የአቦሰጥ ንግግር ይብቃ!

0
817

እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ ጃፓናውያን ባንሆንም ለራሳችን ያለን ክብር ወደር የሚገኝለት አይደለም። በዴሞክራሲ ቀዳሚ የሚባሉ ሕንድን የመሳሰሉ አገራት እርስ በእርስ የመከባበራቸው ሁኔታ ዝቅተኛ ነው ስለሚባል፣ በፓርላማ ጭምር ሲዘረጣጠጡና አንዳንዴም ሲደባደቡ እንመለከታለን።

በሌላው ዓለም የተለመደ መወራረፍና እንደፈለጉ መናገር እኛ አገር ዝም ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። ቂም ቋጥረን የብዙ ዓመታት ቁርሾን ለማወራረድ ዛሬም ቅስቀሳ የምናደርግ ሕዝቦች እንደመሆናችን፣ አሁን ቴክኖሎጂ ተራቅቆ ለታሪክ ሁሉ ነገር ተሰንዶ መቀመጥ በሚችልበት ዘመን የምናደርገው ብቻ ሳይሆን የምንናገረውም ብዙ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

የቅኔ ጥቅምና ዓላማ ብዙ ቢሆንም፣ በዋናነት የበላይንም ሆነ ባላጋራን በነገር ሸንቆጥ ለማድረግም ነው። ብዙኀኑ በቀላሉ እንዳይረዳ በማድረግ ባለታሪኩ በዘዴ እንዲያውቀው በክብር ተጠንቅቆ የሚነገርበት ስልት እንደመሆኑ ተከባብረን ብዙ ሺሕ ዓመታትን እንድንዘልቅ አስችሎናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ነገሮች እየተቀያየሩ መሪንም ሆነ ተራ ዜጋን ማክበር የሰማይ ያህል የራቀን ይመስላል። ለመከበር መጀመሪያ ሌላን ማክበር እንደሚጠበቅብን አብዛኞቻችን የተገነዘብን አይመስልም።

ሠሞኑን በተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ሪፖርት ብንመለከት ብቻ ብዙ ማለት ይቻላል። እንደራሴዎቹ በተለመደው አሰራር መሠረት ጥያቄያቸውን ሥርዓት ባለው መልኩ በቅድሚያ አስገብተው ሪፖርት አቅራቢው እንዲዘጋጁበት አድርገው ነበር። ሕግና መርህን በተከተለ መልኩ “ክቡርና የተከበሩ” እየተባባሉ ጥያቄያቸውን በእለቱ ለሕዝብ ያሰሙ ቢሆንም፣ መከባበራቸው በሥም ብቻ የመሰለበት አጋጣሚም ነበር።

ጠያቂዎችንና ተናጋሪዎቸን ለማሸማቀቅ እንደእንግሊዝ ፓርላማ ዓይነት ያልተገባ እጅግ አሳቃቂ ረብሻ ባይኖርም፣ እንደ ባሕላችን የሚሞገስ ሂደት እንዳልነበር አዲስ ማለዳ ታምናለች። በተለይ ተዘጋጅቶና አስቦ ጥያቄ አቅርቦ ቀጥተኛ መልስ ለሚጠብቀው እንደራሴ ይቅርና ለኅብረተሰቡም እንግዳ የሆነ ምላሽ የተሰማበት ነበር።

“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንደሚባለው፣ በምላሹ የሚወረወረው ቃላት ወደተፈላጊው ዒላማ ያነጣጠረ ሳይሆን ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ የጎረፈ እንደነበር ከብዙዎች አስተያየትም መረዳት ይቻላል። የሕዝብን ጥያቄ ጭምር አምጥተው ያቀረቡ እንደራሴዎች የመኖራቸውን ያህል በሪፖርቱ አቀራረብ የሚደሰት ይኖራል ብሎ ለመገመት ያስቸግራል።

አንደበተ ርቱዕ ለመባልና አድናቆት ለማግኘት ሲባል ብቻ በቅቤ የማይታሽ የንግግር ወለምታ እያጋጠማቸው ወደፊት መራመድ ያቃታቸው ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ካጋጠማቸው ስህተት አሁንም መማር አለመቻሉ ይታያል። ይህን የመሰለው እንደልብ የመናገር አባዜ ሊቀር የሚገባ ሥርዓት አልበኝነት መሆኑን ልንረዳ ይገባል።

አለአግባብ ሕግ ተጥሶ እየታሰሩ ስላሉ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ሲቀርብ፣ በዘፈቀደ ታሰሩ የተባሉትን በጅምላ ለመፈረጅ የተሄደበት አካሄድ አደገኛ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። የዘረፉ፣ የገደሉና የከዱ ናቸው ብሎ ለአገር ብለው ባመኑበት መስመር የሚታገሉን ከሕዝብ ለመነጠል የተሄደበት አካሄድ የታሰበበትና ዝግጅት የተደረገበት አይመስልም። ጋዜጠኞችን ባለሙያዎች አይደሉም፣ ፋኖዎችንም ትክክለኞቹ አይደሉም፣ አንደኛ ደረጃ ሌባ ዳኛ ነው ብለው አስቀድመው መዛኝ ሆነው በመፈረጅ፣ ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ጫና የሚያሳድር ንግግር ማድረግ አገርን ከሚመራ አካል የሚጠበቅ አይደለም።

የታሰሩትን ተጠርጣሪ በማለት ፈንታ፣ ንፁሐን አይደሉም ለማለትና ሕዝብን ጭምር ለማሳመን የሄዱበት መንገድም ትዝብት ላይ የሚጥል ነው። ከ4 ሺሕ ታሳሪዎች 3 ሺሕ 500 የሚሆኑት የከዱ የፀጥታ አካላት ናቸው በሚል አገርንም የሚያሳዝን መረጃ ተገፋፍተው ይፋ አድርገዋል።

ጉዳዩን የክልል የፀጥታ ኃይሎች ነው የያዙት ተብሎ፣ ከአንድ ክልል ብቻ ይህን ያህል ኃይል ከዳ ለማለት ያላሳፈረበት ምክንያት ግልፅ አይደለም። ለምንስ ከዱ? የሚል ጠያቂ ባለመኖሩም፣ ችግሩ ከማን እንደሆነ ሳይታወቅ እንዲድበሰበስ ተደርጓል።

ለእንዲህ ዓይነት ምላሾች መከሰት ምክንያቱ ሕዝብንም ሆነ አድማጭን አለማክበርና በበቂ ሁኔታ አለመዘጋጀት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ትረዳለች። እንደፈለጉ አፍ እንዳመጣላቸው እየተናገሩ ሕዝብን የሚያስከፉ ባለሥልጣናትም ሆኑ ፖለቲከኞችና ግለሰቦች በበዙበት ዘመን፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሹማምንት ምሳሌ ለመሆን መጣር ይገባቸዋል።

በሌላ በኩል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ማንም ማንንም መሳደብ የለበትም። እሳቸውም ቢሆኑ ቡድንንም ሆነ ተከታይ ያለውን ማንኛውንም ግለሰብ ለማሸማቀቅ የሚውል “የቀን ጅብንም” ሆነ ሌላ ምሳሌያዊ ስድቦችን ከእንግዲህ መጠቀም ማቆም ይኖርባቸዋል።

የድሮ ነገሥታት ሲዋጉ እንኳን ተከባብረው አንቱ እየተባባሉ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። አፄ ቴዎድሮስ “የኮሶ ሻጭ ልጅ” እያሉ በሥልጣን ዘመናቸው የሰደቧቸውን በዘመነ ሥልጣናቸው እየያዙ ኮሶ እያጠጡ እስኪበቃቸው አስግተው ካስተማሩበት ሂደት ሁላችንም ልንማር ይገባል። አፄ ምኒልክና ንጉሥ ተክለሀይማኖትም ተዋግተው ከተሸናነፉ በኋላ እርስ በእርሳቸው ያሳዩት መግባባትና ሀዘኔታ ተከታዮቻቸው መካከል ቁርሾ እንዳይኖር በማድረጉ አሁንም ድረስ ያከናወኑት ተግባር ምሳሌ የሚሆነን ነው።

አንድ ሰው ሌላውን ሳያከብር ንቆ በሚናገርበት ወቅት የተናቀው ግለሰብ ደጋፊና ተከታይ ባይኖረው እንኳን የሚወደው ቤተሰብ እንደሚኖረው ልንረዳ ይገባል። በስንት ልፋትና ጥረት እየቀነሰ የመጣው ደም የመቃባት ባህላችን ተመልሶ እንዳያንሰራራ ሁሉም ሊያስብበት ይገባል። በተለይ መንግሥት ብቸኛ ኃይልን የመጠቀም መብት አለኝ እንደማለቱ፣ ጉልበቱን ብቻ ሳይሆን አንደበቱንም መጥኖ መያዝ ይኖርበታል። ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይልን መጠቀም እንደማይገባው ሁሉ፣ ያልተገባ ንግግርንም አድርጎ ኅብረተሰቡን ወደአልተፈለገ አቅጣጫ መግፋት እንደሌለበት እሙን ነው።

የቀድሞ ባለሥልጣናት አፋቸው እንዳመጣላቸው፣ ጠባብና ትምክሕተኛ አልያም አክራሪና አጋንንታም እያሉ የሰደቡት ማኅበረሰብ የት እንዳደረሳቸው መመልከት ተገቢ ነው። “በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ”፤ “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባበትም” የሚሉትን ብሂሎች፣ “ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል” ከሚሉ ዓይነት አባባሎች ጋር በማጣጣም ሁላችንም የምንናገረውን እያስተዋልን እንዲሆን አዲስ ማለዳ መልዕክት ታስተላልፋለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here