ዳሰሳ ዘ ማለዳ ሰኞ መስከረም 19/2012

1-ኢትዮጵያ በካናዳ ሞንትሪያል እየተካሄደ በሚገኘው 40ኛው አለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ጉባኤ ላይ በትራንስፖርት ሚንስትር  ዳግማዊት ሞገስ በኩል ተሳትፋለች ።አለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ዘንደሮ 75ኛ አመቱን ያስቆጠረ ሲሆን ኢትዮጵያ  ከመስራቾቹ መካከል አንዷ ነች።  በጉባኤው ኢትዮጵያ በኢንተርናሽናል ሬቨኑ ፓሴንጀር ሬት (IRPR) 90 በመቶ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ 36 የአለም ሃገራት ውስጥ አንዷ መሆኗ ተናግረዋል።(አዲስ ማለዳ)

…………………………………………….

2–ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ ወደ ናይጀሪያው ሮቻስ ፋዉንዴሽን ለነጻ የትምህርት እድል የሚልኳቸዉን 5 ወላጅ የሌላቸው ታዳጊዎችን በቢሮአቸዉ አነጋግረዋል።ታዳጊዎቹ ከ4 ህጻናት ማሳደጊያዎች የተመረጡ የ7ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸዉ።(አዲስ ማለዳ)

………………………………………………

3-የቢሾፍቱ -ጨፌ ዶንሳ-ሰንዳፋ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ በ914 ሚሊየን ብር ወጪ የሚገነባ ሲሆን ዛሬ መስከረም 19/2012 የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።መንገዱ 55ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን፥ ግንባታውንም ራማ የተሰኘ ሀገር በቀል የስራ ተቋራጭ የሚያከናውነው መሆኑ ታውቋል። በ3ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።(ፋና ብሮደካስቲንግ)

 

4-በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ የተቋቋመው የኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ግብጽ የሦስትዮሽ ብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን 5ኛ ስብስባውን በካርቱም ሱዳን ማካሄድ ጀመረ።የጥናት ቡድኑ  መስከረም 4 እና 5/2012 በካይሮ በተደረገው ስብሰባ ወቅት በተለዩ አጀንዳዎች ላይ የተወያየ ሲሆን ቡድኑ በካርቱም በሚካሄደው የሦስቱ ሀገራት ውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

……………………………………………..

5- ዘጠኝ አባላት ያሉት የሩሲያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ሰኞ መስከረም 19/2012 ለጉብኝት ጎንደር ከተማ ገብቷል። ልዑካኑ በከተማው የኹለት ቀናት ጉብኝት እንደሚያደርግ ይጠበቃል። (አብመድ)

…………………………………………….

6-አገር በቀል የመድኀኒት ሕክምና እውቀትን በመሰነድ እና በመጠበቅ የተጠናከረ ጥናትና ምርምርን ለማከናወን ይረዳል የተባለው የኢትዮጵያ የባህል መድኀኒት ጥናትና ምርምር የ5 ዓመት ፍኖተ ካርታ ይፋ ተደርጓል፡፡ፍኖተ ካርታው የባህል ህክምናውን በሳይንሳዊ  ምርምሮች በመደገፍ፣ ጠቀሜታውን በማጎልበት፣ የጎንዮሽ ጉዳቶችን በመቀነስ እና ከዘመናዊ ሕክምና ጋር ለማቀናጀት ያለመ ነው እንደሆነ የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን ተናግሯል።(ኤዜአ)

……………………………………………..

7- የአረጋዊያን ቀን በሀገር አቀፍ ደረጀ ለ28ተኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ ነገ መስከረም 20/2012 እንደሚከበር የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ (ኢቢሲ)

……………………………………………………………………………..

8 – ትላንት ሌሊት በተከሄደ በዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሃያ ኪሎ ሜትር እርምጃ ውድድር አትሌት የኀልዬ በለጠ 16ኛ ደረጀ ይዛ አጠናቀቀች፡፡(ዋልታ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here