በአዲስ አበባ ለአደባባዮችና የመስመር ዳር አረንጓዴ ማስዋብ ሥራ በ50 ሚሊዮን ብር በጀት ሥራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ማልማት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ኘሮጀክቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ማልማት ቢሮ በተጨማሪ ሌሎች የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች እንዲሁም ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የራሱን አሻራ የሚያሳርፍበት ቢሆንም፣ በቢሮው በኩል ግን ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለት ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ማልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ይመኙሻል ታገስ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ ከተማን ውብና ጽዱ ከማድረግ በተጨማሪ የቀጣይ የክረምት ወቅት መምጣቱን ተከትሎ በ11 አደባባዮች የአረንጓዴ ማልማት ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።
አደባባዮችን ጨምሮ በመንገድ ዳርቻዎች እና በፓርኮች በአጠቃላይ በ37 አካባቢዎች ላይ የአረንጓዴ ማልማት ሥራ መጀመሩ ተነግሯል። ኃላፊዋ አክለውም፣ የክረምት ወቅት ተገን ተደርጎ የተጀመረው የአረንጓዴ ማልማት ሥራው ግንቦት 24/2014 በመዲናዋ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ ከተማ በተለይ በትላልቅ አደባባዮች፣ በመንገድ ዳርቻዎች የአረንጓዴ ማልማት ሥራ ነው የተጀመረው።
በእነዚህ ቦታዎች ላይ 80 በመቶ የሚሆነው በችግኝ፣ በአበቦች፣ በሳር እንደሚሸፈን እና 20 በመቶ እንዲሁም ውኃ ለማጠጣት፣ ለአንዳንድ ዕይታዎች ምቹ እንዲሆን እና ለመንቀሳቀስ ክፍት መደረጉን ኃላፊዋ ጠቁመዋል።
የልማት ሥራው ኘሮጀክት በቀጣይ ኹለት ወር የሚተገበር ሲሆን፣ ቢሮው በመደበኛነት የሚያከናውናቸውን ሥራዎችም ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላም እንደሚያስቀጥል እና ከተማዋን በማስዋብና የዜጎችን አኗኗር በመቀየር ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል። በሥራው ላይ 40 ማኅበራት እና በአንድ ማኅበር ውስጥ ከ10 ያላነሱ ሰዎች በቢሮው በኩል በቋሚነት፣ እንዲሁም ከ 1ሺሕ በላይ ሰዎች በጊዜያዊነት የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል ተብሏል።
መዲናዋን በአረንጓዴ የማልማት ሥራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ማልማት ቢሮ ብቻ መከናወኑ በቂ ባለመሆኑ፣ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ አካባቢውን አረንጓዴ አሻራውን በማሳረፍ የበኩሉን እንዲወጣ ኃላፊዋ ጠቁመዋል። በተጨማሪ አዲስ አበባ ከተማን እንደስሟ አዲስ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የከተማው ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶችና በጎ ፍቃደኞች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያስቀምጡ ተጠይቋል።
ቢሮው በተጨማሪ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ቀጣይነትን ለማረጋገጥና የትውልድ አንዱ የባህል አካል እንዲሆኑ ለማስቻል የችግኝ ጣቢያዎቻችንን አቅም ማሳደግና ማዘመን ላይ እየሠራ መሆኑን አመልክቷል። የከተማዋን ሥነ ምህዳር ለመጠበቅ የሚረዱ አገር በቀል እፅዋትን፤ በምግብ ራስን ለመቻል የሚረዱ ፍራፍሬዎች፣ ለሕክምና እና መሰል ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች እንደሚዘጋጁም ተነግሯል።
በበጀት ዓመቱ ቢሮው 2.5 ሚሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት እንደ አቀደ እና አሁን ላይ 1.5 ሚሊዮን ችግኞችን ማዘጋጀት መቻሉ ተጠቅሷል።
የእንጦጦ ችግኝ ጣቢያ የከተማዋን የችግኝ አቅርቦት ፍላጎት ለመሸፈን የሚያስችል ጣቢያ ቢሆንም፣ ሙሉ አቅሙን ለመጠቀም የውኃና የመብራት ችግር እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የበጀት ማነቆ መኖሩ ተመላክቷል።
በበጀት ዓመቱ ችግኝ ለማዘጋጀት ከታቀደው ስድስት መቶ ሺሕ ውስጥ አምስት መቶ ሃምሣ ሺሕ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ጣቢያው ዘግይቶ ሥራ መጀመሩ ለእቅዱ አፈጻጸም ማነስ ምክንያት ነው ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014



