መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየሰላም እና የጦርነት ጉትቻ

የሰላም እና የጦርነት ጉትቻ

ኢትዮጵያ የሰላም ያለህ እያለች መጠየቅ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተነሳውና አሁንም ድርድር አልያም ዳግም መቀስቀስ መካከል የሚንከላወሰው ጦርነትም ሰላሟን ከነሷት ክስተቶች መካከል ይጠቀሳል። ይህ ጦርነት ብዙ ጥፋትንና ውድመትን ያደረሰ ሲሆን፣ አሁንም ከዛ የባሰ እንዳይደርስ ሰላም ይምጣ፣ ተስማሙ ባዩ ብዙ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ድርድር የሚለው ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይሰማል።

የድርድር ጥረቶችም እየተደረጉ መሆኑ በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ ለድርድር ይቀመጣሉ የሚባሉት ሁለቱ አካላት ግን በየፊናቸው ‹እኛ የጀመርነው ድርድር የለም› እያሉ ይገኛሉ። ሁለቱም በተመሳሰይ ግን ሰላምን እንደሚሹ በመግለጽ ‹ሰላምን የማይፈልጉ እነሱ ናቸው› እያሉ ጣት እየተቀሳሰሩ ይገኛሉ። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ በማንሳትና የተለያዩ ባለሞያዎችን በማነጋገር፣ ስለነበረውና ስላለው ሁኔታ በመዘርዘር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የሰላም እና የጦርነት ጉትቻ
የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ ኹለተኛ ዓመቱን ሊያስቆጥር አራት ወራት ገደማ ይቀሩታል። ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ እንደቀጠለ ሲሆን፣ አሁንም መቋጫ አላገኘም። ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በደረሰባቸው አካባቢዎች ያስከተለውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ መነሻ በማድረግ ጦርነቱ በሰላማዊ ድርድር እንዲያበቃ የሚጎተጉት እና በአንጻሩ በኃይል የበላይነት ጦርነቱ እንዲቋጭ የሚፈልጉ ሰዎች ሐሳባቸውን በተለያየ መንገድ እያንጸባረቁ ይገኛሉ።

በፌዴራል መንግሥት እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ፣ የተቀሰቀሰው የሰሜኑ ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ሳይስፋፋ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ምክር ሐሳብ ያቀረቡ አካለት እንደነበሩ አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ወደ ኹለቱ ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ ትግራይን ጨምሮ በሦስቱ ክልሎች ያደረሰው ሰብዓዊ እንዲሁም ቁሳዊ ኪሳራ ክልሎቹንም ሆነ ኢትዮጵያን እንደ አገር ወደ ኋላ የሚጎትት ሆኗል።

የሕወሓት ኃይሎች ወደ አፋር እና አማራ ክልል ገብተው የተለያዩ አካባቢዎችን በተቆጣጠሩበት ወቅት፣ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማመቻቸት ወደ መቀሌ ተጉዘው ከሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ልዩ መልዕክተኛው ከዚያ በኋላም በተደጋጋሚ ወደ መቀሌ ተጉዘው ከሕወሓት አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል። የኦባሳንጆ ተደጋጋሚ የመቀሌ ጉዞ በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል ድርድር እየተካሄደ ነው የሚሉ ሐሳቦች በስፋት እንዲንጸባረቁ ማድረጉም አይዘነጋም።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያፈላልጉ በልዩ መልዕክተኝነት መሰየማቸው ይታወሳል። ይህንኑ ተከትሎ ኦባሳንጆ ከፌዴራል መንግሥት፣ ከሕወሓት፣ ከአማራ ክልልና አፋር ክልል ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርገዋል። ልዩ መልዕክተኛው ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከሕወሓት ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ‹‹ለማደራደር የማደርገውን ጥረት አልቀበልም ያለ የለም›› ሲሉ ከ‹ቢቢሲ – ፎከስ ኦን አፍሪካ› ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የድርድር ወሬዎች መሰማት ከጀመሩ ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ እስከ አሁን ይሄ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ አላሳየም። ስለ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ በኩል በተደጋጋሚ የሚሰማ ቢሆንም፣ በሕወሓት በኩል የሚሰማው ከድርድር ይልቅ የጦርነት ጉሰማዎች ናቸው የሚል ክስ የፌዴራል መንግሥት በሕወሓት ላይ እያቀረበ ነው።

ሕወሓት በበኩሉ የፌዴራል መንግሥት ‹‹የሰላም በሮችን ዘግቶብኛል›› በማለት ፍላጎቱን በኃይል ለማሟላት ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው። ሕወሓት ተቆጣጥሯቸው የነበሩ የአፋርና የአማራ አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ ባይባልም ለቆ ከወጣ በኋላ የሰላም አማራጮች አላገኘሁም በማለት በዚህ ወቅት ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ለችግር የዳረገው ጦርነት አሁን ላይ ረገብ ያለ ቢሆንም፣ በድርድርና በጦርነት ማገርሸት አጣብቂኝ ውስጥ መሆኑን የሚያሳብቁ ሁኔታዎች ከኹለቱም ወገኖች እየተስተዋሉ ነው። የድርድር ጥረቶች በአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ በኩል እየተደረጉ ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ባለሥልጣናት የሚያንጸባርቁትን ሐሳብ መነሻ በማድረግ የሰሜኑ ጦርነት በድርድር የመፈታቱ አዝማሚያ ላይ ስጋታቸውን የሚገልጹ አካላት ተፈጥረዋል።

የድርድር ጉምጉምታ
የሰሜኑ ጦርነት በድርድር እንዲቋጭ አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ የውጭ አካላት ጥረት ማድረግ ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል። አፍሪካ ኅብረት ለጉዳዩ በመደባቸው ኦባሳንጆ በኩል አሁንም የድርድር ጥረቶችን እያካሄደ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎች ከልዩ መልዕክተኛው እየወጡ ነው። የኦባሳንጆ የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓትን የማደራደር ጥረት ከተጀመረ ወራት ቢቆጠሩም በመንግሥት በኩል ድርድር አልተጀመረም የሚል መረጃ በተደጋጋሚ አየተሰማ ነው።

ይሁን እንጂ ኦባሳንጆ የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ባለሥልጣናትን አነጋግረው የድርድር ጥረታቸውን እንደቀጠሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር ድርድር አልጀመርኩም ይበል እንጂ፣ ኦባሳንጆ ባለፈው ሳምንት ከመቀሌ መልስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ወደ ባሌ ለጉብኝት ማቅናታቸውን ብዙዎች የድርድር ሂደቶች እንዳሉ የሚያሳይ ነው እያሉ ነው።

ኦባሳንጆ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ባሌ ሮቤ ለጉብኝት ያቀኑት፣ ወደ መቀሌ አቅንተው ከሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ተወያይተው ከተመለሱ በኋላ ነው።

መንግሥት ስለ ድርድር የሚሰጣቸው መረጃዎችና ከኦበሳንጆ የሚሰሙ መረጃዎች አለመጣጣም፣ ስለሚሰማው የድርድር ሐሳብ በተስፋና በስጋት የሚመለከቱት ወገኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል። መንግሥት በድርድር ጉዳይ የሚሰጣቸው መረጃዎችና የኦባሳንጆ መረጃ አለመጣጣምን በመመልከት፤ መንግሥት ስለ ጉዳዩ ግልጽ መሆን አልፈለገም የሚሉ ሐሳቦች ሲነሱ ይሰማል።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኙ የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ታመነ አባተ፣ ኦባሳንጆ በጀመሩት የድርድር ጥረት ላይ በመንግሥት በኩል የግልጽነት ችግር እንዳለ በግልጽ እንደሚታይ ይገልጻሉ።
በአንድ በኩል የድርድር ሐሳቦች እየተደመጡ በመንግሥት በኩል የተጀመረ የድርድር ውጥን የለም ማለቱ ሕዝቡ እንዲደናገርና ግልጽ መረጃ እንዳይኖረው እያደረገ መሆኑን መታዘብ ይቻላል ይላሉ የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኙ። መንግሥት ለሕዝብ ግልጽ ሆኖ መቅረብ አለበት የሚሉት ሻለቃ ታመነ፣ ከኦባሳንጆ ምልልስ አንጻር አልተጀመረም ማለት አይቻልም ብለዋል።

ስለ ድርድር ከኦባሳንጆ የሚሰሙ መረጃዎች ድርድር መጀመሩን የሚያሳዩ ናቸው የሚሉት ሻለቃ ታመነ፣ የመንግሥት አቋም አሳማኝ አይደለም ይላሉ። በመሆኑም መንግሥት ድርድር ካለ በግለጽ ለሕዝብ ማሳወቅና “አዎ ድርድር ነው” ማለት አለበት የሚል ሐሳብ አላቸው።
ሌላኛው ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ፖለቲከኛ፣ ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት እንዲያበቃ በኦባሳንጆ በኩል የሚሰሙ የድርድር ሐሳቦችና መንግሥት ለሕዝብ የሚሰጠው መረጃ ጥርጣሬ የሚፈጥር ነው ይላሉ። ‹‹ዞሮ ዞሮ የጦርነት መጨረሻው ድርድር ነው›› የሚሉት ፖለቲከኛው፣ መንግሥት ኦባሳንጆ የሚያደርጉትን የማደራደር ሂደት ‹ለሕዝብ በአደባባይ እየካደ› ነው ይላሉ።

የድርድር ወሬዎች ሲናፈሱ ወራት ተቆጥረዋል የሚሉት ፖለቲከኛው፣ በመንግሥት በኩል ለሕዝብ የሚሰጡ መረጃዎች ድርድር እንዳልተጀመረ ቢያስረዱም፣ የአደራዳሪው ኦባሳንጆ ምልልስና የሚሰጧቸው መረጃዎች የድርድር ሂደቶች እንደተጀመሩ የሚያመላክት ነው ይላሉ።
ይሁን እንጂ ስለ ድርድር የሚነሱ ሐሳቦች ግልፅነት የጎደላቸውና ተጨባጭ አለመሆናቸው የኦባሳንጆን የማደራድር ጥረት በሥጋት እንድንመለከተው አድርጎናል ይላሉ ፖለቲከኛው። ኦባሳንጆ ከሕወሓትና ከፌዴራል ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ኹለቱን ኃይሎች ወደ ድርድር ለማምጣት የሚደረግ ጥረት መሆኑን መረዳት ይቻላል የሚሉት ፖለቲከኛው፣ ከወዲሁ ግልጽነት ከጎደለው ስኬቱ ላይ አጠራጣሪ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።

- ይከተሉን -Social Media

የድርድር ጉምጉምታው ከኢትዮጵያ መንግሥት በግልጽ ባይገለጽም፣ የአፍሪካ ኅብረት መልዕክተኛው ኦባሳንጆ እና አሜሪካ ለአፍሪካ ቀንድ የምትቀያይራቸው መልዕክተኞች የሚሰጧቸው መረጃዎች ኹለቱም ኃይሎች የድርድር ሐሳብን እንደተቀበሉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ማክሰኞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ መንግሥት ከሕወሓት ጋር የጀመረው ድርድር የለም ብለዋል።

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን በበኩላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ በኋላ፣ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በትግርኛ በሰጡት መግለጫ፣ ሕወሓት የጀመረው ድርድር የለም ብለዋል።

የሰላም እና የጦርነት ጉትቻ
የሰሜኑ ጦርነት አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ እስከ አሁን መቋጫ መፍትሔ ሳይገኝለት ተጉዟል። ጦርነቱ ጋብ በሚልበት ፋታ የሚነሱ የሰላም ሐሳቦች እስከ አሁን ፍሬ የታየባቸው አለመሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ።

በአንድ በኩል የሰላም አማራጭ ሐሳቦች ሲደመጡ፣ በሌላ በኩል በኹለቱም ኃይሎች የጦርነት ዝግጅት መኖራቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው። የፌዴራል መንግሥትም ይሁን ሕወሓት ጦርነቱን በሰላማዊ ሁኔታ የመፍታት ሐሳብ እንዳላቸው በየፊናቸው ለአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ ቢገልጹም፣ የጦርነት ዝግጅቶች እንደቀጠሉ ናቸው።

ሕወሓት የመጨረሻ ያለውን ትግል ለማካሄድ ዝግጅት እያካሄደ መሆኑን እወቁልኝ ብሏል። የፌዴራል መንግሥትም ለሰላማዊ ድርድር በር ዘግቶብኛልና ፍላጎቴን በኃይል አሳካለሁ ያለው ሕወሓት በክልሉ ከፍተኛ የኃይል ዝግጅት እያደረገ ነው ብሏል።

አሁን ላይ ጦርነቱን በሰላም መቋጨት ይበጃል በሚሉ አካላትና አሁንም ጦርነቱ ቀጥሎ በኃይል የበላይነት መቋጨት አለበት በሚሉ አካላት ጉትቻ ውስጥ ኢትዮጵያ እንደ አገር ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያስተናገደች ነው።

የኹለቱ ሐሳቦች ጉትቻ የተፈጠረው በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል እስከ አሁን የቀጠለው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች፣ ግልጽ ባልሆነ የድርድር ውልብታ እና በውረድ እንውረድ የጦርነት ጉሰማዎች አጣብቂኝ መሆኑን ወታደራዊ ተንታኙ ሻለቃ ታመነ ይገልጻሉ።

- ይከተሉን -Social Media

ኹለቱ ኃይሎች ጦርነቱ ተጨማሪ ኪሳራ ሳያስከትል በሰላማዊ ሁኔታ እንዲቋጭ ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም፣ በየፊናቸው ወታደራዊ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም በየፊናቸው እየገለጹ ይገኛሉ። ይህ ሁኔታ አሁን ላይ ጋብ ያለው ጦርነት በሰላምና በጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተተው ወታደራዊ ባለሙያው ይገልጻሉ።

ሕወሓት ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ ነው የሚለው የፌዴራል መንግሥት፣ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ለሚካሄድ ማንኛውም የሰላም ጥረት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል። በሌላ በኩል አገር መከላከያ ሠራዊት በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ጨምሮ በስፋት ወታደራዊ ልምምዶችንና ሥልጠናዎችን እያደረገ መሆኑን መግለጽ ከጀመረ ሰነባብቷል።

የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት በየፊናቸው ስለ ሰላማዊ መፍትሔ ፈቃደኝነት ቢገልጹም፣ በየፊናቸው የሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ እድል የሚከፍት አይመስልም የሚሉ ሐሳቦች ከወዲሁ መደመጥ ጀምረዋል።

በተለይ ኹለቱም ኃይሎች በወልቃይት ጉዳይ ከወዲሁ የሚያንጸባርቁት አቋም፣ በድርድሩ ላይ ጥላ እንዳያጠላ ስጋት እንዳላቸው ሻለቃ ታመነ ይገልጻሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት በወልቃይት ጉዳይ በመንግሥት በኩልና በሕወሓት በኩል ያለው የአይነኬነት ሐሳብ ለውጤታማ ድርድር የሚጋብዝ አይደለም ይላሉ። የአማራ ክልል መንግሥት በወልቃይት ጉዳይ አልደራደርም የሚል ሐሳብ በተደጋጋሚ ያንጸባርቃል፣ ሕወሓት በበኩሉ በወልቃት ጉዳይ እንደማይደራደር እየገለጸ ነው።

ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የአፍሪካ ኅብረት መልዕክተኛ ኦባሳንጆ እስከ አሁን ሲያደርጉ የነበረውን ጥረት የሚያጣጥል ሐሳብ ከሕወሓት በኩል ተሰምቷል። ሕወሓት በኦባሳንጆ የአደራዳሪነት ሚና ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ እንዳለውና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የሚደረግ የድርድር ጥረት መቀጠል እንደማይፈለግ፣ በዚሁ ሳምንት ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።

ተጨባጭ ለውጥ አላሳየም የሚባለው የኦባሳንጆ የወራት ጥረት፣ በሕወሓት በኩል ይባስ ብሎ የገለልተኝነት ጥያቄ ተነስቶበታል። በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚደረግ ድርድር ላይ ከወዲሁ የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት ፍላጎት ተለያይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርድርን በተመለከተ ስላለው ሁኔታ ከፓርላማው ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚወክል የድርድር አጥኚ ቡድን ተቋቁሟል ብለዋል። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ደመቀ መኮንን ይመራል የተባለው ኮሚቴ፣ መንግሥትን ወክሎ የሚደራደር አካል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ኮሚቴው ሰላምን በሚመለከት በሚሠራው ሥራ ላይ ‹‹ኢትዮጵያ ምን ትፈልጋለች፣ ምን ሲሟላ ድርድር ይካሄዳል›› የሚሉ ጉዳዮችን በማጥናት ላይ ነው ተብሏል። ‹‹ሰላም እንፈልጋለን ማለታችን የተደበቀ ድርድር እናደርጋለን ማለት አይደለም›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጊዜው ሲደርስ መንግሥት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የሰሜኑ ጦርነት እንዲያበቃ ኹለቱም ኃይሎች ፍላጎት እያሳዩ ቢሆንም፣ የሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታና የሚታየው የጦርነት ዝግጅት ለተጨማሪ እልቂት እንዳይዳርግ ብዙዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፖለቲከኛ በበኩለቸው፣ ቀድሞውንም ሰላማዊ መፍትሔ የሚሻን ጉዳይ ኹለቱ ኃይሎች በየፊናቸው እየለጠጡ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ኪሳራ ውስጥ እንድትገባ አድርገዋል ይላሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ከኹለቱ ኃይሎች አንዱ የሚያስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የሚሰማውን የድርድር ሐሳብ ሊያበላሸው እንደሚችልም ስጋት አላቸው።

ለኢትዮጵያ የሚበጀው?
የሰሜኑ ጦርነት ገና ከጅምሩ የተራዘመ እንዳይሆን ከፖለቲካ ባለሙያዎች እስከ ወታደራዊ ባለሙያዎች ሲወተውቱ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ጦርነቱ የተራዘመ ጦርነት መሆኑ አልቀረም። በዚህ በተራዘመ ጦርነት ዜጎች ለሞትና ለመፈናቀል፣ ለረሀብና ጥም ተጋልጠዋል።
እንደ አገር የሰሜኑ ጦርነት ያስከተለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ቀላል የሚባል አይደለም። ለሺዎች ሞትና ለሚሊዮኖች መፈናቀልና እንግልት ምክንያት የሆነው ጦርነት፣ በሰላማዊ መንገድ ከተቋጨ ኢትዮጵያ ከተጨማሪ ከሲራ እንደምትድን ብዙዎች ይመክራሉ።

‹‹ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት ከተጀመረ እልቂቱ የከፋ ነው የሚሆነው›› የሚሉት ወታደራዊ ተንታኙ ሻለቃ ታመነ፣ በእርስ በእርስ ጦርነት ማንም አሸናፊ የለም ይላሉ። ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ጦርነት ውስጥ ዳግም ከመግባትና የሕዝቡን ችግር ከማራዘም፣ በሰላማዊ መንገድ መቋጨት እንደሚገባ ይመክራሉ።

‹‹ሁልጊዜ በዚህ ሰላም፣ በዚህ ጦርነት ቢባል የሚቀድሞው ሰላም ነው›› ሲሉ የገለጹት ሻለቃ ታመነ፣ ከጦርነት ጉሰማ ሰላማዊ ድርድርን ማስቀደም እንደሚበጅ ጠቁመዋል። ሰላም በመጥፋቱ ሕዝቡ የተረፈው መፈናቀል፣ ረሀብና የኢኮኖሚ ድቀት መሆኑን የሚያነሱት ሻለቃ ታመነ፣ ተጨማሪ ጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው ኹለቱም ኃይሎች መገንዘብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ፖለቲከኛው በበኩላቸው፣ ከዚህ በኋላ ኹለቱ ኃይሎች “መሽቷልና ይጠንቅር” የሚመስለውን የጦርነት ጉሰማ ትተው፣ ተጨማሪ ጦርነት ውስጥ ላለመግባት ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። አስቀድሞ ሰላምን መግፋት ትርፉ ኪሳራ ነው የሚሉት ፖለቲከኛው፣ ለሰላም ሲባል ሰላማዊ ዋጋ መክፈል፣ በጦርነት ከሚከፈል ዋጋ የተሻለ ነው ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች