መነሻ ገጽዜናወቅታዊየአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላው ዘመቻ

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላው ዘመቻ

ከአንድ ሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዛፍ ችግኞችን የመትከል ልማድ እንዳለውና እንደነበረው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። የዛፍ ጠቃሚነትን ከማንም በላይ ሕዝብ መረዳት መቻሉም ጠብቆ ለማቆየት የረዳ ሲሆን፣ እያደር የዛፎች መቆረጥ በመብዛቱና እነርሱን የመተካት ጥረቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የደን መራቆት ዳርጓታል።

ይህንን መራቆት ለማስቀረት ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እንደታዩት እና በተያዘው ዓመትም ከአንድ ወር በኋላም እንደሚቀጥል በሚጠበቀው የችግኝ ተከላ ዘመቻ፣ አገሪቱን በደን ለማልበስ መታቀዱን መንግሥት እያወሳ ነው።

ቻይናን የተመለከትን እንደሆነ፣ ዓመታዊውን አገር ዐቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከሁለት ወር በፊት ማስጀመሯ አይዘየጋም። የቻይናው ፕሬዚደንት ሺ ጂን ፒንግ ዓመታዊውን አገራዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከተማሪዎች እና ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ነበር ያስጀመሩት።

ቻይና በፕሬዚደንቱ አነሳሽነት አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የጀመረችው ከ10 ዓመት በፊት እኤአ በ2013 መሆኑን እና ዘንድሮ የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 10ኛው ዙር እንደሆነም ተገልጿል።

ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ፣ ቻይናን በአረንጓዴ ተክል ለማልበስ በማለም በፕሬዝዳንቱ ሐሳብ አፍላቂነት የተጀመረው መርሃ ግብር አለ። በዚህ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር፤ ቻይናን ውብ እና ምቹ ለማድረግ እየሠሩ ያሉት፣ አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በተለይ ለወጣቶች የተሻለ ከባቢ አየርን ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማበረታታት መሆኑንም ገልጸዋል።

በአንድ ድንጋጥ እንዲሉ፣ በዚህ መሠረት በቻይና ከአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ 64 ሚሊየን ሄክታር መሬት በችግኝ እንዲሸፈን ሆኗል። በዚህም የአገሪቱ የደን ሽፋን ቀድሞ ከነበረበት 2.68 በመቶ ወደ 23.04 በመቶ ከፍ እንዲል ችሏል።

ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ዓላማን ያነገበ አረንጓዴ አሻራ ብላ የሰየመችውን ዓመታዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት ከአራት ዓመታት በፊት አስጀምራለች። በየዓመቱም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ስትተክል ቆይታለች።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአገር ውስጥ ባለፈ በጎረቤት አገራትም እንዲጀመር ለማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ለጎረቤት አገራት አበርክታለች።

ዘንድሮም አራተኛውን ዓመታዊ አገር ዐቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለማከናወን ሰፊ ዝግጅት እያደረገች ስለመሆኑ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

በዘንድሮው ዓመት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ችግኞች መዘጋጀታቸውን የግብርና ሚኒስቴር አውስቷል። መርሐ ግብሩ ተግባራዊ መደረጉ በየዓመቱ 92 ሺሕ ሄክታር የነበረውን የደን ውድመት መጠን ወደ 32 ሺሕ ሄክታር ዝቅ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢያሱ ኤልያስ (ፕሮፌሰር) በዘንድሮ ዓመት በደን፣ በፍራፍሬና በደን ጥምር እርሻ መስኮች ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።

ለመርሐ ግብሩ የችግኝ ማፍላትና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው፣ በዘንድሮው ዓመትም ከ6 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።

በመጪው ሰኔ 15 ቀን 2014 የዘንድሮው ዓመት የአገራዊ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር እንደሚኖርም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ክትትል እና እንክብካቤ አድርጎ የመጽደቅ ምጣኔውን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበረው የደን ሽፋን በሕዝብ ቁጥር፣ በመሬት አጠቃቀም፣ በኢንቨስትመንትና ሌሎች ችግሮች ተመናምኖ እንደነበርም ገልጸዋል። ለአብነትም ከአራት ዓመት በፊት የደን መጨፍጨፍ ምጣኔ በዓመት ከነበረበት 92 ሺሕ ሄክታር ወደ 32 ሺሕ ሄክታር ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተተከሉ ያሉ ችግኞችን ለውጤት በማብቃት፣ ኢትዮጵያ ለተለያዩ ሥራዎች በዓመት የምታስገባውን 4 መቶ ሚሊዮን የእንጨት ውጤቶች በአገር ውስጥ ለመተካት ቁልፍ ተግባር ነው ብለዋል።

የተተከሉ ችግኞች ሙሉ በሙሉ እንዲጸድቁ ተስማሚ ቦታ ላይ መትከል፣ ባለቤት እንዲኖራቸው ማድረግና የአረንጓዴ አሻራ ሥራን ተቋማዊ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

አክለውም፣ በ2013 ላይ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ መትከል መቻሉንና ባለፉት ዓመታት በተደረገ የችግኝ እንክብካቤ የችግኝ የመጽደቅ ደረጃ ጥሩ የሚባል ነበር። አጠቃላይ የሦስት ዓመቱ ተከላ አማካኝ ውጤት 80.5 በመቶ የጽድቀት ደረጃ ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል።

የ2014 የ6 ቢሊዮን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እቅድ መሳካት፣ ከተከላ ቦታ መረጣ ጋር ተያይዞ ተዳፋታማና ጥልቅ ቦታዎችን ለተከላ በመምረጥ መወሰድ ያለበት ጥንቃቄ አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ድንጋያማ ቦታ እና ነባር ዛፍ ስር ችግኝ መተከል እንደሌለበት እና ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመጠበቅ በቆላማ አካባቢዎች ለአየር ንብረቱ ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችን በመትከል እንዲሁም በደጋማ አካባቢዎች እንደ ቀርከሃ፣ ዝግባና ኮሶ የመሳሰሉ አገር በቀል ዝርያዎችን መትከል እንደሚገባ ተገልጿል።

ዘንድሮ ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ 3.3 ቢሊዮን የደን፣ 2.1 ቢሊዮን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ የጥምር ደን ችግኞች፣ 518 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኞች፣ 35 ሚሊዮን የቀርከሃና 800 ሚሊዮን ለእንስሳት መኖ ጥቅም የሚሰጡ ቁጥቋጦዎች እና ለከተማ ውበት የሚሆኑ ችግኞች በአጠቃላይ 6.7 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል።

ከምግብ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ሰፋፊ ዘመቻዎች የተደረጉ ሲሆን፣ ቡና ወደ ውጪ ልኮ ጣውላ ማስገባትን ታሪክ ማድረግ የአረንጓዴ አሻራ አንዱ እሳቤ መሆኑ ተገልጿል።

የሙቀት አማቂ ጋዞችን ከመቀነስ እና ከመቆጣጠር አንጻር ከሚሠሩ ሥራዎች ባሻገር፣ ገቢ ለማስገኘት በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ወጣቶች ተደራጅተው ችግኝ በማፍላት ለተለያዩ ተቋማት በማቅረብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ተወስቷል።

ከበልግ ተከላ ጋር ተያይዞ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በሚሠራበት አካባቢ ሰፋፊ የችግኝ ጣቢያዎች በማቋቋም ለአካባቢው ተስማሚ ዝርያዎችን በመምረጥ ተከላ እንዲካሄድ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ ተፋሰሶች ባለቤት ተፈጥሮላቸው ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ ነውም ተብሏል።

እስከ አሁን ባለው መረጃ ከሦስት ቢሊዮን በላይ ጉድጓድ ለተከላ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና በማስፋት ረገድ ከክልል እስከ ወረዳ ካሉ የቴክኒክ ኮሚቴዎች ጋር በቅንጅት በመሥራት ድጋፍ የማድረግና መረጃ የመለዋወጥ ሥራ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተፈራ ታደሰ በበኩላቸው፣ ከ2011 ጀምሮ በየዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ በተቀናጀ ሁኔታ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የአረንጓዴ ልማት የተከላ ጊዜያት በርካታ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ 2011 ላይ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ፣ በ2012 ደግሞ 5 የጥብ 9 ቢሊዮን ችግኝ፣ በ2013 እንዲሁ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ በአጠቃላይ ከ17 ቢሊዮን ያላነሱ ችግኞች መተከላቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ለመድኃኒት ሊውሉ የሚችሉ እና የእንጨት ባህሪ ያላቸው እፅዋት፣ ቀርከሃ፣ የውበት ዛፎች እና ፍራፍሬዎችም እንደተተከሉ ተነግሯል።

ችግኞች ከተተከሉ በኋላ በኹለት ዓይነት መንገድ የችግኝ ቆጠራዎች እንደሚካሄድ እና የመጀመሪያ ችግኝ ከተተከለ በኋላ በክረምቱ ወራት ሲጠናቀቅ እና የበጋው ወራት መጠናቀቂያው ላይ ቆጠራ ይካሄዳል።

በሦስት ዓመታት ውስጥ ከተተከሉት ችግኞችም በአማካኝ በአጠቃላይ 80 ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆኑ ችግኞች መፅደቅ የቻሉ ሲሆን፣ ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ ተተክለው መፅደቅ ያልቻሉ እና በከብቶች ተነቅለው፣ ተረግጠው እና በሌሎች ምክንያቶችም መፅደቅ ያልቻሉ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በ2014 የክረምት ወቅት እንዲሁ 6 ነጥብ 8 ቢሊዮን ቀርከሃ፣ የውበት ዛፎች፣ ፍራፍሬዎች እና የተለያዩ ዛፎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 6 ቢሊዮን ችግኝ በቀጣይ ሐምሌ ወር እንደሚተከል እና ቀሪው ችግኝ እንዲሁ የክረምት ወቅት ከወጣ በኋላ የከሸፉ ችግኞችን ለመተካት የታሰበ ነው ብለዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች ችግኞች የሚተከሉበትን ቦታ የመለየት እና የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ የሆኑት ተስፋዬ ሽምብር (ዶ/ር) ባለፉት ሦስት ዓመታት አረንጓዴ አሻራን ለማሳረፍ የተካሄደው የችግኝ ተከላ ሂደት የሚበረታታ ነው ይላሉ።

የፍራፍሬ ዛፎች፣ የውበት ዛፎች እና ሌሎችም ችግኞች እንደመተከላቸው ሁሉ በበጋ እና በድርቁ ወቅት እንክብካቤ በማድረግ ረገድ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ናቸው።

- ይከተሉን -Social Media

አክለውም፣ የችግኞችን እድገት ሊገቱ የሚችሉ ችግሮች እንዳይኖሩ እና ከእንስሳት ንክኪ ማራቅ ካልተቻለ የተተከሉ ችግኞች የታለመላቸውን ዓላማ ሊያሳኩ እንደማይችሉ አስረድተዋል።

የአፈር እርጥበቱን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ችግኞች ከተተከሉ በኋላ ራሳቸውን በራሳቸው መመገብ እስከሚችሉ ድረስ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በሚቀጥለው የክረምት ወቅት ለሚተከሉ ችግኞች እንክብካቤ በማድረግ የራሳቸውን አሻራ ሊያስቀምጡ ይገባልም ብለዋል።

በተጨማሪ የችግኝ ተከላ ሥራዎች በዘመቻ እንደሚካሄድ ሁሉ ችግኝ ከጸደቀ በኋላ እንክብካቤ ላይኖር ስለሚችል መንግሥትም ሆነ ኅብረተሰቡ በየወቅቱ የመከታተል ሥራ እንዲሠሩ ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች