መነሻ ገጽዜናትንታኔመዝናኛ ቦታዎች ማዘኛ ይሆኑ ይሆን?

መዝናኛ ቦታዎች ማዘኛ ይሆኑ ይሆን?

‹ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት› የሚለውን ተረት አስታወሰን እያሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ የሚታየውን የአካባቢ ማስዋብ ሁኔታ የሚተቹ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሰላም ማጣትን ጨምሮ ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው ድጋፍ የሚሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ባሉባት፣ ኑሮ ውድነት፣ ድርቅ እና ረሀብ ቤተኛዋ እየሆኑ በመሰለች አገር ችግኝ እና አደባባይ፣ ፓርክ እና መናፈሻ ቅንጦት መሆኑን በምሬት የሚናገሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ አለቃ ዮሐንስ በበኩላቸው ይህን ጉዳይ አንስተው፣ በቀድሞ ዘመን የነበሩ የመዝናኛና መናፈሻ ስፍራዎችን በማውሳት፤ አሁን ያሉት ‹መገንባታቸውስ ይሁን ግን መች ለተጠቃሚ ምቹና ቀላል ሆኑ!› ሲሉ ከገጠመኛቸው በመነሳት ተከታዩን ሐሳብ አንስተዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ካስተናገደቻቸው ግንባታዎች መካከል እንደዘንድሮው መዝናኛን ትኩረት ያደረጉ ንድፎችን የገነባችበት ጊዜ እንደሌለ ከታሪክ ድርሳናት እያስተያዩ መናገር ይቻላል። በቅዱስ ላሊበላ፣ በአብርሃ እና አጽብሃም ሆነ በእነ አፄ ፋሲል የተገነቡ ታላላቅ ግንባታዎች ዛሬም ድረስ ቢታዩም፣ ዓላማቸው ሀይማኖታዊ ወይም ደኅንነትን መሠረት ያደረጉ ናቸው።

በነገሥታቱ የታነፁ የተለያዩ ድንቃ ድንቅ አብያተ ክርስትያናት ዘመናትን እንዲቀዳጁ ከጠንካራ መገንቢያ ቁሳቁስ፣ አልያም ከአለት የተሠሩና ለትውልድ የሚተላለፉ ማምለኪያዎች እንደመሆናቸው አሁንም የተወሰኑት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

የፋሲል ግንብ እየተባለ የሚጠራው የተለያዩ ነገሥታት ቤተመንግሥትን ያቀፈው ግቢም፣ ዓላማው የነገሥታቱንም ሆነ የሥርዓቱን ደኅንነት ማስጠበቅና ከጠላት መከላከል ነው። የሐረሩ ጀጎል ግንብም በተመሳሳይ የከተማውን ነዋሪ ከውጭ ጠላት ለመጠበቅና ለሕዝብ ደኅንነት ታስቦ የተገነባ ነበር።

ከሃይማኖታዊ ፋይዳቸው ባሻገር፣ ለሕዝብም ሆነ ለመንግሥታቱ ደኅንነት ተብለው የተገነቡት ታላላቅ ሥራዎች፣ እስከ ዛሬም የቆዩት በሕዝቡ ዘንድ ባላቸው ተቀባይነት መሆኑ ግልፅ ነው። ይህ የሆነው ግንባታዎቹ የሚካሄዱት በሕዝብ ሀብት እንደመሆኑ ጥቅማቸውንም ከሀብታሙ እስከ ድሀው የኅብረተሰብ ክፍል ስለሚገነዘበው ነው።

በተመሳሳይ አስተሳሰብ ለዘመናት የተጓዘው የኢትዮጵያ እድገት በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን ዘመናዊነትን ተላብሶ ቀጥሎ ነበር። ባንክን የመሳሰሉ ሀብትን ማከማቻና ለብቻ መጠቀሚያ መንገዶች ባልዳበሩበት በእነዚያ ዘመኖች፣ የመኳንንቱና የገበሬው ሕይወት የአሁኑን ያህል በተጋነነ መጠን የተለያየ አልነበረም። ቅንጡ የሆነ ሕይወትንም በተንደላቀቀ ሁኔታ እንዲመሩ የሚያደርጋቸው መዝናኛም ሆነ የመቅበጫ ቦታም እንደ አሁኑ አልነበረም። ሌላ አገር ለመዝናናት እንሂድ ቢሉም ሁኔታዎች ምቹ ስላልነበሩ ገዢና ተገዢዎች በተመሳሳይ አቅጣጫ ሕይወታቸውን ይመሩ እንደነበር መገመት ይቻላል።

ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ወዲህ ግን ነገሮች መቀያየር ጀምረው ነበር። ዘውዳዊው ቤተሰብ ከሕዝቡ ተነጥሎ በራሱ ዓለም በቅንጡ መገልገያዎች ተከብቦ ሕይወትን ይገፋ እንደነበረ የተካሄዱት አመፆችና ያስከተለው መዘዝ አሁንም ድረስ ታሪኩን እንድናየው አድርጎናል። ንጉሠ ነገሥቱ ዓለም ዐቀፍ ዝናን ባገኙበት በዚያ የሥልጣን ዘመናቸው፣ የውጪውን ዓለም ድሎት መመልከት በመቻላቸው ለቤተሰባቸውም ሆነ ለቅርብ ሰዎቻቸው የሚሆን ቅንጡ ነገሮችን በብዛት ማስገባት የጀመሩበት ዘመን እንደነበርም ይነገራል።

በተለምዶ ሲባል እንደሚሰማው፤ ከውሻቸው ጀምሮ ብዙኀኑ ኢትዮጵያዊ የማያገኘውን ምቾት ለራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው በማድረጋቸው ከኅብረተሰቡ እንዲለዩና የኋላ ኋላ ተቀባይነት እንዲያጡ ማድረጉም በምክንያትነት ይነሳል። ለልደታቸው ከተጋገረላቸው ኬክ ጀምሮ ቅንጡ መኪኖቻቸውና ቤተመንግሥቶቻቸው ውብ እንዲሆኑ ለዓመታት መድከማቸውና ለዚያም ዓላማቸው ከፍተኛ ሀብት እንዳወጡ ይነገርላቸዋል።
የገንዘብ ምንጫቸው የግል ሀብታቸው ነው ወይስ የሕዝብን ሀብት ነው ለግል ፍላጎታቸው ማራመጃ የተጠቀሙበት የሚለው አሁንም ድረስ አጠያያቂ ነው። ሆኖም ከግላቸውም ይሁን ከሕዝብ ሀብት ላይ በቀጥታ ይቆንጥሩት፤ ዞሮ ዞሮ እዚሁ አገራችን የተፈራ ሀብት መሆኑን የሚከራከር የለም።

ለንጉሣዊው ሥርዓት መቋረጥ ምክንያት ተደርገው የሚነሱ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የሕዝቡ ረሃብና መደህየት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የንጉሠ ነገሥቱን ጨምሮ የመኳንንቱ ቅንጡ ሕይወት በዋናነት ከሚጠቀሱት ምክንያች መካከል ናቸው።

የዘውዳዊው ሥርዓት ከሕዝብ መነጠሉን እንደመነሻ አድርጎ እሳቸውን ከሥልጣን ገለል አድርጎ በትረ መንግሥቱን የጨበጠው ደርጉ በመባል የሚታወቀው ወታደራዊው መንግሥት የተጓዘው በተቃራኒው ነበር።

የቅብጠት የተባሉ መዝናኛዎችንም ሆነ መገልገያዎችን ሹመኞቹ እንዳይጠቀሙ ከማዘዝ ጀምሮ ሰማያዊ ካኪን ባለሥልጣናቱ እንደ ደንብ ልብስ እንዲለብሱ ጭምር ያስገደደ ነበር። ሥርዓቱ ሥልጣን ላይ በቆየባቸው 17 ዓመታት መሠረተ ትምህርትን በዘመቻ መልክ ለኹሉም ለማዳረስ በመሞከር የሚያስመሰግን ተግባር አከናውኗል። ለሕዝብ መዝናኛ ብሎ ግን በየቀበሌው ካቋቋማቸው ስፖርት ማዕከላት (የእግር ኳስ ሜዳ) እንዲሁም ሕዝቡ በርካሽ ከሚጠቀምባቸው መጠጥ ቤቶች ውጪ ይሄ ነው የሚባል ብዙ ወጪ የወጣበት መዝናኛ ቦታንም ሆነ ማዕከልን ስለማስገንባቱ የተነገረ ነገር የለም።

የአብዮቱ 10ኛ ዓመትን ለማክበር ግን ዋና ከተማዋንና የክፍለ አገር ከተሞችን በብዙ ወጪ አሸብርቆ እንደነበር በጊዜው የነበርንም የምናስታውሰው ነው። የቅስቀሳ ማስታወቂያዎችም ሆኑ አደባባዮችንና ሐውልቶችን ለማሳመርና አገርን ውብ አድርጎ እንግዳን ለመቀበል የተደረጉ ጥረቶችም ነበሩ። እንዲየም ሆኖ ግን ለምሳሌ ወሎ ሰፈር መታጠፊያ በስተግራ የነበሩ ደሳሳ ሰፈሮች እንግዶች ሲገቡ ዐይተው ላለማፈር በአጥር እንዲዘጉ ተደረገ እንጂ፣ እነሱ ተነስተው በምትካቸው ባለሀብት ሕንፃውን እንዲያሰፍርባቸው አልተደረገም ነበር።

የጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያምን ሕይወት በተመለከተ፣ ከሐረር የጦር ካምፕ ያመጡትን የግል የቤት እቃዎቻቸውን ለፕሮቶኮል ሲባል እንዲቀይሩ ቢጠየቁም፣ አሻፈረኝ ብለው በአሮጌ ሶፋቸው የአገር መሪዎችን ጭምር ያስተናግዱ ነበር። በዚህ ቅር የተሰኙ ሹማምንት ግን ለጉብኝት ወደ ውጭ ሲወጡ ጠብቀው በችኮላ ዘመናዊ ሕንፃ አስገንብተው ዓለም ዐቀፍ ደረጃውን በጠበቀ እቃ ቤታቸውን እንደሞሉት ታሪኩ ሲነገር ይሰማል።

ስለቀደሙት መንግሥታት ቅንጡነትም ሆነ የመዝናኛ ወጪ ይህን ያህል ያልናችሁ ታሪኩን ለማስታወስ ብቻ ሳይሆን ከአሁኑ ዘመን ተግባራት ጋር እያስተያየን ለመናገር ነው። ኢሕአዴግ ሥልጣንን በተራው ከነጠቀ በኋላ ነገሮች እጅግ ተለዋውጠዋል። ከሶሻሊዝሙ ርዕዮተ ዓለም በመላቀቅ ሕዝቡ ወደ ካፒታሊስቱ ጎራ፣ “ቅይጥ” እየተባለም ቢሆን የተቀላቀለው እጅግ በፈጠነ ሂደት ነበር።

ባለሥልጣናቱ ለግል ምቾታቸውም ሆነ ለሕዝብ ብለው ግንባታዎችን ማከናወን ከመጀመራቸው አስቀድሞ፣ ቅንጡ ሕይወትን ማስተዋወቅ የጀመሩት በግለሰቦች ነበር ማለት ይቻላል። ሼክ ሙሐመድ አል አሕሙዲን ሸራተንን አስገንብተው ቅንጡ ሕይወትን ኅብረተሰቡ ቢያንስ ለበዓላት ዋዜማ በቴሌቪዥን መስኮት እንዲመለከት ከማድረጋቸው ባሻገር እምብዛም የሚባል መዝናኛ አገሪቱ ተገንብቶላት አያውቅም ነበር።

ቀስ በቀስ ግን ባለሥልጣናቱ ሀብት እያካበቱ መንግሥትም ምቾትን እየተዋወቀ ሲመጣ፣ ነገሮች በፍጥነት ተቀያይረው ነበር። እዚህ መዝናኛ ገንብቶ ከመንደላቀቅ አልያም በነበሩት ከመጠቀም ይልቅ ውጪ አገር እየተጓዙ ከፍተኛ የአገር ሀብትና ምንዛሬ ማባከኑ እስከ አሁን ያልቆመ አገር አውዳሚ ተግባር መሆኑን መመልከት ይቻላል።

- ይከተሉን -Social Media

በቀዳሚው የኢሕአዴግ ዘመን ያልነበረ የፓርክም ሆነ የመዝናኛ ቦታ ግንባታ አሁን አሁን የተለመደ ትልቁ የመንግሥት ወጪ የሚመስልበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ከእዮቤልዩ ቤተመንግሥትና ከኢሲኤ መካከል ያለው በፊት መኪና ይቆምበት የነበረው ቦታ በግል ባለሀብት እንዲለማና ታጥሮ ፓርክ እንዲሆን ከተደረገው ውጭ ለመዝናኛ ያን ያህል ትኩረት ተሰጥቶ አያውቅም። እንደውም ደርግ ለወጣቱ ብሎ በየቀበሌው ያዘጋጃቸው ሜዳዎች ለሥርዓቱ ቅርበት ላላቸው ባለሀብቶች በነፃ ተሰጥተው አሁን ጥቂቶቹ ቀርተው አስተሳሰቡ ወደ ወጣት ማዕከልነት ተቀይሯል።

ለውጥ መጣ ተብሎ ባለሥልጣናቱ ወንበር ከተቀያየሩና ከተሸጋሸጉ በኋላ ግን የመንግሥት አመለካከት እጅጉን ተቀይሯል። “ወጣቱ ፎቶ መነሻ አጥቷል” እየተባለ ከፍሎ መግባት የማይችልባቸው መዝናኛ ፓርኮች እንደ አሸን እየፈሉ ይገኛሉ።

በድሀ አገር ሀብት ቅንጡ የሚባሉና ውጪ አገርም ሄዶ መዝናናት የሚችለውን ሀብታሙን የማኅበረሰብ ክፍል ያማከሉ ግንባታዎች በከፍተኛ ወጪ እየተካሄዱ ይገኛሉ። ከቤተ መንግሥቱ ብንጀምር፣ አጥሩ ዙሪያ ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው የሚሉ ማስታወቂያዎችን ለማየት የሚፈራበት ዘመን አልፎ ውስጥ ተገብቶ ፎቶ መነሳትም ተችሏል።

የተሠሩት ሁሉ እንደተጠቃሚያቸው ልዩነት በጎም መጥፎም ያላቸው ናቸው ሊባሉ ቢችልም፣ የድሃ አገር ሀብት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ብዙ ነገር እያለ እዚህ ዓይነት መዝናኛ ላይ መዋሉ ብዙ ሲያስተቸው ይሰማል። ገንዘቡ በግል ለአንድ አገር መሪ ተሰጥቶ ነው እንደሚባለው ከሆነ፣ ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው የተቀበሉት እንደመሆኑ ሙስና ሊሆን ነው በሚል የሚተቹም አልጠፉም። ገንዘቡ የተሰጠው በኢትዮጵያ ሥም እንደመሆኑ የተሠራው በልገሳ እንኳን ቢሆን የሕዝቡ ፍላጎት ላይ ሊተኮር በተገባ ነበር የሚሉም በርካቶች ናቸው።

የቤተ መንግሥቱ ግንባታና ወጪ ብቻ ሳይሆን፣ የወዳጅነት ፓርክም ከተማ መሀል የነበረን በርካታ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ወደ ከተማ ጠረፍ የተወሰደበትና ሙሽሮች ፎቶ ለመነሳት ብቻ 35 ሺሕ የሚከፍሉበት የሀብታሞች መናኸሪያ እንዲሆን መደረጉ ብዙዎችን ያሳዘነ ድርጊት ነው።
ከወጣበት የሕዝብ ሀብት አኳያ ብዙኀኑ ምን ተጠቀመበት? ወጪውንስ በምን ያህል ጊዜ ይሸፍናል? የሚለው ምላሽ ሳያገኝ፣ አሁንም ተመሳሳይ ግንባታዎች እንደቀጠሉ ናቸው። ሥራው በጨረታ ይሰጥ አይሰጥም ምንም ሪፖርት የቀረበበት ሂደት ስለሌለ ለምዝበራ የተጋለጠ እንደሆነም የሚናገሩ አሉ።

ወደ እንጦጦው ፓርክ ስንጓዝ ደግሞ ሌላ ቦታን ሳያዩ በግል ፍላጎታቸው መሠረት አዘው ያሠሩት እንደሆነ ለመናገር ግድ ራሳቸው ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተናገሩትን መጥቀስ ያስፈልግ ይሆናል። የየካውን የአዲሱን ቤተመንግሥት ሳይት፣ “ባየው እንጦጦ አልሄድም” ብለው ተናገሩ የተባለውን መሠረት በማድረግ የፓርኩ ግንባታን ለመገምገም ጊዜው ገና ሊሆን ይችላል።

አሁንም ድረስ ቅዳሜና እሁድ ተመልካች ያለው ቢሆንም፣ እያደር እየቀነሰ መምጣቱን ለመናገር ይቻላል። መንግሥት ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት አፍስሶበት የተሠራ ነገር ቢኖር የአካባቢው መንገድ ነው። መንገድ ለእድገት ወሳኝ እንደመሆኑ ለጎብኚው ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሕይወት መቀየር የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱ አይቀርም።

መንግሥት ያስገነባው በዋናነት መንገድን እንደመሆኑ ሌሎች አብዛኛዎቹ ግንባታዎች ግን አገልግሎት ሰጪ ባለሀብቶቹ ያስገነቧቸው ናቸው። መዋጮ ላይ እጃቸውን የዘረጉ ባለሀብቶች ይሁኑ አልያም በጨረታ አሸንፈው ይሁን ለሕዝብ ግልፅ ባይደረግም፣ አመራረጣቸው ሕጋዊ አካሄድ ስለመሆኑ የሚያመላክተው ነገር ሊኖር ይገባል። በፓርኮቹ የሚገኙት ውድ ውድ አገልግሎት ሰጪ ቤቶች ከመሆናቸው ባሻገር፣ የገቡበትን ሕዝብ የማገልገል ግዴታ ለመወጣት ምን ያህል ፈቃደኛ እንደሚሆኑም የሚታወቅ ነገር የለም።

- ይከተሉን -Social Media

በመዝናኛ ማዕከሉ ግንባታ ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት እንደወጣ ግልፅ ቢሆንም፣ አብዛኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ያማከለ ስለመሆኑ ማሰብ ያስፈልጋል። መጓጓዣም ሆነ መገልገያ የሚሆን ለድሃው የሚሆን ቦታ በሌለበት አኳኋን፣ መግቢያ በነፃ መሆኑን እያሰቡ ልዩነቱን ለማጣጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ከሁሉም ከሁሉም የሚያሳዝነው መግቢያ ቦታ ላይ ከተለጠፉት ጥቂት ካርታዎች በስተቀር ኅብረተሰቡ የት እንዳለ መንገዶችም ወዴት እንደሚወስዱት የሚያውቅበት ነገር የለም። ባለፈው ሳምንት ቦታው ተገኝቼ እንደተመለከትኩት፣ አቅጣጫ ጠቋሚ የሚባል ምልክትም ሆነ ሰው የለም። ኅብረተሰቡ እግሩ እንዳመራው ተጉዞ የሚወጣበትን በር እንኳን ማወቅ አይቻለውም።

በሱሉልታ በኩል መኪና አቁመው በቡድን የገቡ ጎብኚዎች ያለ ምንም አመልካች ውስጥ ገብተው ለመለያየት ተገደዋል። አንዱ ቡድን በእንጦጦ ማርያም በኩል ወጥቶ መኪና ለማምጣት አስቦ መንገድ መሪም ሆነ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክት ባለመኖሩ በቁስቋም በኩል እታች ለመውረድ ተገዷል። ይህም ሆኖ በታክሲ የ20 ደቂቃ መንገድ እላይ ድረስ ተጉዞ ወደ ሱሉልታ ኬላ በኩል ያለውን በጣም ረጅሙን መንገድ በእግር ተጉዟል። ያም ሆኖ ግን ውስጥ የቀሩት ወደ ቁስቋም እንዲመጡ ለመንገር ቢሞከርም፣ አመላካች ነገር ባለመኖሩ ሳይሳካላቸው ቀርቶ እነሱ ሸገር ሬዲዮ ባለበት በድል-በር በኩል ወጥተው በስንት ልፋት ዙሪያ ጥምጥም ተጉዘው ለመገናኘት በቅተዋል። ይህ የሚያሳየው የብዙዎች ችግር መሆኑን ሲሆን በርካቶችም ይህን ሳያውቁ ሲንገላቱ መታዘብ ችያለሁ።

ይህ ዓይነት ከፍተኛ ወጪ የወጣበት መዝናኛ ቦታ ጥቃቅን ሊባሉ በሚችሉ ትኩረት በተነፈጋቸው ምክንያቶች ተቀባይነቱን እንዳያጣ ያሰጋል። ሌላ ቅርብ የሆነ ተመሳሳዩ ፓርክ ሲገነባም ሕዝቡ ትኩረቱን ቀይሮ ሀብቱ ባክኖ እንዳይቀርም ያሳስባል።

በሌላ በኩል፣ የተጀመሩ ግንባታዎች ሳይጠናቀቁ ሌላ የመጀመርም አባዜ አሁንም አለቀቀም። የቤተ መንግሥቱ (አንድነት ፓርክ) ሆነ የወዳጅነት አልያም እንጦጦው ሙሉ ለሙሉ ሥራው አልቋል ማለት አይቻልም። ይህ ቢሆንም ግን መንግሥት ሌላ የፓርክና የአዲስ ቤተመንግሥት ግንባታን ከማስጀመር አላገደውም።

የየካ ተራራ የጫካ ፕሮጀክት እየተባለ የሚታወቀው ግንባታ ከሁሉም ቅልቅ ወጪ እንደሚያስወጣ ቢነገርም አሁን መንግሥት ዝርዝር መረጃውን ከመናገር ተቆጥቧል። ግዙፍ የአፈርና ድንጋይ ክምር ለኩሬ ሲባል ሌት ተቀን እየተጓጓዘ ነው። ከአዲሱ ቤተ መንግሥት ውጭ ያለውና አሁን እየተገነባ ያለው ፓርክ ከሚያርፍበት የቦታ ስፋትም ሆነ ከሚከናወንበት ግንባታ አኳያ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው።

አሁን ኑሮ ውድነት ሕዝቡን ባስጨነቀበት ወቅት መዝናኛዎችና ማስዋቢያዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነቡ ይገኛሉ። ለሕዝብ ዓላማ ተብሎ የሚከናወን ማንኛውም ተግባር ብዙኀኑን ያስተናግዳል ወይ? የሚለው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ማግኘት ቢገባውም፣ አሁንም ሕዝቡ መረጃ ሳያገኝ በስማ ስማ ለአሉባልታ ተጋልጦ ይገኛል።

የቤተ መንግሥቱ ጉዳይ የቅንጦት እንደሚሆን የብዙዎች ግምት ነው። ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች አስከፊ በሚባል ሁኔታ ሕዝቡን እያገለገሉ ባሉበት ሁኔታ፣ ባለሙያዎቹን በሚያሳፍር ሁኔታ ትኩረት ሁሉ ለባለሥልጣናትና ሹመኞች ምቾት መሆኑ አሳዛኝ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ሕዝብ የሚበላውና የሚያድርበት የሚኖርበትም አካባቢ ባጣበት በዚህ አሳሳቢ ዘመን፣ መንግሥት በከፍተኛ ወጪ አዲሱን ቤቴን ላሳንፅ ማለቱ ከኃይለሥላሴ ስህተት አለመማሩን ያመላክታል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ለባለሥልጣናት ቅንጦት ሲባል በአበልና በወጪ መልክ የሚያዘው ሀብት የሚያንገበግበው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ሌላ ትኩሳት መጨመር ይመስላል። ውብ ነገርን ማየት የሚጠላ ባይኖርም ሆዱ ርቦት ወይም በርዶት ማንም ቢሆን የሚያምር ስለሆነ ብቻ የሆነ ቦታ ላይ አይቆይም።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የከተማ ውበት እየተባለ በየመንገዱ የሚተከል አበባ ከፍተኛ ወጪ እንደሚወጣበት ይታወቃል። “የማስዋብ” በተባለለት ፕሮጀክት አበባና ዛፉም ሆነ ግንባታው በማን እንደሚከናወን ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ፣ ለአደባባይና ደሴቶች ውበት መንግሥት ብቻ 50 ሚሊዮን ብር መመደቡ ብዙዎችን አስገርሟል።

ኤልሲዲ መብራትን ያለምንም ምክንያት ለማስዋብ በሚል ብቻ ዘላቂነት የሌለው ብልጭልጭ መብራት በቋሚ ብረት ላይ ጠቅልሎ ማንጠልጠል የትዝብት ጥያቄ ሲያስነሳም ተስተውሏል።

ሕዝቡ የሚበላው አጥቶ ኑሮ እያንገበገበው ባለበት በዚህ ወቅት በየመንገዱ ለተተከሉ ዛፎች ዙሪያ በብሎኬት ገንባ እየተባለ ሕዝቡ መገደዱም እየተሰማ ነው። በፈቃደኝነት የሚያስውብ ባለሀብት ፈልጎ እንዲያግዝ በማድረግ ፋንታ፣ ‹‹ይህ የእናንተ ደጃፍ ስለሆነ በዚህ መልክ ካልገነባችሁ ወየውላችሁ›› የሚሉ የቀበሌ ካድሬዎች ኅብረተሰቡን ማስፈራራት መጀመራቸው የአሠራሩን ውጤትም ሆነ ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው።

እነዚህ ሁሉ የማስዋብም ሆነ የመዝናኛ ማዕከሎች ግንባታ ከአንድ ባለሥልጣንም ሆነ ከመንግሥት ሥርዓት ጋር መገናኘት አልነበረባቸውም። በሕዝብ ሀብት የሚሠሩ እንደመሆናቸው ኅብረተሰቡ የራሱ አድርጎ እንዲቀበላቸው በማድረግ ፈንታ፣ በአንድ ሰው በጎ ፈቃድ አልያም ምኞት ብቻ የተከናወኑ ተደርጎ መግለፁ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። “የዐቢይ አበቦች” ተብለው ተቃውሟቸውን በሚያሰሙ ወጣቶች በቅርቡ ከወደሙ የመስቀል አደባባይ ተክሎችም ሆኑ ንብረቶች መጨረሻ መንግሥት ሊማር እንደሚገባ ግልፅ ነው።

እኛም እንደ ኅብረተሰብ የትኛውም ንብረትም ሆነ ሀብት የኛ ነው በሚል ማሰብ ይጠበቅብናል። አይደለም የራሳችንን ይቅርና የሌላንም ቢሆን ላለማውደም ልንጥር ይገባል። ታሪክ መማሪያ እንደመሆኑ ከፋም ለማ ቅርሶች ሆነው መኖራቸው ጉዳት የሚያስከትሉ እስካልሆኑ ድረስ ግንባታዎችም ሆኑ ተግባራት እንደነበሩ ሊቀመጡ ግድ ይላል። የምናስበው አሁን ላለነው ለእኛ ችግር ብቻ ሳይሆን ለቀጣዮቹ ትውልዶች ጭምር እንደመሆኑ ዘላቂ ነገር ላይ ብናተኩር ይመረጣል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች