ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወር ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በቀጣይ የክረምት ወቅት በጎርፍ ሊጠቁ ይችላሉ በተባሉ ዝቅተኛ አካባቢዎች ላይ አደጋው ጉዳት እንዳያስከትል የጎርፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩ ተመላክቷል። ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ እንዲሁም በወንዝ ዳርቻ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን፣ በክልሎች በኩል ወደ ሌላ ምቹ ወደሆኑ ቦታዎች የማዘዋወር ሥራ መጀመሩን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘውዴ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በቀጣይ የክረምት ወቅት በሰሜን፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ በሰሜን ምዕራብ በሚገኙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከመደበኛው በላይ ዝናብ ይኖራል መባሉን ተከትሎ፣ ኅብረተሰቡ በጎርፍ ተጠቂ የሚሆንበት እድል መኖሩን ኃላፊው ጠቁመዋል።
ከላይ በተጠቀሱት እና በድሬድዋ ከተማ፣ በአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ እና በሌሎች ዝቅተኛ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ጉዳት እንዳያደርስ በፌዴራል እና በክልሎች በኩል ራሱን የቻለ የጎርፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ደበበ አክለውም፣ ባለፈው ዓመት ጀምሮ በጎርፍ ተጠቂ በሆኑ ዝቅተኛ ቦታዎችና በወንዝ መፋሰሻ አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲነሱ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፍሩ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ዝቅተኛ የወንዝ መፋሰሻ አካባቢዎች ላይ መፋሰሻዎች አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ የቅድመ ዝግጅቱ ሥራ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች በኩል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የጎርፍ አደጋ የመከላከል አቅምን ለማሳደግም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኦሮሚያ ክልል፣ በአፋር ክልል እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ለኅብረተሰቡ እና ለሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ሥልጠና የመስጠት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስተባባሪነት የጤና ተቋማት፣ የግብርና ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ እና በደቡብ ክልል እና በሌሎች አካባቢዎች የመሬት መንሸራተትና መሰንጠቅ እንዳያጋጥም ከባለፈው ዓመት መነሻ ጀምሮ የዝግጅት ሥራ መጀመሩም ተነግሯል።
በሌላ በኩል፣ በአዲስ አባባ ከተማ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ 161 ቦታዎች ተለይተው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ ሊጀመር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
በመዲናዋ በብዙ ቦታዎች መጠኑ ቢለያይም፣ ለጎርፍ አደጋ የሚጋለጡበት እድል እንዳለ እና ከነዚህ ቦታዎች በዋናነት ፒያሳ፣ አምባሳደር፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወንዝ ዳርቻ አካባቢዎች እና በሁሉም ክፍለ ከተማ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች መለየታቸውን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የወንዝ መፋሰሻዎች አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ የድጋፍ የግንባታ ሥራ እና በተለያዩ ቦታዎች በአዲስ መልክ የፍሳሽ ማስወገጃ ድሬኔጅ መስመሮችን ከመሥራት ባለፈ በባዕድ ነገር የተደፈኑ መስመሮችን የማፅዳት እንዲሁም የማደስ ሥራ ይከናወናል ተብሏል።
የቅድመ ዝግጅቱ ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እና ከወንዞች ዳርቻና የአረንጓዴ ልማት ማስፋፊያ ቢሮ እና ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሠራ ተነግሯል።
በመጪው የክረምት ወቅት ጎርፍ እና መሰል አደጋዎች ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ስለሚኖር፣ የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ማስታወቁም ይታወሳል።
በኢትዮጵያ በሰሜን ምሥራቅና ምዕራብ አካባቢዎች ላይ ዝናብ እየጨመረ እንደሚሄድ እና የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ከወዲሁ አደጋዎች እንዳይፈጥሩ ኅብረተሰቡም ሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀድመው የመከላከል ሥራ እንዲሠሩ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014




ዜና መስራቱ ጥሩ እኛም ሰርተነዋል ።
የሚገርመኝ ከዛሬ 1አመት በፊት 59አባወራዎች የኦሮሚያ ክልል የቢሻን ጉራቻ ነዋሪዎች የሀዋሳ ሀይቅ ሊበላቸው ነው ብለን ዜና ሰራን ሰዎቹም በኮሚቴ ተደራጅተው አዲሳባ ደረስ ሄደው ምትክ ይሰጣቸው ይቋቋሙ ብሎ ወስኖ ላከደብዳቤ ደብዳቤውን ለምርጫ ፍጆታ 18ሰዎች ከሰጡ በሆላ ምርጫ አለፈ የሚገርመው በዚያ ግርግር ከንቲባውን ጨምሮ የቢሮ ሰራተኞች መሬት ተሰጣቸው
ይህን ጉዳይ በደንብ አውቃለሁ ጋዜጠኛም ነኝ።በጉዳዩ ላይ ለሰራ ሰነሳ በርካታ ማስፈራሪያ ከመንግስት ሰዎች ደርሶኛል
ሰዎቹ ከግማሽ በላይ ልጆቻቸው ጠር ግንባር ዘማችና ዘምተው ምስዋኤትነት የከፈሉ የሚገርመው አሁንም የሜትርዮሎጂ ዜና ሳገላብጥ እየነዛ43አባወራዎች ህይወት ያስጨንቀኛል።
ብትችሉ የፍለፊታችን ክረምት ሳይገባ የነዚህ ሰዎች የጀግኖች እናት በመታደግ ታሪክ እንስራ። የፖለቲካው ዥዋዥዌ ከዚህ በላይ ብላችሁ ሌላ ትርጉም ስለሚሰጠኝ ነው።