መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየመዲናዋን ውበት ለመጠበቅ በሚል የኮንቴይነርና ቆርቆሮ ቤቶች በግዴታ ይታደሱ ተባለ

የመዲናዋን ውበት ለመጠበቅ በሚል የኮንቴይነርና ቆርቆሮ ቤቶች በግዴታ ይታደሱ ተባለ

የአዲስ አበባ ከተማን የውበት ደረጃ ለመጠበቅ ሲባል በመንገድ ዳር የቆርቆሮና የኮንቴይነር ባለቤቶች እንዲያድሱ በመንግሥት መገደዳቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ በመንገድ ዳር የቆርቆሮ እና የኮንቴይነር ቤቶችን ገንብተው በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ የከተማዋን ውበትና ጽዳት ለመጠበቅ በማሰብ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት ቤቶችን በቀለም እና ሌሎች እድሳቶችን እንድናደርግ እየተገደድን ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች በመውጫ በሮች አካባቢ የአረንጓዴ ልማት ወይም ‹ግሪን ኤሪያ› በግዴታ እንዲያለሙ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ማልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ይመኙሻል ታገስ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ መዲናዋን እንደ ስሟ ፅዱ እና የከተማዋን የውበት ደረጃ ከመጠበቅ ረገድ በተቀመጠው ሕግ መሠረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከኃላፊነት ባለፈ ግዴታም አለበት ብለዋል።

በዚህ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተማ በመንገድ ዳር የሚገኙ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ወይም የዛጉ፣ የቆሸሹ የቆርቆሮ እና የኮንቴይነር የቤት ባለቤቶች በቀለም የመቀባት፣ የማስዋብ እንዲሁም የማደስ ሥራዎችን እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

በተጨማሪ፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ እንዲሁም በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት መውጫ በሮች አከባቢ በ50 ሜትር ክልል ውስጥ የአረንጓዴ ማልማት ሥራ እንዲሠሩ እየተደረገም ነው።

ይህም የኅብረተሰቡን ክፍል በመቀስቀስ እና ግንዛቤ በመፍጠር ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ ኅብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት እየሠራ እንዳለና ኃላፊነታቸውን ተገንዝበው መፈጸም ያልቻሉት ላይ ግን የማስገደድ ሥራ አልሠራንም ሲሉ፤ ነዋሪዎች ‹በደጃፋችን የሚገኝን ዛፍ በብሎኬት ዙሪያውን በፍጥነት ገንብተን እንድንጨርስ ተገደድን› ያሉትን ቅሬታ አስተባብለዋል።

አዲሱ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ከ100 ሺሕ በላይ የቆርቆሮ እና የኮንቴይነር ቤቶችን የቀለም ቅብ ሥራ፣ ከ500 ሄክታር መሬት በላይ መንገድ ዳር እና በተለያዩ አካባቢ የሚገኙ መውጫዎችን በአረንጓዴ ማልማት እንዲሁም የማስዋብ ሥራ እንደተሠራ ተነግሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የመንገድ ዳርቻዎች የሚገኙ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የቆርቆሮ ቤቶች ያሉ ሲሆን፣ ከተማዋን ጽዱ ከማድረግ ባለፈ ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን፣ በቀጣይም በተለያዩ ክፍለ ከተማዎች በመንቀሳቀስ የግንዛቤ እና የማስተማር ሥራው እንደሚቀጥል ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

ከአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ማልማት ቢሮ በተጨማሪ የከተማዋን ውበት እና ፅዳት ለማረጋገጥ የሁሉንም የመዲናዋን ነዋሪ ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ቢሮው እና ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉትን የግንዛቤ ማስጨበጫ ነዋሪዎች መተግበር አለባቸው ተብሏል።

ቢሮው የከተማዋን ውበት ከመጠበቅ ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና የትውልድ አንዱ የባህል አካል እንዲሆኑ ለማስቻል የችግኝ ጣቢያዎችን አቅም በማሳደግ እና በማዘመን ረገድ እየተሠራ ነው ብሏል።

የከተማዋን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ የሚረዱ አገር በቀል እፅዋትን፣ በምግብ ራስን ለመቻል የሚረዱ ፍራፍሬዎች፣ ለሕክምና እና መሰል ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችም እየተዘጋጁ ነው ተብሏል።

ለአደባባዮችና የመስመር ዳር አረንጓዴ ማስዋብ ሥራ በ50 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ማልማት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ መግለጹ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች