በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃቶችን በማክሸፍ የ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ማዳን ተችሏል ተባለ

0
735

በኢትዮጵያ በ11 ወራት ከተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ከ97 በመቶ የሚልቀውን በማክሸፍ የአንድ ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ገለጸ።

የሳይበር ጥቃቱ በፋይናንስ እና የሚዲያ ተቋማት ላይ በብዛት ዒላማ ያደረገ መሆኑም ታውቋል። የሳይበር ምሕዳር በባህሪው ድንበር የለሽና ኢ-ተገማች በመሆኑ ዓለም በዚህ መጠን ሰፊና ተለዋዋጭ ወንጀል በየቀኑ በአማካይ 16 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሀብት እንደምታጣ ተመላክቷል።
የሳይበር ወንጀል በ2015 በዓለም ላይ 3 ትሪሊዮን ዶላር ካደረሰው ኪሳራ በእጅጉ እየጨመረ መጥቶ በ2021 ደግሞ 6 ትሪሊዮን ዶላር አሳጥቷል ነው የሚባለው።

በየዓመቱ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣው ዓለም ዐቀፍ የሳይበር ወንጀል በ2025 ከ10 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሊያሳጣ እንደሚችል ተገምቷል።

በኢትዮጵያም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 5 ሺሕ 860 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸው ነው የተገለጸው። ይህም በዓለም ላይ በየቀኑ በቢሊዮን ዶላር የሚያሳጣው የሳይበር ጥቃት ለኢትዮጵያም ፈተና መሆኑን ነው የተነገረው።

በ2011 ብቻ 790፣ በ2012 1 ሺሕ 80፣ በ2013 እንዲሁ 2 ሺሕ 900 የሳይበር ጥቃቶች መድረሳቸው ተጠቅሰዋል። በዘንድሮው በጀት ዓመት 11 ወራት ደግሞ 6 ሺሕ የሚደርሱ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸው ነው የተገለጸው።

በኢትዮጵያ ላይ የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ከየት እንደተሞከሩና የወንጀሉን ባለቤቶች በቀላሉ ለመለየት ባይቻልም ያነጣጠሩባቸው ተቋማት መለየታቸው ተጠቁሟል። መንግሥት ቁልፍ መሠረተ-ልማቶች፣ የፖለቲካ አደረጃጀቶች፣ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የጤና እና የትምህርት ተቋማትም በርከት ያለ ጥቃት ተሞክሮባቸዋል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here