‹‹የእንስሳት ሞት ለግብርናው ዘርፍ ያለው ጦስ››

0
1288

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረውና ገና ባልተቋጨው የጦርነት ቀጠና ውስጥ የነበሩ የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች ከሚሰነዘረው ጥቃት ህይወታቸውን ለማትረፍ ሰላም ወዳለባቸው ስፍራዎች ተፈናቅለው በመቆየታቸው፤ ሰብላቸውን ተንከባክበው ለመሰብሰብ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ሽብርተኛ የተባለው ቡድን ታጣቂዎች በአማራና አፋር ክልል ያሉ ነዋሪዎችን ከማፈናቀላቸውም ባሻገር እንስሳቶችን፤ የመንግስትና የህዝብ ንብረቶችን ወስደዋል። ራያ አላማጣ፤ ዋጃ ጥሙጋ፤ አድስቅኝ፤ ጋሸና፤ ላሊበላ፤ ሙጃ፤ አቡዬ ጋራ በተሰኙ ስፍራዎች ሰብሎችን አጭደው የመውሰድ ሙከራ እንዳደረጉ ነዋሪዎቹ በወቅቱ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ እንስሳቶች ስለመገደላቸውና ስለመዘረፋቸው በወቅቱ ሲወጡ የነበሩ ዘገባዎች ህያው ምስክር ናቸው። ባልተቋጨው ጦርነት እስካሁን ድረስ ጦርነቱ በከፊል ባለባቸው ስፍራዎች የአርሶ አደር ከብቶች እየተዘረፉና በታጣቂዎች እየታረዱ ለምግብነት ጥቅም እየዋሉ መሆናቸውን ችግሩን ለመጋፈጥ የሚጥሩ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ከሆነ፤ ታጣቂ ቡድኑ እህልን ጨምሮ ብርና ንብረታቸውን እንደወሰደና ከብቶቻቸውን ለምግብነት እንደተጠቀመ ነው። ጥላሁን በላይ የራያ አላማጣ አርሶ አደር ናቸው። በተለይም ሽብርተኛ ቡድኑ የአማራና ትግራይ ክልል የድንበር ቦታዎች ሲገባና ተቆጣጥሯቸው ከነበረበት ስፍራዎች፣ ጥምር ኃይሎች ባደረጉት ጥቃት ወደ ኋላ ሲመለስ ከብቶችን እንደገደለና እህል እንደዘረፈ፤ እንዲሁም ለፍሬ ያልደረሱ ቡቋያዎችን እንዳኮላሸ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በራያ አላማጣ ዙሪያ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ከእያንዳንዱ ሰው 70 ሺሕ ብርና አንድ ኩንታል እህል የመሰብሰብ ዘመቻ እንዳካሄደና መስጠት ያልቻሉትን ሰዎች ልጆቻቸውን አግቶ እንደወሰደ ጥላሁን የአይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
በጋሸና ዙሪያ የሚኖሩ አፈወቅር እክሊሉ የተባሉ አርሶ አደር በበኩላቸው፣ ታጣቂ ቡድኑ በርካታ የበቆሎ ሰብሎችን እያንዳንዷቸውን ከጥቅም ውጭ እንዳደረጓቸው መስክረዋል።

በወቅቱ በርካታ የበቆሎ ቡቋያዎች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል ያሉት አፈወርቅ፤ አንድ አርሶ አደር በታጣቂ ቡድኖቹ ቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበርና “እርሱን ከግንድ አስረው ሚስቱን ደፍረዋታል” ብለዋል።

እንዲሁም ላሊበላ ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች የአርሶ አደር ከብቶች እንደተዘረፉ ነው ማረጋገጥ የተቻለው። የአካባቢው ነዋሪ ምስጋን አከለ የሕወሓት ቡድን የአርሶ አደር ከብቶችን፤ ፍየሎችን እንደዘረፈ ነዋሪዎቹ ለእርሻ አገልግሎት የሚውል ከብት እንደተቸገሩ የተመለከቱትን መስክረዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ያለፈው የምርት መጠን እንዳሽቆሎለ ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃም ያመላክታል። በመሆኑም፣ በዘንድሮው ዓመት በጦርነቱ ምክንያት ከተከሰተው የምርት ማሽቆልቆል በተጨማሪ የእንስሳቶቹ መገደልና መዘረፍ አርሶ አደሮቹ ለእርሻ አገልግሎት የሚውል ከብት ለማግኘት በመቸገራቸው ለቀጣይ ዓመትም ቢሆን የምርት መጠኑን ይቀንሳል የሚል ስጋት በማህበረሰቡ በኩል አሳድሯል።

እንደሚታወቀው የገጠሩ ማህበረሰብ የቤት እንስሳት አይነቶችን በማርባትና ለገበያ በማቅረብ ነው ብር ማግኘት የሚችለው። ነገር ግን፣ የእርሻ ከብቶች ብቻ ሳይሆን ሌሎች እንስሳቶችም ሲዘረፉ ለገበያ የሚያቀርበው ንብረት ባለመኖሩ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ የነበሩ ማህበረሰብ ክፍሎች ችግር ላይ የወደቁ ናቸው። ለአብነትም በሰሜን ወሎ ዞን (ቆቦ፤ ወርቄ፤ ጋሸና)፤ ደቡብ ጎንደር ላይ ጋይንት (ጭና)፤ ጉና በጌምድር፤ ሳርጻ፤ እሴ ወረዳዎች ከብቶች የተገደሉባቸው ቦታዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግስት ለአርሶ አደሩ ትራክተር በማዳረስ ዘመናዊ መልኩ ለማምረት እንዲችል ይደረጋል በማለት ሲያወሳ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በአማራ ክልል 10 ሺሕ ሄክታር መሬት ዜሮ ነጥብ ሰባት በመቶ ብቻ የትራክተር ሜካናይዜሽን ተጠቃሚ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ/ር) ተናግረው ነበር።

ታዲያ የትራክተር ተደራሽነት አናሳ መሆኑ እንዳለ ሆኖ የማሳ ከብቶች መሬት በጦርነት በሞቱበት ሁኔታ የምርት እድገት ለማሳየት ከባድ እንደሚሆን አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
በ2014/15 የምርት ዘመን ከፍተኛ ጥረትን በማድረግ 300 በላይ ትራክተሮች ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለአርሶ አደሮች ማከፋፈል መጀመራቸውን አስረድተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት፣ ክልሉ 30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ የግብርና መካናይዜሽን ቁሳቁስ እያስገባ ነው። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ክልሉ 26 ሺህ ትራክተሮችን፣ 8ሺህ ኮንባይነሮችን ለማስገባት ማቀዱም ተመላክቷል። ይህም በክልሉ 500 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ሜካናይዝድ ለማድረግ ታስቧል መባሉ አይዘነጋም።

“የምርት ወቅትን ከፍ ማድረግ” እንዴት?
መሰረተ ልማቶች በወደመበት አካባቢ ለእርሻ አገልግሎት የሚረዱ እንስሳቶች መሞታቸውን ተከትሎ፣ አርሶ አደሮች በኹለት በሬ ከማረስ በአንድ በሬ ለማረስ የተገደዱባት፤ ዜጎች ቄያቸውን ትተው በመፈናቀላቸው ማሳዎች ጾም የሚድሩባት በጦርነት የምትቆላ ኢትዮጵያ ላይ የምርት ወቅትን ከሦስት እስከ አራት ከፍ ማድረግ እንዴት ይቻላል? የብዙዎች ጥያቄ ነው።

በቀጣይ አስር ዓመታት መንግስት ለይቶ ካስቀመጣቸው የግብርና ልማት የትኩረት አቅጣጫዎች “የመስኖ መሠረተ ልማቶች ተጠቅሞ በዓመት ውስጥ ያሉንን የምርት ወቅቶች ወደ 3 ወይም 4 ከፍ ማድረግ” በኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ ተመዝግቧል።
በዚህም “በእያንዳንዱ ክፍለ ኢኮኖሚ ያሉ አቅሞችንና ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ዝቅተኛ የምርታማነት መነሻዎች ታሳቢ በማድረግ ኢኮኖሚው ከ2013 እስከ 2022 ባሉት አስር ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ በ10 በመቶ እንዲያድርግ ታቅዷል” ነው የተባለው።

ድርቅ – “ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ”
ጦርነቱ በእንስሳት ላይ ካሳደረው የሞትና የዝርፊያ ክስተት በተጨማሪ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች የተከሰተው ድርቅ ሌላኛው መፍትሄ የራቀው “ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኗል።
በሶማሌ ክልል ካሉ 11 ዞኖች መካከል በ10ሩ ውስጥ ከሚገኙት 93 ወረዳዎች 86ቱ በድርቅ መጎዳታቸውን ተከትሎ ከ 800 ሺሕ በላይ እንስሳቶች መሞታቸው ተመላክቷል። በተጨማሪም ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የምግብ ድጋፍ የሚያሻቸው ሲሆን፤ አንድ ሺሕ 100 የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸውን ተከትሎ ከ150 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለመራቅ ተገደዋል።

በተጨማሪም፤ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በሚገኙ 13 ወረዳዎች ድርቅ በመከሰቱ 13 ሺሕ ከብቶችና ፍየሎች የሞቱ ሲሆን፤ በቅርቡ 212 ቀበሌዎች ዝናብ ቢያገኙም 38ቱ ከእነዚህ በተቃራነው ናቸው ተብሏል። በዚህም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች ችግር ላይ መሆናቸውን የተለያዩ የሚዲያ ተቋማቶች መዘገባቸው አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ምርት የምታገኘው በብዛት የክረምት ወርን ጠብቆ በሚዘንበው ዝናብ፤ በከፊል ደግሞ በበጋ ወቅት አልፎ አልፎ በሚገኝ የበልግ ዝናብ አማካይኝነት ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የመስኖ ውሃን በመጠቀም ነው።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የግብርና ምርት (agricultural GDP) ዕድገት ከ2003 እስከ 2012 በጀት ዓመት በአማካይ በየዓመቱ የ5.3 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ቢሆንም፣ በዕቅድ ከተያዘው ከ8 በመቶ በላይ አማካይ የዕድገት ምጣኔ ግብ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን ያለፉት አስር ዓመታት (2003-2012) የልማት አፈጻጸም አመላክቷል።

ላለፉት 10 ዓመታት በግብርና ውስጥ ከሚጠቃለሉት ዋና ዋና ንዑስ ዘርፎች መካከል የሰብል እና የእንስሳት ሀብት በአማካይ በየዓመቱ በቅደም ተከተል 6.1 በመቶ እና 3.7 በመቶ እድገት ቢያሳይም፤ ከዓመት በላይ ተጋርጦ የቆየውና ያልተቋጨው ጦርነት እንዲሁም ድርቅ የእንስሳት ዕድገቱን ዝቅ ያደርጋል የሚል ስጋት ከወዲሁ አጭሯል።

በአማራና በአፋር ክልል በጦርነቱ ሳቢያ የሞቱት እንስሳቶች “በርካታ” ከመባል ውጭ በትክክል በቁጥር ባይታወቁም በድርቅ ምክንያት በሶማሌና በአፋር ክልል ከ813 ሺሕ እንስሳቶች በላይ ሞተዋል። ከሟች እንስሳቱ መካከል የእርሻ ከብቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ ይህም በግብርናው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በርካቶች ያወሳሉ።

ቅድሚያ ጦርነቱ ይቋጭ
ከተለያዩ ቦታዎቸ የተፈናቀሉ ከ11.6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአማራ ክልል ብቻ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ሲሆን፣ በጦርነት ምክንያት አካባቢያቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ከ300 ሺሕ በላይ ዜጎች እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት ዘግባ ነበር።
እንደ ዘገባው ከሆነ፤ በአፋር ክልልም እንዲሁ ከ350 ሺሕ በላይ ዜጎች በጦርነቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው እየተገለጸ ቆይቷል። ዜጎች ላይ ርሃብ በተጋረጠበት ሁኔታ ከምንም በላይ ጦርነቱን እንዲቋጭ ማድረግ ተቀዳሚ የማይኖረው ቀዳሚ ጉዳይ መሆን አለበት የሚለው ትክክለኛው ድምጽ ነው።

ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን በምርት የተሻለ ዕድገት ማምጣት የሚቻለው እርፍ የሚጨብጠው አርሶ አደር ውሎ ሲገባ የሚያርስበትም ከብት ሲኖረው ጭምር መሆኑ ይታመናል።
በመጀመሪያ ደረጃ አርሶ አደሮች ታግተው የሚገደሉበት ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት ሊቆም እንደሚገባ ቅሬታ እየተነሳ ነው።
በኢትዮጵያና በህወሓት ጦርነት መካከል መከላከያ ከባድ መሳሪያ ለጠላት እየተወ ሲሸሽ ባልተሟላ ትጥቅ ጦርነቱን የመመከት ግዳጅ ተጥሎበት የነበረው አርሶ አደሩ ነው።
በጎንደር በኩል ጭና፤ ላይ ጋይንት፤ ንፋስ መውጫ ተሰኙት ቦታዎች በርካታ አርሶ አደሮች ህይወታቸው እንደተሰዋ እንስሳቶች እንደተዘረፉ ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን በሽርተኝነት የተፈረጀው የኦነግ ሸኔ ቡድን የሚሰነዝረውን ጥቃት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች አርሶ አደሮች ለዓመታት እየታገቱ እየተገደሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ በበኩሏ በርካታ ዜናዎችን አጠናቅራለች።
በተለይም በሊሙ ወረዳ የሚገኘው ሰፊ የእርሻ መሬት የመታረስ ጊዜው አልፎበት ፆም እንዳደረ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። በወለጋ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው እርሻ እንዳልተዘራ፣ በአንዳንድ አካባቢ የተዘሩ እህሎችም እንክብካቤ እንዳላገኙና የምርት ውጤታቸው አጥጋቢ እንደማይሆን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ስፍራው የበቆሎ፣ የአኩሪ አተር፣ የቦለቄ፣ የሰሊጥ፣ የለውዝና የኑግ ምርት በስፋት እንደሚመረትብት ያወሳሉ።

ታዲያ ይህ ድርጊት እልባት ሳይሰጠው ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በዚህ ሁኔታ ምርት መጠንን ከፍ ማድረግ ይቅርና ለአካባቢው ነዋሪዎች የዕለት ጉርስ ማግኘት ችግር የሆነበት ወቅት ሆኗል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጳጉሜ አንድ 2013 ባወጣው መረጃ መሰረት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በሚሰነዝረው ጥቃት የእርሻ ማሳዎች በዘር ሳይሸፈኑ እንደቀሩና፤ ቀድመው የተዘሩት ሰብሎችም በወቅቱ እንክብካቤ ባለማግኘታቸው በአረም፣ ተባይና በእንሰሳት መውደማቸውን አመላክቶ የመልሶ ማሻሻያ ዕቅድ ዝግጀት ላይ ሲገልጽ ቆይቷል።

አሁን ላይ በዕቅዱ መሰረት በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች መስኖን በመጠቀም የማካካስ ሥራ እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል።
ይሁን እንጂ፣ ከውድመቱ አንጻር ሲታይ ይህ በቂ እንዳልሆነም እየተገለጸ ነው። ይህ ሙከራ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ተመሳሳይ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የምርት ማካካሻ አለመደረጉ የአካባቢውን ነዋሪ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ዜጎችንም ወደ ኋላ ይጎትታል።
በመሆኑም በአጣየ፤ በወለጋ እንዲሁም በጭና ያሉ አርሶ አደሮች መንግስት መለስ ብሎ እንዲመለከታቸው እያሳሰቡ ይገኛሉ። አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ባረጋገጠችው መሰረት አጣዬ ዙሪያ የሚገኙ የነዋሪ ቤቶች ወድመዋል፤ የመስኖ ማሳዎች እህል በሚያበቅሉበት ፈንታ የእሾህና አሜኬላ መብቀያ ሆነዋል።

የማዳበሪያ ነገር
ማዳበሪያ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችል ግብዓት ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በጥቅም ላይ እያዋሉት ይገኛሉ። በመሆኑም ማሳው ማዳበሪያን መመገብ ስለለመደ የተለመደውን ማስቀረት የምርት መጠኑን እንዲቀንስ ማመቻቸት መሆኑን አርሶ አደሮች ይገልጻሉ።

ዘመናዊ ማዳበሪያ ከመምጣቱ በፊት ሲጠቀሙት የነበረው ባህላዊ ማዳበሪያ የከብት እዳሪ (በተለምዶ ፍግ) እና የቆሻሻ ጥራጊ እንደነበር የገለጹት አርሶ አደር ዘውዱ መንገሻ፣ የዘመናዊ ማዳበሪያ ዋጋ በመጨመሩ የመግዛት አቅም ስለሌላቸው ሳይጠቀሙ ሲቀሩ የምርት መጠኑ እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

ዘንድሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የማዳበሪያ መግዣ ዋጋ በቅጽበታዊ ሁኔታ እንደጨመረባቸው እየተናገሩ ነው።
የማዳበሪያ ነገር የክልሉ፤ እንዲሁም የፌደራሉ ችግር ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ችግር ነው ያሉት አምሳሉ፤ የማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩንና ዕጥረት መከሰቱን ጠቅሰው፤ ለችግሩ መንስኤም በሩሲያና በዩክሬን የተፈጠረው ጦርነት ወደሐገር የማስገባት መጠኑን ስለጎዳው ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ባህላዊው ማዳበሪያ ተረሳ?
ዘመናዊ ማዳበሪ (ዩሪያና ዳፕ) ከመምታቱ በፊት ብዙሃኑ የማህበረሰብ ክፍል ማዳበሪያ ሲያገኝ የነበረው የከብት እዳሪ (በተለምዶ ፉግ) በማበስበስ፤ የተለያዩ ጥራጊዎን፣ የትንንሽ እጽዋትን ጉድጓድ ውስጥ በመቅበርና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አውጥቶ ማሳው በመታረስ በሚለሰልስብት ወቅት ላይ በመነስነስ ነው።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ወይም ብስባሽ በስነ-ህይወታዊ ሂደት የተብላላ ኦርጋኒክ ወይም ካርቦኒክ ቁስ ሲሆን የተፈጥሮ በስነ-ህይወታዊ ሂደትን የማፋጠን፣ ማለትም በቀላሉ ሊብላላ የሚችላቸውን ሁኔታዎች (ለምሳሌ፡- አደራደር ማናፈስ እና የሚፈለገውን ያህል ብቻ ማርጠብ) በማመቻቸት የሚዘጋጅ መሆኑን ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ድረ ገጽ አብራርቷል።

ዘመናዊ ማዳበሪያ ከመጠቀም ይልቅ የተፈጠረውን መጠቀም ምርትና ምርታማነትን የመጨመር ድርሻው የላቀ መሆኑን ለስራው ቅርብ ሆኑ አርሶ አደሮች ይናገራሉ።
ይህ የሚሆነውም ዘመናዊ ማዳበሪው የምርቱን ፍሬ ከማብዛትና ከማፋፋት ይልቅ የሰብሉን አገዳና ቅጠል ብቻ ሲለሚያሳድግ ነው። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን አምዴ አምባ ተብላ በምትጠራ ቀበሌ የሚገኙ አርሶ አደር ተመስገን አለሙ በበኩላቸው፣ ከዘመናዊ ማዳበሪያ ይልቅ የተፈጥሮው ጠቃሚ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የአካባቢው አርሶ አደር ማዳበሪያ ሲገዛ ተመስግን ገዝተው አያውቁም የሚያመርቱት ግን ዘመናዊ ማዳበሪያ ከሚጠቀሙት ያልተናነሰ እንደሆነ ይናገራሉ።

“ኮምፖስት ወደ አፈር ከሚጨምረው ንጥረ ነገር በተጨማሪ አፈሩ ውስጥ በነበረው በራሱ እፅዋት ሊወስዱት በሚችሉበት መልክ እንዲኖሩ ያደርጋል። ስለዚህ ኮምፖስትን በመጠቀም የአፈሩን ፊዚካል ባህሪይ ከማሻሻልም በተጨማሪ የሰብሉ ምርታማነት ሳይቀንስ፣ ነገር ግን የሚያስፈልገውን የሰው ሰራሽ ኬሚካል ማዳበሪያ ፍላጎት በግማሽ ቀንሶ ማምረትን ያስችላል” የሚለው ጉዳይም በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በሰፊው ተብራርቶ ይገኛል።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here