሆን ሂደቶች አሉት። በሐሳብ ተጠንስሶ፤ በንግግር ዳብሮ፤ በድርጊት ገድሎ ይሄው 21ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን፤ ዘመናችንን የሃሴት ሳይሆን የመከራ አድርጎብናል፤ በትወልድ ሀገራችን።
የሚገርመው የውጪ ሀገር ሰው ተከብሮ ባላገሩ ይገዳደላል። የምንሰማው አይጥምም። የምናየው አያምርም። ነፍስያችን በጎ ነገር ናፍቋት ሊያድር አይረፍድባትምና እነሆ እቺን መጸሐፍ እንያት። የልጆቻችን መጪው ዕድል ማሳቀቁ ላይቀር…!
የእኛን የማይመስል መከራ ሀገራችንን ወሯታል። እልቂት አጥለቅልቋታል። በየቦታው የእንባ ጎርፍ ምድሯን ሞልቶ ተርፏል። ደቡብ ያነባል። ሰሜን መፍትሔ አልሆነም። ምሥራቅ ፀሐይ ልትጠልቅበት ከሰዓት ላይ ናት። ምዕራብ ከፍቅር ወደ ሞት ያዘነበለበት ‹የሄሚስፌር› ፍጥነት ያስደንቃል። ከእስራኤል ሀገራት መከራዎች ቀጥሎ የኩነኔ ሪኮርድ ለመያዝ ያልተጣጣርነው፤ ያላደረግነው የመከራ ዓይነት የለም። ያልተከሰተበት ቦታ፤ ያልሆነም ዓይነት ክፋት ያለ አይመስልም። እኔ እንኳ እኛ ነን ወይስ ሌላ የሚል የነፍስ ጥያቄ አለኝ።
የመከራ ዓይነቶች፤ ከዓይነቶቹም በማኅበራዊ ሚዲያ ቀጥታ ማየታችን አንጀታችንን አላውሶ ሰው መሆናችን እስኪቀብርብን ድረስ ብዙም ልዩ ልዩም ዓይነት መከራዎችን በምድራችን፣ በሀገራችን፣ በቀያችን በኢትዮጵያ ምድር ዐይተናል፤ ሰምተናል፤ አንብበናል። አንብበን ለማበድ አንድ ሐሙስ እስኪቀረን ድረስ ለተወዳጇ ሀገራችንና ለሕዝባችን ለመጪው ትውልድም የባይሆን ትለማ አንብተናል።
ጎበዝ! ሰው ኦኮ የቤተሰቡን ሀዘን በፌስቡክ ሰምቶ አዝኗል። አሁንም የሞት ዜና ልምምድ መጨረሻ ላይ ስለሆንን ነው መሰለኝ፣ ‹እዚህ ቦታ ሰዎች ሞቱ› ስንባል ቀድመን የምንጠይቀው ‹ስንት ሰው ሞተ› ሆኗል። ይሄ ማለት ሰው ከኑባሬ ወደ ቁጥር በፍጥነት ወርዷል። የሞተው ሰው አይደለም፤ ቁጥር እንጂ።
ያ ሰውኮ ባል ነው። ያ ሰውኮ ወንድም ነው። ያ ሰውኮ አያት ነው። ያ ሰውኮ አባት ነው። ያ ሰውኮ እህት አለው፤ የምትጠብቀው፣ የምትተርበው። ያ ሰውኮ ከምንም በላይ የምትሳሳለት እናት አለችው፤ በር በሩን ገባ አልገባ ብላ የምትጠብቅ፤ አግብቶ ከቤት ወጥቶ እንኳ መቀነቷን የምትፈታለት እናት።
ከታሪካችንም፤ ከሃይማኖታችንም፤ ከባህላችንም፤ ከግብረ ገብነትም ከሥነ ምግባርም ያፈነገጡ፤ ሰይጣን ምናልባትም ስልቱና ሁኔታው ገርሞት እስኪደንቀው ድረስ ያልተከሰተ የስቃይ ዓይነት ያለ አይመስልም። እንደዚህ ዓይነት ታሪኮች የትና እንዴት ተከሰቱ ለሚለው ጥያቄ መልስ ስንፈልግ ደግሞ፣ ከምናገኛቸው የዓለማችን ታሪኮች የአይሁድ፤ የጀርመን፤ የአርመን፣ የኦስትሪያና የሩዋንዳ ታሪኮች ቀድመው በአዕምሯችን መሳላቸው አይቀርም።
በዚህ የዘር ፍጅት ታሪክ ረገድ ነፍሳቸውን ይማርና ታላቁ ደራሲ ማሞ ውድነህ፤ ኦሽዊትዝ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ጥንታውያን ጸሐፍት፤ …በዚህ ባለንበት ዘመን ደግሞ ወደ አማርኛ ከተተረጎሙት የሩዋንዳ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች ውስጥ እያለቀስንና ሰው መሆናችንን እስክንጠላ ድረስ ልብ ከሰበሩን መጻሕፍት ውስጥ የደብረ ብርሃኑ መዘምር ግርማ የተረጎመው የኢማኩዌሊ አሊ ባጊዛ “Left to Tell” ‹ሁቱ ቱትሲ› በሚል የተረጎመውና/ ይሄ አሁን የምንዳስሰውና በታላቅ እህታችን ገነት አየለ አንበሴ የተተረጎመው “Petit Pays” ወይም ትንሿ ሀገር አንዱ ነው።
እዚሁ ጋራ ሥማቸውን እስከ አያታቸው የሚጽፉ ደራስያንና ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ብናውቅ ደስ ይለናል። ሁላችሁንም ዐይናችንን ስለገለጣችሁልን እናመሰግናለን። አንባቢዬ ሆይ ‹ሆቴል ሩዋንዳ›ን ካዩ ከኔ ጋር ነዎት ማለቴ ነው።
በሩዋንዳ የዘር እልቂት ጉዳይ ከግል እስከ ‹ደቦ› አንብበናል። ብዙ ባለሙያዎች ከተራ ጎብኚ እሰከ ጉምቱ ፕሮፌሰሮች አሁን የሚሆነው እንዳይሆን ወትውተዋል። በቃልም፤ በጽሑፍም፤ በፊልምም፤ በመጽሐፍም አንብበናል። ወሳኙ አልሰማም አለ እንጂ። አንባቢም ንባብም ‹በከተማ› ተወሰነ እንጂ።
ከደቡብ እስከ ሰሜን፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስከ ኦክስፎርድና ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲዎች እንኳን ሌላው ዓለም ኢትዮጵያውያን እንኳ ጽፈናል፤ ተመራምረናል፤ አጥንተን አስጠንተናል። መክረናል፤ ዘክረናል። ሀገር ውስጥ አንዴት እንደወደቅን እኔም አላውቅም እንጂ። መርማሪ ‹ኢትዮጵያ› ተመርማሪ ስትሆን፣ ተፈጥሮም መልስ ያላት አይመስልም፤ እጅን በአፍ ላይ ከመጫን በቀር።
በነገራችን ላይ Petit ማለት በላቲን ትንሽ ማለት ሲሆን grand ማለት ደግሞ የትልቅም ትልቅ ማለት ነው። Grand ERD እንደ ማለት። ከትልቅ ትንሽ እንዲሰውረን እየተማጸንን “Petit Pays” ወይም ትንሿ ሀገር ዳሰሳችንን እንቀጥላለን።
ሀገር ግን እንዴት ትንሽ ልትሆን ትችላለች? ሰው ነው ወይስ ሀገር የሚያንሰው? ከትንሽ ሀገር ‹በስፋት ለምሳሌ› ትልቅ ሰው አልወጣምን? ማነው ያነሰው? ሰው ወይስ ሀገር? የሀገር ትንሽ የለውም፤ እኛ ካላሳነስናት በቀር። በሀገራችን ትንሽነት ውስጥ የትውልድ ሚና ምንድን ነው?
ደራሲው ጋይል ፋይ ተናዶ መሆን አለበት ትንሽ ሀገር ያለው። በእርግጥ ፈረንሳዊ መሆኑንም አንዳንድ ነገሮችንም ስናስብ ደግሞ ነገር ነገር ይለናል እንጂ።
ሩዋንዳ ትልቅ ሀገር ናት። ኢትዮጵያማ ቀደምትና የትልቅም ትልቅ ናት። ቀደምቶቹ ፋርስ፤ ግሪክ፤ ሮም፤ ቻይናና ግብጽ ዛሬም አለመመስከር አይቻላቸውምና። በነገራችን ላይ ትንሽ ብዙ አይጠመድም። እነሱ ግን ‹ግሬት› ሲሉን እኔ እፈራለሁ። ‹ግሬተር› አትዮጵያና ብዙ ‹ግሬቶች› አፍሪካን አውከዋል።
አንድ የ‹ግሬት ቴሲስ› ኢትዮጵያንና 25 ሚሊዮን ሕዝቦቿን ይሄው ዛሬም ለመከራ ዳርጓል። መጽሐፉ የአንድ ቤተሰብ ታሪክ ነው። ፈረንሳያዊው ሚሼል ከሩዋንዳዊት ‹ቱትሲ› ሚስቱ ጋብርኤልና አናን ይወልዳል። ጭምጭምታ የነበረው፤ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የከረመው የብሔር ተቃርኖ የኤፕሪል 07 ቀን፤ 1994 ኪጋሊ አየር ማረፊያ ሊያርፍ ሲል ተመትቶ የኹለት ሀገር ፕሬዝዳነቶች ማለትም የሩዋንዳና የቡሩንዲ ፕሬዝዳንቶች ግድያ ተከትሎ ሁሉም ነገር እንዳልነበር ይሆናል።
እኔ አንተን አይደለሁም። ልዩና ብዙ ነን። ኢትዮጵያን ጡዘውና አስጡዘው [መጦዝም ማጦዝምኮ አይደለም፣ የያዝነው ጸረ-ተፈጥሮ ነው]። ብሔር ለምሳሌ ተፈጥሮ፤ ጸጋና በረከት ነው። የማይቀየር ማንነትም ነው [Given Identity] እንዲል የማንነት ተንታኙ። ማንኛውንም ነገር ማጦዝና ማክረር ግን መጠፋፊያ ይሆናል።
ማክበር ማስከበር ያስፈልጋል፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ። ለማያኗኑር ነገር ቀን ከሌት መሥራት የጤና አይደለም። እሳቱ ብሶ ሲመጣ የሚተርፍ የሚመስለው ካለ ሞኝ መሆን አለበት። እሳቱ ከሩቁ እንኳን ምን ያህል እንደሚፋጅ እያየነው ነውና።
ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም፤ ያልተከሰተበትን ቦታ ብቻ መጥቀስ ስለሚቀል እንተወው እንጂ፤ የመከራ ዓይነቶች፤ ከብዛትና ዐይነቶቹም በዐይንና በማኅበራዊ ሚዲያ ቀጥታ ስቃይን፤ ግርፋትን፤ ግድያን፡ ዕገታን፤ ወዘተ ማየታችን አንጀታችንን አላውሶ ሰውነትን እስኪቀብርብን ድረስ ብዙም ልዩ ልዩም ዓይነት መከራዎችንም በዘመናችን ዐይተናል። ካልዋሸን በቀር። ካላደላን ጭምር።
እንዋሻለን እንጂኮ ተስፋ ቆርጠናል። ላለማየት ዐይናችንን ጨፍነን ነው እንጂ ኑሮኮ ውል አጥታለች። ከታሪካችንም፤ ከሃይማኖታችንም፤ ከባህላችንም፤ ከግብረ ገብነትም ከሥነ ምግባርም ያፈነገጡ፤ ሰይጣን ምናልባትም ስልቱና ሁኔታው ገርሞት እስኪደንቀው ድረስ ያልተከስተ ኩነኔ ያለ አይመስልም።
የተጠናነውን ሆነን ተገኝተናል። የውስጥም የውጪም ጠላት ቀዳዳ ሰፍቶት ዛሬም ይዋኛል። ዐይጥ በቀደደው ጅብ መግባቱ ባህል ነውና፣ ሀገር ዛሬም በቋፍ ላይ ትፍጨረጨራለች። በራሳችን በልጆቿ ብልሃት ማጣት የፊጥኝ ታስራ። የ‹ዜግነት ክብር› መፍትሄ አልሆን አለ።
እንደዚህ ዓይነት ታሪኮች የትና እንዴት ተከሰቱ ብለን መለስ ብለን መልስ ስንፈልግ፤ ከምናገኛቸው የዓለማችን ልምዶች የአይሁድ፤ የጀርመን፤ የአርመንና ኦስትርያ እንዲሁም የሩዋንዳ ታሪኮች ቀድመው በአዕምሯችን ይሳላሉ።
እባክዎ! ወደ ዩትዩብ ጎራ ብለው ፕሮፌሰር ኤሊ ዌዘል ብለው አንጋፋዋ ኦፕራህ ዊነፍሬይ በ‹ኮንሰንትሬሽን ካምፕ› ከተራፊው ጋራ ተወያይታ ስታለቅስ ይጋበዙ። የግል ቃለ ምልልሳቸውንም መጨመር ይቻላል። ዛሬ ዓለም ወደዛ እንዳትገባ በስተ-እርጅና ቢመክርም ፕሮፌሰሩ ሰሚ ያገኘ አይመስልም። እሱ ግን ዛሬም ያለቅሳል፡ ስሙኝ እያለ።
ይቀጥላል…
ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014


