መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛአራቁቶ የማሰለፉ ስጦታ

አራቁቶ የማሰለፉ ስጦታ

ሰሞኑን መነጋገሪያ ከነበሩ አንኳር አገራዊ ጉዳዮች ተርታ ባይመደብም፣ እንደ ሕዝብ ትዝብት ላይ የጣለ ተግባር በመሆኑ የተኮነነ ድርጊት ነበር። ተግባሩ ሙሉ በሙሉ የተተቸ ባይሆንም ለበጎ ዓላማ ተብሎ የተደረገ አሳፋሪ ተግባር ነው በሚል ነበር፣ ‹ክብር አዋራጅ› የተባለው ልግስና የተተቸው።

ባለታሪኩ ብዙዎች የሚያውቁት ባለሀብት ነው። ከሌሎች በሀብት በልጦ ሳይሆን በጉራ የሚደርስበት እንደሌለ የሠራቸውን የተቀረፃቸውንና ራሱ የሚናገራቸውን ይዘቶች እያቀረቡ የሚናገሩ አሉ። ሥሙን መጥቀስ ባያስፈልግም፣ አንድ ሕይወቴ ብሎ ቅንጡ ውሎውን በድህነት ሕይወቱን እየገፋ ላለ ሕዝብ ከሚያስጎበኝ ግለሰብ በስተቀር፣ በኩፈሳ የሚደርስበት እንደሌለ ይነገራል።

ይህ ባለሀብት ነኝ እወቁልኝ በማለቱ መነጋገሪያ የሆነ ሰው፣ በአንድ ወቅት የነበረበትን ችግር ከማውራት ውጪ፣ እንዴት እንዲህ ጉረኛ ያደረገውን ሀብት እንዳገኘ ሲናገር አይደመጥም። ሌሎች ሠርተው እንዲለወጡ ከማድረግ ይልቅ እንዲሸማቀቁና እንዲያፍሩ በማድረግ ራሱን ለማግነን እንደሚሞክርም የሚያውቁት ሲናገሩ ይደመጣል።

ይህ መነጋገሪያ ሰው የሌላን ክብር የሚነካ ተግባርን ፈፀመ ብለው ሠሞኑን በርካቶች ሥራውንና ስብዕናውን ሲተቹ ተደምጠዋል። ግለሰቡ ልደቴን ላክብር ብሎ ያደረገው ነገር ነው ሌላ መነጋገሪያ እንዲሆን ያደረገው። ለልደቱ ለራሱ ስጦታን በመቀበል ፋንታ ለሌሎች ልብስ ልስጥ ማለቱ ሊያስመሰግነው በተገባ ነበር። ነገር ግን፣ በእለቱ ያደረገውን ልግስና እንደለመደው በምስል አስቀርቶ እዩልኝና አድንቁኝ ማለቱ ብቻ አይደለም መነጋገሪያ ያደረገው።

በእለቱ ልብስ እሰጣችኋለሁ ብሎ በርካታ ወጣቶችን አሰልፎ ነበር። ታዲያ የሚሰጣቸውን ልብስ ይዘው እንዳይሄዱና እንዳይሸጡት አስቦ ይሁን አይሁን ባይታወቅም፣ እዛው እንዲለብሱ አስደርጓል። ተራ ሲደርሳቸው እያስወለቀ እንዲለብሱ ማድረግ ሳይሆን እርቃናቸውን ተሰልፈው እንዲጠብቁና የስጦታ ሸሚዛቸውን እንዲቀበሉ አድርጓል። እንዲህ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ይህን ሲያደርግ በተንቀሳቃሽ ምስል አስቀርፆ ድፍን ጦቢያ እንዲያየው ማስደረጉ ብዙዎችን አሳዝኗል።

በፊት በፊት ለተቸገረ ልብስ የሚሰጡ፣ ተቀባዮቹ ገላቸውን እንዲታጠቡ አድርገው የተቀዳደደ ልብሳቸውን መልሰው ለብሰው የተሰጣቸውን እራፊ እንዳይሸጡ ተረክበው ያቃጥሉባቸው እንደነበር ይነገራል። ይህን ሲያደርጉ ግን ተረጂዎቹ ቢያንስ ሲቆሽሽ የሚቀይሩበት ልብስ እንዲኖራቸው አድርገው ነበር ልግስናቸውን የሚያከናውኑት ይባላል። ይህን ሲያደርጉ ግን የአስተዳደጋቸው ሥነምግባር ስለሚገድባቸው፣ ያከናወኑትን ልገሳ እንደ አሁን ዘመን እወቁልኝ እያሉ ሥም ለማትረፍ አይጥሩበትም ነበር።

ከሠሞኑ መነጋገሪያ የሆነው የባለሀብቱ ተግባርን ብዙዎች ስለለመዱት እምብዛም ባይከነክናቸውም፣ አንዳንዶች ግን ወጣቶችን አሰልፎ ክብራቸውን በሚያጎድፍ መልኩ ማስታወቂያ ሠራ ብለው ወቀሳቸውን ከማስፈራሪያ ጋር ሰንዝረዋል። የተወሰኑት ሀብትህን እንዴት እንዳገኘኸው ስለምናውቅ ከእንግዲህ እንደሌሎች መሰሎችህ አንገትህን ደፍተህ የማትኖር ከሆነ አንተንም እናዋርድሃለን ሲሉ ዝተውበታል።

ከግለሰቡ ተግባር ጋር በተገናኘ፣ ምን አገባችሁ እርቃናቸውን የተሰለፉት ሳይናገሩ እናንተ ምን ቤት ናችሁ ያሉም ነበሩ። ያም ተባለ ይህ፣ የትኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ሀብቱን ያፈራ ግለሰብ ከድሃው ማኅበረሰብ አላግባብ በልጽጎም ይሁን በዝብዞ እንዳገኘው በመገንዘብ፣ ፍትኃዊ ስርዓት በሌለበት አገር በሀብቱ መመፃደቅ እንደማገባው ማስገንዘብ ያስፈልጋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

2 አስተያየቶች

  1. መቼም የጅማው ባለሃብት ነኝ ባይ መንሱር ነው ይህን ሊያደርግ የሚችል

  2. አድስ ማለዳ ጋዜጣ የምታነሣው ሀሣብ ለየት ያለና ቀልብ እሚሥብ ነው ለምሣሌ የኑሮ ውድነትን በተመለከት እምሠሩት ዘገባ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን/ ተቀጣሪዎችን እንደምሣሌ እያነሣችሁ እምትሠሩት ዘገባ ፤ የተለያዩ ባለሙያዎችን በተለያዬ ርእስ ላይ ሀሣባቸውን እንዲያጋሩ በመጋበዛችሁ ያሥመሠግናችኋል። በዚሕ ሠው ሕሊናውን ሸጦ ለሆዱ ባደረበት ዘመንና መንግሥት ነኝ ባዩ አካል ሙሠኛና አግበሥባሽ በሆነበት የዜጎችን ሕይወት መለስ ብሎ ከማየት ይልቅ ድግስና ቼበር ቻቻን ዋና የሥራ ዘርፍ አድርጓል። እመረዋለሁ እሚለው ሕዝብ ያለው አዉሮጳ ይመሥላል ድርጊቱን ሥናይ።
    ለምሣሌ በሚሊዬን እሚቆጠሩ ዜጎች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በድንኳን፣ በየዋሻውና በመሣሠሉት በሥቃይና በመከራ ውስጥ ሆነው የየእለት ሕይወታቸውን እሚገፍትን ማንም ባለሥልጣን ዞር ብሎ 1 ቀን እንኳን ያያቸዉ የለም። በተቃራኒ በየጊዜው የበጋ ስንዴ ልማት እያሉ ይጎበኛሉ ከዛም ዘለል ካለ ሥለ ከተማ ግብናና የጓሮ አትክልት ያዎራሉ ለዛውም መሬት ላይ ጠብ እሚል ነገር አላየንም። ምርታማነት ወይም የምግብ አቅርቦት እሚጨምረው በሠፋፊ እርሻ ልመትና የዜጎች ተዘዋዉሮ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብት በሕግ ሲረጋገጥና ለተግባራዊነቱም የሚተጉ ተቋሟትና መንግሥት ሲኖር ነው።
    በዚሕ ደላላ በሚራዉና ዘር የሐብት ምንጭ በሆነበት እንዳሁም ምሥቅልቅሉ በወጣ ኢኮኖሚ ከባለሥልጣናት ጋር በጥቅም ሠንሠለት በመተሣሠር ድሀውን በመበዝበዝ በሚያከማቹት ሀብት ከዚሕም የባሠ ያደርጋሉ ምክንያቱም የሞራል ልዕልና የለማ። ሌላው ባለፈው ሣምንት በሁለት ተከታታይ ርዕሥ አፈናውንና የጋዜጠኞችን እስር በተመለከተ በሠራችሁት ዘገባ ከልብ አመሠግናለሁ። እሚገርመው ባደረግሁት ዳሠሳ ይሕን ርእስ በተመለከተ ዘገባ የሠራችሁት እናንተና ቢቢሲ አማርኛ ብቻ ናችሁ ከተሣሣትሁ እታረማለሁ። ይሕ ደግሞ ትልቅ መልእክት አለው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች