መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛየጎርፍ ሰለባው ሕጻን

የጎርፍ ሰለባው ሕጻን

ሠሞኑን በመዲናችን ተከስቶ የብዙዎችን ልቦና ከሰበረ ክስተት መካከል የ4 ዓመት ሕጻን በጎርፍ ተወስዶ ለቀናት የደረሰበት አለመታወቁ አንዱ ነው። ይሙት ይትረፍ እስካሁን ምንም ዓይነት ፍንጭ ያልተገኘ ሲሆን፣ አሁንም ወላጆች መጨረሻውን ለመስማት ጓጉተው በሀዘን ተቆራምደው መቀመጣቸው እየተነገረ ነው።

ሕጻን ማርኮን ሰኔ 1 ቀን 2014 ከትምህርት ቤት ከወንድሙ ጋር ሲመለስ መንገድ ዳር ያለ ትቦ ውስጥ አዳልጦት እንደገባ ወንድሙና በቅርብ የነበሩ የአካባቢው ወጣቶች ሲናገሩ ነው የሰነበቱት። የመንግሥት አካላት ከመድረሳቸው አስቀድሞ ወዲያው ዝናቡ ሳያቆም የነፍስ አድን ፍለጋውን የተያያዙት የሰፈሩ ወጣቶች ነበሩ።

ገባ ከተባለበት ቦታ አንስቶ ሊያልፍ የሚችልባቸውን ትቦዎችንም ሆኑ የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ከእለቱ ጀምሮ ቢያስሱም፣ ምንም ውጤት ሳይገኝ ቀናት ተቆጥረዋል። የሚመለከተው የመንግሥት አካልም የፍለጋው አካል በመሆን ለቀናት ቢታሰስም፣ ከአንድ እግሩ ጫማ በስተቀር ምንም ሳይገኝ የእናት አንጀት እንዳዘነ ቀናት ተቆጥረዋል።

ይማርበት ከነበረው የላዛሪስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች አንስቶ የተለያየ የማኅበረሰብ ክፍል ፍለጋው በቀጠለበት ወቅት ሀዘኑን ቤተሰቡ ጋር በመገኘት ጭምር ሲገልጥ ቆይቷል። ይህን ያህል ቀን በዘመቻ መልክ ተፈልጎ ያለመገኘቱ ሁኔታ ብዙዎችን ቢያሳዝንም፣ የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፍለጋውን በአነፍናፊ ውሻ ጭምር ባካሂድም ማግኘት አልቻልኩም ሲል አስታውቋል።

አዲስ አበባ ውስጥ ሰው በጎርፍ ተወስዶ በተፋሰሱ የታችኛው ክፍል ሳይገኝ ቀርቶ እንደማያውቅ ተቋሙ ቢያሳውቅም፣ የሕጻኑን እጣ ፋንታ ግን ሊቀይረው አልቻለም። ተርፎ ይሆን የሚለውን የቤተሰብን ሰቀቀን ያራዘመው ያለመገኘቱ ሂደት፣ በመንግሥት ሚዲያ ትኩረት አለማግኘቱ ወላጆቹን ጨምሮ ብዙዎችን ያሳዘነ ነበር።

በሌላ አገር አንድ ሕጻን ጉድጓድ ሲገባ የሚያገኘውን ዓለም ዐቀፍ ትኩረት ይህ ሕጻን ልጅ ባያገኝም፣ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ያቅማቸውን ትኩረት ሊነፍጉት እንደማይገባ ሲነገርም ነበር። የኅብረተሰቡን ቀልብ ለመሳብም ጭምር በሚል የሻማ ማብራት ሥነስርዓት በቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ታሪኩን በሰሙት ግለሰቦች ጭምር በሀዘኔታ ተደርጓል። ሆኖም በፍለጋው ሂደት ላይ ግን ያመጣው ለውጥ የለም።

የብዙዎቸ ሀዘን እየጨመረ በሄደበት ወቅትም ያልታሰቡ እሳቤዎችንም ያመላከቱ ነበሩ። ሕጻኑ በጎርፍ እንደተወሰደ ያልፍበት የነበረ ትቦ በደለል መሞላቱ፤ በአቅራቢያ በጥልቀቱ ሳቢያ በባለሙያ ካልሆነ ሊታሰስ ያልቻለ የውሃ መጠራቀሚያ ጥልቅ ጉድጓድ መኖሩ እንዲሁም የቦዮች አሰራር ለፍለጋው አስቸጋሪ መሆናቸውን ያመላከቱ ነበሩ።

የሚመለከተው አካል ከእንዲህ ዓይነት ክስተት ተምሮ ትልቅ ወንዝ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ያልተሠሩ ትቦዎችም የጎርፍ አደጋ ሰለባ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በመገንዘብ፣ ለግንባታም ሆነ ለፍሳሽ ማስወገጃ ተብለው የሚቆፈሩ ጉድጓዶች ሕግና ደንብ እንዲኖራቸው ተጠይቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች